ሃብትሽ ተኳኩላ የምታወራው ሁሉ የፋኖን ሃጢያት ለማጠብ ነው። “በቃህ ሊባል ይገባዋል” በማለት ጥምብር ኩሱን ሲያወጣው የነበረውን ዘመን ካሴን መቼ ማምለክ እንደጀመረ ባይታወቅም እየጠቀሰ ወያኔ ይኩላል። ሙክት ካኮላሸው እንዲሉ ወያኔ የወልቃይት ጉዳይን እንደማንኛውም የአገሪቱ የወሰን ችግር አድርጎ በፋኖ ጫና መቀበሉን ይናገራል። “ወልቃይት ጠገዴ ራያ እያልክ አታልዝን፤ ኤርታራና ትግራይ ያ ሁሉ ግፍ ደሶ ዛሬ ባድመና ዛላንበሳ ማለት አቁመው ጥምረት ፈጥረዋል” በሚል ከደረቅ እጥበት አገልግሎቱ እየጎተተ የፈጠራ ትርክት ይረጫል። ሱዳን ኢትዮጵያ ድንበር ከፋኖ ጋር አብሮ የተሰለፈው የአርሚ ሰባ አባል “ፋኖ የመሬት ጥያቄ የለውም አራት ኪሎን ነው የሚፈልገው። እኛ ወልቃይት ስንገባ እነሱ ወደ አራት ኪሎ ያመራሉ” ሲል በዚህ ጉዳይ ስምምነት መደረሱን “የወልቃይት ዘብ የሌባ ስብስብ ነው …” በማለት ትግራይ እንደምትገነጠል ያረጋግጣል። ሃብትሽ ስንቴ ትገላበጪ?
ነጻ አስተያየት ከተሻገር መላኩ ጎንደር
አዲስ ሪፖርተር ዜና “ብልጽግናን ለመጨፍጨፍ እየተዘጋጃችሁ ነው አይደል?” ይላል ጠያቂው። “ሱዳን ነኝ ነው ያልከው? አርሚ ሰባ ነህ?” ሲለው “አዎ” ይላል። ዋና ዓላማቸው ምን እንደሆነ ይጠይቀዋል። “ሰላም” ሲል ይመልሳል የአርሚ ሰባው አባል። ጠያቂው “ጫካ ገብተህ፣ ሱዳን ተቀምጠህ ሰላም አለ?” ይለዋል። የአርሚ ሰባው አባል “ዓላማችን ሰላም ነው” በማለት ይመልሳል።
በዋናነት ምን ለማድረግ እንደሚጓጉ በማንሳት ጠያቂው ደግሞ ይጠይቃል። “መሬታችንን ማስመለስ። ወደ ሌላ መሄድ አንፈልግም” የሚል ምላሽ ይሰጣል። ጠያቂው ደጋግሞ “የትኛውን መሬት?” ይለዋል። “ወልቃይትን” ሲል የአርሚ ሰባ ታጣቂ ይመልሳል። በዚህ አስገራሚ ምልልስ የአርሚ ሰባ ታጣቂ እጅግ ቁጥብ ሆኖ አጫጭር ምላሾችን ይሰጣል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አስተዳደርን ማፍረስ፣ ይህ ከተሳካ ከብልጽግና ጋር የሚያጋጭ ሌላ አጀንዳ እንደሌላቸው ጠያቂው አነሳ። “ወልቃይትን ካስመለስን ወደ ሱዳን መውጫ ይከፈታል። ወደ ሱዳን ትሄዳለህ በቃ” በማለት የጉዳዩን አስኳል የአርሚ ሰባ ታጣቂ አስታወቀ።
በሱዳን ኢትዮጵያ ድንበር ከሰላ ውስጥ እንዳሉ ካረጋገጠለት በኋላ፣ ከኤርትራ ወታደሮች ጋር አብረው ስለመሆናቸው ሲጠየቅ “ለየብቻ ነን” በማለት አንድ ላይ ባይቀላቀሉም ተለይተው በአንድ አካባቢ እንዳሉ ይመልሳል። የትግራይ ሕዝብ የከፋ ችግር ላይ ነው እየተባለ ትጥቅ ከየት እንደሚያመጡ ጠያቂው ያነሳል። “ይህን አላውቅም” ይለዋል።
