አዲስ ሪፖርተር – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዲያስፖራ ሰፈር የሚሰራጨው ተመጋጋሚነት ያለው ዜና ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ሊወድቅ በጣት የሚቆጠር ቀን ስለመቅረቱ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከመንግስት ወገን ኮሽ ስለማለቱም ድንጋጤ ያለ አይመስልም። እግሩን ሰሜን አሜሪካ የተከለው የተከለው የተቃዋሚ ኃይል ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያን እንደሚታደጉ፣ ለውጡን እየመሩ አራት ኪሎ እንደሚያደርሷቸው እያስታወቁ ነው። መንግስት በበኩሉ “አይጀምሩም ከጀመሩ የመጨርሻቸው ነው” ይላል።
ከትግራይ የሚወጣው በየቀኑ የሚቀያየር መረጃ አንዴ ለስለስ፣ አንዴ ከረር ሲል ኖሮ በይፋ ከኤርትራ፣ ፋኖና መስለ አቋም ካላቸው ኃይሎች ጋር አብሮ መንግስት ለመጣል ዝግጅቱን እንዳጣናቀቀ ነው። ከትግራይ ከትህነግ በስተቀር በይፋ “ጦርነት መፍትሄ ነው” የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች አይሰሙም። ሕዝብ በተለያዩ አጋቦች “ጦርነት በቃን” እያለ ሲሆን፣ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ወጣቶች ጦርነት ፍርሃቻ ትግራይን ለቀዋል።
የትግራይ አስተዳደርን መሪነት እንደወሰዱ የሚነገርላቸው ዶክተር ደብረጽዮን፣ “የትግራይ ወጣቶች ትግራይን ጥላችሁ አትሰደዱ፤ እዚሁ ሆናችሁ ለህልውናችሁ ተፋለሙ” ሲሉ ባሰሙት ጥሪ ፍልሰቱ ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል። ራሳቸውን የትግራይ ሰላም ኃይሎች የሚሉት ታጣቂዎች ከሐራ መሬት “ኑ ወደ እኛ” በማለት የትግራይ ወጣቶች “እምቢ ለጦርነት” እንዲሉ በየዕለቱ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በትግርኛ ቋንቋ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፣ ለትግራይ ወጣቶች “ጦርነትን እምቢ በሉ። መንግስት ጦርነት የመክፈት አንዳችም ፍላጎት የለውም” በማለት ይፋዊ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚያ በፊት ሌተና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከትህነግ የተለዩ አመራሮች የትግራይን ሕዝብ “ጦርነት እምቢ ብለ” በማለት ትህነግን ከሕዝብ የመነጠል ስራ እየሰሩ መሆናቸው በየአጋጣሚው ሁሉ ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል።
መንግስትን በመቃወም የሚታወቁ የትግራይ አክቲቪስት ሚዲያዎችም “ያለ ጦርነት መኖር የማይችል” በማለት ለመስማት በሚከብድ ቃላቶች ትህነግን በመዝለፍ ዳግም በትግራይ እልቂት እንዳይፈጸም እይወተወቱ ነው። ከሻዕቢያ ጋር የተመሰረተውን ጥምረት “ድንቁርና፣ የትግራይን ህዝብ የሸጠና በትግራይ ህዝብ ደም መነገድ” እንደሆነ በመዘርዘር አጥበቀው ነጋ ጠባ ይተቻሉ። ያስጠንቀቃሉ። ሻዕቢያ ትግራይን የጦርነት ሜዳ በማድረግ ራሱን ለመከላከል የተጠቀመበት የብልጣ ብልጥነት ስልት እንደሆነ በመግለጽ የትህነግን መሪዎች “ይህን የማትረዱ ካርቶን ራሶች፣ አሰላለፍ፣ የዓለምን ሁኔታና የምስራቅ አፍሪካን ወቅታዊ ፖለትኪካ ያማታነቡ ድንጋዮች” ይሏቸዋል።

