“ኤርትራ እንደ አገር ትክሰማለች”

Date:

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋና ስጋትን መቋቋም ከማይችሉት አገራት መካከል ኤርትራ የመጨረሻ ደካማዋ አገር ሆና ተመዝግባለች። በቃላት ወይም በአሃዝ ሊገለጽ የማይችለው የኤርትራ ኢኮኖሚ ድቀትና በሸንበቆ የሚመለስል መንግስት ይህን አደጋ መቋቋም ስለማይችል ኤርትራ እንደ አገር መክሰሟ እንደማይቀር ተመልክቷል። ይህን አደጋ ከመከላከል ይልቅ የኤርትራ መንግስት ያለችውን ሃብት ጎረቤት አገራትን ለማተራመስ ማዋሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚወቅስበት ነው።

በአልፋጂኦ የሃገራት የአየር ንብረትን ለውጥን መቋቋምና የመላመድ ጥንካሬና የፓለቲካ አስተዳደር መረጋጋት ደረጃ (The periodic table of states) ኤርትራ ከዓለም መጨረሻውን ደረጃ መያዟ የተተነተነው በመረጃና በሰፊ ማስረጃዎች ነው።

ብሄራዊ ጥቅማቸውን ከፖለቲካ ልዩነትና የስልጣን ፍላጎታቸው ጋር የሰፉ ” ኢትዮጵያዊያን” በፕሮፓጋንዳ ኤርትራን ያሳብጣሉ። የቀጣናው ሃያል አገር አድርገው ያስሏታል። ኢትዮጵያ በግሪን ሌጋጋሲ ያስመዘገበችውን ውጤትና የታየውን የመለሶ ማገገም እመርታ ደግሞ ያራክሳሉ። ኤርትራ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አደጋ የመቋቋም ሃብት እና የፓለቲካ አስተዳደር የሌላት አገር መሆኗ ተጠቅሶ የመክሰም አደጋ ውስጥ መነከሯ ሲገለጽ የሚያስተባብሉት “ኢትዮጵያዊ” ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ይህን ሪፖርት እንዴት የግመግሙታል?

በአለባቸው ጉብሳ – የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ

የአየር ንብረት ለውጥ ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ ውጤቱ በገሃድ መሬት ላይ የሚታይ በመሆኑ ከማናቸውም ጊዜ የበለጠ የዓለም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ሃያላን ሃገሮችና ባለ ብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተቋማት(Multilateral Institutions) ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑት እንደ ዩክሬንና ራሽያ ወይም በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት መካከል ከሚካሄደው ጦርነት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተፅዕኖ (Technological disruption) ፣ የንግድ ጦርነትና የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል… ወዘተ ባልተናነሰ መልኩ የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ የዓለም የደህንነት ስጋት አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል።

ሃገራት የካርበን ልቀታቸውን ለመቀነስ የሚያስችልና ግዴታ የሚጥል የፓሪስ አየር ንብረት ስምምነት የባለብዙ ወገን ተቋም ጥረት ውጤት ነው። በዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የቀጥታና የጎንዮሽ መወያያ ከሆኑት ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋነኛው አጀንዳ የአየር ንብረት ለውጥ ነበር። በተለያዩ እንደ ሙኒክ የፀጥታ ኮንፈረንስ ያሉ የመረጃና ደህንነት ዓመታዊ ጉባኤዎች ላይ ጭምር የአየር ንብረት ለውጥ እንደ አንድ የሃገር ፀጥታና ደህንነት ስጋት ተደርጎ በጥናት ተለይቷል። ይህ ዓለም አቀፍ ክስተት እያስከተለ ያለው እና ወደፊትም የሚያስከትለው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ መረዳት አይከብድም ነው።

አሁናዊ የአየርን ንብረት ለውጥ ስጋት

በሙቀት መጨመር ምክንያት የአርክቲክ ግግር በረዶ መቅለጥ ጀምሮ የባህር ጠለል ከፍ ሊል ችሏል፣ ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብና ድርቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ይገኛል፣ የሰደድ እሳት ከታላላቅ ሃገሮች የመቆጣጠር አቅም በላይ ሆኖ በሚሊየን ሄክታር የሚቆጠር ደን ወድሟል፣ ከተሞች በቁማቸው ተቃጥለው ወደ ምድረበዳነት ተቀይረዋል። የባህር ዳርቻዎች በሙቀት መጠን መጨመርና የባህር ጠለል ከፍ በማለቱ ምክንያት ለሰው ልጅ ኑሮ የማይመቹ ሆነዋል።

