“ታሪኩን በዝርፊያና በሌብነት ደመደመ” የተባለው ኢትዮ360 በርካታ የዘረፋ ታሪክ እንዳለው በተለያዩ ጊዚያት እየተሰነጣጠቀ በመጣባቸው ልምዱ፣ ተለይተውት በወጡ አባላቱና “መስሎን ስንደግፍ ነበር” በሚል ኪሳቸውን ሲያራግፉ የነበሩ ክስ እያቀረቡበት ቆይቷል። በቅርቡ ይፋ እንደሆነው ደግሞ አንዱ ዘራፊ፣ ሌላኛው ወገን ተዘራፊ ሆነው ሲከተሏቸው የነበሩትን ሁሉ አሳፍረው መበተናቸው የማህበራዊ ሚዲያ መሳለቂያ ሆነው ከርመው ነበር። “አሁን ይፋ የሆነው ይኸው የሌብነት ገድላቸው ነው” በማለት 60 ሺህ ዶላር በአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪነት ስም መዘረፉን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በርክታ ገንዘብ ከሕዝብ ተሰብስቦ መዘረፉን በማስረጃ የሚሞግቱና ገቢ ወይም ዝርፊያው ሲያንስ ጽብ መነሳቱን ብዙዎች እየገለጹ ነው።
በድንገት ባለሃብት እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ወርቁ አይተነው ስልሳ ሺህ ዶላር እንደተወሰደባቸው፣ ገንዘቡ 360 ለሚባለው የተቃዋሚዎች ሚዲያ ድጋፍ እንዲውል ታስቦ የተሰጠ ቢሆንም፣ እሳቸው እንዳሉት “ለታሰበው ጥቅም” ሳይውል ተዘርፏል። አዲስ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የኢትዮ 360 አባት መካከል ሁለቱ ገንዘቡን የዘረፈው አቶ ምናላቸው ስማቸው እንደሆኑ አመልክተዋል።

አዲስ ሪፖርተር መረጃው የደረሰው የተጠቀሰውን ገንዘብ ካዋጡት የጎጃም ባለሃብት አንዱ ሲሆን ገንዘቡ የተላከው ከዱባይ በቀጥታ ለአቶ ምናላቸው ስማቸው ነበር።
አቶ ምናላቸው ስማቸው የተመረጡት ከጎጃም አካባቢ የሚወጡ መረጃዎችን በማሰባሰብና በስም ከሚታወቁና ይፋ ቢሆኑ ለጊዜው ለዚህ ዜና አግባብ ከማይሆኑ የክልሉ የብልጽግና ባለስልጣናት ጋር በባለሃብቶቹ አማካይነት የግንኙነት መስመር የተዘረጋላቸው በመሆናቸውና ነው። ሃብታሙ አያሌው ደጋግሞ እንደሚለው “ጎጃሜ” በመሆኑ ነው።
አዲስ አበባ የሚኖሩና ለአቶ ወርቁ አይተነው ቅርብ የሆኑ ባልደረባቸው ለአዲስ ሪፖርተር እሳቸውን አነጋግረው በሰጡት መረጃ ምናላቸው የተጠቀሰውን ብር ለኢትዮ360 ገቢ አለማድረጉን እንዳረጋገጡ ነግረዋቸዋል። ይህንን ጉዳይ የኢትዮ360 አባላትም “የጸቡና የመለያየቱ ምክንያት” በማለት ይገልጹታል።
ኢሳት እያለ በቀጥታ ከአቶ ወርቁ አይተነው ኪስ በየወሩ 30 ሺህ ብር በአዲስ አበባ በተከፈተለት የሂሳብ አካውንት ደሞዝ ይከፈለው የነበረው ምናላቸው አዲስ አበባ እያለ ከሚሰራበት የጋዜጠኛነት ሙያው በመውጣት በዝርፊያ ታሪኩ እንደተዘጋ በተነገረለት ሕብር የስኳር ፋብሪካ አክሲዮን ውስጥ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ይሰራ እንደነበር ይታወሳል። አክሲዮኑን አስመልክቶ የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም አቶ ምናላቸው አሜሪካ ገብቶ ቅድሚያ በኢትዮቲዩብ፣ ቀጥሎ ኢሳት፣ ከዚያም 360 ገብቷል። ሚዲያ በመቀያየር “አኔልካ” በሚል ክለብ ከሚቀያይረው የአርሰናል ተጫዋች ጋር የሚያምሳስሉት ምናላቸው፣ የተጠቀሰው ገንዘብ እጁ ከገባ በሁዋላ “ገንዘቡን አምጣ” በሚል ከሃብታሙ አያሌው ጋር ክፉኛ እሰጥ እገባ ውስጥ እንደገቡ የሚናገሩት የኢትዮ 360 አባል፣ ምናላቸው ስማቸው ከ360 የለቀቁበትን ምክንያት ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ በጻፉት ጽሁፍ መገረማቸውን ይገልጻሉ።
“ባለፈው አንድ አመት በመስራችነት እና በዋና ስራ አስኪያጅነት እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያ ያለምንም የሀላፊነት ደሞወዝ ያለመታከት ስሰራ መቆየቴ ይታወሳል:: ይህ ሚዲያ እዚህ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስም ትልቅ ዋጋ ከፍያለሁ:: ይህም ሆኖ ግን በስራየ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ ስለሌለ በትናትናው እለት ባካሄድነው ጠቅላላ ጉባዔ ስራየን የለቀቅሁ መሆኑን ለማስታወቅ እወዳለሁ:: ይህ በእንዲህ እያለ በሶሻል ሚዲያ 3 የቦርድ አባላት እና 3 ቴክኒሻኖች ለቀቁ እንዲሁም ተሰነጣጠቁ የሚለው ወሬ እና ዜና ሀሰት መሆኑን ለመግለፅ እፈልጋለሁ:: እስካሁን ድረስ “ለምጣዱ ሲባል ” እንዲሉ ብዙ ችግር እያጋጠመኝም ቢሆን ለሀገሬ እና በስቃይ ላይ ለሚገኘው ህዝባችን ስል ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ:: በሀገራችን ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ ካለመሄዱም በላይ ኢትዮጵያዊያን በጋራ የመስራት ችግር እንዳለብን ስላረጋገጥኩ ከዚህ በኃላ ወደ ግል ህይወቴ በማምራት ቀሪውን ዘመኔን ለማሳለፍ መወሰኔን እንድታውቁልኝ ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ አስታውቃለሁ” ምናላቸው ስማቸው
አሁን ይፋ እንደሆነው ግን ምናላቸው ከ360 ግዮን የሚባል ሚዲያ ከፍቶ የተለየው ገንዘቡን የግሉ አድርጎ፣ ወደ 360 ሂሳብ እንዲያስገባ ወይም እንዲያካፍለው በሃብታሙ አያሌው ቢጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሚቀርባቸውን የትውልድ አካባቢ ባለሃብቶችና ባለስልጣናት አሳምኖ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ሃብታሙ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሚዲያ ያለወጣው ትንሽ ቀምሶ ነው።

