Addisreporter – የአሜሪካ ጦር ሰራዊት መስሪያ ቤት (Department of War) ማህበራዊ ሚድያን መሰረት ያደረገ የስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ጥብቅ የሆነ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል።
እንደ መግቢያ
የአሜሪካ ጦር ሰራዊት መስሪያ ቤት (Department of War) ማህበራዊ ሚድያን መሰረት ያደረገ የስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ጥብቅ የሆነ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል።
ከላይ በርዕሱ በቀረበው አሳብ ዙሪያ የቀረበው ማመላከቻ ጽሁፍ የአገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮችም ይሁኑ መንግስት መረጃ የላቸውም ወይም መረጃው ኖራቸው ዝምታን መርጠዋል ከሚል እሳቤ አይደለም። ይልቁኑም እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመጠቆም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መተግበሪያውን ካቀረቡት ባለቤቶቹ ፍላጎትና ዓላማ አንጻር ሊቀኝና ልጓም ሊበጅለት እንደሚገባ ለማሳሰብ ነው።
በተለይም ጽሁፉ ማዕከል ያደረገው የአገር መከላከያ ሰራዊትን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሊፈትኑ ከሚችሉ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች የደህንነት ስጋት አንጻር የሰራዊቱ አባላት አጠቃቀምን አስመልክቶ ዛሬ ነገ ሳይባል ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማረቂያና የጥንቃቄ እርምጃዎች ስጠቁም ፍጹም አገርን ከመውደድ አንጻር ብቻ እንዲሆነ ቀድሞ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
ነጻ አስተያየት በአለባቸው ጉብሳ
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ጦር ሰራዊት መስሪያ ቤት (Department of War) ዋና ፀሃፊ የሆኑት ፔት ሄግዜን የሃገሪቱን ከፍተኛ መኮንኖች ሰብስቦ ስለአዲሱ ወታደራዊ ዶክትሪን የሰጠው መግለጫ ነው። ትኩረቴን የሳበው ማህበራዊ ሚድያዎች በሳይበር ግንባር (Cyber space Domain) ላይ ከፍተኛ የስጋት ተጋላጭነት እየፈጠሩ እንደሆነ የገለፀው ነው።
ዋና ፀሃፊው እንደገለፁት የጠላት የዲጅታል ታጣቂዎች ማህበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም ሉዓላዊ የግዛት ድንበር ሳይበግራቸው ወደ ሃገር ውስጥ ዘልቀው በመግባት የአዕምሮና የስነልቦና ጦርነትን (Psychological warfare) በበላይነት እየመሩ እንደሆነ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ልቅ የሆነ የሰራዊቱ አባላት የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም የወታደራዊ ግዳጅ እቅድ ደህንነትንና ሚስጢራዊነትን (Operational Security)፣ ወታደራዊ የአመራርና ዓላማ አንድነትን እና የሰራዊቱን ሕዝባዊ አመኔታን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከባድ ፈተና ውስጥ ጥለውታል ብሏል።
ከዚህ አንፃር የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና የትራምፕ አስተዳደር አመራሮች ቀይ ባህር ላይ የንግድ መርከቦችን በማጥቃት የባህር ላይ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ ሲያስተጓጉል የነበረውን የሁቲ አማፅያን ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ወታደራዊ ግዳጅ እቅድ ዙሪያ በማህበራዊ ሚድያ የመልዕክት ሳጥን በመጠቀም በፅሁፍ ሲወያዩ በስህተት ጋዜጠኛ እንዲሳተፍ በማድረጋቸው ሙሉ መረጃው ለህዝብ ይፋ ሊሆን ችሏል። ይህም መረጃውን የሁቲ አማፅያን እንዲያገኙት በማድረግ የግዳጁን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥለው ችሏል።

እንዲሁም የሰራዊቱ አባላት ማህበራዊ ሚድያን በመጠቀም ከፍተኛ መኮንኖችን በመተቸት እና በመዝለፍ የአመራር እዝንና ጓዳዊ አንድነትን እየሸረሸሩት ይገኛል። የሰራዊቱን የፓለቲካ ገለልተኝነት የሚጎዳ መልዕክት በማስተላለፍ እንዲሁ የሠራዊቱን የህዝብ አመኔታን እያሳጡት እንደሚገኝ ገልጿል።
