አዲስ ሪፖርተር – እስካሁን በመላው ኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች፣ በትግራይ ለደረሰው አጠቃላይ ቀውስና ችግር ወደፊትም ለሚፈጠሩ አደጋዎች ብቸኛው ተጠያቂ የከሸፈው ትህነግ ነው” ሲሉ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አሉላ ኃይሉ አስታወቁ። “ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ መከራ የሆነውን ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያና ትግራይ ምድር መንቀል ዋና ዓላማችን ነው” አሉ።
አቶ ኃይሉ ይህን ያስታወቁት ትህነግ ለጦርነት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስመልክቶ ስላላቸው መረጃ እንዲያስረዱ ከአዲስ ሪፖርተር ተጠይቀው ነው። ትህነግ ለዳግም ጦርነት በማሰፍሰፍ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አሉላ፣ በትህነግ አማካኝነት የትግራይ ክልል በአሁን ወቅት ፣ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ፣ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ እየሆነ ስላለው ችግር እንዲሁም ወደፊት ስለሚመጣው የትውልድ ጣጣ ተጠያቂው ትህነግ መሆኑን ትውልድ ሊረዳው እንደሚገባ ለአዲስ ሪፖርተር የተናገሩት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አሉላ ሐይሉ፣ የፓርቲያቸው ዋና ዓላማ ትህነኝ መንቀል እንደሆነ አመልክተዋል።

ለበርካታ ዓመታት በመልካም አስተዳደር ዕጦት ነዋሪው ሲሰቃይ መቆየቱንና ይህንኑ በደሉን በተደጋጋሚም ከትህነግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበረ ውይይት በግንባር መናገሩን ያወሱት የሳልሳይ ወያኔ ሊቀመንበር፣ ህዝቡ በምላሽ ያገኘው ከጠየቀው በተቃራኒ እንደሆነ አመልክተዋል። ምላሹም ጠብመንጃ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በፌዴራል መንግስትና በሕወሓት መካከል ከተደረገው ጦርነት ወዲህ በትግራይ ባለፉት ዓመታት ምንም አይነት መረጋጋት እንደሌለ የሚያነሱት አቶ አሉላ፣ የክልሉ ነዋሪው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የገባው “ቆሞ ቀር” በሚባሉትና ባረጁ ፖለቲከኞች አማካኝነት መሆኑንን አመልክተዋል። ይህ ቀውስ አሁን ላይ ትህነግ እየደገሰው ያለው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሕዝቡ ሊቆም ወደማይችል የችግር አዘቅት ውስጥ እንደሚገባ አስጠንቀቀዋል።
“ለዳግም ጦርነት እየተንደረደረ የሚገኘው ትህነግ እንደ ከዚህን ቀደሙ የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ በማጣቱ ምክንያት ፣ መልሶ የክላሹን ቃታ ወደ ሕዝቡ አዙሯል” ያሉት አቶ አሉላ፣ አስተያየታቸው በትግራይ ሕዝብና ሰራዊቱ በጭራሽ ጦርነት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ የሚመለከታቸውን አነጋገረን ካተምናቸው ዘገባዎች ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።
“ለዳግም እልቂት አንተባበርም” የሚሉ የትግራይ ወጣቶችን በእስርና ፣በሞት እየቀጣ እንደሚገኝ አቶ አሉላ ተናግረዋል።ይሕም እየሆነ ያለው በትህነግ አንድ ክፋይ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ፊት አውራሪነት፣ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስፈጻሚነት እንደሆነ አመልክተዋል።አክለውም በባሕላዊ ጀኔራልና ፖለቲከኞች አማካኝነት ክልሉ ዳግም ማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ የቁልቁለት ጉዞው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ ፣በትህነግ ላይ ያለው እምነት መመናመኑና የድርጅቱ ግብአት መሬት እንደተፈጸመ የሚያስረዱት ሊቀመንበሩ፣ አሁን ላይ ሕዝቡ ከትህነግ ይልቅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚመርጡ ተንማግረዋል።
በክልሉ ስለተፈጠረውም ሆነ ስለ ሚፈጠረው ችግር በጠቅላላ መፍትሔው የፌድራል መንግስት እጅ ላይ እንደሚገኝ የሳልሳዊ ወያኔ ሊቀመነበር ገልጸዋል። የፌዴራሉ መንግስት በትግራይ ክልል ስላለው ችግር ምላሽ ለመስጠት ማመንታቱ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
“ትህነግ የሚባል ድርጅትን ከትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ምድር እስከወዲያኛው መንቀል የፓርቲያችን ዋንኛ ዓላማ ነው” ያሉት አቶ አሉላ፣ ይሕንኑ ቀዳሚ የፓርቲያቸው ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተባበራቸው ከሆነ የታቀደውን ዕቅድ እውን ለማድረግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል። የዝግጅቱን ዝርዝር ጉዳይ ግን አላብራሩም።
ትህነግን መንቀል የድርጅታቸው ዋና አለማ መሆኑን ያስታወቁት አቶ አሉላ ፓርቲያቸው ሳልሳይ ወያኔን ጭምሮ በረካቶች የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ስሞች ከነጻ አውጪነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በርካቶች ” የስም እንጂ የዓላማ ልዩነት የላቸውም” ሲሉ ይከሷቸዋል። በቅርቡ ውድብ እና ስምረት የተሰኙ ፓርቲዎች እስኪቋቋሙ ድረስ የነበሩት ፓርቲዎች ልዩነት ስለሌላቸው አንድ ቢሆኑ እንደሚሻል ተቺዎች ይናገራሉ። በትግራይ ድርጅቶች በሙሉ ለምን ከነጻነትና ከመገንጠል ጋር የተያያዘ ስም ላይ እንደሚቸከሉ ለበርካቶች እንግዳ ጉዳይ ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






