አዲስ ሪፖርተር – የአል ጀዚራ በቅርቡ ያቀረበው “አብይ አህመድ፣ ኤርትራ እና ህወሓት፡ መሀዲ ሀሰን እና ጌታቸው ረዳ ፣ ፊት ለፊት / “Abiy Ahmed, Eritrea & the TPLF: Mehdi Hasan & Getachew Reda | Head to Head” የተሰኘ ፕሮግራም የክርክር መልክ ተላብሶ ቀርቧል። ይሁን እንጂ በተግባር አንዳችም የክርክር መልክ አልታየበትም። የጋዜጠኝነት ሙያዊ ስለ ምግባርም አልነበረም። ይልቁንም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ ለመግለጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለማጥላላት፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ መንግሥት ለዘላለም ለመገንጠል እና በአዲስ አበባና በመቀሌ መካከል እየጎለበተ የመጣውን የፖለቲካ ድልድይ ለማፈራረስ ታስቦ የተነደፈ፣ በሚገባ የተቀናበረ፣ ጥሩ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና አጭበርባሪነት የነገሰበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነበር።
ፕሮግራሙ እንደ ስሙ “ፊት ለፊት” የክርክር ወግና ካባ ተላብሶ እንዲቀርብ ቢደረግም፣ እውነታው ግን “a courtroom without a defense attorney” ተከላካይ ጠበቃ የሌለበት ፍርድ ቤት ይመስል ነበር። አቃቤ ሕጎቹ ሀሰን፣ የፓናል አባላቱ የጋዜጣኛ ካባ የደረበቸው ጸዳለ ለማ እና ተመራማሪ የተባሉት ሼትል ትሮንቮል በአንድ ላይ ተባብረው ሲሠሩ፣ በአካል ቢገኙም በስልት አንደበታቸውና መከራከሪያቸው የተበጣጠሰባቸው ብቸኛው የኢትዮጵያ ድምጽ የነበሩት ብስራት ለሜሳ ነበሩ።
ከሁሉም በላይ፣ ስለ ጦርነቱና ስለ መንግሥት አቋም ቀጥተኛ ዕውቀት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን አገሪቱን እንዲከላከል አልተጋበዘም። የክርከር ተብዬው ብይን ቀድሞ የተጻፈ ነበርና ተጀመሮ እስኪያልቅ ድግሱን ጨምሮ፣ ጠ/ሚ አብይ አህመድን ማሳጣት፣ መፈረጅና፣ በክፉ ተግባራት መሳል፣ ሲልሆን ከአቶ ጌታቸው ረዳ እና መሰል የትግራይ ፖለቲከኞች ጋር የተገነባውን አዲስ ሰላማዊ ግንኝነት ማንኛውም ድልድዮች ከመሠረቱ መናድ ነው። ይህ ነበር የመድረኩ ልዩ ምክንያት።
ዋናው ሴራ፡ ትግራይን ከሥልጣን ማራቅ
ይህ ድራማ በጥቅሉ በስድስት ክፉትን የተላበሱ ዓላማዎች ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ለይቶ የፕሮፓጋንዳ ቃታ በመሳብ በጦርነቱ ወቅት ሲነሱ የነበሩ የፍረጃ ክሶችን በመደጋገም፣ እያንዳንዱ ቃል፣ ድምጸት እና እሳቤ የእሳቸውን ስልጣን ላይ መቆየት ላይ የተንጠለጠለና እሳቸውን በነቀፌታዎች አጅቦ ከስልጣን ለማዋረድ መንገድ መጥረግ። ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት ሲባል የፓናል አባላቱም ሆነ አከራካሪው የአብይ መንግሥት የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ጥረቶችን ጨምሮ፣ ከጦርነቱ በኋላ ለትግራይ የተደረገውን በገሃድ የሚታይ፣ በአሃዝ የሚታወቅ፣ በአገልግሎት የሚልካ ከፍተኛ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ፈጽሞ እንዲነሳ አልተደረገም።
