“ህወሃት በበተነው መግለጫ ‘የአፍሪቃ ቀንድን የሚያተራምስ’ ያለው አይቀሬ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጠይቋል። ህወሃት የንግግር ጥያቄ ሲጠይቅ ኤርትራ፣ በሽብርተኛነት የተፈረጀው የሱዳን መንግስት፣ ፋኖን ጨምሮ ስምንት የሚሆኑ የነጻ አውጪ ኃይሎችን አንድ ይዞ የጦር ህብረት ወይም ጽምዶ መመሰረቱን ሊያውጅ በዋዜማው ላይ ሆኖ ነው፤ የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ይህንን ሩጫና ሱዳን ሳይቀር የተፈጸመውን ጽምዶ ያውቃሉና ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙም ምርምር የሚተይቅ እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ። ሂዝቦላን፣ የመን ሁቲ እና አልሸባን ካደረጃው የኢራን መንግስት ጋር አብሮ ከሚሰራው የሱዳን አሸባሪ መንግስት ጋር ወታደር አሰማርቶ እየሰራ ያለው ህወሃት፣ ለአፍሪቃ ቀንድ አሳቢ ሆኖ የቀረበውና ይህንኑ ስጋቱን ጠቅሶ ‘እኔን ስሙኝ’ የሚለው ጉዳዩን በደንብ ለሚረዱት አገራትና ሃያ አራት ሰዓት በአየርና በምድር ስላለላ ላይ ላሉት አገራት ነው” ይላሉ መግለጫውን የገመገሙ። ሰላም በውይይት ቢፈጠር ክፋት እንደሚለውና እንደሚደግፉ ያመልከቱት የስምረት አባል “አገራቱ ሙሉም መረጃ አላቸው። ከራሳቸው መረጃ በተጨማሪ ከነሱ ይልቅ እኛን ያምናሉ” ብለዋል።
አዲስ ሪፖርተር ሰኔ 2026 ዓ.ም (አዲስ አበባ) — በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሃት) መካከል የተደረገው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት (CoHA) በተደራጀ መልኩ መፍረሱን እና ሰሜን ኢትዮጵያ በድጋሚ “አስከፊ እና ሊቀለበስ የማይችል” አዲስ የጦርነት አፋፍ ላይ መድረሷን በመግለጽ ህወሃት ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አስቸኳይ የዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት ጥሪ አቀረበ።
ፋኖን ጨምሮ ስምንት የሚሆኑ ታጣቂ ኃይሎችን መቀለ ሰብስቦ የጦር ህብረት ለመመስረት ምክክር ከጀመረ የሰነባበተው ህወሃት ሰኔ 3 ቀን 2026 ዓ.ም ለዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች እና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ያሰራጨው ባለ 3 ገጽ ይዘት ደብዳቤ፣ “ኤድ-ሜሞሬ” አስቸኳይ ማስታወሻ፣ በሀገሪቱ ስለተካሄደው ምርጫ፣ ስለ ፌዴራል መንግስቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና በትግራይ የውስጥ ፖለቲካ ላይ ስለተወሰኑ ወሳኝ ውሳኔዎች ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።
“የፕሪቶሪያው ስምምነት ሞቷል” ማን ገደለው?
