አዲስ ሪፖርተር – ግብፅ፣ ኢሳያስ እና የሱዳኑ ጄኔራል አል ቡርሃን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና መረጋጋት ለማዳከም እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ መኖራቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ የቆየ ጉዳይ ነው። ከሱዳን የሚወጡ የቪዲዮ ማስረጃዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው።
አልቡርሃን ፋኖን እና የህወሃትን “አርሚ 70” ስታስታጥቅታጥቅ የቆየ ሲሆን፣ እንደ ቅጥረኛ ኃይልም እየተጠቀመባቸው ይገኛል። ይህም በምስልና በቪዲዮ ተደግፎ በወጡ መረጃዎች ተደጋግሞ የተረጋገጠ እና ሱዳንም ሆነች አብረዋት የተሰለፉት የማይክዱት እውነት ነው።
ከጥቂት ቀናት በፊት አልቡርሃን በሱዳን ውስጥ ከዲያስፖራ ከተወከሉ፣ ከፋኖ፣ ህወሃት እና ጥቂት የጉሙዝ አማፂያን የተውጣጡ የቡድኖቹን ወኪሎች በኤርትራ አቅራቢነት በግብፅ ባለስልጣናት ታዛቢነትና መሪነት ሰብስበው ኢትዮጵያ ላይ መክረዋል።ይህም በምስል፣ ድምጽና በቪዲዮ የተረጋገጠ መረጃ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያንና የሱዳንን ወንድማማችነት በማክበር ከፍተኛ ትዕግስት ለማሳየት የመረጠ ሲሆን፣ ለአልቡርሃን ወገን በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ቆይቷል። ባለስልጣኖቹን ፖርት ሱዳን ድረስ በመላክ ምክክር ማድረጉ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ይህንን ዜና የራሱ የሱዳን መንግስት የዜና ማሰራጫዎች ይፋ አድረገውትም ነበር።
ምንም እንኳን በዚህ ደረጃ ምክክር ቢደረግም፣ በግብጽ ፕሬዚዳንት አልሲሲ እና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ መሪነት ኢትዮጵያ ወደ ብሄራዊ ምርጫ ለመጓዝ ጥቂት ሳምንታት ሲቀራት የተቀናጀ ዘመቻ ጀምረዋል። “ሀገሪቱን ለማወክ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው” በሚል በቻሉት መንገድ ሁሉ እየሰሩ ነው።
ሱዳን፣ ግብጽ እና ያሰማሯቸው በጋራ ሆነው የፕሮፓጋንዳ፣ በ”ኢትዮጵያዊነት” ሽፋን አገራቸውን በሚያደሙና “ሱዳን ለምን ትነካለች” በሚሉ አካላት የታጀበው ህወሃትም “መንግስት ገልብጬ የትግራይን መሬት በኃይል አስመልሳለሁ። አራት ኪሎ ያለውን መንግስት እገለብጣለሁ” ያለው ተግባራዊ አድርጓል።
ህወሃት በስሌት የጊዜ ገደቡ ከአንድ አመት በፊት የተጠናቀቀውን፣ በህገ-ወጥ መንገድ የተመረጠውን የክልል ምክር ቤት በመመለስ ወደ ቀድሞው የጦርነት አቋሙ እንዲመለስ በማድረግ፣ ሱዳንና ኤርትራ እንዲሁም ግብጽ “በወንጀል አጋር የምንሆናቸው አገኘን” ብለው አስበዋል።
በዚህም ምክንያት አልቡርሃን የኢትዮጵያ መንግስትን በመወንጀልና ታሪኮችን በማዛባት ድብቅ ሴራውን እንደ መንደርደሪያ በመጠቀም፣ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ግንባር ቀደም አገልጋይ መሆኑን የሚያሳይ ከቀድሞው የበለጠ ግልጽ መረጃ ይፋ ሆኖበታል።
የኢትዮጵያ መንግስት እውነተኛ የጎረቤትነት ወዳጅነት የሚፈልጉ ከሆነ ትንኮሳዎችን ለማስወገድ ምን መደረግ እንዳለበት በተደጋጋሚ ማስታወቋን፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ባለው ግጭት ገለልተኛ በመሆን፣ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከግጭቱ ለማትረፍ ከሚሯሯጡ አካላት ጣልቃ ገብነት ውጪ በቀጥታ በሚደረግ የሰላም ስምምነት ሰላማቸውን እንዲያገኙ አቋሟ መያዟን ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ይፋ ያደረጉት ጉዳይ ነው።
ይህን ሁሉ የኢትዮጵያን ጥረት ጠንቀቀው የሚያውቁት አልቡርሃን ከሱዳን ይልቅ ለግብጽ ስለሚሰሩ ኢትዮጵያን አመድ አፋሽ አድርገዋል። እና ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ስትፈርስና የጎበዝ አለቆች መፈንጫ ስትሆን ዝም ልንል ይገባል?
ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት በመርህ፣ በፖለቲካ መስመር፣ በህገ መንግስት ጉዳይና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተዝጎረጎረ አቋም ያላችው ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ ሲረባረቡ ኢትዮጵያዊያን ዝም ብለው እ ንዲመለከቱ ይጠበቃል?
“ገና ካሁኑ በሱዳን እና በኤርትራ ብር እንጠቀማለን” የሚሉንን ወገኖች አምነን፣ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለሱዳን እየተሟገቱ ያሉ ቡድኖች የሚነገሩንን እየሰማን ኢትዮጵያዊያን አገራችንን እንዲሁ በዋዛ ለማፈራረስ እንስማማለን?
ሻዕቢያ ወያኔን አዝሎ መከላከያን አፈረሰ፣ ኢትዮጵያን ዘረፈ፣ አሁንም በየስርቻው የሰገሰጋቸው ጀሌዎቹ ከተራ ቲማቲም ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ እየሸቀጡ መኖራቸው አንሶ አብረው ሲበሉን፣ ዳግም የተገነባውን መከላከያችንን ለማፍረስ ዕቅድና የዝርፊያ ፕላን አውጥተው መነሳታቸውን እየነገሩን ኢትዮጵያዊያን እንተኛለን?
ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያቸውን እንዲሁ በሽለላ፣ ፌስቡክና ዩቲዩብ ጫጫታ ለታሪካዊ ጠላታቸውና ለአስፈጻሚዎቻቸው አሳልፈው እንዲሰጡ ይጠበቃል? ረጋ ተብሎ የሚታሰበበት ወቅት ነው። ማስተዋልና በእርጋታ ነገሮችን መመርመር ከጸጸት ይጠብቃል።
ይህን ያልነው በቀናነት፣ ሁሉም ዜጋ እንዲያስብ፣ እንዲመክር እና የወደፊቱን ለማየት እንዲነሳሳ ነው። ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጠላት ስታደራጅ፣ ኤርትራ ኢትዮጵያ ላይ ተላት ስታደራጅ፣ ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ጠላት ስትፈለፍልና ዓለም ዓቀፍ ሽብር ስታስነሳ ያላወገዙ “ኢትዮጵያዊያን”፣ ይባስ ብለው ሱዳን ለመን ትገነካች የሚሉን “ኢትዮጵያችን” ምን እንድታገኝ ተመኝተውላት ይሆን? ይህን መጠየቅ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። ኢትዮጵያ ብታደርገውና የሱዳን መንግስት እንዲወድቅ ብትሰራ፣ ሱዳን ከድሮ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሰራችው እልፍ ሴራና ጥፋት አንጻር እንዴት ስህተት ነው ተብሎ በራሷ ዜጋ ያስወቅሳታል? “እንዲህ ያለው ኢትዮጵያዊነትስ ምን የሚሉት ዓይነት ኢትዮጵያዊነት ነው?
መንግስት እንደመጣው ይሄዳል። ባለስልጣን እንደመጣ ይሄዳል። ሁሉም አላፊዎች ናቸው። በሌላ ይተካሉ። ከሚሄዱት ውስጥ በጣም ጥቂቶች ናቸው ለመታሰቢያ የሚሆን ድንጋይ እንኳን የሚቆምላቸው። በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሄር ቡሉኮና በቡድን ድጋፍ ካልሆነ በቀር መታሰቢያ የሚቆምላቸው ላይ የጋራ ስምምነት የለም። እናም በዚህ መዘባረቅ ውስጥ የከተቱን ኃይሎች ናቸው ኢትዮጵያን ይረከቡ እየተባለ ያለው። ይሳካል አይሳካም ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊያን ይህን የተቀነባበረ ሴራና አገር የማፍረስ ዕቅድ መረዳት አንዴ ከዘመመ የማይመለሰውን ምሶሶ እንዲንከባከቡ ይረዳቸዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






