አዲስ ሪፖርተር ታደሰ ወረደ የአቋም ለውጥ ሳያደርጉ ችግር ላይ ናቸው ያሉዋቸው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ጠየቁ። ጥያቄውን ሲያቀርቡ ትህነግ “የቀድሞ አስተዳድርና የጸጥታ ኃይል አብሮ መመለስ አለበት” የሚለውን አቋም በማንጸባረቅ ነው፤ አሁን ይፋ ከሆነው የረሃብ አደጋ በተጨማሪ መቶ አርባ አምስት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ተመሳሳይ አደጋ ላይ መሆናቸን አመልክተዋል።
ከአናቱ “የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች!” ይላል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር መሪ የሌ/ጀ ታደሰ ወረደ ደብዳቤ፣ “…እንዲሁም ኤርትራውያን የወገናችሁን ሕይወት ለማትረፍ ሌት ተቀን እየሰራችሁት ላለው ሰብአዊ ተግባር በራሴ፣ በትግራይ መንግስትና ህዝብ ስም ላመሰግን እወዳለሁ” የሚል ሃረግ ደግሞ እውስጡ አካቷል። የፊደራሉን መንግስት “እግረ መንገዴን” በማለት ነው ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ ያሳሰቡት።
ምርጫ ቦርድ ያገደው ድርጅታቸው “ትዕግስቴ አለቀ” የሚል የጦርነት ማስጠንቀቂያ ካሰራጨ በሁዋላ የክልሉ መሪ ባወጡት መግለጫ “የረሃብ አደጋ” ሲሉ የጠሩትን የተፈናቃዮች ችግር ከስር የጠቀሷቸው አካላት ይፋ እስኪያድርጉት ድረስ ዝምታ የተመረጠብትን ምክንያት አላስታወቁም። “የረሃብ አደጋ” ያሉት መነጋገሪያ ጉዳይ እንዴትና በማን ጥፋት እንደተፈጠረ፣ መቼ እንደተከሰተ በዳታ የተደገፈ መረጃ አላቀረቡም።
ታደሰ ወረደ ከሰሞኑ በክልላችን ሕፃፅ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ተከሰተ የተባለውን የረሃብ አደጋ ተከትሎ በጽህፈት ቤታቸው ስም ባሰራጩት መልዕክት፣ “የረሃብ አደጋ የሚያሳይ ቪድዮ ለህዝባቸው በሚቆረቆሩ ጥቂት ወጣቶች በመውጣቱ” ይሉና በራሳቸው፣ በትግራይ ሕዝብና በሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ቪዲዮውን ያሰራጩትን ቢያመሰግም ምረጃው ከተሰራጨ በሁዋላ በአካባቢው ከተሰራጨው የትህነግ የአንድ ለአምስት ጠርናፊዎችና ካድሬዎች በቀር ወደ መተለያው ማንም ድርሻ እንዳይል፣ ፎቶም ሆነ ቪዲዮ እንዳያነሳ አመራር ስለመስጠታቸው ያሉት ነገር የለም። የሳቸውን መግለጫ በደፈናው የሚያጋሩም ይህንኑ ጉዳይ አላስተዋሉም።
“የሰተራጨውን ምስል ያያችሁ እና በሰማችሁት ችግር ኣዝናችሁ ወገናችሁ የሆነውን የተፈናቀለ ህዝብ ለመርዳት እያደረጋችሁ ላለው ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረብኩ፣ በተለይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ኤርትራውያን የወገናችሁን ሂወት ለማትረፍ ሌት ተቀን እየሰራችሁት ላለው ሰብአዊ ተግባር በራሴ፣ በትግራይ መንግስትና ህዝብ ስም ላመሰግን እወዳለሁ። እንደ ሕፃፅ ሁሉ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ባሉባቸው ሌሎች 145 መጠለያ ጣብያዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ያሉት ታደሰ ወረደ ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ” የሚል ጥሪም አቅርበዋል፤ ይሁን እንጂ የሚሰበሰበው ገንዘብ እንዴትና በምን መልኩ በቀጥታ እንደሚደርስ ያሉት ነገር የለም። እርዳታ ማሰባሰብ ከተጀመረ በሁዋላ ለሚነሱት የታማኝነትና ስርዓት ባለው መልኩ የሚከናወንበትን አግባብ አላመላከቱም።ከልመናቸው ስር “በአጋጣሚ” በማለት ለፌደራል መንግስት ማሳሰቢያ ልከዋል።
“በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግስት፣ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታትና መላው የኢትዮዽያ ህዝቦች፣ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ከየቄያቸው ተፈናቅለው በሞት ኣደጋ ላይ ያሉትን ወገኖች ህይወት መታደግና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ከውዴታም በላይ ግዴታ ነውና የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ከኣክብሮት ጋር ጥሪዬን ኣቀርባለሁ” ያሉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መንግስት ያጓደለውን ሳይገልጹ መፍትሄ ምልጃ አሰምተዋል።
