- አዲስ ሪፖርተር – የእስራኤል ፓርላማ በፍልስጤማውያን ላይ ያነጣጠረ ነው የተባለውንና ለ”አሸባሪዎች” የሞት ቅጣት የሚደነግገውን አዲስ ሕግ ማፅደቁን ተከትሎ፣ የዓለም ሀገራትና ፖለቲከኞች ድርጊቱን በጽኑ እየኮነኑት ይገኛሉ። የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ሕጉን “ወደ አፓርታይድ ስርዓት የሚወስድ አንድ ተጨማሪ እርምጃ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ የአየርላንድ መንግስት በበኩሉ ሕጉ ፍልስጤማውያንን ለይቶ የሚያጠቃና ሰብአዊ መብትን የሚጥስ ነው ሲል ወቅሷል።
የአውስትራሊያ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የሞት ቅጣት ኢ-ሰብአዊ ከመሆኑም ባለፈ ሽብርተኝነትን የመከላከል አቅም እንደሌለው ገልጸዋል።
ይህ በአይታማር ቤን-ግቪር የቀኝ ዘመም ፓርቲ የቀረበው ሕግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ዘረኛና መድልዎ ያለበት” ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን፣ በተለይም የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እስራኤል በይዞታዋ ስር ባሉ የፍልስጤም ግዛቶች ላይ ይህን መሰል የሞት ቅጣት መደንገጓ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አሳስቧል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም “የሞት ቅጣቱ አሁን ፍልስጤማውያን እየደረሰባቸው ያለው የአፓርታይድ፣ የዘር ማጥፋትና የወረራ አካል ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ሕጉ ሲጸድቅ ሚኒስትሩ ቤን-ግቪር በሻምፓኝ ሲያከብሩ መታየታቸው ደግሞ የብዙዎችን ቁጣ ቀስቅሷል።
በተቃራኒው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እስራኤል በሽብርተኝነት የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የምትጥለውን ቅጣት የመወሰን “ሉዓላዊ መብት” እንዳላት ገልጸው፣ ሂደቱ ፍትሃዊ በሆነ የፍርድ ቤት ክርክር እንደሚመራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የሞት ቅጣትን አሁንም ተግባራዊ የምታደርግ ብቸኛዋ የኔቶ አባል ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