- ትግራይን ከፌዴራል ሥልጣን ተጋሪነቷ ማግለል። ይህንኑ ለሚፈለገው ዓላማ ሲባል ማጠናከር። ጸዳለ ለማ “በተደጋጋሚ አንድነት የማይቻል ነው” በማለት አጥብቃ ስትናገር ይሚሰማው፣ ከእነ ጃዋር ጋርና ከዚያ ቀደም በመገንጠል ከሚያምኑ የኦነግ አክራሪ ኃይሎች ጋር ስታራምደው የኖረቸውን ኢትዮጵያን የመበጣጠስ አቋሟን አቀርባለች፣ እናም “ትግራይ የፌዴሬሽኑ አካል አይደለችም” በማለት ኢትዮጵያ ቀድሞውንም እየተበታተነች እንዳለች አድርጋ አሳይታለች።
- አቶ ጌታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር አብሮ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ለመስራት የወሰዱትን ድፍረት ማጥላላት። ይህም አቋም ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚያሴሩትን አካላትና አገራት ክፉኛ አበሳጭቷል። ይህ አዲስ ግንኙነት ኢትዮጵያን የመለያየቱን ዓላማ ስጋት ላይ የሚጥል ነበር። ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑ እንደ ክህደት ተደርጎ የተቀረጸው፣ የአቶ ጌታቸው ውሳኔ ሴራውን ስለሚንደው እሳቸውን በክህደት ስም ከትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ማግለል።
- ትግራይን ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያላትን የፖለቲካ ውህደት ለማፍረስ የአቶ ጌታቸውን የቀደሞውን የበረሃ ወይም የጦርነቱ ጊዜ የቀረቡ ንግግሮችን በመጠቀም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና የአቶ ጌታቸው አዲስ ድልድይን መደርመስ። የአቶ ጌታቸው ያለፉት/ የጫካና የጦርነቱ ወቅትየፕሮፓጋንዳ መግለጫዎች በእርሳቸው ላይ ዛሬ ለያዙት አቋም ማጥቂያ መሳሪያ ሆነዋል። ከጦርነት በኋላ በሚደረጉ የሰላም ስምምነቶች ተደርጎ እንደማያውቅ፣ አቶ ጌታቸው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በሁዋላ የያዙትን አቋም ልክ ትግራይን እንደ ከዳተኛ አድርጎ መጠቀም፣ ወይም የፌደራሉ መንግስት ተራ አገልጋይ አድርጎ ማሳየት፣
- እነዚህ እርምጃዎች ሳይሳኩ ሲቀሩ፣ “የማይቀር ጦርነት” በማለት መጮህ። ይህም ለትግራይ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት እና ኢትዮጵያ ላይ በፖለቲካዊ መንገድ ጫና ለመፍጠር ታስቦ የተነደፈ የሰብአዊ ቀውስ ትርክት መፍጠር ነው። በሌላ አነጋገር ትህነግ ያዋለደውን የትግራይን ቀውስ እንደገና ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ በማውጣት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማጽደቅ ነበር።በመጨረሻም፣ ዋናው ግብ ትግራይ ተነጥላ እንድትቀር፣ ኢትዮጵያ ደግሞ አንድነቷን ጠብቃ መመራት የማትችል እና የመበታተን አፋፍ ላይ ያለች እንድትመስል ማድረግ ነበር። ይህ የኢትዮጵያ ‘ባልካናይዜሽን’ ተብሎ የሚጠራው መልዕክት በመሀዲ፣ በጸዳለ እና በትሮንቮል ደጋግሞ የተላለፈ መልእክት ነው።
