ሼትል ትሮንቮል“መንግሥቱ ኃይለማሪያም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስደት ክሚኖሩበት ሀራሬ ደወሉለት፣ ሰላም ጓድ አንተም እንደ እኔ በወያኔ ተቸግረሃል፣ እባክህን እኔ እንዳደረኩት ወደ ሃራሬ እንዳትሰደድ ምክንያቱም ወያኔዎቹ አንተን ፍለጋ ሃራሬ ሲመጡ እኔንም ይውስዱኛል” በማለት ዝነኛ ጆክ ትዊት አድረገው የነበሩ ሰው ናቸው።
አዲስ ሪፖርተር – የኖርዌይ ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮል “ነጩ ወያኔ” በሚል ስያሜ ይጠራሉ። የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ያህል በትህነግ ጉዳይ ወሳኝ ሰው ነበሩ። ዛሬም ድረስ አፍቃሪ ትህነግነታቸው ባይቀየርም የመከፋፈሉ ወጀብ እርሳቸውንም የናጣቸው ይመስላል። በትግራይ የተካሄደውን ምርጫ መቀሌ ተገኝተው “ሕጋዊ ነው” በማለት ያጸደቁና የተሟገቱ ናቸው። በተለይም በኅልውናው ጦርነት ወቅት ለትግራይ ታጣቂ ኃይሎች TDF የሚል የወል ስም ማውጣታቸውን ራሳቸው በአንደበታቸው በኩራት መናገራቸው አይዘነጋም። እኚህ ሰው ናቸው ስለ ትህነግና ሻዕቢያ “ፅምዶ” የተናገሩት። አይረባም በማለት።

እኚሁ ሰው ዛሬ ላይ ቀድሞ ከሚታወቁበት ትህነግን የሚያደንቁበት አግባብ የተለየ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። “የፕሬዚዳንት ኢሳያስን መወገድ ሳይሆን ከኢሳያስ በኋላ ስለምትኖረው ኤርትራ ምከሩ” ሲሉ ቅድሚያ ኃላፊነቱን ኢትዮጵያ ልትወስድ እንደሚገባ አመልክተዋል። የትህነግና የሻዕቢያን “ፅምዶ” በአጭሩ “ረብ የለሽ” ብለውታል። ጥምረቱ የሚያስነሳው ጦርነት ቀጠናውን የሚያተራምስ እንደሆነ አመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ሼትል በትህነግና በሻዕብያ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነትን ጨምሮ የሕገ መንግሥት መርቀቅ እንዲሁም የኤርትራን እንደ አገር መቋቋም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ የብሔርተኞች መሰባሰብያ መንደር እስከ መሆን ያደረሰ መልክ እንደነበረው ያስታውሳሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በተለይም የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ ባሕር አልባ አገር እንድትሆን የተወሰዱ እርምጃዎችና ሒደቶች አጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ጎረቤት አገራት የተረፈ ችግር የወለደ አካሄድ እንደነበር ሼትል ይናገራሉ። ይህ ገለጻቸው ኢትዮጵያ የባሕር በር ስታገኝ ቀጠናው ላይ የሚርመሰመሰው የሽብር ኃይል ይገታል ከሚሉት ጋር ያስማማቸዋል።
ሼትል የምስራቅ አፍሪቃ በ1990ዎቹ ገደማ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን እንደ ሉዓላዊት አገር የምትቆጥረው የሱማሊላንድ የመገንጠል ጥያቄዎች እንዲቀሰቀሱና እንዲፋፋሙ ከማድረጉም ባሻገር የውጭ ኃይሎችን የጋበዘ ድብልቅልቅ ፓለቲካ የተስተዋለበት ሆኖ አልፏል ይላሉ። አሁን ደግሞ በቀይ ባሕር ዙሪያ እየታየ ያለው ውጥረት በምስራቅ አፍሪካና አካባቢዋ ያስነሳው አዋራ በቀጠናው የውጭ አገራትን ፍላጎት በሚታይ ደረጃ ከፍ አድርጓል።
በተለይም፣ የኤርትራ እንደ አገር መቋቋም በኢትዮጵያ እንደ አገር ያሳደረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ዓልባ እንድትሆን ከተደረገበት ማግስት ወዲህ የከፈለችው ዋጋ ብዙ ነው። ለመሆኑ ቢሰላስ ስንት ይሆን ዋጋው ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