ሻዕቢያ የሚነዳቸውና የሚደግፋቸው እንደሆኑ የሚታወቁት ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች፣ የሚታወቁ ፖለትከኞች ደግሞ የሻዕቢያ፣ የፋኖና የትህነግ ጥምረት፣ የግብጽ፣ የሱዳንና የሶማሊያ ጥምረት የኢትዮጵያን መንግስት የሚደፋ ኃይል እንደሆነ በመግለጽ በሚዲያዎቻቸው በሙሉ የተቀናጀ ዘመቻ ላይ ናቸው።
ይህ ሁሉ ሲሆን በየመካከሉ ታዋቂ የትግራይ ተወላጅ መኮንኖች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል። የሲቪል አስተዳደር ውስጥም ትህነግን ጥለው ወደ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑ እየተሰማ ነው። በርካታ ወጣቶች ትግራይን ለቀዋል። ይህ ብቻ አይደለም አራት መቶ የሚጠጉ የኤርትራ ወታደሮች ከምሽግ ፈልሰው ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ እጅ ሰጥተዋል። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት በትግራይ የጦር መኮንኖችና ቁልፍ የፖለቲካ አመራሮች መልቀቅ፣ ከህዝብ የጦርነት ጥላቻ ጋር ተዳምሮ በቅርቡ አንድ ነገር ሊታይ መሰማቱ አይቀሬ ነው።
እነዚህ ወገኖች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የትግርኛ ቃለ ምልልስ በልዩ ሁኔታ የሚመለከቱትም በዚሁ አግባብ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዝን ለትግራይና ኤርትራ ህዝብ ትህነግና ሻዕቢያ ያሰባሰቡት አሰባሰበው ጦርነት ለማስጀመር እቅድ እንዳላቸው ግልጽ አድርገዋል። ትህነግ ጦርነት ለመጀመር ደፋ ቀና እያለ መሆኑን ሲገልጹ በህገወጥ ማዕድን እይሸጠ መሳሪያ ይገዛል። ለትግራይ የሚሰጠውን በጀት ለሰራዊት እያዋለ ህዝቡን ይበድላል።
ከህገመንግስቱ ጋር በሚጋጭ መልኩ ከውጭ አገራት ጋር የሚደረግ ግንኙነትን መታገስ እንደማይቻል የትግራይ ሕዝብ እንዲገባው አድርገው ያስረዱት አብይ አሕመድ፣ የሰሜን ዕዝ ላይ የተከፈተውን የክህደት ጦርነት ተከትሎ እግሩን ያስገባው የሻዕቢያ ሰራዊት በወቅቱ ያደረሰውን ግፍና በደል ዘርዝረው አሁን ያ እንደማይፈቀድ አስታውቀዋል። ከሞከረም የመጨረሻው እንደሚሆን በይፋ ተናግረዋል።
ከሶስት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የመጡት ብርጋዴር ጀነራል ጉዑሽ ገብረ TBS ከተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሻዕቢያ ለትግራይ ሕዝብ ምንም እንደማይጠቅም በዝርዝር አስረድተው “ጽምዶ” የተባለውን ህብረት እንዲቃወም ጥሪ አቅርበዋል።
የትግራይ ህዝብና ሰራዊት ትህነግና ሻዕብያ የፈጠሩት “ፅምዶ” በፅኑ እንዲቃወሙትና እንዲታገሉት ያስገነዘቡት ጀነራሉ የኢፌዲሪ መንግስት በፕሪቶሪያ ውል መሰረት ተፈናቃዮች በመመለስና ግዛታዊ አንድነት በማረጋገጥ ትህነግን ምክንያት አልባ ሊያደርገው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አመራር ብርጋዴር ጀነራል ጉዑሽ ገብረ በኤርትራ መንግስት፣ በህወሓት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ስላለው ውስብስብ ግንኙነት ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል። ጀነራሉ የኤርትራ መንግስት የትግራይ ህዝብ “ዋና ጠላት” ነው በማለት የገለጹ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ አመራርና በሻዕብያ መካከል ተፈጥሯል የተባለውን ግንኙነት በጽኑ ተቃውመዋል።