የህወሃት ከፍተኛ አመራር ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አልነበረውም ሲል ይከሳል።
“የሰላም ስምምነቱን ድንጋጌዎች መሬት ላይ ለማውረድ የተቋቋሙት ተቋማት ስራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው፣ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት መሰረታዊ የሰላም ስምምነቱ ድንጋጌዎች በተግባር አልተተገበሩም፤ ይህም ስምምነቱን ህይወት የሌለው አድርጎታል” ይላል የሰነዱ መግለጫ።
በዚህ የሰላም ሂደት መገታት ምክንያት በትግራይ ክልል ከፍተኛ የአስተዳደር እና የሉዓላዊነት ክፍተት መፈጠሩን ህወሃት አስታውቆ ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት የቀድመውን ምክር ቤት ለመመለስ መገደዱን ወደሚያብራራበት የመግለጫው ክፍል ይንደረደራል። በዚህ ክፍሉ በፕሪቶሪያው ውል መሰረት የተቋቋመውን የአቶ ጌታቸውን ካቢኔ ከህግ ውጭ በጠበምንጃ ኃይል እንዴት እንዳፈረሰ አላብራራም።
የትግራይ የውስጥ ፖለቲካ ውሳኔ፦ የ2012ቱ ምክር ቤት መመለስ እና የተቃዋሚዎች እጣ ፈንታ
በክልሉ የተፈጠረውን የአስተዳደር ክፍተት ለመሙላት እና ተቋማዊ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ህወሃት ሰፊ የውስጥ ምክክር ማድረጉን ገልጿል። በመግለጫው መሰረት፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ ከተሞች፣ ወረዳዎች እና የገጠር ጣቢያዎች ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያሳተፈ የህዝብ ምክክር ተካሂዷል። በዚህም መሰረት የተወሰኑት ዋና ዋና የፖለቲካ ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- የምክር ቤቱ መመለስ፦ በ2012 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2020) የተካሄደውን የትግራይ ክልላዊ ምርጫ ተከትሎ ተመስርቶ የነበረው የትግራይ ተወካዮች ምክር ቤት በድጋሚ ወደ ስራው እንዲመለስ እና ህጋዊ የሉዓላዊነት ስልጣኑን እንዲረከብ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል።
- የ1/3ኛ ስልጣን ክፍፍል ኮታ፦ ህወሃት ምንም እንኳን በ2012ቱ ምርጫ ሰፊ ድል የተቀናጀ ቢሆንም፣ አዲሱ የአስፈጻሚ አካል (ካቢኔ) ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን የካቢኔ ወንበሮች አንድ ሶስተኛው (1/3) ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሰጥ ለምክር ቤቱ ሃሳብ ማቅረቡን እና ምክር ቤቱም ይህንን ማጽደቁን ገልጿል። ይህ ውሳኔ በትግራይ የውስጥ የፖለቲካ አንድነትን እና ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ህወሃት ምርጫው ትክክል እንኳን ቢሆን የጊዜ ገደቡ ያከተመ መሆኑን በመጠቀስ፣ በወቅቅት የተመረጡት አብዛኞቹ የሌሉና ስራ ይጀመር እንኳን ቢባል ኮረም የማይሞላ መሆኑን በማንሳት ድርጅቱን ከስህተቱ የማይማር፣ ለህግ የማይገዛ፣ የትግራይን ሕዝብ ስቃይ የሚያበረታ፣ ከስልታን ውጪ ምንም የማይታየው፣ ስልታንን ለሰራቸው ወንጀሎች መደበቂያና ዋስትና አድርጎ የሚጠቀም መሆኑን በመጠቀስ ተቃዋሚዎች አካሄዱን ማጣታላቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
የኢኮኖሚ ከበባ እና የሰብአዊ መብት ቀውስ