የዛሬ ሁለት አመት በሊቢያ የሜድትራኒያን የባህር ዳርቻ ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዶፍ ዝናብ ዘንቦ ሁለት የኤሌክትሪክ ማመንጫ የውሃ ግድቦች ከመሸከም አቅማቸው በላይ ውሃ መሸከም ባለመቻላው ፈንድቶ ሙሉ ከተማ አውድሟል፣ ከ4 ሽህ ሰው በላይ ሲሞቱ፣ በአስር ሺዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል፣ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት ጉዳት አድርሷል። በተመሳሳይ ዓመት ፓኪስታን ውስጥ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ33 ሚሊየን በላይ ህዝብ ቀጥተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሃብትና ንብረት ወድመት ደርሷል። አሜሪካን ሃገር ውስጥ የተከሰተው የሰደድ እሳትና ድንገተኛ ጎርፍ በመቶ ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሃብት አውድሟል፣ ሰብአዊ ጉዳት አድርሷል። በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተ ድርቅ አርብቶ አደሩ የማህበረሰብ ክፍል የለት ኑሮው ምንጭ የሆኑ ከብቶቹን በግጦሽና በመጠጥ ውሃ እጦት አይኑ እይየ ተፈጥሮ ቀምታዋለች። የምግብ ዋስትና እና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ሊፈጠሩ ችለዋል።

ይህ ክስተት በተለይም በባህር ዳርቻዎች አቅራቢያ የሚገኙ የሶስተኛው ዓለም ሃገራት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሉአላዊነት የህልውና ስጋት እየሆነ መጥቷል። ቀድመው ለተከሰቱ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ይበልጥ በማባባስ (Threat Multiplier በመሆን) የሃገራትን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ቀውሶች እየተፈጠሩ ይገኛል። በተለይም ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ሌላ ሃገር ስደትን በመፍጠር በላኪና በተቀባይ ሃገራት ላይ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል።

ለዚህም ነው፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጀዋና ዋድፔል ባለፈው ወር በተካሄደው የተባበሩት መንግስት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረገው ንግግር” በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የባህር ጠለል መጨመር ምን አደጋ እንደሚያስከትል አውቃለሁ። ደህንነታችሁና ኑሯችሁ በዚህ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀ በባህር ዳርቻ የምትኖሩ ህዝቦች አልረሳናችሁም ጎናችሁ መሆናችንን እናረጋጥላችኋለን” በማለት የአጋርነት መልዕክቱን ያስተላለፈው።

የሃገራት መክሰም አደጋ

የታዋቂው አልፋጂኦ ስትራቴጂክ አማካሪ ድርጅት ዋና ሃላፊ የሆነው ፓራግ ካህን በቅርቡ ለንባብ ያበቃው “Move: The forces uprooting Us” በተሰኘው ድንቅ መፅሃፉ የአየር ንብረት ለውጥ ሌሎች የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የፓለቲካ እና የማህበራዊ ችግሮችን በማባባስ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ለቁጥጥር በሚያስቸግር መልኩ ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ ሃገር ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያለው ፍልሰት (climate refuges) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ዓለም ዓቀፍ ጥናቶች መሰረት አድረጎ ያብራራል።

በአሁኑ ጊዜ ከ50 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን ይህም የፓለቲካ ተፈናቃዮችን በቁጥር ሊበልጥ ችሏል። አሁን ባለው የሙቀት መጠን ላይ አንድ ተጨማሪ ድግሪ ሴሊሲየስ ቢጨምር ከ200 ሚሊየን በላይ ህዝብ ሊፈናቀል እንደሚችል ፓራግ ይገልፃል። ዓለም አቀፍ ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶችን ለመቀነስ እና ለመላመድ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ቢጠቁሙም በድርቅ ምክንያት ጥሪቱን እና ተስፋውን ያጣ የአፍሪካ ወይም የኤዥያ አርብቶ አደር እና ባህር ዳርቻ ላይ የሚኖር ሰው ወደ ሌላ ሃገር ለመሰደድ አያመነታም።