ጀነራል ጉዑሽ የኤርትራ መንግስት ኢሮብ ፣ዛላአንበ፣ ባድመ እና ሰብዖ፣ እንዳሃወርያ፣ ዓዲ ፀፀር፣ ዓዲ ኣሰር እና ዓዲ ተኻሉ የተባሉ አካባቢዎችን በኃይል መያዙን አስታውሰው የትግራይን ሕዝብ የሚያከብርና የሚወድ ከሆነ እስኪ ለቆ ይውጣ ሲሉ ጠይቀዋል።
ጀነራል ጉዕሽ በትግራይ ኃይሎች ውስጥ ቁልፍ መኮንን ነበሩ። አሁን ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውና የሰጡት መግለጫ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ነጥቦች ጋር መስማማታቸው በመግባባት እየተሰራ ያለ ነገር ስለመኖሩ አመልካች ነው ተብሏል።በትህነኛ እና በሻዕብያ መካከል ተመስርቷል የተባለውን “ፅምዶ” የተሰኘ ግንኙነት ጀነራሉ “አፍራሽ እና የማይረባ” ሲሉ አጣጥለውታል። እንደሳቸው ገለጻ፣ ይህ ግንኙነት፣ የተለመደው የሰላም ግንኙነት ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግስት ለመውጋት የታለመ “እኩይ ፕሮጀክት” ነው። የትግራይን ህዝብ ለዳግም ጦርነትና ሰቆቃ የሚዳርግ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያገናኝ ሳይሆን የጥቂት አመራሮች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰሜኑ ጦርነት መነሻ ምክንያቶችን በዝርዝር ካስረዱ በኋላ ትህነግ ለውጥን ባለመቀበሉ፣ እኔ ብቻ በሚል ስሜት በመዋጡ ግጭት መነሳቱን አስረድተዋል። አቶ ጌታቸው “ልዩነታችንን አቻችለን ካልተስማማንና ግጭት ከተጀመረ ሻዕቢያ አጋጣሚውን ይጠቀምበታል” በማለት ደጋግመው ነገረናል፣ በተደጋጋሚ ሰዎች ልከዋል” ምስክርነት መስጠታቸው አይዘነጋም።
ትህነግ ወደ መሬት መውረድ በማይችል ያረጀ በቀድሞ ያረጀ አስተሳሰብ የታሠረ ድርጅት መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከኋላ ቀር አስተሳሰቡ በሚመነጭ ዓይኑን ጨፍኖ ራሱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱንም ተናግረዋል።
የለውጡ ኃይል የጀመረውን ጉዞ ለማደናቀፍ መሞከሩን ገልጸው፤ በትህነግ ቆሞ ቀር አስተሳሰብ የተቀሰቀሰው ጦርነት ይህ ነው የማይባል ጉዳት ማስከተሉን በዝርዝር አብራርተዋል።
ከማይለወጠው ያረጠ አስተሳሰቡ በተጨማሪ ለጦርነቱ ምክንያት የነበረውብ ጉዳይ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ጋር የተሣሠረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ትህነግ ኢትዮጵያ በጥርጣሬና በሥጋት ውስጥ እንድትኖር ሲሰራ እንደነበር አመላክተው፣ ይህ አቋሙ ለችግሮች መባባስ ለተከሰተው ጦርነት ነዳጅ እንደነበርም አስታውሰዋል። ላለፉት 50 ዓመታት ድርጅቱ ራሱ ላይ ጭኖ የኖረው አስተሳሰቡ ለውጡን እንዳይቀበል እንዳደርገውም አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸውና ባልደረቦቻቸው በተደጋጋሚ “ቆሞ ቀር” የሚሉት ትህነግ ለአዲስ አሳብና ለአዲስ ፖለቲካ አለርጂክ በመሆኑ ነገሮች በትግራይ ከድጥ ወደ ማጡ እየሄዱ እንደሆነ በየአቅጣጫው ይገለጻል። ትህነግ በታሪኩ አንድም ጉዳይ በውይይት ጨርሶ አለማወቁ አሁንም የትግራይን ሕዝብ ሌላ ዋጋ እንዳያስከፍለው ስጋት አለ።
