አዲስ ሪፖርተር ዜና – የባሕር በር ለአንድ ሀገር የሉዓላዊነት፣ የክብር፣ የስትራቴጂክ ጠቀሜታ እንዲሁም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አቅም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። የባሕር በር ከሌለ ገበያው የጎረቤት ሀገር ብቻ ሲሆን፣ ወደብ አልባ ሀገራትም የጎረቤቶቻቸው እስረኞች ለመሆን ይገደዳሉ።
ደማቁ የታሪክ ማህደር፦ ከአዱሊስ እስከ ዜይላ ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ የባሕር በር ባለቤት የነበረች እና በራሷ ከዓለም ጋር ስትገበያይ የኖረች ሀገር መሆኗን የታሪክ ማስረጃዎች በሚገባ ያሳያሉ። በሀገራችን ወደብ በተደራጀ መልኩ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ገና በአክሱማውያን ዘመን ነበር።
አክሱማውያን እና ከእነሱ በፊት የነበሩት የዳማት ነገሥታት በአዱሊስ ወደብ በመጠቀም ከግሪክ እና ከባዛንታይን ነገሥታት ጋር ይገበያዩ ነበር። በዚህም የዳማት ልዑላን እና አክሱማውያን ነገሥታት እጅግ እንደከበሩ እና መንግሥታቸውንም ገናና ያደረጉት ከዚህ ንግድ በሚገኝ ገቢ እንደነበር ፕላይኒ ትልቁ በጽሁፉ አብራርቷል።
የአክሱም መንግሥት መዳከም ኢትዮጵያን የባሕር በር አላሳጣትም ነበር። የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ላሊበላን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቋቋሙት መንግሥታት የምጽዋን ወደብ ለፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ፍላጎታቸው ማሳኪያነት ይጠቀሙበት ነበር።
በኦቶማን ቱርኮች ጫና ሲፈጠር ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት ፊታቸውን ወደ ሕንድ ውቅያኖሷ ዜይላ ወደብ በማዞር የአርጎባ ሕዝቦችን በመጠቀም ዜይላን የኢትዮጵያ ዋና ወደብ አድርገውት ነበር። በኋላም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከፈረንሳይ ጋር ባደረጉት ስምምነት ጅቡቲን በሚገባ ተጠቅመውባታል።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እ.አ.አ በ1876 ዓ.ም ለንጉሥ ኡምቤርቶ በላኩት ደብዳቤ የዜይላን በር ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ የባሕር በር ባለቤትነታቸውን ለማስከበር ያደረጉትን ዲፕሎማሲያዊ ትግል ያመላክታል።
ይህ የሚያሳየው፣ ሀገራችን በውጭ ኃይሎች ወረራ ተግዳሮት ቢገጥማትም፣ በየጊዜው የተፈራረቁት ነገሥታት የባሕር በርን ለማስከበር ሁለገብ ትግል ከማድረግ የቦዘኑበት ጊዜ አለመኖሩን ነው።
የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍልሚያ
ዛሬ ላይ የቀይ ባሕር አካባቢ ከፍተኛ የዓለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግበት እና በርካታ ሀገራት ኃይላቸውን የሚያሳዩበት ስትራቴጂያዊ ቀጣና ሆኗል። በቀጣናው ያሉ ኃያላን ሀገራት ከባሕር ውንብድና ጋር በተያያዘ በሚል ሰበብ በጅቡቲ ላይ ወታደራዊ ካምፕ መስርተው ከከተሙ ቆይተዋል። እነዚህ ኃያላን ሀገራት ግዙፍ ወታደራዊ ሰፈሮችን የገነቡ ሲሆን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እና ዘመናዊ የጦር መርከቦችን በቀጣናው አሰማርተዋል።
ከሩቅ ከሚመጡት ኃያላን በተጨማሪም የቅርብ ሀገራትም ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር እጅግ በተወሳሰበ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ይህ የኃያላኑ ፉክክር በቀጣናው ሊፈጥር የሚችለው ግጭት ለኢትዮጵያና ለመሳሰሉት የአካባቢው ሀገራት ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የደቀነ ነው።
ፍትሐዊ ያልሆነው እጣ ፈንታ
አሰብ በደቡባዊ ቀይ ባሕር ጫፍ የሚገኝ ወደብ ሲሆን፣ ኤርትራ ነፃ በወጣችበት ጊዜ አሰብ የኤርትራ አካል አልነበረችም፤ ይልቁንም ራስ ገዝ አስተዳደር ነበረች። ሆኖም ኤርትራ አሰብን በሕገ-ወጥ መንገድ በመጠቅለሏ ኢትዮጵያ የባሕር በሮቿን ተነጥቃ በዓለም በህዝብ ቁጥር ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር ሆናለች።
በኢትዮጵያ ወሰን እና በቀይ ባሕር መካከል ያለው ርቀት ከ60 ኪሎ ሜትር ያነሰ ቢሆንም፣ የሀገራችን ወጪ ንግድ እና ስትራቴጂያዊ ደኅንነት ግን በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል። ፕሮፍሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም በመጽሐፋቸው እንደሚያስረዱት፣ በሕዝብ ብዛት ግዝፈቷ እና ለባሕር ባላት ታሪካዊ ቅርበት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር መሆን አይገባትም።
የአልጀርሱ ሥምምነት የወደብ ባለቤትነት መብትን ለማስከበር ጥሩ አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው ሳይነሳ መቅረቱ ለወደፊቱም የሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው። የማዕበል ሽውታ እና የባሕር ጠረን ለዘመናት የኢትዮጵያ የነፃነት እና የብልፅግና ታሪክ አካል ነበሩ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈችባቸው መነሳት እና መውደቆች ከባሕር ጋር ከነበራት ቅርበት እና ርቀት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። የባሕር በሮቿ በእጇ በነበሩበት ዘመን የጎለበተች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን መመስረት የተቻለ ሲሆን፣ በሯን በተነጠቀችበት ጊዜ ግን ኢኮኖሚዋ የኮሰሰና ፖለቲካዋ የተናጋ ሆኗል።
በእርግጥም የባሕር በር ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን የሚገባት ታላቅ ሀገር ናት። ታሪካዊ መብቷን፣ የሕዝብ ብዛቷን እና እየተወሳሰበ የመጣውን የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ግምት ውስጥ በማስገባት የባሕር በርን ማረጋገጥ የቅንጦት ሳይሆን የሥልውና ጉዳይ ነው።
የአሁኑ ትውልድ ያለፈውን ደማቅ ታሪክ ጠንቅቆ በመረዳት፣ በቀጣናው ካሉ ጎረቤቶቹ ጋር በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ዳግም ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ ተነስቷል። የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በየብስ ላይ ብቻ ሳይሆን በባሕርም ላይ የተፃፈ ነው። ይህን ታሪካዊ አደራ ከዳር ማድረስ የትውልዱ ጽኑ ቃል ኪዳን ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






