የሽግግር መንግስት ቀመኞች ከአሜሪካ ወደ አምስተርዳም ፤ በባንዳነትና ማሕጸን ውስጥ ድሮ የተወለደው “አዲሱ ፍኖተ ካርታ”

Date:

በአለባቸው ጉብሳ

ባልንጀራየ ሰሞኑን አምስተርዳም ውስጥ በተካሄደ የዲያስፓራ የኢትዮጵያ የፓለቲካ “ሊህቃን’ ስብሰባ ሰነድ እንደሆነ ገልፆ እንዳነበው በመልዕክት ሳጥን ላከልኝ። የሰዎቹን ከንቱነት ስለማውቅ አንብቤ አስተያየት ለመስጠት አልፈለኩም ነበር። ሳስበው ግን ይህ አቋሜ ተገቢነቱ አልታየኝም። በሰነዱ አንዳንድ ነጥቦች ዙሪያ የግል ምልከታየን ባቀርብ ይበጃል ብየ ስላሰብኩ ብዕሬን አንስቻለሁ። እነሆ።
ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር የሚችልን የፖለቲካ ሽግግር ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ያቀርባል። ሰነዱ “የለውጥ ኃይሉ” አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ወይም መንግስትን ወደ ድርድር ሲያስገድድ ስለሚቋቋመው የሽገግር መንግስት፣ ሕገ መንግስት ማሻሻያ እና ሀገራዊ ምርጫ በማካሄድ ቋሚ መንግስት እስከሚመሰረትበት ድረስ ያለውን ሂደት በተመለከተ በቀቢፀ ተስፋ የተሞላ ምኞታዊ (aspirational) ሰነድ ነው።
ይህ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ከአሁናዊ የሃያላን ሃገራት ስትራቴጂክ ፉክክር፣ ከመንግስት አሁናዊ ተጨባጭ ብሄራዊ የተፅዕኖ መሳሪያዎች አቅምና ይዞታ አንፃር እና “ከለውጥ ሃይሉ” ልምድና አቅም ማነስ አንፃር የእቅዱን ገቢራዊነት በመፈተሽ ቀቢፀ ተስፋ መሆኑን ለማሳየት እንሞክራለሁ።

ቆሞ ቀሩ ተቸካዩ ስብስብ…

በአምስተርዳም ስብሰባቸው ሊመክሩበት ያዘጋጁት ይህን ሰነድ የተዘጋጀው ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ የፓለቲካ ቁማር ተበልተው እርቃናቸውን የቀሩ እና ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ምህዳር ገለል ማለት የማይፈልጉ፣ ወይም ያማይችሉ ዕድሜ ጠገብ “ልሂቃን” ተብዬዎች ናቸው።

እነዚህ ተሸናፊዎች በአብዮቱ የተማሪዎች ትግልና ሽግግር፣ ደርግን ለመጣል በተደረገ የትጥቅ ትግልና ሽግግር እንዲሁም ትህነግ ኢህአዴግን ለመጣል በተደረጉት ትግል ተሳትፈው በመጨረሻም የተሸነፉ ናቸው። ሽንፈታቸው በፈጠረባቸው ታህታይ ምስቅልና፣ ብስጭትና ቂም በቀል ራሳቸውን በማታለል የሚታገሉ፣ የገሃዱን ዓለም ተጨባጭ እውነታ እንዳይረዱ አይናቸውን የጋረደባቸው ከንቱ ፍጡራን ናቸው ማለት ይቻላል።
ይህ ሰብስብ በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ የሚያደርጋቸው የበቀልና የጥላቻ ፓለቲካ ካልሆነ በስተቀር የጋራ የፓለቲካ ኢኮኖሚ ራዕይ፣ የግዛት ፍላጎት እና ጥቅም የላቸውም። በሰነዱ ላይ “እነዚህ ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች በጋራ የተቀናጀ ፕሮግራም ባይኖራቸውም…..” በማለት ላይግባቡ በጋራ ጠላታቸው እንደተግባቡ አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራሉ።