ሪፖርታዡ እንደሚያሳየው በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ህወሃት የፌዴራል መንግስቱን ክልሉን የማዛል ከበባ ጥሎብናል ሲል ይከሳል። በተለይም በነዳጅ እና በንግድ ፍሰት ላይ የተጣለው ገደብ የክልሉን የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የንግድ እንቅስቃሴ እና የግብርና ምርትን ሙሉ በሙሉ ወደ መቆም አድርሶታል። ይህም በከተሞች ውስጥ ሊቋቋሙት የማይችሉት ከፍተኛ የዋጋ ንረትን አስከትሏል።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች (IDPs) በተለይም በምዕራብ ትግራይ ያሉ ወገኖች ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዳይመለሱ በፌዴራል መንግስቱ እና “ህገ-ወጥ” ባላቸው የአካባቢው አስተዳደሮች እና ታጣቂዎች እንቅፋት እየተፈጠረባቸው መሆኑን፣ አዲስ የክረምት ዝናብ ወቅት ከመግባቱ ጋር ተያይዞም የተፈናቃዮች ህይወት ይበልጥ አደጋ ላይ መውደቁንና አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም ድጋፋቸውን እያቋረጡ መሆኑን ገልጿል።
በጠመንጃ ኃይል የተባረረው የአቶ ጌታቸው ካቢኔና አመራር ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ ስልታን በኃይል የያዘው የህወሃት ስንጣቂ ወታደራዊ አቅሙን በመጠቀም እንቅፋት መሆኑን በመአስረጃና መረጃ በማቅረብ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ማስታወቁ አይዘነጋም። ይህንኑ አስመልክቶ በጽሁፍና በተለያዩ መግለቻዎች ላገርና ለውጭ መገናኛዎች የተባረረው ካቢኔ ሲያስታውቅ አዲስ ሪፖርተርም መዘገቧ የሚታወስ ነው።
ወታደራዊ ንቅናቄ እና የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅቡልነት ጥያቄ
የህወሃት መግለጫ በትግራይ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ትችቶችን ሰንዝሯል። በተለያዩ አውዶች ትግራይን እንደ አገር እየቆተረ፣ በኤርትራ ናቅፋ ለመጠቀምና ምጽዋና አሰብን በመጠቀም አስፈላጊ ሸቀጦችን ለማስገባት ከስምምነት መደረሱን፣ ከሱዳን ጋር ወታደራዊ ህብረት መፈጠሩንና ከኤርትራ ሰራዊት ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች እያስታወቀ የአገር መከላከያ ወደ ትግራይ እየተጠጋ ነው በሚል መግለጫው ይከሳል።
መግለጫው የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት (ENDF) በትግራይ ድንበሮች ዙሪያ መጠነ-ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት እና ክበባ እያደረገ መሆኑን፣ ይህም በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ጫና መፍጠሩን ያነሳል። አክሎም የፌዴራል መንግስቱ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እያካሄደ ያለው የምድር፣ የመድፍ እና የድሮን ጥቃቶች የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን በመጥቀስ ተቆርቋሪነቱን ያሳያል። ህወሃት ሶስት ጊዜ አማራና አፋር ክልልን ወሮ ማውደሙን፣ ግፍ፣ ግድያ፣ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር ወዘተ በመግለቻው ጠቁሞ ይቅርታም ሆነ ማስተባበያ አሳብ አላነሳም። በዚሁ ሳቢያ በውጭ አገር እንኳን ያሉት የአማራና የትግራይ ተወላጆች አንድ ላይ ማምለክ እንደማይችሉ በአመጽ አመቻች ግብረኃይል ስብሰባ ላይ በግምገማ ሰሞኑን መገለጹ ይታወሳል። እዚህ ላይ ያንብቡ።
የብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግስት ሰላምን ከመፈለግ ይልቅ ህዝባዊ ቅቡልነትን ለማግኘት በሚል ኝቦት 24 ቀን 2018 ያካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታት ህወሃት አመልክቷል። ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ያካሄደውንና በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ህገወጥ እንደሆነ አምኖ ያፈረሰውን ምክር ቤት ወደ ስልታን የመለሰው ህወሃት “የለሁበትም” ያለውን ምርጫ ተችቷል። በመላው አገሪትይ ከ97 በመቶ በላይ መካሄዱ ይፋ የተደረገበትንና ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጭ የተመዘገብበትን ምርጫ ያጣጣለው ህወሃት ይህን ሁሉ ካለ በኋል የጠየቀው ወይይት እንዲደረግ ነው።