ወልቃይትንና ራያን ካስመለሳችሁ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚቀጥሉ ሲጠየቅ “ኧረ… የሚቀጥል የለም። ልቀጥል የሚል አመራርም ካለ እራሱ መጥፋት የሚፈልግ ነው የሚባለው። እኛ እላይ ያሉትንም ስለምናውቅ ወደ ኢትዮጵያ የሚተጋ የለም” በማለት የሰማውንና የሚያውቀውን ይመሰክራል።
“ወልቃይትን ስትይዙ ከአማራዎች ጋር አትጋጩም?” በማለት ጠያቂው ዋናውን ጉዳይ ያነሳል። “እዚህ እኮ አማራዎች ፋኖዎች አሉ” በማለት የአርሚ ሰባ ታጣቂው ይጀምራል። “ቅማንት አለ። መተማ ያለው ፋኖ አብሮን ነው” በማለት ይዘረዝራል።
ከጀግናው ፋኖ ጋር በወልቃይት ጉዳይ ስምምነት እንዳላቸው ሲጠይቀው “አዎ ጀግናው! እነሱ ለመሬት ስለማይዋጉ በወልቃይት ጉዳይ ተስማምተናል” በማለት ይመልሳል የአርሚ ሰባ አባል። አክሎም “እነሱ ዓላማቸው አራት ኪሎ ነው። ወልቃይት ምናምን ውስጥ የሉበትም” በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል።

“እነሱ በደንብ ያውቃሉ። የተማሩ ሰዎች ናቸው የሚመሯቸው። ወደ እኛ ከተኮሱ አሥር ዓመትም ቢዋጉ አይሆንላቸውም፣ ከጫካም በጭራሽ መውጣት አይችሉም” በማለት የፋኖ ኃይሎች ከእነሱ ጋር መስራታቸው ወደ አራት ኪሎ ለመጓዝ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ የአርሚ ሰባ አባሉ ይናገራል።
“እናንተ ወይስ እነሱ ናቸው በትብብሩ ተጠቃሚ?” ሲለው “እኛ ነን። ብዙ የተማሩ አዋቂዎች አሏቸው” በማለት ይመልሳል። አክሎም “አገር እንድንሆን ቅማንትና እነሱ ይረዱናል” በማለት በዚሁ አግባብ ለተጠየቀው ይመልሳል።
“ጦርነቱ ሲጀመር አራት ኪሎ እንዲገቡ ታግዟቸዋላችሁ?” ለተባለው “ዋ! ጦርነቱ አንዴ ከተጀመረና ሁመራ ከተያዘ ራሳቸው ያሸንፋሉ። ወዲያው ነው የሚያልቀው። እናውቀዋለን፤ የት ምን ምናምን እንዳለ እናውቃለን” የሚል ምላሽ ይሰጣል። የኦነግ ሰራዊትን አስመልክቶ ሲጠየቅ “በውስጥ መስመር እልክልሃለሁ” ብሎ ያልፈዋል። በውስጥ መስመር እንደሚልክለት ይስማማሉ።
“የተከዜ ዘብን እንዴት ታየዋለህ?” በማለት ላነሳለት ጥያቄ የአርሚ ሰባ ታጣቂው “እነሱ የሌባ ስብስብ ስለሆኑ የአማራ ሕዝብ ወዛ የሚገባበት ነገር የለም። እየጠፋ ያለ ሕዝብ ስለሆነ እኛ ከደረስን ‘አሸበል ገዳዬ’ የሚል ሕዝብ ነው። በፍላጎት ነው የሚቀበለን፣ ስለምናውቀው ማለት ነው። አሁን ጦርነት ብንጀምር መንገድ አይዘጋም። ሰላም የሚፈልግ ሕዝብ ነው” ሲል ይደመጣል።
ሕዝቡ የተከዜ ዘብ እና አስተዳደሩ ፈርሶ እነ ኮሎኔል ደመቀ ሲወገዱ “እልል ብሎ” እንደሚቀበላቸው ይገልጽና ከጠያቂው ጋር ይሰነባበታል።
ይህን ከላይ የተቀመጠውን ቃለ ምልልስ እንደ ወረደ ያቀረብኩት፣ ሀብታሙ አያሌው ሰሞኑን ለአማራ ሕዝብ ያስተላለፈውን ድርሰት በጥሞና መመርመር ስለሚገባ ነው።
