አዲስ ሪፖርተር – አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አረቄን ከዶፒንግ ጋር አያይዞ በግልጽ በሚዲያ መናገሩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዕግድ ቅጣት ማስተላለፉንና በአትሌቱ ንግግር ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አሉታዊ ጉዳዮችን የሚከታተል ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታወቀ። ኃይለ ምላሽ ካለው በሚል በግል ስልኩ በተደጋጋሚ ቢደወልም ምላሽ አልሰጠም።
ከስር ሊንኩ በተቀመጠው ዩቲዩብ ላይ ኃይሌ “ወርቅሻ” ካለው አትሌት ለውድድር ወደ ውጪ አገር አረቄ ይዘው እንደሚሄዱና እንደሚጠቀሙ ሲገልጽ ይሰማል። በንግግሩ “ጥንቃቄ” እንደሚያስፈልግ ገልጾ ቢናገርም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እሳቤው በራሱ አደጋ እንዳለውና ኃይሌ የመልካም ነገሮች ምሳሌ መሆን ሲገባው አረቄን በገሃድ ማስተዋወቁና ማበረታታቱን ነቅፏል። ስፖርትና የአልኮል መጠጥ እጅግ የተለያዩና በምንም አግባብ ሊዛመዱ እንደማይችሉ የተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ህጎች ያዛሉ።


ከለውጡ በሁዋላ መንግስት በኢትዮጵያ የመጠጥ ማስታወቂያዎችን ሙሉ በሙሉ ማገዱ ካከናወናቸው ደግ ተግባራት መካከል የሚነገርለትና በሕዝብ ዘንዳ የተወደደለት እንደሆነ በወቅቱ በስፋት አስተያየቶች የተሰጠበት ጉዳይ ነበር። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሚዲያ ሰዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ አንዳንድ ሚዲያዎችች ” በገቢ ራሳችንን መቻል አቃተን፣ ቢሮ በአንድ ህንጻ ላይ ይሰጠን፣ የአልኮል መጠጦችን ማስታወቂያ እንድንሰራ ይፈቀድልን” በማለት መጠየቃቸው በስብሰባው የተካፈሉ በግል ሚዲያቸው ይፋ ሲያደርጉት ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ እንዳለፈ አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ይህን አታስቡት” በማለት ስለ ማህበራዊ ኃላፊነት በጥልቅ አስረድተው ጥያቄው ሁለተኛ እንዳይነሳ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እጅግ አምርሮ ኃይሌን በነቀፈበት መግለጫው አረቄንና ዶፒንግን ማገናኘት አደገኛ መሆኑን አትቷል።
የአልኮል መጠጥ በዓለም ዓቀፍ ጸረ ዶሚንግ ኤጀንሲ እንደማይደገፍ መግለጫው አንስቶ፣ ኃይሌ ይህን እያወቀ “አረቄን እንደ ዶፒንግ ትጠቀማለህ?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ በአገር ደረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል አመልክቷል።
ኃይሌን የድል፣ የሪኮርድና የሀብት ተምሳሌት ያደረገው መግለጫው፣ ኃይሌ በዚሁ አርአያነቱ ከመቀጠል ይልቅ አረቄን ሲያበረታታ መታየቱ ወጣቱን ተውልድ፣ ተተኪ አትሌቶችንና ግንዛቤያቸው አነስተኛ የሆኑትን የሚያሳሳት እንደሆነ አመልክቷል።
በዚሁ መነሻ በአገር ውስጥና በውጭ ጉዳዩን የሚከታተሉ ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋሙን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል። በመሆኑም ኃይሌ በተናገረው ጉዳይ ዙሪያ የሚደረጉ ማጣራቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኃይሌ ላይ ጊዜ ገደብ የሌለው ዕግድ አጽንቷል።
በውስኔው መሰረት ኃይሌ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ስም ተጠቅሞ ምንም ዓይነት ተግባር እንዳያከናውን ታግዷል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስምን ተጠቅሞ ማናቸውን ማስታወቂያዎች ከሚታወቁ ስፖንሰር ሽፕ አድራጊዎች ጋር እንዳያከናውን መከለከሉን መግለጫው አመልክቷል። ለስፖንሰር ሺፕ አድራጊዎችም የውሳኔውን ቅጂ መላኩን አመልክቷል።
ዕግዱ በተለያዩ ቋንቋዎች ታዘጋጅቶ ለዓለም ዓቀፍ ተቋማት እንዲሰራጭ መታዘዙን መግለጫው አመልክቷል። ይህን ተከትሎ ኃይሌ ከአረቄ ጋር ተያይዞ የሰሞኑ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። በ
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለድርሻ አካላት በዚሁ ዙሪያ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩና አረቄ ለስፖርተኞች እጅግ ጎጂ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን እንዲያወግዙ አሳስቧል። ጥሪ አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኃይሌን ማገድ ስለመቻሉ የህግ ባለሙያ ጠይቀን “አዎ ይችላሉ፤ ጉዳዩ ለእኛ ቀላል ይመስላል። ለዓለም ዓቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው። የኃይሌንም ስምና የነበረውን ክብር ያጎድፈበታል፤ ዜናው በዓለም ዓቀፍ መድረክ መነጋገሪያ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም” ብለዋል።

ኃይሌ ከውጭ አገር ትጥቅ አምራቾች ጋር መጠኑ የማይታወቅ የስፖንሰር ሺፕ ውል እንዳለው ይታወቃል። ይህ ለረጅም ዓመታት የኖረ ውል በኦሊምፒክ ወይም በአትሌቲክስ ወይም በራሱ ስም የተፈጸም እንደሆነ ባይታወቅም፣ ኃይሌ በስፖንሰር ሺፕ ከፍተኛ ጥቅም ከሚያገኙ የዓለማችን ሯጮች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ አንጻር መግለጫው ከአረቄ ጋር በተያያዘ ዕግድ እንደጣለ ማስታወቁ የትጥቅ አምራቾቹ ለስማቸው ሲሉ አቋም እንዲውሰዱ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ተገምቷል።
ኃይሌ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስላሰራጨው መግለጫ ምላሽ እንዳለው ለማነጋገር በግል የእጅ ስልኩ ቢደወልለትም ምላሽ አልሰጠም። ምላሽ ሲሰጥ የሚስተናገድ ይሆናል።
ጉዳዩ በዘፈቀደ የሚነገሩ ንግግሮች በተለይም ከሚታወቁ ሰዎች ሲሆን የሚያስከትሉት አሉታዊና አዎንታዊ መልዕክት ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ትምህርት እንደሚሆን የህግ ባለሙያው ተናግረዋል። ኃይሌ በተለያዩ ጉዳዮች ያለ በቂ መረጃ አስተያየት በመስጠት በተደጋጋሚ የሚተች እንደሆነ ይታወቃል።