በህወሓት በኩል ዳግም ጦርነት እየተቀሰቀሰ መሆኑን የጠቆሙት ዐቢይ፤ በፌደራል መንግሥት በኩል በትግራይ ላይ ውጊያ “በፍጹም” የመክፈት ፍላጎት የለም ብለዋል። ነገር ግን ትህነግ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፤ “የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ እምቢ ለጦርነት ማለት አለበት” ሲም ጥሪ አሰምተዋል። ይህ ንግግራቸው ከጄኔራሉ ጥሪ ጋር የሚስማማና የሚናበብ ሆኖ ተገኝቷል።
በንግግር ይሁን በተግባር ወደ ግጭት ከሚወስዱ ተግባራት መቆጠብ ይገባል የሚል ምክረ ሀሳብም አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትህነግ ለዳግም ጦርነት ቅስቀሳ እየተጠቀመባቸው ያሉ ጉዳዮች ከሞላ ጎደል መፈታታቸውን አመልክተዋ፣ ወልቃይት ውጪ፤ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ እንደ ጠለምትና ራያ ባሉ አካባቢዎች ተፈናቃዮች መመለሳቸውን አስታውሰዋል። አቶ ጌታቸውን በእርካታ የትግራይ ፖለቲከኞች ትህነግ ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ዓላማው ማስፈጸሚያ እንዳደረጋቸው በስፋት ሲዘገቡ ነበር።
ከትህነግ በኩል የፌደራል መንግስቱን የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደማያከብር ጠቅሶ በተደጋጋሚ እንደሚከስ ይታወቃል። ትግራይን እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር በመቁጠር ጥያቄው “የነጻነት” ነው የሚል አቋም ወደማራመድም ተሸጋግሯል። በወልቃይትና ራይ በኩል “አማራ ነን” በሚል ላለፉት ሰላሳ አምስት ዓመታት ጥያቄ ሲያቀርቡ የኖሩ ደግሞ ይህን አይቀበሉም፤ መንግስት ጉዳዩ ወደፊት ሕዝብ ከተረጋጋ በሁዋላ በሪፈርነደም ሊዳኝ እንደሚገባ ያምናል። ይህን ጉዳይ ትህነግ ከቶውን ም መስማት አይፍለግም። ሌሎቹ ወገኖችም ትህነኝ መስማት አይፍለጉም። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ለዓመታት ውሳኔ አለማግኘታቸው ጉዳዩን አሳዛኝ ያደርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ውይይት በማድረግ ነገሮች እንደሚፈቱ ባሳሰቡበት ቃለ ምልልሳቸው ለኤርትራ ቁርጥ ያለ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
የሰሜን ዕዝ ሲጠቃ ወደ ኤርትራ ሲሸሽ የተደረገለትን መልካም ነገር ሁሉ በማንሳት በወቅቱ ምስጋና መቅረቡ ትክክል እንደነበር አመልክተው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጥፋት የሚፈጽም ከሆነ ግን የመጨረሻው ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል።
የሻዕቢያ መንግስት በልማትና በመሰረት ልማት ግንባታ እንደማያምን አስታውቀው እንዳሉት ከሆነ የኤርትራ ሕዝብ የሚመጥነውን መንግስት ማግኘት አለበት።
በሥልጣን ሽግግር የማያምንና ልጆቹን፣ የልጅ ልጆቹን ሳይቀር የሚጠረጥር እንደሆነ የገለጹት ሻዕቢያ፣ ሥልጣን ሲይዝ ከሦስት መቶ በላይ ፋብሪካዎች በኤርትራ ነበሩ ዛሬ ሁሉም በሚባል ደረጃ እንደሌሉ በማመልከት ምን ያህል ከልማት ጋር የተጣላ መንግስት እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ኤርትራን ሲያዩዋት መደንገጣቸን መናገራቸው አይዘነጋም።