እነዚህ ስብስቦች “መንግስትን እንጣለው እንጂ ሌላው በኋላ ይደርሳል” የሚሉ ስለሃገር ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ሃላፊነት የማይሰማቸው አርቆ ማሰብ የተሳናቸው ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። እንኳን በሃገር የሕዝብ አስተዳደር ውስጥ ልምድና እውቀት ሊኖራቸው ቀርቶ የሕብረተሰብ መሰረት የሆነውን የቤተሰብ ተቋም በአግባቡ መምራት ያልቻሉ ገቢራዊ ዕውቀትና ልምድ አልቦ ናቸው። ሕዝብን ነፃ ሊያወጡ ቀርቶ ማህበራዊ ፍትህን በተግባር ያልኖሩ፣ ዜግነታቸውን ቀይረው በሚሰፈርላቸው ድርጎና ድጎማ ሕይወታቸውን የሚመሩ ከቁሳዊ ሰቀቀን ነፃ ያለወጡ ናቸው። የሽንፈት የነፃነት ትግል ታሪካቸው ከማነብነብ ውጪ በሲቪል ሕይወታቸው ለአዲሱ ትውልድ አርኣያ ሰብ ለመሆን የማይችሉ እንደ ጋሪ ፈረስ ግራና ቀኝ የማያዩ ቁሞ ቀር ወይም ተቸካዮች ናቸው።

ቁሳዊ ሰቀቀን ባንዳነትን ስለማዋለዱ …

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው እነዚህ ሊሕቃን ብስጭትና ቂም በቀል የወለደውን የሽግግር መንግስት እቅድ የፓለቲካ ሉዓላዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ ዳር ለማድረስ ቁሳዊ ሰቀቀናቸው አይፈቅድላቸውም። ሰቀቀን ዋነኛው ተጨባጭ መሰናክል ነው። ገንዘብ ከሌለህ ማናቸውንም የፓለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አትችልም። ነዳጁ ገንዘብ ነውና። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ይህን ሰቀቀናቸውን ለመቅረፍ ብቸኛ አማራጫቸው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ተልካሻ ምክንያት ሉዓላዊነትን በሰላሳ ዲናር ሽጦ ተላላኪ ባንዳ መሆን ነው። የሰቀቀናቸው ግዝፈት ህሊናና ልቡናቸው ዘግቶባቸው እንጂ የሌላ ሃገር ተላላኪ፣ ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆን ሃገርን ከማዳከም ውጪ ሌላ አንዳችም ፋይዳ እንደሌለው ማንም የሚረዳው የዘመናችን እወነት ነው። እንኳን ህዝብን ነፃ ማውጣት ቀርቶ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥናትና ምርም ዳይሬክተር የነበረው ፓሊን ኮል “The bottom billion” በተሰኘው መፅሃፉ “ነፃ አውጪ ከራሱ ሰቀቀን ነፃ ካልሆነ በስተቀር ሕዝብን ነፃ አያወጣም” በማለት ሻዕቢያንና ትህነግን በምሳሌነት ጠቅሶ ያስረዳል።

እነዚህ ሁለት ሃይሎች በነፃነት ትግል ስም የውጭ ሃይል ተላላኪ በመሆን በገንዘብ፣ በስልጠና፣ በትጥቅና ስንቅ ድጋፍ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷን እንድታጣ፣ ሕዝብንና ሃገርን ወደ ብልፅግና የሚወስዱ ትልልቅ የልማት ውጥኖቿ እንዲስተጓጎል እና ጂኦስትራቴጂክ ቁመናዋ እንዲኮሰስ በማድረግ ሃገርን ከማዳከም ውጪ ሕዝብን ነፃ አላወጡም። የተለየ ትንታኔ የሚያቀርብ ካለ ለሙግት ዝግጁ ነኝ።