መሃዲ ፣ ጸዳለ እና ትሮንቮል የተሰጣቸውን ሚና በሚገባ ተጫውተዋል። በምዕራባውያን መሪዎች ላይ ያለው የአክብሮት ቃና አፍሪካውያንን በሚገጥምበት ጊዜ የሚያጠፋው ሀሰን፣ አብይ አሕመድን ያለ ተቀናቃኝ “ኢምፔሪያሊስት፣” “የእግዚአብሔር ሹም” እና “ጦር ወዳድ” በመሳሰሉ ስሞች ያለማቋረጥ ሲያነሳቸው የነበረው ዝም ብሎ አልነበረም። ጌታቸውን እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ጠላት ምስክር የቆጠረውም በዚሁ አግባብ ነው። ያለፈውን የጦርነት ጊዜ ንግግሮችን በራሱ ላይ እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል። ዓላማው ግልጽ ነበር፡ አቶ ጌታቸውን የትህነግ ቃል አቀባይነቱ እንደ መለጎሚያ በመጠቀም ኢትዮጵያን ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሯን መከላከል እንዳይችል አድርጎታል።
የፓናል አባላቱ እውነተኛ ወገንተኝነት መጋለጥ

ፓናሉ የወገንተኝነት የሚያሳይ ቅንብር ነበር። እንደ ምሁር የቀረበው ሼትል ትሮንቮል ለረጅም ጊዜ ከትህነግ ጋር አብሮ የሰራና “ነጩ ወያኔ” በሚል የሚጠራ አባላቸው ነው። የትህነግ ታጋዮችን እንደ ህጋዊ ብሔራዊ ጦር ዳግም ለመሰየም ሲነሱ፣ እቅዱን ከመደገፍ ጀምሮ ለተሰራዊቱ “የትግራይ መከላከያ ኃይል” የሚለውን ስያሜ ማውጣቱን በራሱ አንደበት በኩራት ያመነ ፤ ይህ ደግሞ እንደ ትንተና የቀረበ ግልጽ የፖለቲካ ዳንስ ነው። የእርሳቸው መግለጫዎች “የጥናት ሥራ” ሳይሆኑ (Activism) የሚለው የነ ጃዋር ማዕረግ ነበር መገለጫቸው። ሼትል የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትህ ከንቱ እንደሆነ ገልጿል፣ አክሎም በሚረብሽ አግብባ ጉጉቱን “ጦርነት እየመጣ ነው፣ እና በቅርቡ እየመጣ ነው” ሲል ተንብዩል። ይህ ትንታኔ ሳይሆን ምኞት ነበር።
ጸዳለ ለማ ያሳየችው ነገር ደግሞ ይበልጥ ግልጽ ነበር። የአዲስ ስታንዳርድ አዘጋጅ የሆነችው ጸዳለ፣ በአብይ የተጀመረው ጦርነት እያንዳንዱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ክፍል እንደነካ እና የአገሪቱን መበታተን የማይቀር እንዳደረገ በመግለጽ በትግራይ ስም ለትህነግ አልቅሳለች። የእርሷ ሀዘን ለትግራይ ተወላጆች ሳይሆን ትህነግ የበላይነት በመጥፋቱ ነው የተነሳ ሆድ ስለባሳት ነው። አቶ ጌታቸውን “ሥነ-ምግባር የጎደለው” ብላ የሰየመችው ለህዝቡ በማሰብ ሳይሆን፣ ከአብይ ጋር ያለው ተግባራዊ ጥምረት የራሷን የቡድን ዓላማ፣ ማለትም የኢትዮጵያ ፖለቲካን ለመቆጣጠር ትግራይን በዘላቂነት እንደ ተበዳይ የውጭ አካል ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት ስላናጋባት ነው። “ጋዜጠኛዋ” ለታጣቂዎች እየተዘዋወረ ነው በሚል መንግስት የወሰደውን አቋም አልፋዋለች። “የፌዴራል ገንዘብ መንግስት ወደ ትግራይ ይልካል፣ የሚላከውን ገንዘብ ለሰራዊት ክፍያ ይውላል” በሚል በሰፊው መዘገቧ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፤ በፕሮግራሙ ወቅት ግን ይህንን ወሳኝ ነጥብ መጥቀስ ተስኗታል። ምክንያቱም የመደረኩን ዋና ዓላማ ያናጋዋል።
ውስጣዊው ስብራት፡ የትግራይ ቀውስ የተፈጠረው በትህነግና በደጋፊዎች ብቻ ነው
