በዘመናዊው ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ትክክለኛው ሃይል የሚለካው በቴክኖሎጂ ልዕልና፣ በኢኮኖሚ ጥንካሬና በዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እንጂ፣ ከዓለም ተገልሎ በሚደረግ ወታደራዊ ሽኩቻ አይደለም። የሱኒ ሃገራት የመረጡት መንገድ የዜጎቻቸውን ህይወት የቀየረና ለዓለም ወሳኝ የሆኑበት ብልህ ስትራቴጂ ነው። እናም ጎበዝ! በስሜት የሚነዱ ትንታኔዎች ተጨባጩን እውነት እንዳይጋርዱብን መጠንቀቅ አለብን
አለባቸው ጉብሳ- ነፃ አሰተያየት
አህመዲን ጀበል በጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ሰሞኑን እየጻፈ ነው። ሃሳብን ማጋራት ይበረታታል። እኛም አንብበን ጠቃሚውን እንወስዳለን፣ የተጣመመውን ደግሞ እናቃናለን። ዛሬ በፌስቡክ ገፁ ባጋራው የጂኦ-ፖለቲካ ጽሑፍ የሱኒ ሙስሊም ሃገራት ለምን እንደ ኢራን ራሳቸውን ችለው ሉዓላዊነታቸውን አላስከበሩም በሚል በመጠየቅ፣ ኢራንን ከሱኒ ሃገራት ጋር በማነፃፀር የኢራንን ልዕልና ለማሳየት ሞክሯል። በተጨማሪም የኋለኞቹ ሃገራት ሊከተሉት ስለሚገባ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ጠቁሟል።
ጀበሉ ስለ ኢራን ያጋራው የተጋነነ እይታ በመሬት ላይ ካለው የዲጂታል፣ የኢኮኖሚና የወታደራዊ የበላይነት ሚዛን ጋር የሚቃረን ነው። ሉዓላዊነትን ከድህነትና ከገለልተኝነት ጋር አቆራኝቶ የማቅረብ ዝንባሌው፣ የባህረ-ሰላጤው ሃገራት ያላቸውን ስውርና ግልፅ አቅም ያላገናዘበ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እኔም ይህ ድምዳሜ በህፀፅ የተሞላና ከተጨባጭ እውነታዎች(facts) ጋር የተፋታ መሆኑን በቅንነት ለማሳየት እሞክራለሁ። እነሆ!
የሱኒ ሃገራት ከኢራን የሚበልጡ ስለመሆኑ
ጀበሉ በዚህ የመረጃ ዘመን የሱኒ ሙስሊም ሃገራት፣ በተለይም የተባበሩት ኤምሬትስና ሳውዲ አረቢያ፣ የመጪውን ዘመን የሃገራትና የሰው ልጅን ዕድል ፈንታ የሚወስኑትን የዲጂታልና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መሪዎች መሆናቸውን አለማወቁ ገራሚ ነው። እነዚህ ሁለት ሃገራት ጀበሉ እንደሚያጣጥላቸው ሳይሆን፣ ኢራንን በወታደራዊ ቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይበልጧታል። በቀላሉ የድሮን ቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶቻቸውን ጎልጉሎ ማየት ይችላል፣ የትምህርት ተቋሞቻቸውን ጭምር።
በአሜሪካ መራሹ ጥምር ጦርና በኢራን መካከል በሚደረገው ጦርነት ሳውዲና ኤምሬትስ ቤታቸውን የሰሩት በመስታወት ስለሆነ (መሰረተልማቶቻቸው በቀላሉ ለጉዳት ተጋላጭ) ፣ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ሰላማዊ ጉርብትናን ግምት ውስጥ በማስገባት ስልታዊ በሆነ መልኩ ራሳቸውን ማቀብ (Strategic Restraint) መርጠዋል። ከማጥቃት ይልቅ መከላከል ላይ መሰረት በማድረግ ኢራን የተኮሰችባቸውን የድሮንና ሚሳኤል በብቃት መከላከል ችለዋል። ይህ አቅመ ቢስነት ሳይሆን፣ የንብረትና የህዝብ ደህንነትን የማስቀደም ጉዳይ ስለሆነ ነው።
አንደ ኢራን እብደት ቢሆን ኖሮ፣ የሳውዲና የኤምሬትስ የነዳጅ ዘይት መሰረተ ልማቶች ሳይሆኑ የኢራን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በወደመ ነበር። የባህረ-ሰላጤው ሃገራት ያላቸው ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችና የሚሳኤል መከላከያ ቴክኖሎጂ ከኢራን ጦር መሳሪያዎች እጅግ ዘመናዊና የላቁ ናቸው። ኢራንን በቀላሉ ማጥቃት ይችሉ ነበር፣ ነገር ግን ሃገር የሚመራው በስሜታዊነት ሳይሆን፣ የልማትና የሰላም ዋስትናን በማረጋገጥ መሆኑን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።
የምዕራባውያን ቴክኖሎጂ ጥገኝነት ወይስ ስልታዊ ትስስር?