“በአብዮቱ” ወቅትም እንዲሁ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማህበራት ስም በሕቡዕ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው የጃንሆይን አስተዳደር በመጣል እና ወታደራዊ መኮንኖች የደርግ ስብስብ እጅ እንድትወድቅ በማድረግ ሃገሪቱ ወደ ሶስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የምታደርገው ጉዞ አደናቀፉ። ርሃብና ስደት መለያ አርማችን ሆነ። ኢሳት በሻዕቢያ የመቶ ሺ ዶላር እንደተቋቋመ ከአንዳርጋቸው ፅጌ አንደበት የሰማነው እውነታ እዚህ ላይ ማስታወስ ግድ ይላል።

አሁንም የዚህ ሰነድ አዘጋጆች ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሃገራት ተጉዘው አምስተርዳም ለመሰባሰብ የተገደዱበትን ምክንያት ለዛሬው ልለፈውና፣ ሰነድ አዘጋጅተው ተወያይተውና ተመካክረው የቅዠት መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ አቅም እንደሌላቸው እና በውጭ ሃይል እንደተደገፈ መገመት አይከብድም። እንደተደገፉም ግልፅ ነው፣ ከአንደበታቸው ንግግር ከእጃቸው ፅሁፍ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ባንድነትን እንደ ፓሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ይዘውታል። ከታሪክ ሊማሩ አልቻሉም። “መታለል እስከ ሞት ይዘልቃል” ለሚባለው ብሂል አስረጂ አብነት እነዚህ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀርም። ነውም። ይህን መራር የፓለቲካ ሃጢያት (original sin) አፍ አውጥተው ሊጋፈጡት አይፈልጉም፣ ብዙዎችም እስከወዲያኛውም አሸልበዋል። አዙሪቱ ለአራተኛ ዙር ይቀጥላል።

የሃያላን ሃገራት ስትራቴጂክ ፍክክር እንደ መሰናክል

የሽግግር መንግስት ምስረታው ታሳቢ ያደረገው በትጥቅ እና በሕዝባዊ እምቢተኝነት ትግል መንግስትን መጣል ወይም ወደ ድርድር ማምጣት ይቻላል የሚል ነው። ሆኖም ግን ይህ ታሳቢ አሁናዊ የዓለምን የጂኦፓለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው። በአሁኑ ወቅት ባለሁለት ሃያላን ሃገራት ፉከክር ሲደረግበት ከነበረው የመጀመሪያው ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በተለየ ሁኔታ ባለብዙ ሃያላን ሃገራት ስርዓት ተፈጥሮ ሁሉም ባቅሙ ጥቅምና ፍላጎቱን ለማሳካት እስትራቴጂክ ፉክክር እያደረገ ይገኛል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሃያላን ሃገራት (ቻይና፣ አሜሪካ፣ አውሮፓና ራሽያ)፣ ክልላዊ ሃይሎች (ግብጽና የአረብ ሃገራት) እና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት እንደ አቅማቸው እየተፎካከሩ ይገኛል።

እነዚህ ሃገራት የኢትዮጵያን መንግስት በፍቃዳቸው ለማሳደር እንዳስፈላጊነቱ የውዴታ ማባበያንና ግዴታን (Accommodation and coercion) በነጠላ ወይም በአንድነት ይጠቀማሉ። በግዴታ ፍቃዳቸውን ከሚያስፈፅሙበት መንገድ መካከል አንዱ የሃገር ውስጥ ሰላማዊና ሕገ-ወጥ የፓለቲካ ሃይሎችን መጠቀም ነው። ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና የትጥቅ ትግል ድርጅቶችን በመደገፍ የሚፈልጉት ስትራቴጅክ ግብ ለማሳካት እንዳስፈላጊነቱ የገንዘብ፣ የስልጠና፣ የትጥቅና ስንቅ፣ የፕሮፓጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ይህን ድጋፍ የሚሰጠው ሃገር የውጭ ጉዳይ እስትራቴጂክ ግብ ምንድነው የሚለው ነው። የሃገሪቷን ትኩረት፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ በተራዘመ ጦርነት ማራቆትና በድህነት አዘቅት ውስጥ ማቆየት? መንግስት ስትራቴጂክ ሃብቶቹን (እንደ ህዳሴ ግንብ) የማስተዳደር አቅም እንዳይኖረው ማድረግ? ወይስ የሚፈልጉትን የፓለቲካ ስርዓትና ሃይል ስልጣን ላይ ማንበር? ወይስ ለይስሙላ የተቃዋሚዎች ጥላ መንግስት በማደራጀት ማስፈራራትና የውሳኔ ሰጪና ፓሊሲ ቀራጮችን ባህሪ እና ውሳኔ ማስቀየር? ሌላም ሌላም።

