- አዲስ ሪፖርተር – በዳቮስ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ (ኢሮ) ያስመዘገቡት ዲፕሎማሲያዊ ድል፣ በአፍሪካ ቀንድ ለዘመናት የነበረውን የኃይል ሚዛን የናጠ ታሪካዊ ክስተት ተደርጎ ተወስዷል። ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ወደ ባህር ባለቤትነት ከማቅረቡ ባለፈ፣ በአስመራ እና በካይሮ የሚመራውን “የከበባ ፖለቲካ” የመጨረሻ ምዕራፍ መዳረሱን እያበሰረ መስሏል።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት በዓለም አቀፉ መድረክ “ኢትዮጵያ ወደ ባህር የመውጣት ፍላጎቷን እውቅና እንሰጣለን” ማለታቸው፣ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጡንቻ ትልቅ ግብዓት ሲሆን፣ ይህ ንግግር ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን የኢኮኖሚ ግዙፍነት እና ለጎረቤቶቿ ያላትን የገበያ ፋይዳ የሚያሳይ ነው። በዳቮስ መሰል የኃያላን መድረክ ላይ ይህ አቋም መንጸባረቁ፣ የኢትዮ-ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እንዲያገኝ በር ይከፍታል።
ኤርትራ ለሦስት አስርት ዓመታት የገነባችው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሁለት “ፈረሶች” ላይ የቆመ ነበር፤ ግብፅ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የብጥብጥ ኃይሎች ውስጥ፣ ዛሬ ሁለቱም ፈረሶች እየወደቁ ነው።
ካይሮ በአባይ ጉዳይም ሆነ በቀይ ባህር ፖለቲካ ያላት ተሰሚነት እየተሸረሸረ ሲሆን፣ ትራምፕ በዳቮስ “ታላቅ ጓደኛዬ” ቢሏቸውም፣ በተግባር ግን አሜሪካ ከግብፅ ይልቅ ለቀይ ባህር ጸጥታ ኢትዮጵያንና ሶማሊላንድን እንደምትመርጥ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ኤሪክ ትራምፕ የጀመሩት ንግግር ማሳያ ነው።
በሀገር ውስጥ በኤርትራ ይረዱ የነበሩ ታጣቂዎች እጅ መስጠታቸው፣ አስመራ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን “የማዳከም” አቅም አሳጥቷታል። ኤርትራ አሁን ያለችበት አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እሱም እንደ ሶማሊላንድ ሁሉ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት በድርድር ማስተናገድ። የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦች ያለ ኢትዮጵያ ገበያ “የድንጋይ ክምር” ሆነው እንደሚቀሩ አስመራ በሚገባ ትረዳለች።
ኤርትራ ከግብፅ ጋር ያላትን “ስውር ጋብቻ” ፈትታ፣ የቀይ ባህርን ሰላም ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የምታስከብርበት ጊዜ እጅግ ቀርቧል። ይህ ካልሆነ ግን በሶማሊላንድ በኩል የሚከፈተው በር ኤርትራን ከቀጠናው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውጭ ያደርጋታል።
በቀይ ባህር አካባቢ ያለው ውጥረት (የሁቲዎች ጥቃት እና የታላላቅ ኃይሎች ፉክክር) ኢትዮጵያን የግድ የባህር ኃይል ባለቤት እንድትሆን አስገድዷታል። የሶማሊላንድ አጋርነት ይህንን የባህር ኃይል ግንባታ ሕጋዊ መሠረት ይሰጠዋል።
የቀይ ባህር ሞገድ ዛሬ የኢትዮጵያን የከፍታ ድምፅ እያስተጋባ ሲሆን፣ የሶማሊላንድ ድፍረት የኤርትራን ዝምታ የሚሰብር፣ የግብፅን ሴራ የሚያመክን ነው። ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ ትከሻ ላይ ቆማ ሳይሆን፣ ከጎረቤቶቿ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ወደ ባህር ትገሰግሳለች።
ኤርትራ ታሪካዊ ዕድሏን ተጠቅማ የሰላም እጇን የምትዘረጋበት ሰዓት አሁን ነው!” ሊንኩን ላይክ በማድረግ ወቅታዊና ጂኦፓለቲካዊ መረጃዎችን በትንታኔ ይኮምኩሙ።
መሐመድ ስራጅ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