በትግራይ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመረዳት የትህነግን ዘላቂ ውስጣዊ ክፍፍሎች መገንዘብ ያስፈልጋል። በ2018 የፌዴራል ስልጣን ካጣ በኋላ ቡድኑ ለሁለት ተከፈለ፡ አንደኛው ወገን ከኢትዮጵያ ጋር ተግባራዊ የኮንፌዴራል ስምምነት ለማድረግ ፈለገ፤ ሌላኛው ግን በወታደራዊ ኃይሉ በመተማመን አዲስ አበባን ለመያዝ ኖቬምበር 2020 አደገኛ የሆነ ጦርነት ከፈተ። ይህ የተሳሳተ ስሌት ወደ ሽንፈት እና ተጨማሪ የቡድን መከፋፈል ነዳው። ራሱ መከላከያን አርዶ የለኮሰው አውዳሚ ጦርነት ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያንም የትግራይ ምስኪን ሕዝብም እየለበለበ ነው።
ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ፣ ተጠያቂነትን ያነሱት እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች “አሻፈረኝ” ባሉ ጽንፈኛ ኃይሎች እንዲገለሉ አደረጋቸው። ዛሬ፣ ትግራይን የሚቆጣጠሩት እነዚህ ጽንፈኛ አካላት ራሳቸው ተከፋፍለዋል፤ ይህም በድጋሚ ግጭት በሚፈሩ ወገኖች እና በተዘገበው “Tsimdo” ስምምነት ስር ከቀድሞ ጠላታቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጥምረት ለመፍጠር በሚጥሩ አካሎች መካከል ነው። የጥፋተኝነት፣ የጽንፈኝነት እና ለአዲስ ቀውስ የከፋ ፍላጎት ያለው ይህ ወሳኝ አውድ በአልጀዚራ ፓነል ሙሉ በሙሉ ችላ ተብሎ ታልፏል። ለምን? ቢባል የማህዲን የውክልና ድግስ ዓላማ ያከሽፋል።
በግልጽ ችላ የተባሉ ጉዳዮች፡ የጋዜጠኝነት ክልከላ
“አብይ አህመድ፣ ኤርትራ እና ትህነግ” በሚል ርዕስ የቀረበው ፕሮግራም የመከራው እውነተኛ ጠንሳሾች ላይ ያሳየው ዝምታ አሳፋሪ ነበር። ይህ በስህተት የተዘለለ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ የተመረጠ የትርክቱ አቅጣጫ ነው።
•ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ?
“ገለልተኛ” ነኝ ባዩ የፕሮግራሙ አወያይ መሀዲ ሀሰን፣ የማያሻማውን እውነት አንድ ጊዜም ቢሆን አልተናገረም። ጦርነቱ የተጀመረው ኖቬምበር 3 ቀን 2020 ነበር። ለ27 ዓመታት የያዘችውን የሥልጣን የበላይነት በማጣቷ የተበሳጨችው ትህነግ፣ በሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ላይ “መብረቃዊ እና የተቀናጀ” ያለቸውን የክህደት ጥቃት ከፈጸመች በሁዋላ ነው። በወቅቱ ይህን ያደረጉትም ሠራዊቱን በማንበርከክ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ነበር። ይህ በግልጽ በመንግሥት ላይ የተደረገ የመንግስት ግልበጣ ዓመፅ ነበር።
የህወሓት ግፍ እና የዘር ማጥፋት ትርክ

የውይይት መድረኩ ስለ «የጦር ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት» በደፈናው ሲያላዝን፣ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች የተመዘገቡትን የተወሰኑ የትህነግ አስከፊ ግፎች ግን ሆን ብሎ ችላ ብሏል። በአማራ ክልል ጪና እና ቆቦ ላይ የተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች ለምን አልተነሱም?
ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች ሲመሰክሩ “መጀመሪያ ወንድሜ ታደሰን ተኮሱበት… ሌላው ወንድሜ እና አማቼ ለመሸሽ ሲሞክሩ ሁለቱም ተመቱ… እኔን በግራ ትከሻዬ ላይ መቱኝ… እንደሞትኩ አስመስዬ ተረፍኩ” ሲሉ የሰጡት ምስክርነትስ? የሚረሳ ነው?