የአቶ ወርቁ አይተነው የቅርብ ሰው የሆኑትና በስልክ እያናገሯቸው ለአዲስ ሪፖርተር መረጃውን ሲሰጡ እንዳሉት ስልሳ ሺህ ዶላር የተሰባሰበው ከተለያዩ ባለሃብቶች ሲሆን የተላከው በአቶ ወርቁ አይተነው በኩል ከዱባይ ነበር። ገንዘቡ ለኢትዮ360 መላኩ ለአባላቱ ቢገለጽም ከነገ ዛሬ ገቢ እንደሚያደርግ በመጠቆም አለሳልሶ ገንዘቡን ኪሱ እንደከተተ አቶ ወርቁ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። አቶ ወርቁ አክረረው ለምን እንዳልጠየቁና ገንዘቡ ለተባለለት ዓላማ እንዲውል ያላደረጉበት ወይም ጫና ያልፈጠሩበት ምክንያት ካለ እንዲያስረዱ የተጠየቁት እኚሁ የባለሃብቱ ቅርብ ሰው፣ “በዚህ አገባብ መረጃ የለኝም” ብለዋል።
በቅርቡ ከሃብት ክፍፍልና ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ሲካሰሱ የነበሩት የ360 አባላት ሲነታረኩ ” ባልሽ የፈለገውን ሚዲያ ከፍቶ ይሰራል። እኔ ስልሆን ለምን እከላከላለሁ። ባልሽ የወሰደውን ገንዘብ …” በማለት የአቶ ምናላቸውን ባለቤት ሃብታሙ አያሌው መሞገታቸውን ያነጋገርናቸው የሚዲያው አባል ነግረውናል።
360 መጨረሻው በሌብነትና በዘረፋ ታሪኩ መዘጋቱ እንዳሳዘነው የገለጸው የሚዲያው አባል፣ “በርካታ ጉዳዮች ታሽገው ኖረዋል። ወደፊት በሂደት በኑዛዜ መልክ ይፋ ይሆናሉ” ሲል ለአዲስ ሪፖርተር የዲሲ ተባባሪ ተናግሯል።

“ሰገነት” የሚል ሚዲያ ከፍቶ ከሽመልስ አበራ ጋር እየሰራ ያለው ሃብታሙ አያሌውና ምናላቸው ስማቸው በ”ታጋይነት” ስም ጎንደሬና ጎጃሜን በጥምረት መዝረፋቸውን የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ። ከ360 የተለየው ኤርሚያስ ለገሰ “በ360 ከሚቀርቡት ዜናዎች ውስጥ 90 በመቶ ስቱዲዮ ውስጥ የሚፈበረኩ የሃሰት ዜናዎች ናቸው” ማለቱና የአማራ ክልልን ባለስልጣናት ግድያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ ለማላከክ እንዴት የፈጠራ ትርክት እንደተሰራ ማጋለጡ አይዘነጋም። ለአንባቢያን ግዛቤ ይረዳ ዘንዳ ዳማ ሆቴል የተጠነሰሰውን ሴራና ትርክት እንዚህ ሊንክ ላይ አስቀምጠነዋል።
አቶ ምናላቸውን በግል ስል በግል ስልካቸው ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። አቶ ምናላቸው የአማራ ክልል መሪዎች ሲገደሉ እውቀቱ እንደነበራቸው አዲስ ሪፖርተር መረጃ አግኝታለች። ከክልሉ መረጃ የሚያቀብሉት ወገኖችን ጨምሮ እስከ ካቢኔ ስብሰባ መረጃ የሚያቀርቡለት አካላትና ሙሉ የትስስር መረቡን ለጊዘው ያላተምነው ለአቶ ምናላቸው ምላሽ እድል ለመስጠት መሆኑን በድጋሚ ዝግጅት ክፍሉ ያሳውቃል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