አህመዲን ጀበል የሱኒ ሙስሊም ሀገራት ከምዕራባውያን ቴክኖሎጂና የጦር መሳሪያ ጥገኝነት ወጥተው እንደ ኢራን ራሳቸውን መቻል አለባቸው በማለት ይሞግታል። ይህ አስተሳሰብ ከዘመናዊው የጂኦ-ፖለቲካ እውነታ ጋር ፍጹም የተጣላ ነው። ኢራን በጦር መሳሪያ ራሷን የቻለች ቢመስልም፣ እውነታው ግን ድሮኖችንና ሚሳኤሎችን ዲዛይን ማድረግ እንጂ ወሳኝ ግብዓቶችን የማምረት አቅም የላትም። ይህንን ክፍተቷን ለመሙላት ነዳጇን ለቻይና በመሸጥ በልዋጩ ለጦር መሳሪያ ማምረቻ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ሴሚኮንዳክተር ትገዛለች። ይህ አቅርቦት ቢስተጓጎል ኢራን የምትመካባቸውን መሳሪያዎች ማምረት እንኳን የማትችልበት ደረጃ ላይ መገኘቷ፣ ሉዓላዊነቷ ምን ያህል በሌሎች ቴክኖሎጂ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ያሳያል።
በተቃራኒው የሱኒ ሀገራት ከምዕራባውያን ጋር ያላቸው ግንኙነት የጥገኝነት ሳይሆን የስልታዊ ኢንቨስትመንት የሽርክና ውጤት ነው። ምዕራባውያን ለሳውዲ አረቢያና ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የመጨረሻው ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ (cutting edge tech) እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ሽግግር ዋና ምንጭ ናቸው። ይህ ትስስር ሃገራቱ የጦር መሳሪያ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ራሳቸውን ችለው የቴክኖሎጂ ባለቤትና አቅራቢ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ራስን አግልሎ በድህነት ውስጥ ከመቆዘም ይልቅ ከዓለም ጋር ተሳስሮ የቴክኖሎጂ መሪ መሆን የአስተዋይነት መንገድ መሆኑን እነዚህ ሀገራት በተግባር እያሳዩ ነው።
ጀበሉ ያልተረዳው ሌላው ትልቅ ጉዳይ የሱኒ ሙስሊም ሀገራት ተምሳሌት የሆነችው ቱርክን ከምዕራባውያን ጋር ያላቸውን የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ ነው። ቱርክ የምዕራባውያን ወታደራዊ ጥምረት የሆነው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (NATO) ቁልፍ አባል ስትሆን፣ የአውሮፓ ሕብረት አባል ለመሆንም ለዓመታት ድርድር ላይ ትገኛለች። ቱርክ ራሷን አግልላ ሳይሆን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመጠቀም ነው የሃገር ውስጥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋን ማዘመንና ቀጠናዊ ተጽዕኖዋን ማሳደግ የቻለችው። ይህ የሚያሳየው ጥንካሬ የሚመጣው ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወጥቶ በመገለል ሳይሆን፣ በስምምነቶቹ ውስጥ ሆኖ ብሄራዊ ጥቅምን ማስከበር ሲቻል ነው።
