አዲስ ሪፖርተር ጥቅምት 11 ቀን 2018 – ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የእንስሳት መኖ ላይ ተጥሎ የቆየው ተጨማሪ እሴት ታክስ ሊነሳ መሆኑን ተገለጸ፡፡ የመንግስት ውሳኔ ሰጪ አካላት በተያዘው ጥቅምት ወር መጨረሻ ባሉ ጊዜያቶች ውስጥ የውሳኔ ሐሳብ ሊሰጡበት እንደሆነ ተገልጿል።
በእንስሳት መኖ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተከትሎ በእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦች የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉንና ይህን ችግር ለመፍታትም ታክሱን ለማንሳት በመንግሥት በኩል እቅድ መያዙን የገንዘብ ሚኒስቴር በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ መመርያ ሰነድ ላይ አስታውቋል።
በመመርያው፣ በእንስሳት መኖ ላይ ተጥሎ የቆየውን ታክስ እንደሚነሳ ያመላከተ ሲኾን የውሳኔ ሰጪ ካቢኔ ከፀደቀ በኃላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል። ተጨማሪ እሴት ታክሱ ከዚህ ቀደም እንዲነሳ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም መንግስት ባቀረባቸው አንዳንድ ምክንያቶች የተነሳም እንደገና ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የእንስሳት መኖ እንዲሻር ያቀረበው ሐሳብ እንደሚገልፀው በቅርቡ በእንስሳት ተዋፅኦ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ ያለመ መኾኑን ጠቅሶ፣ መንግስት የእንስሳት ሐብትን ለመጠቀም የተያዘው እቅድ ለማሳካት ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳ ከውሳኔ ላይ መደረሱን በቀረበው ሰነድ ላይ አመላክቷል።
ለዚህም እንደምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠመ ያለውን ፈተናን ጨምሮ፣ የእንስሳት መኖ በአለማቀፍ ደረጃ የተከሰተው እጥረት እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉ አምራቾች በቂ አለመሆናቸውን ተከትሎ በዘርፍ የተጋረጠውን ችግር ለመቅረፍ ያለመ ወሳኔ ነው ተብሏል።
ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ መመርያ አጠቃላይ በእንስሳት መኖ ላይ የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳ ምክረሐሳብ ማቅረቡን ገልፆ ጉዳዮ የመንግስት ውሳኔ ሰጪ ካቢኔ ይሁንታ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል። የውሳኔ ሐሳቡም እስከ ጥቅምት መጨረሻ ባሉ ጊዜያቶች ውስጥ ይፀድቃል ተብሎ እየተጠበቀ መኾኑን መረጃው አመላክቷል።
በተለይም የዶሮ መኖ በገበያው እንደልብ ማግኘት አለመቻሉን አስቸጋሪ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ መኖሩንና ለዚህም በእንቁላል ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት ማድረጉን ተነግሯል። አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የክልል ከተሞች እየተስተዋለ ያለውን ንረት አንዱን የዶሮ እንቁላል ዋጋ ከሐያ ብር በላይ ሲሸጥ መሰንበቱን ተገልጿል።
በዚህ መሰረት ተጠባቂውን የግብር ማሻሻያ በተለይም የስጋ፣ የወተትና የእንቁላል ዋጋን ለማረጋጋት ያስችላል የሚል እቅድ እንዳለና መሰረታዊ በሆኑት የእንስሳት ተዋፅኦዎች ዋጋ ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ በማሻቀቡ የተነሳም መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ውሳኔ ነው ተብሏል።
በገንዘብ ሚኒስቴር በተያዘው በጀት አመት ይፋ ካደረጋቸው እቅዶች መካከል የተቀቀለ የእንስሳት ስጋን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ገልፆ የነበረ ሲኾን የእንስሳት መኖ አቅርቦቶች ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየሰራ መኾኑን ተናግሯል። ከእቅዶቹ አንዱ በእንስሳት መኖ ላይ የተጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ ማንሳት ግንባር ቀደሙ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል፣ በዘርፉ ያሉ ምጣኔ ሐብት አከናዋኞች እንደሚሉት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን ታክሰ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርበው የስጋ ምርት ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱንና አገሪቱ ካላት የእንስሳት ሐብት አንፃር የሚጠበቀውን ያህል መጠቀም እንዳይቻል ማድረጉን መንግስት ላይ ወቀሳ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የሚታወስ ነው።