ይህ ስትራቴጂክ ግብ ከኤርትራ እሰከ ታላላቅ ሃያላን ሃገሮች ፍላጎት አንፃር ይለያያል፡፡ ይህን ከተረዳን ዘንዳ፣ በውጭ ሃይል ድጋፍ የነፃነት ትግል የሚደርጉትም ሆነ በድርድር ወይም በድል የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ነፃ ፍቃድ ሊኖራቸው ይችላል? አይመስለኝም። “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” እንዲሉ የትግሉ የመጨረሻው ግብ (strategic end state) የሚወሰነው በባለገንዘቡ ነው። ታሪክ የሚያሳየን ይህንኑ እውነታ ነው። የመኢሶን፣ የኢህአፓ እና የተማሪዎች ትግል ግብ በተራ መኮንኖች የሚመራ የደርግ ጊዜያዊ ሽግግር መንግስት መመስረት አልነበረም። መናጆ ከመሆን ውጪ የታገሉለትን ዓላማና ግብ መወሰን አልቻሉም። ትህነግ ኢትዮጵያን የመምራት የትግል ግብ አልነበራትም። ሻዕቢያ ኤርትራን ነፃ ሊያወጣ የቻለው አቅም ኖሮት ሳይሆን ከቀለብ ሰፋሪው ስትራቴጂክ ግብ ጋር ስለተጣጣመ ብቻ ነው። ዛሬም ድረስ የዛው የተፈጠረለትና የቀለብ ሰፋሪው አጀንዳ አስፈጻሚ ሆኖ ሰላም የሚነሳንም ክዚሁ ከአፈጣጠሩ በሚመነጭ ጉዳይ አስፈጻሚነቱ የተነሳ ነው። ሌላም ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

አሁን በዚህ በባለብዙ ሃያላን ሃገራት የዓለም ስርአት ውስጥ ደግሞ የፉክክሩ ግብ እንደተዋንያኑ ስለሚለያይና የሽግግር መንግስት ምስረታ እንዳይደረግ ተጨባጭ መሰናክል(material constraint) እንደሚሆን መገመት አይከብድም። እስኪ ይህን ተጨባጭ መሰናክል ለመረዳት የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት እንመልከት። እንደ ዊልሰን ሴንተር ጥናት ግኝት በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አሥራ ሁለት ሃገራት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እየተሳተፉ ሲሆን፣ ዩክሬንና ራሽያ፣ ኤርትራና ኢትዬጵያ፣ ሳኡዲና ዱባይ ኢምሬትስ፣ ግብፅና አልጀሪያ፣ ቻድና ደቡብ ሱዳን ጎራ ለይተው የሱዳን ጦርነት ውስጥ እየተፉተፉ ይገኛል። ይህም ጦርነቱ የተራዘመ እንዲሆንና የሰላም አማራጭ በር እንዲዘጋ አድርጎታል። ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ በጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጧ ምክንያት የተለያየ ስትራቴጂክ ግብ ባላቸው የሃያላን እና ክልላዊ የበላይ ሃገራት ፉክክር ሜዳ ሆናለች። በመሆኑም ይህ የአምስተርዳሙ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሃሳብ እንደማይሳካ ለመገመት ጠንቋይ ቀላቢ መሆን አይጠበቅም። ሌላ ደቡብ ሱዳን የመሆን ቅዠት ካልሆነ በቀር!!

ሰልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጥንካሬ

ራሳቸውን የለውጥ መሪነትን ካባ የሸለሙት ሃይል እነዚህ ሃይሎች ሽንፈታቸው በፈጠረባቸው ታህታይ ምስቅልና፣ ብስጭትና ቂም በቀል ራሳቸውን በማታለል የሚታገሉ፣ የገሃዱን አለም ተጨባጭ እውነታ እንዳይረዱ አይናቸው የተጋረደባቸው ከንቱ ፍጡራን በመሆናቸው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጥንካሬ በቅጡ ለመገምገም አቅም የላቸው።

የእሴት ግልበጣ ውስጥ (Inversion of values) ስለገቡ የሃይል ሚዛን ለመስራት የሚያስችለውን የአስተውሎት ችሎታቸውን አጥተዋል። ደካማነታቸውን እንደ ጥንካሬ፣ የመንግስትን ጥንካሬን እንደ ድክመት ያያሉ። ቅዠታቸውና የተጠናወታቸው ሰቀቀን ሁሉንም ገልብጦ ከማየትና በዘለለ ያለውን ሚዛን ያለው ስሌት አስረስቷቸዋል። የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እና የገቢ ምንጭ በአንፃራዊነት ጨምሮ እያለ ባዶ ካዝና ይታያቸዋል፣ ይኸው ላያቸው ላይ የቀነጨረው ሰቀቀናቸው በዲፕሎማሲው መስክ የሚታይ ስኬት ተመዝግቦ እያለ ሃገሪቱ ከዓለም እንደተነጠለች አድርገው እንደ እነሱ ሰቀቀን በሚያንተከትካቸው ተላላኪዎች ያስዘግባሉ። አለያም በሰቀቀናሞች ሚዲያ ቀርበው ቅዠታቸውን ይተነትናሉ። የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ እንዲሉ!!

የፓለቲካ ቅቡልነትን የሚያሳድጉ በአመራር ብቃት ዳር የደረሱ መሰረተ ልማቶች ሲመረቁ ቀደም ሲል ፕሮጀክቶቹን ያወደሙ፣ የዘረፉ፣ እንዳይመረቅ አድረገው ላሸገቱትና ለውድቀት ለዳረጉት የቀድሞ አመራሮች በወዳሴ ይሸልማሉ፤ ይህ ብቻ አይደለም፣ ትጋትን እንደ ስንፍናና ተራ ሕዝበኝነት አድርገው ይስሉታል፣ ወታደራዊ የበላይነትን እንደ ሽንፈት ወይም አንድ ሃሙስ የቀረው አድርገው ያቀርቡታል።….ሌላም ሌላም። በዚህ ላይ ሆን ተብሎ በተፈበረከ የሃተኛ መረጃ (disinformation) የመታለልና የመጭበርበር ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው። የሚደርሳቸውን መረጃ የማጣራት አቅም ስለሌላቸው “መስማት የሚፈልጉት እየነገሩ” የውጭ ሃይሎች በአነተኛ ወጪ ጥቅምቸውን እንዲያስከብሩ ራሳቸውን አመቻችተው ይሰታሉ። እነዚህ ናቸው እንግዲህ የሽግግር መንግስት ብለው በዳረጎት ከአሜሪካ ሲባረሩ አውሮፓ ያመሩት።

በአጠቃላይ የሽግግር መንግሥት የሚመሰርተው “የለውጥ ኃይሉ” አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ወይም መንግሥትን በማስገደድ ወደ ድርድር ሲመጣ ነው ቢባልም፣ በአሁን ወቅት ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለው የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ እና የፖለቲካ ቅቡልነት አሁንም ከፍተኛ ነው። ይህ ጥሬ ሃቅ ነው። ማመን ይገባል። በተሳሳተ የሃይል ሚዛን ግምገማ የሃገሪቱን ሕዝብና መንግስት በተራዘመ ጦርነት ከማዳከም ውጪ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሕልምም፣ ቅዠትም መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል።