ሀብታሙ አያሌው በሌብነት ከኢትዮ 360 ባልደረቦቹ ጋር አደባባይ ተካስው ከተለያዩ በኋላ፣ በከፈተው ‘ሰገነት ምናምን’ በተባለው የልመና ቻናሉ፣ በትግራይ የፋኖ አመራሮች ገነውና አይለው የወጡበት የትብብር ቻናል እንደተመሰረተ ነግሮናል።
ሀብታሙ ለአማራ ሕዝብ በመቆርቆር የተለያዩ ታጣቂዎች እንደተሳተፉበት የተነገረለትን ካውንስል መመስረት እንደሰማ ማጣራት እንዳደረገ ጠቅሶ፣ በዝርዝር እንዳለው ካውንስሉ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ በሚል አደረጃጀት የተከፈለ ነው።
የአማራ ሕዝብ አጀንዳ ተብሎ ፋኖ ለውጊያ የተነሳበትን አጀንዳውን አንዱን እንኳን እንዳልቀየረ ሀብታሙ ዲሲ ቁጭ ብሎ አረጋግጧል። ዘመነ ካሴን “ከሃዲ” እያለ ሲዛበትበት የነበረውና የእስክንድርን ወገን በመደገፍ የሚታወቀው ሀብታሙ አያሌው፣ መቀሌ የተቀመጠውን ዘመነንና የእሱን መዋቅሮች ጠቅሶ “ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት አማራን ጨቋኝና ገዢ ያደረገው ጨዋታ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ፍጹም እንደማይቀበለው አቅርበው መተማመን ላይ መደረሱን አረጋግጫለሁ” ብሏል።
ከበደኖ እልቂት ጀምሮ በአማራ ላይ የደረሰው ግፍ ተጣርቶ የብልጽግና መንግሥት ከተወገደ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚሳተፉበት ገለልተኛ አካል ፍርድ እንዲሰጥ ፋኖ የማይናወጥ አቋም በመያዝ መቀሌ ሆኖ ሕወሃት ላይ ጫና አሳድሮ መተማመን ላይ መደረሳቸውንም እንዳረጋገጠ ሀብታሙ ድስኩሯል። ምርመራው ሕወሃት ‘ፋኖና ሻዕቢያ ፈጸሙት’ ያለውን “ጄኖሳይድ” እንደሚያጠቃልል ፋኖ መስማማቱን ሀብትሽ እነ ዘመነን ጠቅሶ አመልክቷል።
የወልቃይት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ያሉትን የወሰን ችግሮች ለመፍታት ሕወሃት አዲስ በሚቋቋመው ካውንስል መሠረት መስማማቱን ሀብታሙ ተናግሯል። ይህንን የምታነቡ ከላይ የአርሚ ሰባ አባል ሱዳን ሆኖ የተናገረውን ለሀብታሙ “የድርጅት ባልደረባህ ያለውን ሰምተሃል ወይ በሉና ላኩለት።”
አቶ ልደቱ አያሌው “ለምን ሕወሃት ተነካ” በሚል በሕወሃት የዘር ፍሬና ጡጦ ያደገውን የሕወሃት ምልክት አሉላን ሲሳደብ ከገረመኝ በኋላ፣ ያጠወለወለኝ የሀብትሽ ስላቅ ነው። “ሕወሃት እስር ቤት ውስጥ አኮላሸኝ፣ መቀመጫዬን አበላሸኝ” በማለት በምስኪኖች ፊት አልቅሶ ያስለቀሰው ሀብታሙ፣ “ሕወሃት የወልቃይት ጉዳይ እንደ አፋርና ሶማሌ፣ እንደ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች የወሰን ችግር እንዲታይ ተስማምቷል” በማለት ከላይ የአርሚ ሰባ አባል ያፈረጠውንና በተለይ አማራውን ያበሳጨውን፣ የፋኖ ታሪክ የማይረሳውን የክህደት ድሪቶ ሊያራግፍ የሄደበት ርቀት አስገራሚ ነው።
