አዲስ ሪፖርተር – የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና ወሰን ኮሚቴ “… ውሳኔ በበጎ የምንመለከተዉ እና የማንነት ጥያቄያችን ለመፍታት እንደአንድ እርምጃ የምንቆጥረዉ፣ የሕገ-መንግሥቱን የበላይነት ያረጋገጠ እና ለዓመታት የፖለቲካ መብታቸው ተገፎ ለኖሩ ዜጎች የዲሞክራሲ ጭላንጭል የፈነጠቀ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ኮሚቴያችን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል” ሲል ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ አደነቀ። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።
ለኢፌዲሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክርቤት
አዲስ አበባ ጉዳዩ፡- ውሳኔው የዜጎችን ፖለቲካዊ መብትና ሕገ-መንግሥታዊ ውክልና የሚያረጋግጥ መልካም ጅማሮ መሆኑን ስለመግለጽ
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክርቤት ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑና የማንነት ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በምርጫ የመሳተፍና የመመረጥ መብታቸው እንዲከበር ያስተላለፈው ውሳኔ በበጎ የምንመለከተዉ እና የማንነት ጥያቄያችን ለመፍታት እንደአንድ እርምጃ የምንቆጥረዉ፣ የሕገ-መንግሥቱን የበላይነት ያረጋገጠ እና ለዓመታት የፖለቲካ መብታቸው ተገፎ ለኖሩ ዜጎች የዲሞክራሲ ጭላንጭል የፈነጠቀ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ኮሚቴያችን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል።
ባለፉት ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች፣የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ፣ በማንነታቸውና በአስተዳደራዊ መዋቅር ውዝግቦች ምክንያት መሠረታዊ የሆነውን የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን ተነፍገው ቆይተዋል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 38 መሠረት ያለ አድልዎ የፖለቲካ ተሳትፎ የማድረግ መብት ያለው ቢሆንም፣ በአምባገነኑ እና በጨቋኙ ሕወሓት ታግቶ መቆየቱ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ትልቅ ጉድለት ነበር።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥቱ የበላይ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን፣ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የመፍታትና የዜጎችን መብት የማስከበር ሰፊ ሥልጣን አለው። ምክር ቤቱ ምርጫው በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲከናወን የሰጠው ውሳኔ “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነትን” ሳይሆን፣ በተቃራኒው የሕዝብ ሉዓላዊነት እንዳይሸረሸርና እያንዳንዱ ዜጋ በራሱ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብቱ እንዲጠበቅ የሚያደርግ እና የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የጠየቀዉን የማንነትና ወሰን ጥያቄ ለመፍታት እንደ በጎ ጅምር የምንቆጥረዉ ፍትሃዊና ተገቢ ውሳኔ ነው።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ እና የትግራይ ልሂቃንና ድርጅቶች ይህንን ውሳኔ “የአስተዳደር ነጠቃ” (Annexation) በማለት ሊፈርጁት መሞከራቸው፣ የሕዝቡን መሠረታዊ መብት ከግዛታዊ ይገባኛል ጥያቄ በታች ለማድረግ ከመፈለግ የመነጨ የሰብአዊና ዴሞክራሲ መብት ጥሰት ሂደት ነው። ይሁን እንጂ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋናው መሠረት የግዛት ወሰን ሳይሆን የዜጎች ነፃ ፈቃድና ድምፅ ነው። የወልቃይት ጠገዴና መሰል አካባቢዎች ሕዝብ ምንም እንኳን የማንነትና ወሰን ጥያቄዉ እንደሚመለስለት የጠየቀዉ ጥያቄ ያልተመለሰና የዘገየ ቢሆንም በአገራችን በሚደረገዉ ሰባተኛዉ ብሔራዊ ምርጫ የራሱን ተወካዮች ለመምረጥ የመንግሥት ጥበቃና የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አፈጻጸም ያስፈልገዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ቢሆን ከምክር ቤቱ የተላለፈለትን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ፣ ከአሁን ቀደም በአምባገነኑ ሕወሓት በወሰነዉ ሕገ ወጥ አከላለል ተፅዕኖ ስር ሳይወድቅ፣ የዜጎችን ድምፅ ለማክበር የጀመረውን ዝግጅት እያመሰገን አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን። ይህ እርምጃ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና የማንነትና ወሰን ጥያቄዎች በሕጋዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ በር ከፋች ነው።
በመሆኑም፦
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ መብት ለማስከበር ያስተላለፈው ውሳኔ ያቀረብነዉን የማንነትና ወሰን ጥያቄ በመመለስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤
የወልቃይት ጠገዴና አካባቢው ሕዝብ ያለ ምንም ስጋትና ጫና የራሱን ተወካዮች እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፤
በሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም ስም የሕዝብን መብት ለማደናገርና ለማፈን የሚደረጉ የትኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች መንግሥትና ሕዝቡ እንዲታገሏቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የሕዝብ ሉዓላዊነትና የሕግ የበላይነት ይከበር! የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ እውነተኛና ፍትሐዊ መሆኑን እየገለጽንና አጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን ነገር ግን “ተረፈ-ህወሓት” የሆነው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ተብየው ዛሬም እንደትናንቱ በህገ-መንግስት ስም እየማሉና እየተገዘቱ፣ ያደጉበትን ልማድ ለማስቀጠል እውነተኛውንና ፍትሐዊውን የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጥያቄ ለመደፍጠጥና ለማፈን የሚያደርገውን ህገ-ወጥ ድርጊት አምርረን እንቃወማለን፡፡
በእርግጥ “ድመት መልኩሳ አመሏን አትራሳ” እንደሚባለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የትግራይ ልሂቃንና ድርጅቶች እና ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ-ህወሃት አስቀጥል ዓላማውን በስመ ህጋዊ ለምድ ለብሶ የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔን ዳግም እንዲታይ ያለውን ፍጹም ፀረ-ሕገ-መንግስትና ፀረ-ፍትሕ የሆነ አቤቱታ ነው፡፡
ስለሆነም የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የዘመናት የህዝባችን የእውነትና የፍትሕ ጥያቄ የሆነው ራስን የመሆን ፍትሐዊ ትግል ነውና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕገ-መንግስታዊ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ እንዲከበር ምርጫ ቦርድ የወሰነውን ውሳኔ ፍትሐዊ፤ሕገመንግስታዊና የፕሪቶሪያን ስምምነት መሰረት አድርጎ ስለሆነ ኮሚቴውና ሕዝባችን ሙሉበሙሉ የሚደግፈው ሲሆን ከዚህ በተፃራሪ “ተረፈ-ህወሐትና የህውሃት ማኒፌስቶ አስቀጥል” የሆነው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ቡድን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የበላይ ህግ የሆነውን የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔን ለማጣጣል ስምረት ፓርቲ ያቀረባቸውን ሃሳቦችና ውንጀላ ያሰበውን ህገ-ወጥነት ለመፈፀም ኩልል ብሎ የሚያሳይና ፀረ-ፍትሕ መሆኑን ያረጋገጠ ነው፡፡ ስለሆነም የተከበርከው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብና ፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያውያን የፌዴሬሽን ምክርቤት የጋራ ቤታችንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችን ተግባራዊ የምናደርግበት በመሆኑ ምርጫ ቦርድና የፌደሬሽን ምክርቤት የወሰነው ውሳኔ ፍትሃዊና ተገቢ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡
የእውነትና የፍትሕ ትግል ያሸንፋል!!
የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና ወሰን ኮሚቴ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