መግለጫው ሙሉ የትግራይ ክልልን ጨምሮ፣ ሰፊ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ አካባቢዎች ከምርጫው ውጪ መሆናቸውን እና ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግስት ማዕቀብ እና እስራት ምክንያት ሳይሳተፉ የቀሩበት “የይስሙላ ምርጫ” ነው ሲል ነቅፎታል። በ1997 ምርጫ በአደባባይ ግድያ የሕዝብ ድምጽ የዘረፈና በምርጫ ያሸነፉ ተወዳዳሪዎችን ሰብስቦ ያሰረው፣ ከዛም በቀታዮቹ ምርጫዎች መቶ በመቶ እንዳሸነፈ እያወጀ ቆይቶ በሕዝባዊ አመጽ የተባረረው ህወሃት ሲያሻው የመገንጠል። ሲያሻው የኢትዮጵያዊነት ካርድ በመምዘዝ የዴሞክራሲ ተቆርቋሪ መሆኑ በርካቶችን አነጋግሯል።
አቶ ኦባንግ ሜቴ በአንድ ወቅት ከአራት መቶ በላይ የአኝዋክ ንጹሃንን የጨፈጨፈው ህወሃት ስለ ጋምቤላ ሊያወራ ሞራል የለውም ብለው ነበር። የጋምቤላን ምስኪኖች መሬታቸውን በአንድ ፓኬት ሲጋራ ሁሳብ የቸበቸበ ድርጅት ስለ ጋምቤላ ምንም ማለት እንደማይችል የኦክላንድ ኢንሲቲቱትን ሪፖርት በማስደገፍ ተናግረው ነበር።
የቀጣናዊ ጦርነት ስጋት እና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ፈተና
ይኸው ለዲፕሎማቶች የተበተነው ደብዳቤ እጅግ አደገኛ ነው ሲል ያስጠነቀቀው ነጥብ፣ አዲስ የሚቀሰቀሰው የጦርነት እሳት በኢትዮጵያ ድንበር ብቻ ተወስኖ የማይቀር መሆኑን ነው።
“አሁን ካለው የቀጣናው ውጥረት እና የፌዴራል መንግስቱ ለጎረቤት ሀገራት ከሚያሳየው የጠብ አጫሪነት አኳኋን አንጻር፣ አዲስ የሚቀሰቀስ ጦርነት መላውን የአፍሪካ ቀንድ የሚያናጋ እና ቀውሱን ይበልጥ የሚያሰፋው ይሆናል” ሲል ህወሃት ያስጠነቅቃል። ህወሃት የኢትዮጵያ መንግስት ከየትኞቹ የጎረቤት አገራት ጋር በጸባጫሪነት እንደሚመደብ አላብራራም።
ጄኔራል አልቡራን ከሚመሩት የሽብርተኛ መንግስት ጋር የሚሰራው ህወሃት፣ ሰራዊት ልኮ በቅጥረኛነት ለሱዳን የሚዋጋው ህወሃት፣ የሻዕቢያን ሰራዊት ትግራይ አስገብቶ ሲያበቃ ከነዚህ አገራት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም እንደሌለው አድርጎ መክሰስ ለሪፖርት ማዳመቂያ የሚውል መሆኑን ዲፕሎማቶች እንደሚረዱት አስተያየት እየተሰጠ ነው።
አሜሪካ በሽብር ከፍረጀው የአልቡራን መንግስት ጋር የሚሰራው ህወሃት፣ ከተለያዩ የአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዳለው አባላቱ በይፋ ሲያስታውቁለት የነበረው ህወሃት መግለጫውን ሲቋጭ፣ “ህወሃት አሁንም ቢሆን ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ለሚደረግለት የፖለቲካ ውይይት ዝግጁ ነው” ብሏል። አያይዞም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን ካለው የዝምታ አቋም ወጥቶ በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ጠይቋል።
“ጦርነት አሁንም ሊቀለበስ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ፣ መርህን መሰረት ያደረገ እና ቀጣይነት ያለው ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው” ሲል የህወሃት የዲፕሎማሲ ማስታወሻ ይደመድማል።
ይህ ልዩ ሪፖርታዥ የተጠናቀረው ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ከህወሃት አመራር የወጣውን ይፋዊ የዲፕሎማሲ ሰነድ መነሻ በማድረግ ለአዲስ ሪፖተር አንባቢዎች እንዲመጥን ተደርጎ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