በቀድሞው ዘመን የተከፈተላቸው አስመራ ዩኒቨርሲቲ ብትኖር እሷም ተዘግታ ኤርትራ ዩኒቨርስቲ አልባ አገር መሆኗን በማስታወቅ ኤርትራዊያን ሊያስቡበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ኤርትራዊያን ሀገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ በሁሉም ሀገራት ተሰደዋል ኤርትራ ባዶ እየሆነች ነው። ብለዋል። አክለውም ሕዝብ በአዲስ አበባ የሚያነሳውን ጉዳይ ጠቁመዋል።
ከሀገራቸው የተሰደዱት ኤርትራዊያን በስደት እንኳን ሰርተው ሰርተው በሰላም እንዳይኖሩ ከእነርሱ ጋር ሰላዮችን ጭምር እየላከ ማነው ጤነኛ ማነው በሽተኛ የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች በስለማ ለመኖር መቸገራቸውን አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ኤርትራውያን እንደ ሀገራቸው ይሥሩ የሚል አቋም ነበረን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ “ችግር እየፈጠረ ያለው ከጤነኛው ጋር ተቀላቅሎ የሚመጣው በሽተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ስለሆኑ ማነው ጤነኛ ማነው በሽተኛ ለማለት እንደሚያስቸግር አመልክተዋል።
“በሀገራቸው እንዳይኖሩ ሰላም እያሳጣቸው ነው ስደት ላይ ሆነውም ሰላም እያሳጣቸው ይገኛል” ሲሉ ሻዕቢያን የኮነኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ይህ የሻዕቢያብተግባር “የክፋት ሁሉ መሠረት ነው” ሲሉ ኤርትራዊያን ምን ያህል በመንግስታቸው እንደሚሰቃዩ አሳይተዋል።
“ሰው በሀገሩም በውጭም መኖር ካልቻለ በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ስሜታቸውን የገለጹት አብይ አህመድ፣ “ይህ ይቅር ሊባል የማይገባው ሰብዓዊ በደል ነው” ብለዋል።
“ቀረብ አብረን ብለን ለመስራት ሞክረን ነበር፤ ከልምዳችን የተማርነው ግን ከዚህ ኃይል ምንም ዓይነት መልካም ነገር ማግኘት የማይታሰብ መሆኑን ነው” ሲሉ በሻዕቢያ ተስፋ መቁረጣቸውን አስታውቀዋል።
ሻዕቢያ ካለው ተፈጥሮው አንጻር አቅም ካገኘ ሀገርን ከመበጥበጥ ወደ ኋላ እንደማይል አመልክተው፣ “አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ህዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም፣ ምናልባት ደግሞ ከሞከረ የመጨረሻ ሙከራው ይሆናል የሚል ዕምነት አለኝ” ብለዋል። ይህ ንግግራቸው ሻዕቢያ ካልተነቀለ ኢትዮጵያ ሰላም ልታገኝ አትችልም የሚለውን የበርካታ ኢትዮጵያዊያን እምነት ያንጸባረቀ ሆኗል።
ሻዕቢያ ኤርትራን መምራት ከጀመረበት ቀን ጀምሮም ሆነ ከዛ በፊት ኢትዮጵያ ላይ ጠላት ማደራጀት፣ ማስታጠቅና ማዝመት ዋና ስራው እንደሆነ፣ በጎረቤት አገራትም ሽብርተኛ በማስለጠንና በማስታጠቀ ኢትዮጵያን ማወቅክ ቀዳሚ ተግባሩ የሆነ ድርጅት እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚገለጽ እውነት ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






