አዲስ ሪፖርተር ዜና – ከለውጡ በፊት ኢህአዴግ የሰራውን፣ የሚሰራውንና የሚያቅደውን አስቀድሞ ይታወቅ ነበር። ከለውጡ በፊት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈጻሚው በር ዘግቶ የሚመክርበት አጀንዳ አፍታም ሳይቆይ ይሾልክና ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የወቅቱ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ሰዎች ይከፋፈል ነበር። ኢህአዴግ እየተዳከመ በሄደበት ወቅት ምንም ሚስጢር የሚባል ነገር አልነበረም እስከማለት ተደርሶ ነበር።
ይህንን ጉዳይ አንስተው ለአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ መረጃ የሰጡ ሰሞኑን በተደረገ የዋናዎቹ የአመጽ አደራጆች ስብሰባ እንደቀድሞ መረጃ ቀድሞ ማግኘት አለመቻሉ በዕቅድ፣ በፕሮፓጋንዳ፣ መንግስትን እየቀደሙ ማበሻቀጥና ማጥላላት ረገድ የተሳካ ስራ መስራት አለመቻሉ በድክመት መነሳቱን ይጠቁማሉ። በዚህም ሳቢያ በዘፈቀደ የሚሰሩ ፕሮፓጋንዳዎች ሳይውል ሳያድር መልሰው ገብረኃይሉን ወደ አለመተማመንና በሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል። “ሚስጢራዊ መረጃ ማግኘት አለመቻላችን እየፈረካከሰን ነው” ያሉት ተሰብሳቢዎች፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በንግግራቸው የብልጽግናን አመራሮች በዝምታ ማለፋቸው በጽምዶ አባላቶች ውስጥ ልዩነት ማስነሳቱን አመልክተዋል።
ከለውጡ በኋላም በተመሳሳይ የካቢኔና የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ የሚያሾልኩ በስም የሚታወቁ ባለስልጣናት እንደነበሩ በግምገማው ላይ ተነስቷል። መረጃ የሰጡት እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መረጃ የሚሰጡ ክፍሎች ከመንግስት ቁልፍ የስልጣን እርከን በተለያዩ ምክንያቶች ከወጡና በራሳቸው የፖለቲካ ዝንባሌ ከሸሹ በኋላ ጥብቅ የሆኑ የመንግስት ሚስጢሮችን ማግኘት አልተቻለም። በተባራሪ የሚገኙት መረጃዎችም በሚፈለገው ደረጃ “አገዛዙን” ሊያነቃንቅና ከሕዝብ ሊለይ የሚችል አልሆነም።
እንደ መረጃ ምንጩ ከሆነ አንድ ተሰብሳቢ /ስማቸው ይታወቃል/ “የሻዕቢያ የስለላ ድርጅት ጠንካራና እንደሆነ ይነገራል፤ እንሱ ለምን ብልጽግና ውስጥ እንዲገቡና ሚስጢሩን እንዲያገኙ አይደረግም? አብረን እየሰራን ከሆነ በዚህ አግባብ ለምን አያግዙንም?” በማለት መጠየቃቸው ተሰምቷል። ብዙም ማብራሪያ ሳይቀርብ “ይሞከራል” የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
በስም ለሚታወቁ የዩቲዩብ ቻናሎች በወንዝ ልጅነትና በፓለቲካ ትስስር፣ እንዲሁም ብር ያላቸው በዘረጉት መዋቅር ይፈስ የነበረው ሚስጢር መድረቁ “ሰበር ዜና” እንዲቆም ማድረጉን ያነሱት የመረጃው ባለቤቶች፣ “ቁልፍ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ በግምት ይጠቅማል እየተባለ የሚቀርበው አገዛዙን የማጣጣል ቅሰቀሳ ተመልሶ ራሳችንን ጎድቷል። በዚህም የተነሳ ወደ እርስ በርስ መከፋፈል አምርቶናል። አሁን ላይ የቀደመው ሞራልና ፍላጎት አይታይም” በሚል ሌላ ተሰብሳቢ ትዝብታቸውን እንዳቀርቡ አመልክተዋል።
በተደጋጋሚ ጠንካራ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ሌላ ተሰብሳቢ ደግሞ፣ “የብልጽግናው አገዛዝ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት እና ከአሜሪካ ጋር እያደረገ ያለውም ግንኙነት እንኳን ለመገምገም ፍላጎቱ የሌለን አለን” በማለት አገዛዙ ውስጥ መረጃ የሚሰጡ ከማጣታችን በላይ ወቅትንና የኃይል አሰላለፍን የመተንተን ችግር እንዳለም አስታውቀዋል።