በመሆኑም ይህን ማህበራዊ ሚድያን መሰረት ያደረገ የስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ጥብቅ የሆነ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል።
የራሽያና ዩክሬን ጦርነት እንደ አብነት
ይህ ችግር የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃገራትም በሰፊው እየተስተዋለ ይገኛል። ራሽያ ዩክሬንን ለመውረር እየተሰናዳች እንደሆነ የታወቀው የራሽያ ወታደሮች ወደ ግንባር ለመዝመት ቤተሰቦቻቸውን ሲሰነባበቱ የሚያሳይ ቪድዮ በማህበራዊ ድረገፅ ባጋሩበት ቅፅበት ነበር። እንዲሁም የዩክሬን ወታደሮች ግንባር ላይ ሆነው በቀጥታ ቪድዮ በማህበራዊ ድረገፅ ያሉበት ሁኔታ ሲያሰራጩ የራሽያ ጦር ሰራዊት መረጃውን በመተንተን የሚገኙበትን ትክክለኛ አካባቢ (geolocation) ለይቶ በማወቅ ጥቃት ሊያደርስባቸው ችሏል። የራሽያ ጦር በተቆጣጠራቸው ግዛቶች የሚገኙ የዩክሬን ዜጎች የሳትላይት ኢንተርኔት በመጠቀም በማህበራዊ ሚድያ የራሽያን ወታደሮች በፎቶና በቪድዮ በመቅረፅ መረጃ ለዩክሬን ጦር በማቀበል ለወታደራዊ ኢላማ እንዲጠቀሙበት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፈተና
ይህ ማህበራዊ ሚድያን መሰረት ያደረገው የወታደራዊ ግዳጅ ደህንነት የስጋት ተጋላጭነት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግዳጅ ላይም በከፍተኛ ደረጃ እየተስተዋለ እንደሚያደርግ ይታመናል። ይህ ስጋት የሚመነጨው በዋናነት ከቴክኖሎጂ እና ከወታደራዊ ዶክትሪን/ ዲቺፕሊን ክፍተት ነው። ይህን ዘመንኛ ቀውስ በፈርጅ በፈርጁ እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
የቴክኖሎጂ ተጋላጭነት
ከቴክኖሎጂ አንፃር ማህበራዊ ሚድያ መተግበሪያዎች በሌላ ሃገራት ባለሙያዎች የለሙና የሚተዳደሩ በመሆኑ ለደህንነት ስጋት ተጋላጭ እንደሚያደርጉ አያጠያይቅም። መተግበሪያው የኛ/ የአገራችን ስላልሆነ ማን ምን እንደሚያይ፣ የተጠቃሚ እንቅስቃሴን ማረጋገጥ እና ሶፍትዌሩ ራሱ ደህንነቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም
በዚህ መነሻ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች በእነዚህ መልዕክት መለዋወጫ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ወታደራዊ ግዳጅና ተመሳሳይ እቅዶች ዙሪያ በድምፅ ወይም በፅሁፍ ገንኙነት ሲያደርጉ የግዳጁን ደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሚያስገባው መታወቅ አለበት። ለዚህም ነው፣ ብዙ ጊዜ ወታደራዊ መረጃዎች ከነዚህ መተግበሪያዎች ተመንትፈው ጠላት እጅ የሚገቡት። በዚህ ሳቢያ አንዳንዴም ግዳጆችም በታቀደላቸው መልኩ የማይሳኩበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህም በተጨማሪ የእነዚህ መተግበሪያዎች ባለቤት ሃገራት ብሄራዊ የተፅዕኖ አቅም (National Instrument of power) መሆናቸውን ማወቅ የችግሩን ግዙፍነት በወጉ ለመረዳት ያስችላል።
የመተግበሪያዎቹን ባለቤቶች ስልተቀመራቸውን በጠቀም በጥላትነት የፈረጁትን ሃገር ህዝብ፣ ቡደን እና ግለሰብ የሚፈልጉትን ድርጊት፣ ባህሪ፣ እምነት እና አመለካከት እንዲያመጣ ወይም እንዲያሳይ ለመቅረፅ ይጠቀሙበታል። በዚህም በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመንን በመሸርሸር፣ ዲሞክራሲ ተቋማትን በማዳክም እምነት እንዳይጣልባቸው በማድረግ፣ የሲቪሉና ወታደራዊ አመራሩ እንዳይተማመን፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጠራጡ በማድረግ፣ ከሕግና ከግብረ ገብነት የሚመነጩ የመከባበር፣ የመተባበርና የመረዳደት እሴቶች እንዲላሉ በማድረግ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ አድርጎ መንግስትን በማዳከም ሃገር እንዲፈርስ ለማድረግ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ያውሏቸዋል። ለዚህም ነው፣ ባለፈው ሳምንት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔታናሁ ካቢኔውን ሰብስቦ ቲክቶክና የቀድሞው ቲውተር የአሁኑን ኤክስ እንደ ጦር ግንባር መሳሪያዎች (tools of battle) አድርጎ በመፈረጅ ከወዳጆቻችን አሜሪካኖች ጋር ተነጋግረን መሳሪያዎችን መጠቀም እንዳለባቸው የገለፀው።
