አዲስ ሪፖርተር – በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጦርነት ሊፈርሱ እንደማይችሉ በውጭ ያሉ የተቃዋሚዎች ስብስባና አብረዋቸው የሚሰር በጋራ መገምገማቸው ተሰማ። በግምገማው መሰረት የጠብመንጃው ትግል እንዳለ ሆኖ፣ በስፋት የ”ከተማ አመጽ” እንዲሁም በዕምነት ተቋማት ውስጥ ያለው ሴል ልዩነቱን እንዲያቀጣጠል አቋም ተይዟል።
አዲስ ሪፖርተር ይህን የሰማችው ከፋኖ የተለያዩ አደረጃጀቶች መካከል የኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባ ኃይሎች አመራር ነው፡፡ የአካባቢው የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ የጠቀሳቸው አመራር እንዳሉት “የከተማ ውስጥ የህቡዕ ትግል ይቀጣጠል” የሚለው መረጃው የደረሳቸው ከሻዕቢያና ትህነግ ጋር በጋር እንደሚሰራ ከሚታወቀው የጎጃም ፋኖ አደረጃጀት ሲሆን፣ እሳቸው ባሉበት የፋኖ አደረጃጀት ውስጥ ለጊዜው የተያዘ አቋም ግን እንደሌለ አመልክተዋል። በዕምነት ተቋማት ውስጥ ስላለውና እንዲደረግ ስለታሰበው ጉዳይ ግን ለጊዜው ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመዋል።
በውጭ አገር ያሉ የመንግስት ተቃዋሚዎች በሚከተሏቸው የተለያዩ የትግል ስልቶችና ከጀርባቸው ባሉ አገራትና ቡድኖች ፍላጎት ሳቢያ አለመግባባት ይታይባቸዋል። በተለያዩ ጊዜያት ከውስጣቸው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዚሁ ልዩነታቸው ሳቢያ አብረው ይታዩ እንጂ የማይዘልቁት ይበዛሉ። አለያም “አብረው ሆነው የተለያዩ ናቸው ” በሚባል ዓይነት ጥምረት ውስጥ ይኖራሉ።
እነዚሁ በውጭ አገር ሆነው በገሃድና በህቡዕ አገር ቤት ካሉ ህጋዊና ህገወጥ አደረጃጀቶች፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት መስረተው የሚሰሩ ጥምረቶች፣ ድርጅቶች፣ ማህበሮች፣ “የሙያ ማህበራት” ነን የሚሉ፣ ሚዲያዎች ወዘተ በየአጋጣሚው ሁሉ ይህ መንግስት ሊወድቅ አንድ ሃሙስ እንደቀረው በልበ ሙሉነት በመናገር የሚታወቁ ናቸው። በአገር ቤትም ቀደም ሲል ትህነግ፣ አሁን በቅርቡ ፋኖ የብልጽግና መንግስትን በሳምንታት ውስጥ እንደሚጥሉ ሲያስታውቁ ነበር።
“የከተማ አመጽ” የተሰኘውንና ኢህአፓ ስሙ በተነሳበት ቦታ የሚታወሰውን የትግል ስልት በገሃድ እንደሚጀምር የጎጃም ፋኖ መሪ ዘመነ ካሴ በይፋ ማስታወቁን ጠቅሰን ዜና መዘገባችን ይታወሳል። ይህ ስልት በህቡዕ ከተማ ውስጥ ተመሳስሎ በመኖር በተለያዩ አግባቦች በተመረጡ ሰዎች ላይ ግድያ፣ አፈና፣ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ ንብረታቸውን ማጥቃትን የሚያካትት እንደሆነ በወቅቱ የሆነውን ያዩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ምስክር ይሰጡበታል። በኢትዮጵያ በጭራሽ ሊደገም የማይገባው፣ ኢትዮጵያ በርካታ ልጆቿን የከሰረችበት፣ ጠባሳውም ብዙ ቤተሰቦች ዘንድ አሁን ድረስ ያልሻረ ስለመሆኑ በስፋት የተጻፈበት የኢትዮጵያ ጥቁር ታሪክ ነው።