ሕወሃት በምንም ጉዳይ የሚታመን ድርጅት ባይሆንም፣ ወልቃይት ጠገዴን አስመልክቶ ያለው አቋም ግን አንድም ሳይሸራረፍና ሳይምታታ ግልጽ አድርጎ የኖረበት፣ የሚኖርበት የፖለቲካና ከላይ የአርሚ ሰባ ታጋይ በስልጠና ከጨበጠው ዕውቀት ነቅሶ እንዳለው አገር የመሆን ምኞቱ መደምደሚያ ማኅተሙ ነው።
ሀብታሙ ለዚሁ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ሱዳን ከተላከው ከአርሚ ሰባ ምስክርና፣ ሕወሃት ያለ አንዳች ማቅማማት በገሃድ እንደ ዳዊት የሚደግመውን ሐቅ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የናደበትን ማኅተሙን ፋኖ መቀሌ ሆኖ እንዳስወለቀው ሀብታሙ አያሌው ሲሰብክ ስሰማ “አይ ሰውነት!” ብዬ ብዙ ርቀት ወደ ኋላ ተመለስኩ።
የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ወጣቶች አደራጅ፣ በአቶ ስብሃት ነጋ “ልጃችን” የሚባለው ሀብታሙ አያሌው፣ በሳቅ የገደለን “አቶ አንዳርጋቸውና የኤርትራ ተወካዮች በተገኙበት የሱዳን ‘ጽምዶ’ መድረክ ላይ አፋብን አልተገኘም” በማለት የፋኖን ኃጢአት ለማጠብ የከፈተው “ፋኖ የደረቅ እጥበት ላውንደሪ” በገሃድ በጥሩ ዋጋ መከፈቱን መስክሮልኛል።
“ፋኖ ‘ጽምዶ’ የሚባለውን ቃል እንደማይፈልገው ጠንካራ አቋም ይዞ በመከራከር…” እንደ ሀብታሙ ትንተና ፋኖ ‘ጽምዶ’ የሚባለው ሕብረት እንደማይወክለው መቀሌ ቁጭ ብሎ ሞግቷል፤ አዲስ የተመሰረተውን ካውንስልም እንደማይመጥን አምኖ ስሙን ለመቀየር አንድ እርምጃ ተራምዷል። በተለይም ‘ጽምዶ’ የሚለው ስም ሱዳንና ኤርትራ ያሉበት በመሆኑ ፋኖ እዚያ ውስጥ ሊገባ የማይችል ጻድቅ እንደሆነ ሀብትሽ ተቦትርፋለች። ለምን ቢባል ፋኖ ሱዳንን የማይረግጥ፣ ከሻዕቢያ ጋር የማያብር፣ ኢትዮጵያዊ ክብሩን የጠበቀ ነጻ አውጪ ሆኖ እንዲሳል ሀብትሽ የደረሰችው ድርሰት የበላችውን ከማሳየት ባለፈ ሌላ ትርጉም እንደማይሰጥ ለመረዳት ብዙም አያዳግትም።
“የዛላንበሳ፣ የባድሜ ጉዳይ የኤርትራና የትግራይ ሰዎች ያ ሁሉ ችግር ደርሶ፣ ዛሬ ላይ አያነሱትም። አንተ ዝም ብለህ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እያልክ አታላዝን” የወዶ ገቧ ሀብትሽ ማሳረጊያ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