ቻይናም እንደ ደህንነት ስጋት በመቁጥር የአሜሪካ መተግበሪያ የሆኑትን ፌስቡክ፣ ኤክስ፣ ጎግል እና ሌሎች ማህበራዊ ሚድያዎችን እንዳይሰሩ ከልክላለች። በአንፃሩ አሜሪካም በቻይና መንግስት ኩባንያ ባለቤትነት ሲተዳደር የነበረውን ቲክቶክ አሜሪካ እንዲሸጥላቸው ባደረጉት ጫና አስገድደው ሊገዙት ችለዋል። ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ሌሎች ሃገራት እንዲሁ ቲክቶክ ላይ ገደብ አድርገዋል። በአጠቃላይ፣ ማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ራሳችን አልምትን በባለቤትነት ማስተዳደር እስካልቻልን ድረስ ወታደራዊና ብሄራዊ የደህንነትን ስጋት ምንጭ መሆናቸውን መረዳት ይገባል።
የወታደራዊ ዶክትሪን ክፍተት
የወታደራዊ ዶክትሪን ክፍተት ወይም የአፈፃፀም ውስንነት ምክንያት ማህበራዊ ሚድያዎች በኢትዮጵያ መካላከያ ሰራዊት የግዳጅ አፈፃፀም ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛል። ይህ ችግር የሚመነጨው ከሰራዊቱ አባላት ብቻ ሳይሆን ከሲቪል አመራሩና ከአንቂዎች ጭምር ነው። የሰራዊቱ አባላት የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የጦር ግንባር እንቅስቃሴዎችን ያሳያሉ። በዚህም ጠላት ያሉበትን ቦታ (geolocation)፣ የታጠቁትን መሳሪያ እና ሌሎች ወታደራዊ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኝ እድል ይፈጥርለታል። ይህም የሰራዊቱን የመረጃ የበላይነት በማሳጣት ግዳጁ በታቀደው መልኩ እንዳይፈፀም ያደርጋል። ለዚህ ግዳጅ የወጣው ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ከመባከኑም በላይ ከፍተኛ ለሆነ የሕይዎትና የንብረት ጉዳት እንደሚዳርግ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ የሰራዊቱ አባለት በቲክቶክና መሰል ማህበራዊ ሚድያዎች በመጠቀም ከፅንፈኞች ወይም ከሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ግልፅ በሆነና በቀጥታ የቪድዮና የድምፅ ውይይቶች ላይ በመሳተፍ፣ የፅንፈኞች መልዕክቶችን በመውደድ፣ በማጋራት እና አስተያየት በመፃፍ (like, share, subscribe and comment) የሰራዊቱን ክብር እና የሕዝብ አመኔታ እየሸረሸሩ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የሰራዊቱ አባላት ልቅ የማህበራዊ ሚድያ ተሳትፎ በጠላት የስለላ ወኪሎች ዒላማ እንዲሆኑ ወይም ለዒላማቸው ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። በሌሎች ሃገራት እንደተስተዋለው የስለላ ወኪሎች የሰራዊቱ አባላትን ማህበራዊ ሚድያ ላይ ክትትል አድርጎ በማጥመድና በማታለል ወሳኝ ወታደራዊ መረጃዎችን ለመውሰድ ችለዋል። የኛም ሃገር የሰራዊት አባላት ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ሊያመልጡ አይችሉም።
ቁጥጥርና ሃሳብን የመግለፅ መብት
ሌሎች ሃገሮች ከማህበራዊ ሚዲያ የሚመነጩ የስጋት ተጋላጭነቶችን ለመቀነስ ጥብቅ የሆነ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ፓሊሲና ወታደራዊ መመሪያ አውጥተው እየተገበሩ ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ በማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚጣለው ገደብ “ሃሳብን ከመግለፅ ህገ መንግስታዊ መብት ጋር አይጋጭም ወይ?” የሚለው ነው። በመሰረቱ ሃሳብን የመግለፅ መብት ፍጹም አይደለም በተለይ ደግሞ የሃገር ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ። በመሆኑም የዕዝ ሞራልንና አድነትን፣ የግዳጅ እቅድ ዝግጅትና አፈፃፀም ሚስጢራዊትን፣ የሰራዊቱን የፓለቲካ ገለልተኝነትን በመጠበቅ የህዝብ አመኔታን ለማጠናከር እና የሃገር ደህንነትንና ፀጥታን ለማስከበር ሲባል የሰራዊቱ አባላት በማህበራዊ ሚድያ ሃሳባቸውን የመግለፅ መብታቸው ከሲቪሉ ማህበረሰብ በተለየ ሊገደብ ይችላል። ወታደራዊ ተቋም ከሲቪል የሚለየውም ጥብቅ በሆነ ስርዓትና ድሲፕሊን የሚመራ መሆኑ መረዳት ይገባል።
በመሆኑም መከላከያ ሰራዊት የአባላቱን የማህበራዊ ሚድያ ተሳትፎ ለመገደብ የሚያችል ጥብቅ የሆነ ወታደራዊ ዶክትሪንና መመሪያ በማውጣት ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሳይበር ደህንነት እና የስለላ ተግባራት ለአባላቱ በየወቅቱ የስልጠና አቅም ግንባታ በመስጠት የወታደራዊ ግዳጅ ስጋት ተጋላጭነቱን ለመቀነስ፣ የአመራርና የዓላማ አንድነቱን እና የሕዝብ አመኔታውን ለመጠበቅ መስራት ይገባዋል።