በወቅቱ በአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኩል የተሠራው ሤራ ኢትዮጵያን እንደ አገር ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል ሰለማድረጉ እንደ ፕሮፌሰር ሼትል ያሉ በቀጠናው ፓለቲካ የሚያጠኑ፣ ከፍ ሲልም በትህነግ ደጋፊነታቸው የሚታወቁት ሰው ሲስማሙበት ማየትና መስማት ነገሩ አዲስ ባይሆንም “እውነትና ጥራት” ያሰኘ ሰሞንኛ ጉዳይ ሆኗል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ለማፈላለግ የሞከሩና ሃሳብ ሲሰጡ የነበሩ አገር ወዳዶች እንደነበሩና ይህን በማለታቸው የተሰጣቸው ግብረመልስ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” የሚል ፌዘኛ መሪ ተላቅቃ “የባሕር በር ወይም ሞት” የሚል መሪ ማግኘቷን አስመልቶ ሼትል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የባሕር በር ጥያቄ ተደጋግሞ የተነሳበት ጊዜ አልታየም። ይህንን ሁኔታ የሕልውና ሥጋት አድርጎ የሚቆጥሩት የኤርትራው ገዢ ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ከሥጋት የተነሳ በተለያዩ መድረኮችና ማኅበራዊ አንቂዎች በኩል የተለያዩ ትርክቶች ሲፈጥር ተስተውሏል። ኢትዮጵያን አክቲቪስቶችም ዝም እንዲሉ አሳስቧል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያም የውግያው ቀንደኛ ተሳታፊ የነበረው የኤርትራ አገዛዝ በትግራይ ክልል ለተፈጠሩ ቀውሶች ተጠያቂ የሚያደርጉት እንደ ፕሮፌሰር ሼትል ያሉ ምሁራን፣ በአገር ውሰጥ ለዘብተኛ ዕይታ አላቸው የሚባሉት የፓለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ በክልሉ በርካታ አሳዛኝ ወንጀሎች በሻዕቢያ አማካይነት መፈጸሙን ያምናሉ። ሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋውያን ጨምሮ በክልሉ ለደረሰ የበርካታ መሠረተ ልማቶች ውድመትና ዝርፊያ ተጠያቂም ያደርጉታል። በርካታ ወገኖች በጉዳይ የሌሉበት ገለልተኛ አካላት በደሉን እንዲያጠኑትም ይጠይቃሉ።
ይህ ሁሉ ተረስቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሻዕቢያ “ከታሪካዊ ወዳጁ” ትህነግ ጋር ቀደም ሲል የመዘዘውን ጠብመንጃ አስቀምጦ የፈጠረውን “ፅምዶ” የተሰኘው ቁርኝነት፣ በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ አሰላለፍና ትንተናዎችን በመስጠት የሚታወቁትን ፕሮፌሰር ሼትል ቶሮንቮልን አላሳመነም።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ከሠላሳ ዓመታት በላይ በማጥናትና በመከታተል ከፍተኛ ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት አጥኚ ፕሮፌሰር Kjetil Tronvoll/ ሼትል ቶሮንቮል ስለ “ፅምዶ” ምልከታቸውን ተናግረዋል። በትግራይ ምድር የሆነው ሁሉ ተረስቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤርትራ ገዥ ሻዕቢያ “ከታሪካዊ ወዳጁ” ትህነግ ጋር ቀደም ሲል የመዘዘውን ጠብመንጃ አስቀምጦ የፈጠረውን “ፅምዶ” የተሰኘው ቁርኝነት፣ በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ አሰላለፍና ትንተናዎችን በመስጠት የታወቁት ፕሮፌሰር ሼትል ቶሮንቮል የሁለቱን ቅንጅት “ራዕይ አልባ እና የተንሸዋረረ” የሚል መደምደሚያ ሰጥተውታል።
የሁለቱም ኃይሎች ቅንጅት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን የትርምስና የሕገወጥ ታጣቂዎች መርመስመሻ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ሼትል አስታውቀዋል። የትህነግ ኃይሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ኤርትራ በረሃ ማስገባታቸውን እየተገለፀ ያለ ሲሆን በኤርትራ ሰንዓፈ በተሰኘችው ከተማም ቢሮ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስው የባይቶና ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሮም በርሄ ለአሃዱ በግልጽ ማስታወቃቸው ፕሮፌሰሩ ካሉት ጋር የሚገናኝ ሆኗል።
አሁን ላይ ከምዕራባውያን አገራት፣ አካባቢውንና ቀጠናውን በደንብ ከሚያውቁ ዲፕሎማቶችና አጥኚዎች እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነም በኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት ጉዳይ መግባባት ስለመኖሩ ነው።