አሁን ላይ በጠብመንጃ፣ በሰላማዊ ትግል በአመጽ፣ “በከተማ ውስጥ አመጽ”፣ ሁሉንም በማቀላቀል እንደ ሁኔታው የሚጓዙ፣ ከሁሉም እንዳይሆኑ በፍርሃቻ ወደ አክቲቪዝም የተመለሱ፣ ወዘተ መንግስት በጠብ መንጃ እንደማይወድቅ አቋም መያዛችው ነው የተገለጸው። ይህን አቋም እንደሚያውቁ ነዋሪነታቸው አሜሪካ ያደረጉና አብሮነት ውስጥ የሚሳተፉ ለዲሲ ተባባሪያችን ገልጸዋል።
በኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባ የሚመራው ኃይል አመራር እንደሆኑ የሚታወቁት እኚሁ ሰው ለአዲስ ሪፖርተር የአካባቢው ምንጭ እንዳሉት መንግስት በጠብመንጃ እንደማይወድቅ አቋም የተያዘው በግምት ከወር ተኩል በፊት በወልደያና በላስታ አቅጣጫ የተሞከረው ኦፕሬሽን በሚታወቀው መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ በተደረገ የጋራ ግምገማ ነው። “በሚታወቀው” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ እንዲያብራሩ ተጠይቀው ዝምታን መርጠዋል።
በአካባቢው ሕዝብ በስጋት እንደሚኖር፣ በሚጣልበት ግብርና ቀለብ መማረሩን፣ ትምህርትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመዘጋታቸው ሳቢያ በተስፋ መቁረጥ በርካታ ሴቶች ወደ ሰመራ በመሄድ ጅቡቲን እንደመሸጋገሪያ ለመጠቀም ሲሞክሩ እንደሚያዙ እዲስ ሪፖርተርን ጨምሮ የተለያዩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙ የውጭ አገር ሚዲያዎች በተደጋጋሚ እየዘገቡ ነው።
መረጃውን የሰጡት አመራር ያሉበት ይህ ኃይል አሁን ላይ ደላንታ አካባቢ የተቀመጠ ሲሆን ውጊያም ሆነ ተኩስ እንደሌለ፣ ሕዝቡም ስጋቱ የቀነሰለትና ከመንግስት ጋር መተማመን ፈጥሮ በድርድር ሰላም እንዲወርድ የሚፈልግ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። በዚህ አግባብ አመራሩ ብዙም መረጃ መስጠት እንደማይፈልጉ መረጃውን የላከው የአዲስ ሪፖርተር ዘጋቢ አመልክቷል።
“እንደ ተረዳሁት አገሪቱ ሰላም እንድትሆን ፍላጎት የለም” ሲሉ ለአዲስ ሪፖርተር የተናገሩት ታዋቂ የኦርቶዶክስ መምህር፣ በቀጥታ ከውጭ አገር የተላለፈውን መመሪያ ቃል በቃል ባይሰሙም ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይማኖት መካከል ልዩነት በመፍጠር ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጫረስ እየተሰራ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
እኚህ መምህር እንዳሉት ቤተክርስቲያንን አመራር አልባ አድርጎ በመሳል የዕምነቱ ተከታዮች እንዳይታዘዙ የማድረግ ስራ በዘመቻ እንደሚሰራ አመልልክተው፣ አካሄዱ ቤተክርስቲያኒቱንም፣ ተከታዮቿንም፣ አገርንም ዋጋ እንደሚያስከፍል አስጠንቀቀዋል። ያለቸውን ቤተክርስቲያን በማክበርና በቅርብ አብሮ በመስራት ስህተትም ካለ እንዲታረም ማድረግ እንጂ በደቦ ተቋሚቱን ለማፍረስ በፍትህ ስም መረባረብ መጨረሻው አጉል እንደሆነም አመልክተዋል።