እንደ ፕራግ ገለፃ በተለይ በባህር ዳርቻ ላይ ያሉ ሃገራት በሙቀት መጠን መጨመር እና የባህር ጠለል ማደግ ምክንያት ለሰው ልጅ መኖሪያነት የማይመከሩ በመሆኑ እንዲሁም የሚያስከትለውን ችግር ለመቋቋም ወይም ለመላመድ የሚያስች የመንግስት የፋይናንስ፣ የሰው ሃይልና የፓለቲካ መዋቅራዊ አቅም ስለማይኖር ዜጎች ወደ ሌላ የተሻለ የአየር ንበረት ወዳላቸው ሃገር በመፍለስና በመሰደድ ሃገራት እስከ መክሰም የሚደርስ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል። ፕራግ ኤርትራን እና ቦሊቪያን በምሳሌነት በመግለፅ ያብራራል። በአልፋጂኦ የሃገራት የአየር ንብረትን ለውጥን መቋቋምና የመላመድ ጥንካሬና የፓለቲካ አስተዳደር መረጋጋት ደረጃ (The periodic table of states) ኤርትራ ከዓለም መጨረሻውን ደረጃ ይዛለች። ይህ ደረጃ ኤርትራ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አደጋ የመቋቋም ሃብት እና የፓለቲካ አስተዳደር የሌላት በመሆኑ የመክሰም አደጋ እንዳንዣንበባት ነው።

የኤርትራ ተጋላጭነት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃገራት የአየር ንብረት ሁኔታ መግለጫ እንደሚያሳየው ኤርትራ ከዓለም አማካይ የአየር ንብረት ለውጥ ትንበያዎች ቀድማ በከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶችን በማስተናገድ በአስከፊ ሁኔታ ተጋላጭ ከሆኑት ሃገራት ተርታ ልትመደብ ችላለች።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው አማካይ የሙቀት መጠን በግምት 1.7 ድግሪ ሴልሲየስ መጨመሩን ያሳያል፣ ይህም በአስር ዓመት በአማካይ የ 0.37 ድግሪ ሴሊሲየስ የሙቀት መጠን መጨመርን ያሳያል። ይህ የሙቀት መጨመር ፍጥነት የሚያሳየው ኤርትራ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተቀመጡትን የረጅም ጊዜ የማረጋጋት ግቦችን በማለፍ ለአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆኑዋን ነው።

እንዲሁም ኤርትራ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን በመላመድ በኩል ያላትን ደረጃ በተመለከተ የኖትር ዳም ግሎባል መላመድ ኢንዴክስ (ND-GAIN) በ2025 በመወጣው መግለጫ መሰረት ከ178 አገሮች ውስጥ 176ኛ ደረጃን በማግኘት በቋሚነት እጅግ በጣም ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ትመደባለች። ይህ ደረጃ የኤርትራ የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን የመቋቋም እና ምላሽ የመስጠት አቅሟ በእጅጉ ውስን መሆኑን ያሳያል። መዋቅራዊው ተጋላጭነት እና ድህነት የአየር ንብረት አደጋዎች ሲከሰቱ ሀገሪቱ ሰፊና የረዥም ጊዜ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያስችል አስፈላጊ የፋይናንስ ወይም አጠቃላይ ማህበራዊ ደህንነትን መጠበቂያ ሃብት እንደሌሏት በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ፍልሰትና የኤርትራ ሃገረ መንስት መክሰም

የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአስር ሽህ የሚቆጠሩ ኤርትራውያ ወደ ጎረቤት ሃገር እንደሚሰደዱ ጥናቶችና ሪፓርቶች ያሳያሉ። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮምሽን በጥቅምት 2024 ባወጣው ሪፓርት መሰረት 20 ሽህ ኤርትራውያን በአንድ አመት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የስደተኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን 180 ሽህ የሚሆኑ ደግሞ በስደትኝነት ተመዝገብው በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ መረጃ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች ውስጥ በህገወጥነትና በህጋዊ መንገድ በተለይ በአዲስ አበባ የሚኖረውን ኤርትራዊ አይመለከትም። ይህን የፍልሰት ምጣኔ በየዓመቱ በእጥፍ እየጨመረ ቢሄድ በዓምስት አመት ጊዜ ውስጥ የኤርትራ ወጣቶች በቋሚነት ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ መገመት አይከብድም። ከአየር ንብረት ለውጡ በተጨማሪ እንደ ባሪያ ጉልበት ብዝበዛ የሚቆጠረው የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የኤርትራ ወጣቶችን ለሰድት ከሚዳርጓቸው ገፊ ምክንያቶች የኤርትራ ሰማያዊ አብዮእት የተሰኘው ንቅናቄ በይፋ አስታውቋል።በዚሁ መነሻ የአማራንና የትግራይን ወጣቶችን በመመለመል እያሰለጠኑ መሆናቸውን ደግሞ ከትህነግ የተሰነጠቁት አካላት አጋልጠዋል።

ይህ በአየር ንብረት የተፈጠረ የስነ ሕዝብ ለውጥ ወሳኝ የሆኑ ወጣት፣ የምርታማ የሰው ኃይልን ክስረት ያስከትላል። ይህን ለመከላከል የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት በስፋት ማካሄድ ቁልፍ ጉዳይ ሲሆን፣ ማህበራዊ አስተዋፅዖ የሚጠይቁ የመሠረተ ልማት ጥገና ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ማከናወን መሰረታዊ ጉዳይ ለመሆኑ ዓለም ምስክር ነው።

በተቃራኒው እንዲህ ያለውን የከፋ ችግር ለመቋቋም፣ አስፈላጊውን አቅም ማሰባሰብ የሚይችል እንደ ኤርትራ ዓይነት መንግስት ባለበት አገር ጣጣው ከራስ አልፎ ወደ ጎረቤት ይጋባል። ከላይ የተገለጸው የፍልሰትና ስደት መረጃ የዚሁ ችግር ውጤት ነው።

በአንፃሩ ይህ ፍልሰት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ ወጪ የሚጭን በመሆኑ መንግስት የባህር በር ፍላጎቱን ለማሳካት እንደ አማራጭ መፍትሄ ሊጠቀመው ይገባል። ይህን አማራጭ መፍትሄ ጂኦስትራቴጅሰቱ ፓራግ ካህን ይጋራዋል።

ፓራግ በሃገራት ፍቃደኝነት እና ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ሕዝቦችን ወደሌላ ሃገር በማስፈር እና ግዴታ በመጣል የጋራ ጥቅማቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ይገልጻል። ከዚህ አንጻር የኢጽዮጵያ መንግስት የባህር በር ፍላጎቱን ለማሳካት ይህን የኤርትራውያንን ፍልሰት በምክንያትነት በማቅረብ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ድርድር ከኤርትራ መንግስት ጋር ቢያደርግ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚችል በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ መረጃ ያላቸው ወገኖች ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥቆማ ይሰጣሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ ፣ በሌሎች ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተማረረውን እና ተስፋ የቆረጠወን የኤርትራን ሕዝብ የትኩረት ዒላማ በማድረግ በተጠና፣ በታቀደና በተቀናጀ መልኩ የዲፕሎማሲ፣ የመረጃና ወታደራዊ ግዳጆችን በመፈጸም የኤርትራ መንግስት የባህር በር በዲፕሎማሲ ድርድር እንዲሰጥ፣ ካልሆነም የአገዛዝ እድሜ ለማሳጠር እንዲሰራ መስራት እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ጸሐፊውን በ info@ddisreporter.com አድራሻ ማግኘት ይቻላሉ

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ሃገራዊ የወርቅ ገበያ ዋጋ መናሩ የተለያየ ትንተና እየቀርበበት ነው

አዲስ ሪፓርተር ጥቅምት 12 ቀን 2018 አዲስ አበባ -...

ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ የተለያየ የፓለቲካ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች

አዲስ ሪፖርተር ጥቅምት 2 ቀን 2018 በኢትዮጵያ እየተወሳሰበ የመጣውን...

በወንጀል በተገኘ ሐብት የተከሰሱ አምስት ግለሰቦች በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

አዲስ ሪፖርተር ጥቅምት 12 ቀን 2018 - በወንጀል የተገኘ...