“የመጀመሪያዎቹን አስከሬኖች ያየነው በትምህርት ቤቱ አጥር አጠገብ ነበር። ሃያ አስከሬኖች በውስጥ ሱሪያቸው ሆነው ፊታቸውን ወደ አጥሩ አዙረው ተኝተው ነበር፤ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ደግሞ ሦስት ተጨማሪ አስከሬኖች ነበሩ…. ከጭንቅላታቸው ጀርባ የተመቱት ሰዎች ፊታቸው በከፊል ቆስሎ ስለተበላሸ ሊታወቁ አልቻሉም” የሚለው አሰቃቂ ምስክርነት የት ደረሰ? ከዓለም ዓቀፉ የይቅርታ ድርጅት (Amnesty International) የተገኘው ማስረጃስ? የ14 ዓመቷ “ሉሲ” የተባለች ታዳጊ፣ የትግራይ ታጣቂዎች “ቤተሰቦቻችን ተደፈሩ፤ አሁን ደግሞ እኛ የምንደፍርበት ተራችን ነው” እያሉ እንደደፈሯት የመሰከረችው ለምን ተዳፈነ? ትህነግ ህጻናትን ለጦርነት መማገዱ፣ የሰብአዊ እርዳታ ስርቆቱ፣ ወይም አል ጀዚራ ራሱ እንደዘገበው የፌዴራል መንግሥትን በማምለክ ያካሄደው የውሸት የሴፕቴምበር 2020 ምርጫ ጉዳይ ለምን አልተነሳም? ከሁሉም በላይ የሚገርመው፣ እንደ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ያሉ የትህነግ መሪዎች ራሳቸው የ”ዘር ማጥፋት” ትርክት የፌዴራል መንግሥትን ስም ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የተፈጠረ እንደሆነ መግለጻቸው ነው እንዴት ታለፈ? ፕሮግራሙ ይህንን ወሳኝ እርስ በርስ የሚጋጭ ሀሳብ (Contradiction) በጥንቃቄ አስወግዶታል።
የኤርትራ ሚና ወንጀሎች እና አስገራሚው የ“ጽምዶ” ጥምረት
ፕሮግራሙ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የባሕር በር ንግግር ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ዋናውንና ግዙፉን ጉዳይ ግን ዘሎታል፡ ይኸውም የኤርትራ ጦር በትግራይ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ወረራ ነው። የትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የምርመራ ኮሚሽን (CITG) ባደረገው እና በአዲስ ስታንዳርድ በተዘገበው መሠረት፣ ከ60% በላይ የሚሆኑት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙት በኤርትራ ኃይሎች ነው። እነዚህም በስርዓታዊ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ እና አሰቃቂ የወሲብ ጥቃት ይታወቃሉ። ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመተውን ውድመትም በዋነኛነት የፈጸሙት ሻዕቢያዎች ናቸው። እጅግ የሚያሳፍረውና ያልተጠቀሰው አስቂኝ ነገር ደግሞ፣ በአሁኑ ጊዜ ትግራይን እየተቆጣጠረ ያለው ህገወጥ የትህነግ አስተዳደር “Tsimdo” በተባለ ስምምነት ከዚያው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጥምረት መፍጠሩ ነው። በኤርትራ እና በትህነግ ጉዳይ ላይ ነው ተብሎ በተዘጋጀ ፕሮግራም ውስጥ፣ ይህ ታላቅ ግብዝነት እና የኤርትራ አስከፊ የጦር ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ ተዘንግተዋል። ይህን ጉዳይ መዝለል አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን የፕሮግራሙን እውነተኛ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያጋልጣል።
የአሰብ ወደብ እና ታሪካዊ ቅሬታ