ስማቸውን ለጊዜው መግለጽ ያልፈለጉት በደፈናው መፈረጅ ባለመፍለጋቸው እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ መምህር፣ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ያልሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች ራሳቸውን መሆን ወይም መካከለኛው ስፍራ ሲይዙ እንደሚፈረጁ፣ ፍረጃው ዘመድና ቤተሰብ ሳይመርጥ በጅምላ እንደሆነ በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል። ይህ በዘመቻ የሚካሄድ ፍረጃ በርካቶችን በአገራቸው ጉዳይ ዝም እንዲሉ ጫና እንዳደረገባቸው አመልክተዋ። በቅርቡ ከአዲስ ሪፖርተር ጋር ሰፊ መረጃ በገሃድ እንደሚቀያየሩ አመልክተዋል።
በተደጋጋሚ በአርሲ የተፈጸመውን የንጹሃን ዜጎች ግድያ አስመልክቶ የገዳዮች ማንነት እንዲጣራ የማይፈልጉ መኖራችውን፣ ጉዳዩ ሲነሳም “ለምን ተጠየቅን” በሚል የሚቆጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ጠቅሰን መጻፋችን አይዘነጋም።
እኚሁ መምህር በተመሳሳይ ስለገዳዮች እንዲነሳ የማይፈልጉ ባልደረቦች እንዳሏቸው ገልጸዋል። ዓላማውም ገዳዮቹ ከታወቁ የንጹሃኑን ግድያ ለፖለቲካ አጀንዳነት ወይም በሳቸው አባባል “ ለራሳቸው ፍላጎት እንደ ማገዶ ለመጠቀም ስለማይመች ስለሟቹች እንጂ ስለገዳዮች ማንነት ማንሳት አይወደድም። ይን በትክክል ያየሁት፣ ልቤ የሚያዝንበት ጉዳይ ነው” ሲሉ ይገልጹታል።
ከአሜሪካ ለኢትዮጵያ የትግል ስልት የሚጠምቁላት በኃይማኖቶች መካከልና በተመሳሳይ ዕምነት ውስጥ ልዩነት በመፍጠር አመጽ እንዲነሳ ዕቅድ የያዙት ቡድኖች በተለይም በኦሮሚያ ረብሻ እንዲነሳ የቀድሞውን የ“ድምጻችን ይሰማ” አስተባባሪ ለዕቅዳቸው መሳካት ለመመልመል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ታውቋል። ይህን የገለጹት የአብሮነት አባል እንዳሉት ተጠቃሹ የ”ድምጻችን ይሰማ” አስተባባሪ ምልመላውን ስለመቀበሉና አለመቀበሉ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ ማህበራዊ ገጾች የአርሲ ንጹሃንን ግድያ አስመልክቶ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የሚያመላክቱ ምስሎች እየተሰራጩ ነው። የሚታወቁ ሰዎችንና የኃይማኖት መምህራን ገጽና ስም በመጠቀም የሚሰራጩት ምስሎች የገጹን ባለቤቶችና ምስላቸውን የንቅስቃሴው መሪዎች እንዲጠቀሙ ስለመፍቀዳቸው የሚታወቅ ነገር የለም። አንዳንዶቹን ለመጠየቅ ቢሞከርም ሊመልሱ የሚወዱ ሆነው አልተገኙም።
የኢትዮጵያ የዕምነት ተቋማት ከተለያዩ አካላት ባዋቀረው አጣሪ ኮሚቴ አማካይነት የደረሰበትን የመጀመሪያ ሪፖርት ሲያቀርብ ገዳዮቹ የሸኔና የፋኖ ታጣቂዎች እንደሆኑ የመሰከሩ መኖራቸውን፣ አንዳንዶቹም የገዳዮቹን ማንነት እንደማያውቁ መናገራቸውን ብሪፖርታቸው ማስታወቃቸውና የምርንራው ሙሉ መረጃ በቀርቡ ይፋ እንደሚሆን መናጋራቸው አይዘነጋም። ይህንኑ ሪፖርት በመቃወም በውጭ የሚኖሩ ሚዲያዎች ሪፖርቱ ተባይነት እንዳይኖረው በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ መክረማቸውም የሚታወስ ነው።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





