“የክርስቲያን ቤት ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል” ያሉት ነዋሪው እሁድ ግንቦት 23 ከጠዋት ጀምሮ ጥቃቱ መፈጸሙን ተናግረው ሰኞ ዕለትም መቀጠሉን እና በአካባቢው “የሸኔ ባንዲራ” ተክለው እንደሚገኙ ተናግረዋል። ቢቢሲ
ነጻ አስተያየት በሰለሞን ግርማ አዲስ አበባ
“ባለኝ የጎንዮሽ ግንኙነት የአርሲውን ግድያ ከሰማሁ በኋላ ይህ ጉዳይ ተደጋገመ። ገዳዮቹ እየታወቁ ለምን በገሃድ አይወገዙም? አዲስ አበባ ቢሮ ያላቸው ከእነዚሁ ከሚታወቁት ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ወይም አብረው የነበሩ ስለምን ዝም ይላሉ? ግድያውን አስመልክቶ መግለጫ የሚያወጡትና አካላት ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ገዳዮቹን የሰላባው ቤተሰቦች ስለሚያውቁ ለምን ይፋ አያደርጉም? የሚለውን ጥያቄ ሳነሳ መልስ የሚሰጠኝ አጣሁ። የመንግስት አካላትም በተለይም ኦሮሚያ ክልልና የአካባቢው አስተዳደር ዝምታ ሊገባኝ አልቻለም” በማለት ያጫወቱኝ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ቅርብ የሆኑ አባት አገልጋይ ናቸው። የሳቸው ጥያቄና ስጋት የእኔም ነው።
ግንቦት 23 እና ግንቦት 24 በነበረው ጥቃት ከክርስቲያኖች በተጨማሪ ከአድማ በታኝ፣ ከሚሊሻ እንዲሁም ሙስሊም የአካበቢው ነዋሪዎች ተገድለዋል። ግድያው የተፈጸመው በኦነግ ሸኔ መሆኑን ሰላባዎች አስታውቀዋል። ጃዋር መሃመድ በበኩሉ መንግስት ግድያውን እንደፈጸመ በብርሃን ፍጥነት “የክርድቲያኖች ተቆርቋሪ ነኝ” ብሎ አስታውቋል። ገዳይን ሳይሆን የንጹሃንን ሞት በማጉላት የአዞ እንባ የሚያነቡ ጉዳዩን የፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ አድርገውታል። ጃዋር ሜንጫውን ጥሎ በዘረጋው ድንኳን ውስጥ ገብተው የሚጮሁ ነፈዞችም በንጹሃን ሞት ጀርባ በሚሰራ ድራማ እየተንቦጫረቁ ነው። በተደጋጋሚ ንጹሃን የሚገደሉባት አርሲን የሚመሩ የአካባቢው፣ የክልሉ፣ የፌደራል መንግስት “የት ናቹህ” የሚሉ ፍትህ ፈላጊዎች ከጃዋር ድንኳን ርቀው ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የጅምላ ግድያ ሲፈጸም ገዳዮች በድርጅታቸው ስም ወዲያው ኃላፊነት ይወስዳሉ። ለምን ግድያውን እንደፍጸሙ ይፋ ያደረጋሉ። አለያም ሰለባዎችን መሰረት ባደረጉ ምርመራዎች የገዳዮች ማንነት ይታወቃል። ያኮረፉ ወይም ለሆነ ዓላማ ንጹሃንን የሚገድሉ ሲያዙ ይናዘዛሉ። በአገራችን የሚሆነው የተገላቢጦሽ ነው። ገዳይን ሁሌም እየታወቀ እንቆቅልሽ እንዲሆን ይደረጋል።
በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት ህዝብ የሚያውቃቸው፣ በስም ለይቶ “ገደሉን፣ አፈናቀሉን” እያለ የሚጠራቸው ድርጅቶች ንጹኃን ይገድላሉ ኃላፊነት ግን አይወስዱም። የፖለቲካ፣ የዕምነት፣ አክቲቪስት ነን የሚሉ ወዘተ “ሰዎች በዕምነታቸው ተለይተው ተገደሉ” ከሚለው የዘለለ ገዳዮችን ለይቶ የመኮነን፣ የማውገዝ፣ የመቃወም እርምጃ አይወስዱም። ወይም በራሳቸው የግንኙነት ሰንሰለት ለማጣራት ሲሞክሩ አይታዩም። እንደውም የምስኪኖችን ሞት ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም ሲረባረቡበት ነው የሚስተዋለው። ሰክነው የሚያስቡ ዜጎች የሚያሳስባቸው ይህ ነው። ገዳዮች ላይ ከመረባረብ ይልቅ ለሟቾች በማንባት ተደጋጋሚ ለቅሶ መቀመጥ የተመረጠ ይመስላል። ቢያንስ ቢያንስ የምርጫ እለት ይህ ግድያ መፈጸሙን በማንሳት መጠየቅ የሚወዱ አይታዩም። አይሰሙም። ይህን ለማድረግ የሚሞክሩ ደግሞ ይወገዛሉ።
በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰዎችን ለይተው የሚገድሉ፣ የሚያግቱና የሚያፈናቅሉ ታጣቂዎች ይህን ድርጊት በተደጋጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጽሙ መስማት ተለምዷል። ሰላማዊ ተጓዦችን በጥይት እሩምታ የሚያስፈራሩ፣ የሚገሉ “የብሄርሰብ ነጻ አውጪ ነን” ባዮችና መንግስት ውስጥ የተሰገሰጉ ቡችሎቻቸው ተባበረው አንድ አውቶቡስ ሙሉ ህዝብ በጠራራ ጸሀይ እያፈኑ ገንዘብ ሲቀበሉ፣ሲያሰቃዩ መስማት አዲስ ጉዳይ አይደለም።
የአርሲ እና ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ባወጡት መግለጫ በምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሺርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች 13 የርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መገደላቸውን፣ ከ280 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን እና የ101 ዓመት ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን” አመልክተዋል። ይህ ዜና ከተሰማ ጀምሮ ውርጋጦቹን ጨምሮ የሚታወቁት ፖለቲከኞች ሻማ እያበሩ በማህበራዊ ገጽ የለቅሶ ድንኳን እየጣሉ ነው።
“በሌሎች ዓለማት ለምሳሌ ሂዝቦላ፣ አልቃይዳ፣ አልሸባብ ወዘተ ግድያም ሆነ እገታ ሲፈጽሙ ንብረት ሲያወድሙና የጅምላ ወንጀል ሲፈጽሙ ኃላፊነት ወስደው መግለጫ ያወጣሉ። በመግለጫቸው ወይም በቃለ ምልልስ ሳይሸማቀቁ የፈጽሙትን ድርጊት ለምን እንደፈጸሙም ያብራራሉ። ይህ የተለመደ ነው” የሚሉ የህግ ባለሙያዎች በአርሲ በተደጋጋሚ ደረሰ የተባለው ግድያ የጥቃት አድራሾቹን ማንነት እነሱ ራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ባያስታውቁም የአገሪቱ ሚዲያዎች የግልና የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የሚደብቁበት ምክንያት አሳሳቢ ነው እንደሆነ ይናገራሉ። አክለውም “ተጣርቶ ይቀርባል እየተባለ በዝምታ የሚታለፍበት አግባብ ግልጽ አይደልም፣ ይህም ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው” ይላሉ። ይህ የህግ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን የመልካም ዜጎች ሁሉ አስተያየት ነው። የኔም እምነት ነው።
ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስቲያኖች፣ ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸርካ ወረዳ 3 ክርስቲያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስቲያኖች መገደላቸውን ተከትሎ ቅዱስ ሲኒኖዶስ መግለጫ ሲያወጣ ስለገዳዮቹ የተባለ ነገር አልነበረም። በወቅቱ የአገረ ስብከቱ ኃላፊ ስለገዳዮቹ ማንነት ሲጠየቁ “ይህንን ግለጽ አልተባልኩም” ብለው ነበር። የሲኖዶሱ ጸሀፊም በተመሳሳይ “የተላከልንን መግለጫ ተንተርሰን ነው መግለጫ የምንሰጠው” በማለት ስለገዳዮች ማንነት ምንም ሳይሉ ነበር ያለፉት።
በምሥራቅ አርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች እሁድ እና ሰኞ ዕለት በተፈጸሙ ጥቃቶች 13 ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን ነዋሪዎች እና የአካባቢው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገረ ስብከት ኃላፊዎች በገሃድ ሳይሆን “ምንጭ” እየተባሉ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ምንጭ የተባሉት አካላት ስለገዳዮቹ ማንነት ለቢቢሲ ምንም አልነገሩትም።
ቅድሚያ ወስዶ ግድያውን የፈጽመው መንግስት እንደሆነ ያስታውቀው ጃዋር መሐመድ ነው። “በምዕራብ አርሲ ዞን ሄባኒ ወረዳ አርሲ ወረዳ 9ኙ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ነው” በማለት እያስታውቀ፣ በአንድ ቀን 50 ተሽከርካሪዎች ተቃጠሉ በማለት የምርጫውን መስተጓጎል እየዘገበ ግድያውን መንግስት እንደፈጸመው ያስታወቀው ጃዋር ተፈናቃዮች “ሸኔ አረደን” ላሉት ምላሽ አልሰጠም።
ከሶስት ሚሊዮን በላይ ተከታታይ ባለው የማህበራዊ ገጹ ለአፍሪካ ታዛቢዎች በአዲስ ስታንዳርድ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ መስጠቱን፣ ይህንንም ያደረገው በጽሁፍና በቃለ ምልልስ መሆኑን እያስታወቀ፣ ሞቱ ስለተባሉት የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮችና ተቃጠለ ስለተባለው ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ ድንኳን የጣለው “ወደ እኛ ክልል ከመጣ አንገቱን በሜንጫ ነው የምንቆርጠው” በማለት የዘር ፖለቲካን ሲጠምቅና ግድያን በገሃድ ሲሰብክ የኖረው ጃዋር መሐመድ ነው። በዚህ በጀዋር መሐምድ የስላቅ ድንኳን ውስጥ ገብተው የሚያነቡት ደግሞ የቅርብ ጊዜ ጃዋር ማንነትን የዘነጉ ነፈዞች ናቸው። ለሚያስተውሉ ግን የጃዋር ቀድሞ መጮህ ብዙ ይናገራል።
ጃዋር “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ወለጋ ሄዱ? የዘር ጭፍጭፍ የፈጠራል” ባለበት ሰሞን በምስራቅ ሃረርጌ ጎረጉቱና መሰላ / እሱ ከተወለደበት አካባቢና ከአርሲ የሚዋሰኑ ቦታዎች ናቸው/ የሚነሳ ታጣቂ ኃይል በቅርቡ አካባቢውን እንደሚቆጣጠር ተናግሮ ነበር። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአርሲ አቅጣጫ እስከ መሰላ የሚነቀሳቀሰው ኃይል በጃዋር የሚደግፈና የሚረዳ ነው። ጃዋር ተሽቀዳድሞ በፌስ ቡክ ገጹ “እንቀነጥሳችኋለን” ለሚላቸው ክርስቲያኖች ተቆርቋሪ የሆነበት ሚስጢርም ይህ ነው። ወደፊት በመረጃ ተደግፎ የሚወጣ ይሆናል።
የምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ከፍያለው ሸንቁጤ “እዚያ አካባቢ ትንሽ እርስ በርስ አለመስማማት አለ” በማለት ግድያዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ምርጫ መካሄዱን በማስታወስ በእነዚህ አካባቢዎች እርስ በርስ መጨራረስ የተደረሰው “ምርጫውን ለማደናቀፍ ይሁን ወይም ሌላ ምክንያት ስለመኖሩ አለመታወቁን” ጠቁመዋል። ይህ ለኔ ብዙ ይነግረኛል። ቢቢሲ ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ አድምቶ ያልጠየቀው ይህ ቁልፍ ጉዳይ በጃዋር የክርስቲያኖች ተቆርቋሪ መሆን ግልጥ ብሎ በመታየቱ የነገሩ መድበስበስ ይፋ አድርጎታልና ብዥታ የለም።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥቃቱ የተፈጸመው በምን ምክንያት እና በማን እንደሆነ ለይቶ ለመናገር አሁን እንደማይችሉ፣ በአካባቢው የፀጥታ አካላት እና የሚያጣራ ቡድን ማክሰኞ ዕለት ግንቦት 25/2018 ዓ.ም. መሰማራቱን ተናግረው ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን አመልክተዋል። ተፈናቅለው የተቀመጡ፣ ሮጠው እየተታኮሱ ያመለጡ እነማን እንደሆነ የገለጿቸውን ገዳዮች እሳቸው ለምን ይደብቋቸዋል? ይህ “እኔ ቢቢሲን ብሆን እጠይቅ ነበር” ብዬ የማልፈው ጉዳይ ነው።
በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን በተመለከተም “ግማሹ ዘጠኝ ይላል፤ ግማሹ ሰባት ይላል ይሄም ራሱ መጣራት አለበት” ብለዋል።
በአካባቢው ግንቦት 23 እና 24 የተኩስ እሩምታ እንደተከፈተ ጥቆማ እንደደረሰባቸው መረጃው እንዳላቸው የሚናገሩት ኃላፊው አንድ ቤተክርስቲያን ላይ “ትንሽ የእሳት አደጋ” መድረሱን በመግለጽ ይህንንም ወደ ቦታው የተሰማራው ቡድን አጣርቶ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል። ሙሉ በሙሉ መውደሙ ዋና ዜና የሆነውን ቤተክርስቲያን ትንሽ የእሳት አደጋ እንደደረሰበት ማመልክታቸው ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሳለ እንዲያብራሩት አልተደረገም ወይም መረጃውን ከየት አመጡት አልተባሉም። የትኛው ወገን ነው ሃሰተኛ ?
የተፈጠረውን በዝርዝር ለማስረዳት አጣሪ ቡድኑ የሚያመጣውን መረጃ አይተው ለመናገር እንደሚመርጡ በመግለጽ ኃላፊው ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል። ንግግራቸው ትክክል ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ “ተጣርቶ ይገለጻል” እየተባለ የንጹሃን ደም እንደዋዛ ቀርቷልና እንዴት እንመን የእኔ ጥያቄ ነው። በዚሁ አስተያየቴን በምጽፍበት አዲስ ሪፖርተር የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ያቀደሙትን ግድያዎች አጣርቶ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ የውሃ ሽታ መሆኑን ማስታወስ ግድ ያላል።
የቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው በአካባቢው ባለፉት ስድስት ዓመታት “በሸኔ ታጣቂዎች” ጥቃት በተደጋጋሚ ሲፈጸም እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ግለሰቦች ራሳቸውን ለመከላከል “በግላቸው መታጠቃቸውን” ይናገራሉ።
የተወሰኑ ሰዎች ከታጣቂዎቹ ጋር ሲታኮሱ ቀሪዎቹ ግን እየሸሹ ባሉበት መገደላቸውን ጨምረው ገልጸዋል። እነዚህ ስማቸው ያልተገለጸ የቤትክርስቲያን አገልጋዮች፣ “ገደሉን” ያሉዋቸውን በስም ጠቅሰዋል። እንዚህ ሰዎች እዛው ያሉ፣ በስፍራዉ የሆነውን በተደጋጋሚ የታዘቡ፣ ምን አለባትም በታምራት የተረፉ፣ ከዚያም ባለፈ የቀደሙትን ባልደረቦቻቸውን ቀብረው ታሪኩን ከስር መሰረቱ የሰሙ ምስክሮች ናቸው። እንግዲህ አቶ ጃዋርም ሆነ ጃዋር የጣለው ድንኳን ውስጥ ገብተው በጃዋር አዲስ ዜማ የሚፈተፍቱት ይህ ሃቅ እያለ ነው። እኔም በግል ያነጋገርኳቸው ተመሳሳይ ምላሽ ነው የሰጡኝ።
አገልጋዮቹ ለቢቢሲ ሲናገሩ ግንቦት 23 እና ግንቦት 24 በነበረው ጥቃት ከአድማ በታኝ፣ ከሚሊሻ እንዲሁም ሙስሊም ከሆኑ የአካበቢው ነዋሪዎች የተገደሉ መኖራቸውን ጨምረው ገልጸዋል። ሚሊሻዎች መሞታቸው፣ ሙስሊሞች መሞታቸው በደን ከተገለጸ ዜናው ለታሰበለት ዓላማ ስለማያመች ያነሳቸው የለም። ሙስሊም፣ ሚሊሻም ሆነ ክርስቲያን ህይወታቸው እኩል ነው። የክስርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ላይ መደጋገሙን ማጉላቱ አግባብ እንደሆነ እያመንኩ ሌሎችም ነብስ እንዳላቸው ሊታወቅ እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ሙስሊሞች አብረው ተግድለዋልና!!
ይህንን ሁሉ ስል የዞንና የወረዳ፣ የቀበሌ የመንግስት መዋቅር የት ነህ? የኦሮሚያ ክልል መሪዎች፣ የጸጥታ ሸርፉ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም፣ የፌደራል መንግስት ዝምታ በየትኛውም የሂሳብ ስሌት ትክክል እንዳልሆነ ዘንግቼ እንዳልሆነ መግለጽ እወዳለሁ። መንግስትንም ሆነ ክልሉን ከዛም አልፎ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ላይ ጫና ፈጥሮ ፍትህ እንዲሰፍን ማስገደድ የሚቻለው “ሜንጫ አንስቶ እቀነጥሳለሁ” ሲል በነበረው ክርስቲያን ጠል ጃዋር ድንኳን ውስጥ ገብቶ ለእሱና መሰሎቹ ፍላጎት ማዳበሪያ በመሆን አይመስለኝም።
ከሞቱት ወንድምና እህቶቻችን ህይወት ይልቅ የፖለቲካ ትርፋቸውን እያሰሉ በንጹሃን ደም የሚሞዝቁትን ማድመጥና ከነሱ ጋር ማበድ ለቀጣዩ ደህንነት ዋጋ አይኖረውም። ይልቁኑም ማን፣ ለምን፣ እንዴት፣ ምን ፈልጎ፣ ንጽሁሃንን በማንነት፣ በዕምነታቸው ሳቢያ ወዘተ እንዲህ መሰሉን ኢሰብአዊ ድርጊት ማን እንደሚፈጽመው ማስላቱና ይህ እንዲገለጥ የረጋ ጫና ማድረጉ ይበጃል።
በመጨረሻም ጃዋር መሐመድ “ወደ ትውልድ አካባቢያችን ከመጣህ በሜንጫ አንገት ነው የምንቀነጥሰው” በማለት በአደባባይ የዛተው ጃዋር ዛሬ “እንቀነጥሳችኋለን ላላቸው፣ እንዲፈናቀሉ አዋጅ ላውጣባቸው ክርስቲያኖች ተሟጋች ነኝ” ሲል አብሮ ማበዱ ሃቁን ስለሚደብቀው ጥንቃቄ ግድ ነው።






