አዲስ ሪፖርተር – “ህዝባችን ለክልሉ ምክርቤት ጭምር ምርጫ መካሄድ እንዳለበትና ይህም ሂደት ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ሕገ-መንግስታዊ-ገደብ-ዘለል (beyond constitutional limits, or extra-constitutional) እና ልዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላልፎልለት በባህል፣ በስነ ልቦናና በማንነት ከሚመስለው እና በአለበት አስተዳደር ወሰን ማለትም በአማራ ክልል ምክር ቤት ጭምር ተሳትፎ እንዲኖረው መብቱ ተጠብቆለት እንዲሳተፍ፣ እንዲመርጥና እንዲመረጥ፣ ይህንን የዴሞክራሲ፣ የፍትህና፣ የነጻነት መድረክ ማንም አካል ሳይነፍገው እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ መብቱ በተሟላ እንዲከበርለት ጥሪ ማስተላለፍ እንፈልጋለን” ሲል አብን አስታወቀ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይህን ያስታወቀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጠቅሶ በሁመራ፣ አዲረመጥ፣ ኮረም ኦፍላ፣ ጠለምትና የራያ አላማጣ የምርጫ ክልሎች ቋሚ መፍትሄ እስኪገኝላቸው ድረስ ከትግራይ ውጭ ሆነው ራሳቸውን በመቻል ለተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲያካሂዱ መወሰኑን ተከትሎ ነው። አብን ውሳኔውን ደግፎ ተጨማሪ መሟላት አለበት ያለውን ጠይቋል። ሙሉ መግለጫውን ከስር ያንብቡ።
አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስቸኳይ የአስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁመራ፣ አዲረመጥ፣ ኮረም ኦፍላ፣ ጠለምትና የራያ አላማጣ የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ የሰጠውን የመራጭነት ምዝገባ ውሳኔ ድርጅታችን ገምግሞ የሚከተለውን አቋም ወስዷል።
ምንም እንኳን የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችና የሀገራችን ውስብስብ ችግሮች በምርጫ ብቻ እንደማይፈቱ ብንገነዘብም፤ ድርጅታችን አብን በ7ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፎ የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በሕዝባችን የተራዘመ ትግልና መስዋዕትነት የተገኙ ድሎችን ማፅናትና ለጥያቄዎቹም ዘላቂ እልባት የሚሰጡ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች እንዲፈጠሩ በተደጋጋሚ ጥሪ ስናደርግ መቆየታችን ይታወቃል።
ምርጫ መሠረታዊ የዲሞክራሲ መብትና የሥርዓት ግንባታ መገለጫ ነው። በወልቃይትና ራያ አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ባደረገው መራር ትግል የወያኔ ሥርዓት በሕዝባችን ማንነት ላይ ጭኖት የነበረውን የጭቆና ቀንበር አስወግዷል።
ዛሬም ቢሆን በተለይ በራያ አካባቢዎች ሕዝባችን ሊጸናለት ባልቻለና ተደጋግሞ በፈረሰ ሀገራዊ ድል ምክንያት ዘላቂ መፍትሔ በማጣቱ ለሕወሃት በቀል እየተጋለጠ የማያባራ መከራና የማንነት ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። ሕወሃት በትግል ቢሸነፍም፣ የሕዝባችን ጥያቄ ሕጋዊ መቋጫ ባለማግኘቱ አካባቢው የመፍትሔ ያለህ እያለ ይገኛል። ይህ ችግር በሰላማዊ መንገድ ይፈታል በሚል ሕዝባችን የሀገርን ሰላምና አንድነት በማስቀደም በትዕግስት ሲጠብቅ ቆይቷል።
መንግስት ከሀገራዊ ሁኔታዎች አንጻር የሚወስዳቸው ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ የማይመቹን ቢሆኑም፣ እንዲሁም ሕዝብ በአደባባይና በምልዓት የሚያነሳቸውን ጥያቄወች ያለጊዜ ገደብ አክርሞ መዝለቅ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ለፖለቲካ ሽፍጥ በር ይከፍታል የሚል ስጋት አለን። በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መንፈስ አንጻር ብናከብረውም፤ ችግር ፈጣሪዎች የሚደመጡበት፣ የሕዝብ ድምጽ ግን የሚታነቅበት ሁኔታ ከእንግዲህ እንዲቀጥል አንፈቅድም። የሕዝባችን ጥያቄ የጥፋት ኃይሎችን “ለማባበል” ወይም ለሽንገላ ሊውል እንደማይገባ በጥብቅ እናሳስባለን።
በመሆኑም ህዝባችን ለክልሉ ምክርቤት ጭምር ምርጫ መካሄድ እንዳለበትና ይህም ሂደት ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ሕገ-መንግስታዊ-ገደብ-ዘለል (beyond constitutional limits, or extra-constitutional) እና ልዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላልፎልለት በባህል፣ በስነ ልቦናና በማንነት ከሚመስለው እና በአለበት አስተዳደር ወሰን ማለትም በአማራ ክልል ምክር ቤት ጭምር ተሳትፎ እንዲኖረው መብቱ ተጠብቆለት እንዲሳተፍ፣ እንዲመርጥና እንዲመረጥ፣ ይህንን የዴሞክራሲ፣ የፍትህና፣ የነጻነት መድረክ ማንም አካል ሳይነፍገው እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ መብቱ በተሟላ እንዲከበርለት ጥሪ ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
የካቲት 16/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