“እንደሚታወቀው ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ማኖር የሚቻለው እነዚህን ተፈናቃዮች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቄያቸው መመለስና ማቋቋም ሲቻል ነው” ያሉት ታደሰ ወረደ “ደህንነት” ላሉት ማብራሪያ አልሰጡም።
ደህንነት ሲሉ ከጦርነቱ በፊት የነበረው አስተዳደርና ታጣቂ ኃይል ከተፈናቃዮች ጋር እንዲመለስ መጠየቃቸው ስለመሆኑ ይሁን ሌላ አላብራሩም።
“የፌደራል መንግስት አሁንም ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው በተቻለ ፍጥነት እንዲመለሱ እንዲያደርግ የተለመደው ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” በሚል መግለጫቸውን የቋጩት ታደሰ ወረደ፣ የፊደራል መንግስት ከፕሪቶሪያው ስምምነት ማግስት ጀምሮ “ቅድሚያ ተፈናቃዮች ተመልሰው፣ ከተረጋጉና ካገገሙ በሁዋላ በአገሪቱ ሕገመንግስት መሰረት በህዝብ ውሳኔ ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል” የሚለውን አማራጭ ለምን እንደማይቀበሉና ወደ ተግባር እንደማይገቡ አላስረዱም።
ምዕራብ ትግራይ የሚባለውና ኢህአዴግ ስልታን ሲይዝ ወደ ትግራይ ክልል የተካለለው አካባቢ ሙሉ በሙሉ የማንነትና የግዛት ጥያቄ ሲያስተናግድ የኖረና ጥያቄውን በወቅቱ እልባት እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ በኃይል ማፈን ተመርጦ በትንቅንቅ መቆየቱ ይታወሳል።
አወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ቀደም ሲል ባኃይል እንደተያዙ የሚገልጹት የአካባቢው አስተዳደሮች፣ በኃይል እንደተወሰደ በኃይል ማስመለሳቸውን በመግለጽ ይናገራሉ።
እነዚህ አካላት የተፈናቀሉና በወንጀል የማይፈልጉ ሙሉ በሙሉ መመለስ እንደሚችሉ ይስማማሉ። የትግራይ ታጣቂ ኃይልና አስተዳደር እንዲመለስ የሚቀርበውን ጥያቄ አይቀበሉም። እንደውም በከፍተኛ የዘር ማጥፋት፣ ሰብአዊ መብት ጥሰትና በርካቶችን ከትውልድ አካባቢያቸው እንዲሰደዱ በማድረግ ይከሱዋቸዋል።
በዚህ መነሻ በአካባቢዎቹ ከዛም ከዚህም የሚቀርቡ የግፍ ክሶችን አጥንቶና መርመሮ በሽግግር ፍትህ ፍትሃዊ የህግ ውሳኔ እስኪሰጥ የአገር መከላከያ ጸጥታውን እንዲቆጣጠር፣ ተፈናቃዮች ወደ ቅዬያቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፣ በሂደት ህዝብ በራሱ ድምጽ በፈለገው ክልል እንዲካተት የመወሰን ዕድል እንዲሰጠው የቀረበውን አሳብ ትህነግ ባለመቀበሉ እስካሁን ወደ ስራ መግባት አልተቻለም።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ጉዳይ ረዥም ርቀት የሄዱ ቢሆንም በውስጥ የትህነግ ሴራ የተነሳ ሳይሳካላቸው በመፈንቅለ መንግስት ትግራይን ለቀው እንደወጡ ራሳቸው አስታውቀዋል።
ታደሰ ወረደ “የተለመደ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ከቀረቡት የመፍትሄ አሳቦች የትኛውን ደግፈው እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጡም “ጽንፈኛ” የሚባለውን ትህነግ ውሳኔ መያዛቸውን ከገለጻቸው ለመረዳት ይቻላል።
ይህ የድርጅታቸው ፋልጎት በአማራ ክልል ተቀባይነት አላገኘም። የፊደራሉ መንግስት ያቀረበውን አማራጭ አማራ ክልል ተቀብሏል። ሕዝብ ከሚሰቃይ በዚሁ አሳብ መሰረት ወይም የተለያዩ ቴክኒካል ጉዳዮች ታክለውብት ለምን ተፈናቃዮች ወደ ቅዬያቸው እንዲመለሱ እንደማይደረግ ለበርካቶ ግራ ነው።
“ሕዝብ ተራበ” በሚል ተቀባይነት ባላገኘ አሳብና ሰላምን ሊያጸና በማይችል መንገድ በችክታ እየተጓዙ አልቅሶ ከማስለቀስ በትክክል ሕዝብ ክስቃዩ እንዲያገግም ታደሰ ወረደ ለምን አቋም መያዝ እንዳልቻሉ፣ ቀደም ሲልም የክልሉ የጸጥታ ኃላፊ እያሉም ስለምን አቶ ጌታቸውን አግዘው ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ ከዳር ለማድረስ እንዳልፈለጉ ግልጽ እንዳልሆነላቸው በስፋት ጥያቄ ይነሳል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






