- አዲስ ሪፖርተር – ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መከፋፈሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። የተመዝጋቢ መራጮች ቁጥር 50 ሚሊዮን ማለፉ ተመለከተ።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ እና መሰል እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሙበት ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ መከፋፈሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቧቸው እጩዎች ፣ በሴት እና በአካል ጉዳተኛ እጩዎቻቸው ብዛትና በተለያዩ መስፈርቶች ነው ቦርዱ ገንዘቡን ያከፋፈለው።
ለ7ኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ እየተከናወነ ያለው የመራጮች ምዝገባ አዲስ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል ተብሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መረጃ፣ ለምርጫው የተመዘገቡ ዜጎች ቁጥር ከ50 ሚሊዮን አልፏል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንደገለጹት፣ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በአጠቃላይ 50,514,155 መራጮች ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ወስደዋል። ይህ ቁጥር አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተመዝጋቢዎች የተሳተፉበት ነው። ተመዝጋቢዎቹ 27,390,729 ወንዶችና 23,123,426 ሴቶች እንደሆኑም ታውቋል።
በዘንድሮው የምዝገባ ሂደት ውስጥ ትልቁን ትኩረት የሳበው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነው። ከጠቅላላው ተመዝጋቢዎች ውስጥ 5,503,561 የሚሆኑት በዲጂታል አማራጭ ምዝገባቸውን ያከናወኑ ሲሆን፣ ይህም የምዝገባ ሂደቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ ለወጣቱ መራጭ ትልቅ ምቾትን የፈጠረ ሆኗል።
”ይህ የ50 ሚሊዮን ቁጥር መሻገር ለምርጫ ቦርድ የሎጂስቲክስ ሥራ ትልቅ ፈተና ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግን ትልቅ የባለቤትነት ማረጋገጫ ነው!” ተብሏል። ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱ በሰላም መጠናቀቁን ገልጾ፣ ለቀጣዩ የምርጫ ሂደት ዝግጅቱን እያጠናከረ መሆኑን ጠቁሟል።
በአሜሪካን አገር ያሉ የተለያዩ ማህበራትና ፖለቲከኞች “ይህን ምርጫ ተቀባይነት እንዳይኖረው እናድርግ” በማለት ህዝብ እንዲያምጽ የተቀናጀ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ ደጋግመው እየገለጹ እንደሆነ በተደጋጋሚ መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






