አዲስ ሪፓርተር – ከሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ከእስራኤል እውቅና ጋር ተያይዞ ወታደራዊ ሀይሌን እጠቀማለሁ ስትል የሰነበተችው ሶማሊያ ከአሜሪካ ጋር በፈጠረችው ግብግብ ሌላ ከባድ ትኩሳት ተነስቶባታል።
የዲያስፖራ ህዝቦቿ መዘዝ ምክኒያት ወትሮውን በትራምፕ ዘመነ ስልጣን ከፍተኛ የሆነ ትችት የተሰነዘረባት ሶማሊያ አሁን ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ከአለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) ወደ 76 ሜትሪክ ቶን እህል በመዝረፍ በመጠርጠራቸው ሀገሪቱ ከአሜሪካ የምታገኘውን እርዳታ እንዲቋረጥ አስገድዷል።
ይህ አሜሪካ ለሶማሊያ የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለማገድ የወሰደችው ውሳኔ ከሞራላዊ አቋም የበለጠ ለሶማሊያ አስጊ የሆነ የፖለቲካ ቁማር እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
በውጫዊ የገንዘብ ድጋፍ እና በውጫዊ ወታደሮች ላይ ህልውናዋ ለተመሰረተው ሶማሊያ ይህ የዋሽንግተን እርምጃ ሙሰኞችን ከመቅጣትም ባሻገር ሀገሪቷን አንድ ላይ የሚይዘውን አጠቃላይ የሉዓላዊነት ግንባታም ጭምር አደጋ ላይ ይጥላል።
ምንም እንኳን የሶማሊያው ፕሬዝዳት ከሰሞኑ ወታደሬን በእስራኤል እውቅና ባገኘችው ሀገር ሶማሌላንድ ላይ አሳርፋለሁ ቢሉ፥ ከኢትዮጵያ እና ሌሎች ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ ውጪ የሶማሊያ መንግስት እንኳን የሶማሌላንድን ቀርቶ በአልሸባብ ግዞት የወደቀውን የደቡብ ሶማሊያንም ሰላም ማስጠበቅ እንደማይችል ይታወቃል።
እነዚህ የጎሮቤት ሀገር ወታደሮች ታድያ በሶማሊያ ግዛት የሰፈሩት ከክልላዊ በጎ ፈቃድ የተነሳ ሳይሆን በአብዛኛዉ በአሜሪካ በሚመራው አለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ እንደመሆኑ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ተቋርጦ ወታደሮች ከተቀነሱ የአልሸባብ ታጣቂ ሀይል ጊዜ ሳያጠፋ የሀገሪትን ደቡባዊ ክፍል ይቆጣጠራል።
ይህ ጉዳይ የሶማሊያን መንግስት ሲሸረሽር በአንፃሩ ደግሞ ሶማሌላንድ ለጀመረችው የሉዓላዊነት ጉዞ መንገድ ይቀይሳል።
ለዓመታት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሞቃዲሾን መደገፍ አንድነትንና መረጋጋትን እንደሚያጠናክር ሲያወሳ ቆይቷል። ነገር ግን በሶማሊያ የማያቋርጥ አለመረጋጋት አሁን ደግሞ ይህ የገንዘብ ቅነሳ አባብሶት ሲታይ ይህ አካሄድ አያዋጣም የሚለውን መከራከሪያ ሀሳብ የበለጠ ያጠናክራል። በአንፃሩ ሶማሊላንድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ብዙ የውጭ ተዋጊ ኃይሎችን ሳታስተናግድ እና በምዕራቡ ዓለም ቀጣይነት ባለው የጸጥታ ገንዘብ ላይ ተመስርታ አንጻራዊ ሰላም አስጠብቃለች። የሶማሊያ መረጋጋት በአለም አቀፍ ለጋሾች በሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ወታደሮች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የሶማሊላንድ ደህንነት ከውስጥ የሚመነጨ መሆኑ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል።
ይህም የአሜሪካ እገዳ ሶማሌላንድ ሉዓላዊ ሀገር ለመሆን በምታደርገው እርምጃ በአንፃራዊ ሰላም ከሶማሊያ የምትልቅ ሀገር መሆኗን ከማስመስከርም ባሻገር ሶማሊያ በራሷ ጉዳይ በመጠመድ ግዛቷ ላይ የምታሳድረውን ጫና በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሰው ይሆናል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






