አዲስ ሪፖርተር – ከአስር ዓመት በሁዋላ ከዓለም ሃያ ታላላቅ አየር መንገዶች መካለል አንዱ ለመሆን ዕቅድ የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ጋር መስማማቱን አስታውቋል።
በአፍሪካ በግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚገዛቸው አስራ አንድ ተጨማሪ አውሮፕላኖች ቦይንግ 737 ማክስ የተሰኙ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ናቸው። ዜናው የአየር መንገዱን አቅምና ተወዳዳሪነት በእጅጉ የሚያጎላ እንደሆነ ተመልክቷል። ስምምነቱ የኢትዮጵያን አየር መንገድ የቦይንግ አውሮፕላኖችን በመግዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርገዋል።
ስምምነቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሲናገሩ፣ የአየር መንገዱንና የቦይንግ ኩባንያን አጋርነት እድገት የት እንደደረሰ ጠቋሚ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ወቅቶች ከቦይንግ ጋር ስምምነቶችን መፈጸሙ ይታወቃል። በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት አስራአንድ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር እና ሃያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት የተደረሰው ስምምነት የአየር መንገዱን የአፍሪካ ቁንጮነት ያሳየ ሲሂሆን ከአፍሪቃ ቀዳሚ ያደረገው ነበር።
አዲስ የወጣው ዜና እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ስምምነቱን የፈጸመው በዱባይ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው ዓለም ዓቀፍ የአውሮፕላኖች ኢግዚቢሽን ላይ ነው።
በዱባይ የአየር ትርኢት ስነ ስርዓት ላይ የተፈረመው የ11 B737-8 ግዢ ስምምነት አየር መንገዱ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን እንዲያሳድግ እና የአዲስ አበባ ማዕከሉንም ለማስፋት እንደሚያስችለው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው “ከዱባይ አየር ትርኢት ጎን ለጎን ተጨማሪ አሥራ አንድ B737-8 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ጋር ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኞች ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ግዢው አየር መንገዱ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የደንበኞቹን ምቾት ለመጨመር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፈው የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አየር መንገዱ ባለፉት ዓመታት ከቦይንግ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
የቦይንግ ሽያጭ እና ግብይት ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፤ ምቹ እና ዘመናዊ የሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖች አየር መንገዱ በአፍሪከ፣ መካከለኛ ምሥራቅ፣ ህንድ እና ደቡብ አውሮፓ ለሚገኙት ደንበኞቹ የሚሰጠውን ምቹ፣ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚዱት ተናግረዋል። አክለውም “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀልጣፋ እና ምቹ አውሮፕላኖቻችን ተጠቅሞ የአፍሪካ አህጉርን ከቀረው ዓለም ጋር እያገናኘ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚው የቦይንግ አውሮፕላኖች ተጠቃሚ ሲሆን በርካታ 737 ማክስ፣ 777X እና 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