የኢሳያስ መውደቃቸው ሳይሆን አወዳደቃቸውን አስመልክቶ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ኢሳያስ ሲወገዱ ኢትዮጵያ ኤርትራን የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባትና የበኩሏን እንድትወጣ የሚጠቁሙ አሉ። በቅርቡ አሜሪካዊው አምባሳደር ቲቦር ናጅም ኢሳያስ ይኮበልላሉ ወይም የጋዳፊ ዕጣ እንደሚደርሳቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ዓለምዓቀፍ የፖለቲካ ልሂቃን ከኢሳያስ መውደቅ በኋላ ስለምትፈጠረው ኤርትራ እየመከሩ መሆናቸውን መረጃዎች ጠቅሰው ፕሮፌሰር ሼትል ተናግረዋል። ፕሮፌሰሩ ስለ ድህረ ኢሳያስና ከትህነግ ጋር ስለጀመሩት ወዳጅነትም ተናግረዋል። “የፕሬዝዳንት የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ እርጅና በሚያስከትለው የጤና መቃወስ ወይስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚወደው ዙፋኑ ያነሱታል የሚለውን ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ኤርትራ በአምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ የግፍ አገዛዝ ውሰጥ ትገኛለች” ሲሉ አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።
ኤርትራ አሁን ላይ ያለችበትን ቁመና ከመሠረታዊ የውትድርና ሥልጠና የዘለለ ዘመናዊ መንግሥትን መምራት የሚያስችል ዕውቀትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል ስለሌላት በድህረ ኢሳያስ ችግር ሊገጥማት እንደሚችል ሼትልስ ይናገራሉ። አክለውም ኢትዮጵያ የኤርትራን መንግሥት የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባት ያስገነዝባሉ። ሼትል በኤርትራ ኢሳያስን የሚተካ መንግሥት እየተቋቋመ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተው ይህን ይናገሩ ወይም በሌላ የራሳቸው መነሻ አልተብራራም።
እንዲህ ያለው ጉዳይ በታሪክ አጋጣሚ የተለመደ መሆኑንና በሌሎች አገራት ያለውን ልምድ ጠቅሰው ነው ፕሮፌሰር ሼትል ያስረዱት። እንደ ምሳሌ ሲያነሱ በጀርመን አገር ተፈጥሮ የነበረውን የታሪክ አጋጣሚ በመጥቀስ ነው። በተመሳሳይ ከኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት ማግስት በምትኖረው ኤርትራ ኅልውና ዙሪያ መመካከር አስፈላጊነት የቀጠናው አንገብጋቢው ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ግልጸዋል።

የሳቸውን አስተያየት ግጥምጥም ያሰኘው ደግሞ የኢትዮጵያ ቁልፍ ባለሥልጣናትና የአፋር ቀይ ባሕር ያወጡት መግለጫ ነው። ቡሬ ከሚገኘው ተራራ ላይ ከተወጣ አሰብ መብራቷ ወለል ብሎ ይታያል። ባሕሩም ከሰማይ ጋር የተሰፋ መስሎ የሚታይበት ይህ ሥፍራ አሁን ኢትዮጵያ እያማተረችበት ካለውና በአፋር ክልል ውስጥ ከሚካተተው የአሰብ የባሕር በር ርቀቱ 29 ኪሜ ብቻ ነው። እናም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አሰብን በሃያ ዘጠኝ ኪሎሜትር ርቀት ቃኝተውት፣ ፎቶ ተነስተውበት ተመልሰዋል።
የቀይ ባሕር አፋር መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው “ነጻ ይወጣል” የተባለው አሰብ፣ የቀይ ባሕር ክልል አፍንጫ ሥር ነበር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፍሪቃ ቀንድ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የብሔራዊ ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ የአፋርክልል ብልጽግና ፓርቲ ሀላፊ መሀመድ ሁሴን አሊሳ፤ ምክትሉ መሀመድ አህመድ የሠመራ ሎጊያ ከንቲባ አብዱ መሳ እና ሌሎች መካከለኛ አመራሮች ለሁለት ቀን ሽርሽር ያደረጉት። (አዲስ ሪፖርተር)






