በዘመነ ደረግ ኢህአፓ የከተማ ውስጥ ትግል ሲያውጅ የተጀመረው አድፍጦ መግደል ነበር። ደርግ “ነጭ ሽብር” ያለው ይህ ግድያ በስኳዶች የተደራጀና በሕዝብ መካከል ሆኖ የሚተኩስ ነበር፤ ይህንኑ እርምጃ ለመቀልበስ ደርግ “ቀይ ሽብር” ብሎ እርምጃውን በአደባባይ ያከናውነው ጀመር። ያ በኢህአፓ የትግል ስህተት የተጀመረ መገዳደል ወላጆችን ጧሪ አልባ አድርጓል። ሁለትና ሶስት ልጆቻቸውን ያጡ እናቶች በሃዘን ተቆራምተው ሞተዋ፤ የት ይደርሳሉ የተባሉ ወጣቶች ተቀጭተዋል። የቻሉ ተሰደዋል። ያልቻሉ ሕይወታቸው ተመሳቅሏል። ከምንም በላይ አገር ከስራለች። ይህን የማይሽር ጠባሳ ማንም በድጋሚ ሊያየው አይወድም!!
አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ – በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በጠብ መንጃ ትግል እንደማይወድቅ ከተገመገመ በሁዋላ የጎጃም ፋኖ ክንፍ መሪ የሆነው አርበኛ ዘመነ ካሴ የገጠር ትጥቅ ትግሉን ወደ “ከተማ አመፅ” የመቀየር ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ተሰምቷል። ዕቅዱ አቶ ልደቱ አያሌው በሰላማዊ ትግል ስም “መከተል ይገባናል” የሚሉት አናርኪዝም እንደሆነ የአብሮነት አባላት ጠቁመዋል።
ፋኖ ወደ ከተማ ሽምቅ ውጊያ እንደሚሸጋጋር ዘመነ ካሴ ሲያስታውቅ ትግሉን ለማፋፋም እንደሆነ ቢገልጽም ፣ ዜናው እንደተሰማ “የተስፋ መቁረጥ ውጤት ነው” ሲሉ ያስታወቁና የተችሁ አሉ፤ እንደነዚህ አካላት ከሆነ በከተማ አመጽ ስም ሊጀመር የታሰበው አናርኪዝም ኢህአፓ የፈጸመውን ስህተት የሚልቅ አደገኛና መቆሚያ የሌለው እንደ ሰንሰለት የሚጎተት መበቃቀል ውስጥ እንደሚከት አመልክተዋል።

የዋሽንግቶን የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ከአብሮነት አመራሮች ባገኘው መረጃ የጠብ መንጃ ትግል የሚያምኑት ቡድኖች ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው “ይህ መንግስት በጠብ መንጃ አይወደቅም” የሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። በመሆኑም የተመረጠው መንገድ አቶ ልደቱ በሰላማ የከተማ አመጽ ስም እንከተለው በሚል የሚራምዱት አናርኪዝም ነው። ለዚህም ማሳያው በጦርነት ይህን መንግስት ለመጣል ከሚተባበሩት ጋር በግንባር ቀደምትነት የሻዕቢያ ወኪል ሆነው እንደሚሰሩ የሚነገርላቸው አቶ ነአምን ዘለቀና አጋሮቻቸው ሻዕቢያ ከሚከፍላቸው ሚዲያዎች ጋር በመሆኑ በተከታታይ ሰለ ከተሞች እመጽና አናርኪዝም መናገራቸውን ይጠቃሳሉ።
እንቅስቃሴው በመናበብና በቅብብሎሽ የሚሰራ እንደሆነ የሚናገሩ የጎጃም ፋኖ ክንፍ መሪ የሆነው ዘመነ ካሴ የገጠር ትጥቅ ትግሉን ወደ “ከተማ አመፅ” የመቀየር ዕቅድ እንዳለው ሰሞኑን ባደረገው ንግግር ያነሳሉ። ይህ ዘመነ ካሴ ይፋ ያደረገው የትግል ስልት ለውጥ አሁን ከሚሰማው በባሰ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አሳሳቢ የሕዝብ የደህንነት ስጋት እንደሚፈጥር ለኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ቅርብ የሆኑ ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛል።
ይህ የዘመነ የከተማ ሽምቅ ውጊያ ጥሪ በሰባዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ አብዮት ቁልፍ ተዋናይ የነበረው የኢትዮጵያሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ከወሰደው ስትራቴጂክ የትግል ስልት ስህተት ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ፣ ለትውልድ እልቂት መንስዔ ስለሚሆን ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል።
የኢሕአፓ መንገድ፡ ከዩኒቨርሲቲ አመፅ እስከ ነጭ ሽብር

የኢሕአፓ ታሪክ የተጀመረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ሲሆን፣ በወቅቱ የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ፍልስፍና በአገሪቱ ምሁራን ዘንድ ተስፋፍቶ ነበር። እነ ብርሃነ መስቀል ረዳ እና ጓደኞቻቸው መቃወምን እንደ ዘመናዊነት በመቁጠር የተሻለ የመንግስት አስተዳደር እንዲመጣ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ተማሪዎችን በመቀስቀስ ትግሉን ጀመሩት። አመፁን በማስፋፋት ከሌሎች የፓለቲካ ሃይሎች ጋር ዘውዳዊ መንግስቱን በመጣል ወታደሩ (ደርግ) ሥልጣን እንዲይዝ አደረጉ። ኢሕአፓ ወታደራዊ አገዛዝን በመቃወም ወደ ገጠር ትጥቅ ትግል ቢሸጋገርም፣ የትግሉ መራዘም ፓርቲውን ወደ “የከተማ ትግል” ወይም “አብዮታዊ ነጭ ሽብር” ስልት እንዲያመራ አስገደደው።
የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን የኢሕአፓ ውሳኔ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ ስልታዊ ስህተት አድርገው ይገመግሙታል። ወደ ከተማ ትግል መግባቱ፣ ደርግ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን በጅምላ እንዲያጠፋ ምክንያት ፈጠረለት፤ በዚህም “ቀይ ሽብር” የሚባለው አሰቃቂ የትውልድ እልቂት ተፈጸመ ይላሉ። ኢሕአፓ የውጭ ርዕዮተ ዓለሞችን ከኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ በመከተሉ እና የውስጥ አቅሙን በደንብ ባልገነባበት ከተማ ውስጥ ከመንግስት የደረጀ የአመፃ ኃይል (coercive Machine) ጋር በመጋፈጥ ሺዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆነ። የቀይ ሽብር ሰለባ የሆኑት ሰዎች ቁጥር በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሲሆን፣ ይህ ወቅት በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ስልታዊ የጅምላ ግድያ የተፈጸመበት በመሆኑ የኢሕአፓ የከተማ ትግል ውሳኔ የትውልድ ፍጅትን እንዳፋጠነ የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።
የዘመነ የከተማ አመፅ ጥሪ፡ የታሪክ አዙሪት እና አደጋው
የፋኖ ትግል በ2016 ዓ.ም. በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የተጀመረ ሲሆን፣ ልክ እንደ ኢሕአፓ ሁሉ መጀመሪያው በገጠር ትጥቅ ትግል ላይ ያተኮረ ነበር። አሁን ግን የጎጃም ፋኖ መሪ የሆኑት ዘመነ ካሴ ትግሉን ወደ ከተማ አመፅ የመመለስ ዝንባሌ ማሳየቱ፣ ትግሉ ከዳር ሀገር ወደ መሃል የመመለስ አዝማሚያ እንዳለው ያሳያል።
የዘመነ የከተማ አመፅ ጥሪ፣ የጀመሩት የፋኖ የገጠር ትጥቅ ትግል አሸናፊ እንደማይሆን መወሰናቸውን ወይም የመሪዎቹ የትግል ግምገማ ችግር ያለበት መሆኑን የሚያመላክት ነው። ተንታኞች እንደሚሉት፣ በኃይል ሚዛን የበላይ ከሆነ መንግስት ጋር በከተማ ውስጥ መጋፈጥ ሃገሪቱን ለሌላ የእርስ በርስ ፍጅት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ ሊደርጋት ይችላል። አጀንዳውም ኢትዮጵያን በእርበርስ ግጭት እንድተማቅቅ ከሚሰሩት ኃይሎች በቀጥታ የወረደ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
በፋኖው ንቅናቄ ውስጥ ቀድሞውንም በትግሉ ዓላማ (“መነሻችን አማራ፣ መዳረሻችን አማራ” ወይም “መነሻችን አማራ፣ መዳረሻችን ኢትዮጵያ”) ላይ የነበረው የቅንጦት ንትርክ፣ አሁን ደግሞ “የከተማ አመፅ” በሚል አጀንዳ የልዩነት ምንጭ ይሆናል። “ይህ ውሳኔ ከደርግ፣ ኢሕአፓና መኢሶን የመገዳደል ፍጻሜ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አሳዛኝ መጨረሻ ሊያመጣ የሚችል አደገኛ እና አክሳሪ ነው” በማለት ለአዲስ ሪፓርተር አስተያታቸውን የሰጡ የታሪክ ተመራማሪ ገልፀዋል። አክለውም የመፍትሄው መንገድ ድርድር እና ፖለቲካዊ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የመፍትሄው መንገድ፡ ድርድር እና ፖለቲካዊ መፍትሔ
ይህ በገራችን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ አሳዛኝ የትግል ስልት ታሪክ በኢትዮጵያ ተደጋግሞ ሊታይ እንደማይገባው የፖለቲካ ተንታኞች በጋራ በአንድ ድምጽ ይስማሙበታል፣ የትጥቅ ትግል መራዘም የሀገርን ሀብትና የትውልድን ሕይወት ከማጥፋት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው የቅርብና የሩቅ እንዲሁም በአገር ቤት የደረሰውን ቀውስ በማሳየት ከበርካቶች በተደጋጋሚ የሚሰማ እውነት ነው። የፋኖ መሪዎች የኢሕአፓን መንገድ ከመከተል እና የትውልድ እልቂት ከማወጅ ይልቅ፣ በቅንነትና በአገር ወዳድነት መንፈስ የትጥቅ ትግሉ አሸናፊ እንደማይሆን በተጨባጭ መገምገም እና ከዚህ አደገኛ መንገድ ሙሉ በሙሉ መውጣት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ምክር እየተለገሰ ነው። በመቀጠልም እንደ አንድ ፋኖ በጋራ ቆሞ የአመራርና የዓላማ አንድነት በመፍጠር ከመንግስት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል በድርድር በፖለቲካዊ መፍትሔ ወደ እረቀ ሰላም ለመምጣት መስራት እንደሚገባቸው፣ መፍትሄውም ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደሆነ ሕዝብ ባገኘው መድረክ ሁሉ እያስታወቀ ነው።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