“አቅጣጫ ጠፈቶብናል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት እኚሁ ተሰብሳቢ፣ “ሰሞኑን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ባደረጉት ንግግር ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለአገዛዙ ባለስልጣናት ምንም አለመተንፈሳቸው ግልጽ መልዕክት እንዳለው ማሰብ የማንፈልግ አለን ይህ አግባብ አይደለም። ባለፈው ዓመት በዚያ ደረጃ ሲዛለፉ የነበሩ መሪ አሁን ጸጥ ያሉት ለምን ይሆን?” ሲሉ ጥያቄ አዘል ሃሳብ ሰንዝረዋል።
በግልጽ የግብረኃይሉ የፊት መስመር መሪ እንደሆኑ የሚታውቁት የስብሰባው መሪ፣ “እኔም የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዝምታ አስገርሞኛል” በማለት ተናግረዋል። ምስክሩ እንዳሉት የግብረኃይሉ መሪ “ብልጽግና ውስጥ ሰዎችን ማስገባትና ቀደሞ የነበረውን መስመር ማስቀጠል ይገባል። እዚያ ላይ እንሰራለን” ብለዋል። “እንደተባለው የእኛ ድክመት ነው እንጂ ብልጽግና ጓዳው ሁሉ ክፍት የሆነ ድርጅት ስለሆነ በደንብ እንሰራበታለን” ሲሉ አክለዋል።
በመሪው ንግግር ላይ የተነተራሱት ሌላ ተናጋሪ፣ “እንኳን እነሱ ጋር ያለውን ቁልፍ መረጃ ልናገኝ ስለሚመረቁ ፕሮጀክቶች እንኳን አስቀድሞ ለማበሻቀጥ የአደባባይ ዜና ማግኘት አልቻልንም። ይህን ማመን አለብን” ካሉ በኋላ “የአገዛዙን ሚስጢር ማወቅ ቀርቶ የራሳቸን የዕለት ተዕለት ስብሰባና የስልክ ውይይት እንኳን መደበቅ አለመቻላችን አስደንጋጭ ነው። በግሌ ይህ ዝርክርነት እርስ በርስ እንዳንተማመን አድርጎናል። አንዳንዶቹ ባልደረቦቻቸን /ስም ዘርዝረዋል/ ጥለውን የሄዱት በዚሁ መነሻና ባለን የግልጽነትችግር ሳቢያ ነው” የሚል ጠንካራ አስተያየት በመዘርዘር ወደ ውስጥ ማየት እንደሚሻል አመልክተዋል።
“ኢሳያስ የኢትዮጵያ ምንግስትንም መሆን ባለስልጣኖችን ምንም ሳይሉ ማለፋቸው የሚጠብቅ አልነበረም” ያሉት ሌላ ተሰብሳቢ፣ “በጓሮ ምን እየተደረገ ነው?” የሚል ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አመልክተው፣ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ማወቅ እንኳን አለመቻል ጥርጣሬ እንደሚያሳድግ አስታውቀዋል።
በቀደሙ ስብሰባዎች ላይ “ከማን ጋር እንደምንዋጋ እንኳን አልገባንም” በሚል የአሜሪካና የኢትዮጵያን አሁናዊ ግንኙነት በስጋት ያነሱትን የግብረኃይሉ አባል በማስታወስ የተናገሩ “አሁን አሁን መረጃ ማጣታችን አለመተማመን አስክትሏል። አንዱ ቡድን ሌላውን አሳልፎ ሊሰጠኝ ከጀርባዬ እየሰራ ነው የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ይከተል። ይህ አሁን የታየውን መለያየት የበለጠ ያሰፋዋል። ከዚህ በፊት ሲከሰት እንደኖረው ቀጣዩ እርምጃ ሳይቀድሙኝ መቅደም ይሆናል። ይህም እርስበርስ መበላላት የሚያስከትል የአደረጃጀታችን የመጨረሻው ደረጃ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አምረው ተናግረዋል።
ከግብረኃይሉ ውስጥ ሱዳን እና ኤርትራ የሚመላለሱ መኖራቸው፣ በተለይም በፖርት ሱዳን ተሰባስበው ኢትዮጵያን ለመውጋት ህብረት መመስረቱ ይፋ ሲሆን “ተሸውደን ነበር” በማለት “በቃን” ያሉ ምኖራቸውን የዋሽነግቶን ተባባሪያችን ማስታውቁ አይዘነጋም። ከዚሁ “ጽምዶ” ተመሰረት በተባለ ማግስት “አዝማችና መልዕክተኛ” የሚባሉት ኢሳያስ አፉወቂ መንሸራተታቸው አቶ ነዓምንን ጨምሮ በርካታ በህብረቱ ዙሪያ ያሉትን ማበሳጨቱ እየተገለጸ ነው።
ለውጡ አኩራፊውንም አካቶ የተነሳ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ የነበረውን ክፍተት እየሞላ አሁን ላይ የደረጀ መሆኑን የሚናገሩ ከምርጫ በኋላ ብዙ የሚጠበቁ ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ይናገራሉ።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