ስለ ባሕር በር የተደረገው ውይይት ሆን ተብሎ ላይ ላዩን እንዲነካካ ነው የተደረገው። በመድረኩ የተጋበዙት ብስራት ለሜሳ ብቻ የጉዳዩን መሰረታዊ ኢፍትሐዊነት ጠቁመዋል፡ በ1993 ዓ.ም የትህነግ የበላይነት የነበረበት የኢህአዴግ መንግሥት፣ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልና ወይም ህዝበ-ውሳኔ (Referendum) ሳይኖረው፣ የአሰብን ወደብ ለኤርትራ በስጦታ በመስጠት የኢትዮጵያን የሉዓላዊ የባሕር በር መብት አሳልፎ ሰጠ። የኢትዮጵያ ጥያቄ የሌላን ሀገር መውረር ሳይሆን ይህን ህገወጥ ታሪካዊ ስህተት ማረም ነው። አቶ ጌታቸው ረዳ ራሳቸው ይህንን ብሔራዊ ጉዳይ አቃለው በማቅረብ፣ ስልታዊ የባህር በር ጥያቄን ከተራ “የሪል እስቴት” ጉዳይ ጋር አመሳስሎታል። ነውር ነው።
ለትግራይ የተደረጉ የፌዴራል ጥረቶች
የፕሮግራሙ ትርክት የፌዴራል መንግሥት ክልሉን ሙሉ በሙሉ እንደተወው የሚያሳይ ነበር። ሆኖም፣ በ2023 መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ አገልግሎቶችን ለመመለስ 5 ቢሊዮን ብር ወደ መቀሌ ማስተላለፍ እንደጀመረ ማንም አልጠቀሰም። እንዲሁም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ላይ እነዚህ ገንዘቦች መልሶ ግንባታ ላይ ከመዋል ይልቅ ወደ “ታጣቂዎች እንቅስቃሴ” እየተዘዋወሩ ነው የሚል ሕጋዊ ስጋት ቢያነሱም (ይህም እውነታ በአዲስ ስታንዳርድ ተዘግቧል)፣ የፌዴራል በጀት ወደ ትግራይ መፍሰሱን መቀጠሉን ማንም አልተናገረም። ጽዳለም የራሷን ዘገባ ውጣው አይተናታል።
የውስጥ አዋቂው ምስክርነት፡ ኢትዮጵያን ለመበታተን (Balkanization) የተጻፈ ድራማ

እስከ አሁን ከቀረቡት መረጃዎች ሁሉ የበለጠ ነገሩን የሚያጋልጠው ማስረጃ የመጣው፣ የተዘጋጀውን የውሸት ትርክት ለመጣስ ከደፈሩት ብቸኛ የፓናል አባል ከብስራት ለሜሳ ነው። ብስራት ከቃለ ምልልሱ በኋላ በ’አዲስ ፓራዳይም’ ላይ ባደረጉት ቆይታ፣ ከዚህ “ክርክር” በስተጀርባ ያለውን ክፉ የሴራ አጋልጠዋል። አል ጀዚራ ጥያቄዎችን እና ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ለመቅረጽ ከፕሮግራሙ በፊት ሰፊ ምክክር ማድረጉን ተናግረዋል። እሳቸው ከአሜሪካ ወደ ለንደን የበረሩት ለፕሮግራም ሲሆን፣ ከትዕይንቱ በስተጀርባ ተሳታፊዎች እና የፓናል አባላት ከአዘጋጆች ጋር ሲመሳጠሩ ተመልክተዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አስደንጋጭ የሆነው፣ አንድ አዘጋጅ “መሀዲ ማወቅ ስለፈለገ” በሚል ብሄራቸውን ለመጠየቅ ወደ እርሳቸው መምጣቱ ነው። ይህ ጋዜጠኝነት ሳይሆን በዘረኝነት መፈረጅ ነው። ይህ ድርጊት የፕሮግራሙን ክፉ ዓላማ ያጋልጣል፡ ይኸውም ድምጾችን በጎሳ መነጽር አጣርቶ፣ ለጎሳ ክፍፍል እና ለተወሰነ አጀንዳ ማዋል ነው፤ በዚህም የእንግሊዝ ዲቃላውን የአልጃዚራውን መሀዲን ከማንኛውም ጉዳይ “ገለልተኛ ነኝ” ባይነቱን ያጋልጠዋል። ያዋርደዋል።
ቁልፉ መረጃ፡ የፕሮግራም ዳይሬክተሯ ዝምታ
ብስራት ያጋለጡት እጅግ ወሳኝ ነገር ቀረጻው ከተጠናቀቀ በኋላ ከፕሮግራሙ ዳይሬክተር ጋር ያደረጉት ውይይት ነው። መሀዲ ሀሰን የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካ እና የቡድን ሽኩቻ ዝርዝር ጉዳዮች ከአንድ ጋዜጠኛ ከሚጠበቀው በላይ በሆነ ጥልቀት ማወቁ ያስገረማቸው ብስራት፣ ዳይሬክተሯን ተጋፈጧት። “መሀዲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ዝርዝር በዚህ ደረጃ ሊያውቅ አይችልም የእሱ ፍላጎትም አይደለም ይህ የእናንተ (የአዘጋጆቹ) ሥራ መሆን አለበት ብዬ በእርግጠኝነት እገምታለሁ” አሏት። ዳይሬክተሯ ጥፋተኝነታቸውን አምነው የመቀበል ዝምታ ነበር ያሳዩት፡ “በዚህ ጉዳይ ልትወቅሰኝ ትችላለህ ትክክል ነህ” ሲሉ በይቅርታ መስፈስ መልሰዋል። ይህ ሁሉንም አካሄድ ሴራውን ያጋልጣል። ያረጋግጣል። ፕሮግራሙ ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ ሴራ ሲሆን፣ ብስራት እንዳሉት ኢትዮጵያን ወደ “ባልካናይዜሽን” (መበታተን) ለመውሰድ በሚፈልጉ አካላት የተነደፈና የተደገሰ ነው። ኢትዮጵያን እንደ ዘነዘና ሲቀጠቅጥ የኖረው ትህነግ ጦርነቱን በኖቬምበር 2020 ከጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ሦስት አዳዲስ መንግስታት ከግጭቱ እንደሚወጡ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ “መንገዱን ማመቻቸት” እንዳለበት የሚገልጽ ሰነድ በእንግሊዝ ፓርላማ እየተሰራጨ እንደነበር ብስራት አስታውሰዋል። ወይም በሌላ ቋንቋ ኢትዮጵያ ተበትና ሶስት አገራት እንደሚመሰረቱ ለማለት ነው። አብይም በዚህ ደረጃ ዘመቻ የተከፈተባቸው ይህንኑ ስላመከኑ ነው።
መደምደሚያ፡ እነሱ በእጅጉ የሚፈልጉት ጦርነት

ኢትዮጵያን እንደ ወራሪ አድርጎ ለመሳል፣ ከኤርትራ ጋር የማይቀር ጦርነት እንደሚኖር ለማወጅ፣ እና ትግራይን ለመገንጠል የሚደረገው የማያቋርጥ ግፊት ከሰብአዊነት የመነጨ አይደለም። ለኢትዮጵያና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተቃዋሚዎች ፖለቲካዊ ፍጆታ አስፈላጊ ከመሆኑ አንጻር ከዛው ፍላጎት የመነጨ ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ምርጫ ዓመት (ግንቦት 2018 ዓ.ም. / 2026) እየተጠጋች ስትሄድ፣ ዓላማው እንደ ታሰሩ ጋዜጠኞች እና የፓርላማ አባላት ያሉ ጉዳዮችን በማጉላት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም ማጥፋት ፣ የትህነግ መሠረታዊ ሁከትፈጣሪንት ግን ችላ ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በሌሎች ክልሎች ውስጥ በሚያስደንቅ ፍጥነት እያደገች ነው። በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ በበለጸገች፣ በተዋሃደች ሀገር ውስጥ ባሉት ክልሎችና በወንጀል፣ እንዲሁም በአክራሪ የትህነግ ቅሪቶች ሳቢያ እንድተገለል በተደረገችው ትግራይ መካከል የሚኖረው ልዩነት ስፋቱ የማይካድ ይሆናል። ይህ ሃቅ የትግራይ ህዝብ መሪዎቹን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።
ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት አዲስ ጦርነት እጅግ በጣም አስፈላጊያቸው ይሆናል። ጦርነቱምም በኢትዮጵያ ሳይሆን፣ ሥልጣናቸው በዘላቂ ቀውስ ላይ በመሰረቱ አካላት ዘነዳ ይሆናል።
ሥልጣን ያጡት ወገኖች ዓለም አቀፍ ርኅራኄን እንደገና ለመቀስቀስ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ኃይል ለማስቆም፣ እና ትህነግ በራሱ ህዝብ ለፈጸመው ውድቀት ተጠያቂ እንዳይሆን ለመከላከል ሲሉ “ትግራይ ከበባ ውስጥ ናት” የሚል ትርክት ይቀሰቅሳሉ።
የመህዲ ሀሰን ፕሮግራም ለዚያ ቀውስ ማስጀመሪያ (catalyst) ለመሆን የተደረገ ግልጽ ሙከራ ነበር። ለጋዜጠኝነት ሙያ ውርደት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እና ሉዓላዊነት ጥያቄ ማጥላላትን፣ የአልጃዚራ + እና ይህች ጥንታዊት አገር እንድትወድቅ የሚመኙ አካላት ጥልቅ የሆነ አድሎና ተንኮል የታቀደበት ግልፅ ሴራ ነው።
አንድ መሪ “አገሬን ትልቅ አደርጋለሁ” ማለቱ ወንጀል ሆኖ የቀረበበት የመሃዲ የፊት ለፊት ፕሮግራም ጀርባ ሊደበቅ በማይችል መልኩ እርቃኑን የሚወጣው በዚሁ በራሱ ግብር ነው። ጸዳለና ብስራት የአንድ አገር ሁለት ልጆች!! አንዱ ኩራት ሌላኛዋ ሃፍረት!!
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






