አዲስ ሪፖርተር – የሰብዓዊ ቀውስ ከሚፈራረቅባት ትግራይ ክልል አዲስ መረጃ ወጥቷል። በትግራይ የእርዳታ አስፈላጊነት በስፋት እየተነሳ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተሰማው ዜና ዕርዳታ ማድረገ የፈልጉ አካላት በጎ ስራ እንዳይሰሩ የመከልከላቸው ጉዳይ ነው። ይህን ትዕዝ የሰጡት ደግሞ ስማቸው ያልተጠቀሰ “ፅንፈኛ” የሚባለው ቡድን ከፍተኛ አመራር ናቸው። መረጃውን ያጋሩት እንዳሉት ውሳኔው “አስደንጋጭና አሳፋሪ” በመሆኑ ሕዝብ እንዲያውቀው ይፋ አድርገዋታል። ውሳኔውንም “ረሃብን ለፖለቲካ ፍላጎት የማዋል አባዜና ተፈናቃዮችን ጋሻ የማድረግ ሰብአዊነት የነጠፈበት እርምጃ” ብለውታል።
ከክልሉ ውጪ የሚገኙ ለጋሽ አካላት በሰሜናዊ ምዕራብ ዞን፣ በሰለኽለኻ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተው ጥያቄ ቢያቀርቡም መኮንኑ “አይሆንም” የሚል መመሪያ በማስተላለፋቸውን ያስታወቁት እነዚህ ወገኖች እንዳሉት የክለከላው ምክንያት ፍርሃቻ ነው።

እርዳታ የሚሹ ዜጎችን ከግምት ውስጥ ባለማስገባት፣ ዕርዳታ ሊሰጡ ያሰቡት ወገኖች ዓላማቸው የተፈናቃዮችን ሰቆቃ ለማስታገስ ቢሆንም፣ “የፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሊሆን ይችላል” በሚል የፈጠራ ስጋት፣ ለጋሾቹን እርዳታ ሳይሰጡ እንዲመለሱ እደርጓል” ሲሉ መረጃውን የላኩ ወገኖች አስታውቀዋል።
የቡድኑ አመራር እንደገለጹት፣ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁት እነዚህ በጎ አድራጊ አካላት በሰለኽለኻ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ፈልገው ነበር። ሆኖም ግን“የቡድኑ ከፍተኛ አባላት በበጎ አድራጎት ሽፋን የመጡት አካላት የተፈናቃዮችን ሁኔታ በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርፀው ለሌላ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሊያውሉት ነው” በሚል መከልከላቸውን ተናግረዋል።
በተጠቀሰው መጠለያ ካምፕ “እርዳታ የሚያስፈልገው ተፈናቃይ የለም” በማለት ለጋሾቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን የገለጹት የለጋሾቹ ቡድን አባላት “ውሳኔው እህግ አሳዛኝንና ሰብአዊነት የጎደለው ነው። አፈረናል” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል። አክለውም እገዳው “የፅንፈኛው ቡድን ለተጎጂዎች ህይወትና ደህንነት ከሚሰጠው ትኩረት ይልቅ፣ የራሱን ፖለቲካዊ ጥቅምና ፕሮፓጋንዳ ለማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣል በሚል የሚቀርበበትን ክስ የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።
“ተፈናቃዮች እንዳሉ እያወቀ፣ ተፈናቃይ የለም ብሎ መዋሸቱና እርዳታን መከልከሉ፣ ቡድኑ በችግር ላይ ላሉ ዜጎች ያለውን የጭካኔ አመለካከት የሚያሳይ ነው” እንደሆነ የገለጹት ለጋሾቹ ሙከራቸው አሟጠው ሲጨርሱ ሁሉንም ጉዳይ በስፋት ሕዝብ እንዲያውቀው እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
“እርዳታ የምንቀበለው በራሳችን ህግና ሥርዓት መሠረት ነው” በሚል ሽፋን የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥልና ሰብዓዊነትን የረገጠ ውሳኔ ተወስኖ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸው ለታሪክ የሚተው የትግራይ ሕዝብ ውሎ አድሮ ጥያቄ ከሚያነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆን ለጋሾቹ ጠቁመዋል።
በሰለኽለኻና በሌሎችም መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የእርዳታ እጦት እና የሰብዓዊ ቀውስ ስጥ እንደሚገኙ ክልሉ በመግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል። የክልሉ ጊዜያዊ መሪም በጽህፈት ቤታቸው ባወጡት መግለጫና በትግራይ ቲል ባሰጡት መግለጫ ችግሩ እየተባባሰ መሄዱን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ከነሱም በተጨማሪ ተለያዩ ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።
ይሁንና “ፅንፈኛው” የሚባለው ቡድን ከፍተኛ አመራር በግልጽ በሰጡት መረጃ ለጋሾች ሊያቀርቡ የነበረው ህይወት አድን ድጋፍ ለተፈናቃዮች ሳይደርስ ቀርቷል።
የትግራይ ክልል መስተዳድርን ስለ ጉዳዩ ለማነጋገር የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም። ከዝግጅት ክፍሉ በቀጥታ በዶክተር ደብረጽዮን የእጅ ስልክ ሙከራ ቢደረም ስልኩን ሊመልሱ አልቻሉም። የአረና ፓርቲ ይህንን ጉዳይ ሰምቶ እንደሆነ ለመጠየቅ ለአቶ አምዶም ስልክ ቢደወልም “መልሳችሁ ደወሉ” ካሉ በሁዋላ ሊገኙ አልቻሉም፤
በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉ መንግስትም ሆን ትህነግ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