በአጠቃላይ ራስን ማግለል ሉዓላዊነትን አያስከብርም፤ ይልቁንም ሀገርን ለኋላ ቀርነትና ለድህነት አሳልፎ ይሰጣል። የኢራን “የራስን የመቻል” ትርክት በቴክኖሎጂ ግብዓት ሽያጭ ላይ የተመሰረተ ደካማ መዋቅር ያለው ሲሆን፣ የሱኒ ሀገራት ግን ከምዕራባውያን ጋር ባላቸው ትስስር የሰው ኃይላቸውን እያበለጸጉና የኢኮኖሚ መዋቅራቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ። እውነተኛ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው እንደ ኢራን የቴክኖሎጂ ኮንትሮባንድ ላይ በመንጠልጠል ሳይሆን፣ እንደ ሳውዲና ኤምሬትስ የዓለምን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሰንሰለት መዘወር ሲቻል ነው። በመሆኑም የጀበሉ የ”ገለልተኝነት” ጥሪ ከዘመኑ የዲጂታልና የጂኦ-ፖለቲካ እውነታ ጋር ፍጹም የተፋታ ነው።
የፍልስጤም ጉዳይ
ጀበሉ ይጠይቃል፣ “ኢራን ለፍልስጤም የሰጠችውን ያህል የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለመስጠት የደፈረ አንድስ እንኳ የሱኒ ሙስሊም አገር አለ ወይ?” በማለት። ሆኖም የኢራን ድጋፍ ከሰብአዊነት ይልቅ “ቀጣናዊ የበላይነትን” (Regional Hegemony) የመቀዳጀት ስሌት አካል እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ውስጠ-ወይራው ይኸው ነው። ወዳጄ! ሰብአዊነትና ወንድማማችነት ሽፋን ነው። በተለይ ሃማስን እና ሂዝቦላን እንደ ወኪል ወይም ፖለቲካ ካርድ (Proxy) በመጠቀም የራሷን ተጽዕኖ በቀጠናው ለማስፋፋት ያደረገችው ስትራቴጂክ ጥረት አካል ነው።
በተቃራኒው የሱኒ ሀገራት ለፍልስጤም ያላቸው አቋም በዲፕሎማሲያዊ መፍትሄና በሰብአዊ እርዳታ ላይ የተመሰረተ ነው። ለጋዛ ሕዝብ የሚሰጡት ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር እርዳታና መልሶ የመገንባት ጥረት፣ ከኢራን ወታደራዊ ድጋፍ በበለጠ ለፍልስጤማውያን ህልውና ወሳኝ ነው። ጦር መሣሪያ አለመስጠታቸው ቀጣናዊ ግጭቶችን ላለማባባስና የሃገራቸውን ደህንነት የማስቀደም ሃላፊነት ስላለባቸው ነው። ጌታዬ፣ ሃገር በሰው ልጅ የሞራል እሳቤ ብቻ አትመራም።
ይህ ኢራን ለሃማስ የሰጠችው ድጋፍ ቀጣናውን ወደ ባሰ ግጭት የመራ ሲሆን፣ የሱኒ ሀገራት ግን ለዘላቂ ሰላምና ለፍልስጤም መንግሥት ምስረታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትዕግስት እየሰሩ ይገኛሉ። እውነተኛ ደጀንነትም በስሜታዊነት መሣሪያ ማስታጠቅ ሳይሆን፣ መፍትሄን ማምጣት መቻል ነው። የኢራን መንገድ ፍልስጤምን ለጦርነት አውድማነት አሳልፎ የሰጠ ሲሆን፣ የሱኒ ሃገራት መንገድ ግን ህዝቡን ከሞትና ከረሃብ ለመታደግ የሚደረግ ጥረት ነው።
በመሆኑም የጀበሉ ጥያቄ መሰረታዊ የሆነውን “የድጋፍ ግብ” የዘነጋ ነው። ጦር መሳሪያ መስጠት የጥፋት እንጂ የልማት ደጀንነት አይደለም። የሱኒ ሃገራት በዲፕሎማሲው መድረክ ያላቸው ተሰሚነትና የሚያደርጉት ግፊት፣ ከኢራን ጩኸት በላይ ለፍልስጤም ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚሰጥ ነው። እውነተኛ አጋርነት የሚለካው በጦርነት ነጋሪት ሳይሆን በህዝብ ህልውና መረጋገጥ ነው።
የኃይል ምንጭ እና የገበያ ሉዓላዊነት