እንደ መውጫ…

የሽግግር መንግስት ምስረታ ከራሳቸው፣ ከዓለም አሁናዊ የሃያላን እስትራቴጂክ ፉክክር እና ከመንግስት ጥንካሬ በሚመነጭ ተጨባጭ መሰናክሎች ምክንያት ገቢራዊ የማይሆን ቀቢፀ ተስፋ እንደሚሆን በዝርዝር ለማየት ሞክረናል። ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ “ታድያ ምን ማድረግ ይሻላል?” የሚለው ነው።

የመጀመሪያው ተግባር ተጨባጭ መሰናክሎችን በአግባቡ ተንትኖ በመረዳት ከጥላቻና ቂም በቀል ፓለቲካ ጨክኖ መውጣት ይገባል። “ያለፈው አልፏል” ብሎ ቂምንና በቀልን በይቅርታና በፍቅር ሽሮ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆን ይገባል።

በመቀጠልም መንግስት ባቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ማዕቀፍ ውስጥ በኢትዮጵያዊ አሰባሰቢ ማንነት፣ በአንድ ሃገር ልጅነት መሰባሰብ፣ የሃሳብ ልዩነትን በሰጥቶ መቀበል መርህ በድርድር እና በውይይት ለመፍታት በቅንነት ጥረት ማድረግ ይገባል። ሃገር ማሻገሪያው መንገድ ይህ ብቻ ነው። ሌላው የጥፋት መንገድ ነው። ስለዚህ ወደ አገራችሁ ግቡ!! ዝንተ ዓለም አገራችሁን በጠላቶቿ አሳብና ዕቅድ መሰረት አታዝሉ። ሕዝቡንም አታድክሙ።

ሰላም ለሃገራችን!

ዛሬ ላይ ሕልማችን የባህር በር የመሳሰሉና ሰሞኑን ይፋ የተደረጉትን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ማስፈጸም እንጂ ሱዳንን ለመሆን በሌሎች ፍላጎት መዳከር አይደለም። ዛሬ ሱዳን የገባችበት ቀውስ በሌሎች ፍላጎት በተሸጡ የሱዳን ተወላጆች እንጂ በሌሎች አይደለም። ሱዳን ዛሬ በሽግግር መንግስት ችግሯ ይፈታል ብለው የሚያስቡ ሰቀቀናሞች ኢትዮጵያን እስከዛሬ የነሷት ዕረፍት ሳይንስ፣ ሊበትኗት ብዙ ምሰው ሳይሳካልቸው ሲቀር ጊዜ እየጠበቁ ሊያፈርሷት በሽግግር መንግስት ስም ብቅ ይላሉ። በሕይወት እስካሉ ድረስ ደጋግመው በተከፈላቸው መጠን የሽግግር መንግስት ጩኸታቸውን በቀቢጸ ተስፋ ያሰማሉ!!

ፎቶ የሱዳን አሁናዊ ሁኔታ የሚይሳይ ነው፤ ህዝብ ያተረፈው

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጹሁፍ የጽሀፊው እምነትና አቋም እንጂ የአዲስ ሪፖርተር አይደልም። በጽሁፉ ላይ ምላሽ መስጠት ለሚፈልጉ ሁሉ መድረኩ ክፍት ነው

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ሃገራዊ የወርቅ ገበያ ዋጋ መናሩ የተለያየ ትንተና እየቀርበበት ነው

አዲስ ሪፓርተር ጥቅምት 12 ቀን 2018 አዲስ አበባ -...

ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ የተለያየ የፓለቲካ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች

አዲስ ሪፖርተር ጥቅምት 2 ቀን 2018 በኢትዮጵያ እየተወሳሰበ የመጣውን...

“ኤርትራ እንደ አገር ትክሰማለች”

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋና ስጋትን መቋቋም ከማይችሉት አገራት መካከል...