ጀበሉ አሁንም ይናገራል፣ ኢራን “የጥገኝነት ሰንሰለትን ሰብሮ በራስ እግር መቆም መቻሏን” እንደ ትልቅ ጀብድና አርበኝነት ይቆጥረዋል። ሆኖም ግን በዘመናዊው ዓለም ከዓለም ገበያ ተገልሎ መቆም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ያሳጣል። ኢራን ያላትን የነዳጅ ሀብት በፈለገችው መጠንና ዋጋ መሸጥ አለመቻሏ፣ ሉዓላዊነት ያለ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ትልቅ ማሳያ ነው። በዚህም የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከኤምሬትስ ጋር ሲነፃፃር የሰማይና የምድር ያህል ነው። የኤምሬትስ 50 ሺህ ሲሆን የኢራን 5 ሺህ ነው።
የሱኒ ሀገራት ግን የዓለምን የኢነርጂ ገበያ በመቆጣጠርና ወደ ታዳሽ ኃይል በመሸጋገር “የገበያ ሉዓላዊነትን” አረጋግጠዋል። ሳውዲ አረቢያና ኤምሬትስ በዓለም ነዳጅ ዋጋ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ፣ ማንኛውንም ፖለቲካዊ ውሳኔ ለማስፈጸም እንደ ትልቅ መሣሪያ እያገለገላቸው ይገኛል። ይህ ደግሞ የቀጠናውንና የዓለምን ጂኦ-ፖለቲካና ኢኮኖሚ የመዘወር አቅም ሰጥቷቸዋል። እውነተኛ ነፃነት የሚመጣው ከዓለም ጋር መግባባትና በገበያ ውስጥ ወሳኝ መሆን ሲቻል ነው።
በተጨማሪም የባህረ ሰላጤው ሀገራት የነዳጅ ገቢያቸውን ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በማዛወር ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው። ኢራን ግን አሁንም በነዳጅ ሽያጭ ላይ ጥገኛ ሆና በመቆየቷና ገበያ በማጣቷ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ ወድቋል። ዜጎቿን ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና ለድህነት የዳረገች ሃገር “በራስ እግር መቆም” በሚል መመጻደቋ ትርጉም የለውም።
ስለሆነም አህመዲን ጀበል “የራስን የአቅም ምንጭ መገንባት የማህበረሰቡ የብቃት መለኪያዎች ናቸው” የሚለው ሃሳብ፣ ከዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር ውጭ ትርጉም አይኖረውም። የሱኒ ሀገራት የዓለምን የንግድ መስመር በመቆጣጠር ያገኙት ኃይል፣ ከኢራን የብቸኝነት ጉዞ እጅግ የላቀ ስልታዊ ጥቅም አለው። ሉዓላዊነት ማለት ዓለምን መምራት እንጂ ከዓለም ተለይቶ መቆዘም አይደለም።
በአጠቃላይ የአህመዲን ጀበል ትንታኔ ሉዓላዊነትንና ጥንካሬን በተሳሳተ መነፅር የሚመለከት ነው። በዘመናዊው ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ትክክለኛው ሃይል የሚለካው በቴክኖሎጂ ልዕልና፣ በኢኮኖሚ ጥንካሬና በዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እንጂ፣ ከዓለም ተገልሎ በሚደረግ ወታደራዊ ሽኩቻ አይደለም። የሱኒ ሃገራት የመረጡት መንገድ የዜጎቻቸውን ህይወት የቀየረና ለዓለም ወሳኝ የሆኑበት ብልህ ስትራቴጂ ነው።
ጎበዝ! በስሜት የሚነዱ ትንታኔዎች ተጨባጩን እውነት እንዳይጋርዱብን መጠንቀቅ አለብን። ኢራን ያለችበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ወደ ጎን በመተው፣ ለፈጠረችው “የሀሰት ጥንካሬ” ምስል መማረክ አይገባም። የባህረ-ሰላጤው ሃገራት በዝምታና በስራ የሚገነቡት ታላቅነት፣ ለነገው አስተማማኝ የቀጠናው ሉዓላዊነት ብቸኛው ዋስትና ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






