ኬዝ ኪለርስ [Case Killer] – የጉዳይ ገዳይ ወይም የጉዳይ አምካኝ ያልተበጠሰው ሥውር መረብ ክፍል አንድ

Date:

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባና ሰፋ ሰፋ ባሉ ከተሞች ልክ እንደ ልማት ስራው ሁሉ ክብረ ነክ ጉዳዮች ይስተዋላሉ። በስጋ ንግድ ሽፋን ጀምሮ በየህንጻው የሚታዩ መደብሮችና በ”አቅራቢዎች” አማካይነት እየተከናወኑ ያሉ ጉዳዮች አያስደስቱም። ደፍሮ የሚገልጣቸው ቢገኝ አሳፋሪም፣ አሸማቃቂም፣ አስደንጋጭም ነው። ስፍራ፣ ጾታ፣ ስልጣንና ደረጃ ሳይለይ የሚያተው የከተማ ትዕይንት እልፍ ነው። አዲስ ሪፖርተር “ኬዝ ኪለርስ” ስለሚባለው የፍትህና ጉዳይ ገዳይ መረብ ቅድሚያ በመስጠት ክፍል አንድ ጀምራለች። ኬዝ ኪለርስ ገና ወጠጤና በሰዓታት ኦፕሬሽን ቋንጃውን ሊቆረጥ የሚችል የስግብግቦች ስብስብ ሲሆን፣ ገንዘብ ተናጋሪ ሆኖ ፍትህ እንዲሰቀል ድራቸውን የሚያደሩ ሞራላቸው የተሰበረ፣ ከንዋይ ውጭ ምንም ዓይነት የማሰቢያ ውቅር የሌላቸው “ሰዎች” ናቸው።

አዲስ ሪፖርተር – በሌብነት ሲርመጠመጡ የተገኙት ሚኒስትር የፈጸሙት ወንጀል፣ የፍርድ ሂደቱን ለመጠበቅ እንኳን ጊዜ አልሰጣቸውም። የፍርድ ሂደቱን ማንም ጣልቃ ገብቶ እንደማያቆመው ሲረዱ የሚጎነጩትን መርዝ አዘጋጅተው ብዕራቸውን አነሱ። ይህንን ጻፉና መርዝ ተግተው ተሰናበቱ። ዛሬ የቆራጥ መሪዎች አቋም ማሳያ ሆነው እየተጠቀሱ ነው።

ለጠቅላይ ሚኒስትር፣ “ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጣም አዝኛለሁ፣ እጅግም ተጨንቄያለሁ። ይህ አሳዛኝ ክስተት በመፈጠሩ እኔው ራሴን ተጠያቂ አደርጋለሁ። ሙሉ ኃላፊነቱንም መውሰድ እንዳለብኝ አምናለሁ። ክብሩን እንደሚጠብቅ የምሥራቅ ባህል ያለው ሰው እንደመሆኔ፣ ለሠራሁት ስህተት ከፍተኛውን ቅጣት መክፈል ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ።” ከአክብሮት ጋር፣ (ፊርማ) ቴህ ቼንግ ዋን

ቴህ ቼንግ ዋን የሲንጋፖር ብሔራዊ ልማት ሚኒስትር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት አጭር መልዕክት ነው።

Prime Minister, “I have been feeling very sad and depressed for the last two weeks. I feel responsible for the occurrence of this unfortunate incident and I feel I should accept full responsibility. As an honourable oriental gentleman, I feel it is only right that I should pay the highest penalty for my mistake.” Yours faithfully, (Signed) Teh Cheang Wan

ሟቹ ሚኒስትር ይህን የጻፉት በጉቦ ወይም በሌብነት ክስ ተመስርቶባቸው ሂደቱ ላይ እያለ፣ ክሱ እንዲነሳላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ከተደረገባቸው በኋላ ነው። በሲንጋፖር የኬዝ ኪለር መዋቅርንና ሙስናን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በተደረገው ዘመቻ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኳን ዩ “ለማንም አለማደላትን” በተግባር ያሳዩባቸውና በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የተወሰዱ ዋና ዋና አስተማሪ እርምጃዎች መካከል አንዱ ቴህ ቼንግ ራሳቸውን ያጠፉበት ታሪክ ነው።

ይህ ክስተት በሲንጋፖር ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደንጋጭና በሁሉም ባለስልጣናትና የሌብነት መረብ ተሳታፊዎች ዘንድ ፍርሃትን የለቀቀ ትልቁ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል። ቴህ ቼንግ ዋን የጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኳን ዩ የቅርብ ሰውና አገሪቱን በቤት ልማት ረገድ የለወጡ እጅግ ስኬታማ ሚኒስትር ነበሩ።

እ.ኤ.አ. በ1986 የግል የቤት አልሚዎች (Developers) ከሕግ አግባብ ውጪ መሬት እንዲያገኙ በማድረጋቸው፣ በሁለት ዙር አንድ ሚሊዮን የሲንጋፖር ዶላር (በወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ) ጉቦ መቀበላቸው በስውር ክትትል ተደረሰበት። የሙስና ምርመራ ቢሮ (CPIB) ጉዳዩን መመርመር ሲጀምር፣ ሚኒስትሩ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሄድ “ምርመራው እንዲቆምልኝ” ሲሉ ተማጸኑ። ሊ ኳን ዩ ግን “ሕግ ፊት ማንም ልዩ አይደለም” በማለት ጥያቄውን ውድቅ አደረጉባቸው።

ሚኒስትሩ ፍርድ ቤት ቀርበው ከመዋረድና የዕድሜ ልክ እስራት ከመቀበል ይልቅ፣ ክሱ በይፋ ሊመሰረት ጥቂት ቀናት ሲቀሩት መርዝ ጠጥተው ራሳቸውን አጠፉ። ከመሞታቸው በፊት ለሊ ኳን ዩ ከላይ የተጠቀሰውን ደብዳቤ ጻፉ። መንግሥት ራሳቸውን ስላጠፉ ሳይራራ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውን ያለምንም የመንግሥት ክብር ቤተሰቦቻቸው እንዲፈጽሙት አደረገ። ይህ ሲንጋፖር “መሪ” አግኝታ ከኬዝ ኪለርስ የሌብነትና የቅሌት ብስባሽ ውስጥ ወጥታ ወደ አዲስ ጎዳና ማምራት ስትጀምር የሆነ ታሪክ ነው።

እንደ መነሻ

ዛሬ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን በመታከክ፣ ስማቸውን በየሥራቻውና ባንኮኒው በማንሳት፣ የመንግሥትና የፓርቲ ቀኝ እጅ እንደሆኑ በማስመሰል የሚሰብኩ “አሸማቃቂ” ባለሀብቶችና “ጉዳይ እንገድላለን” የሚሉ ጡንቸኞች ብቅ እንዳሉ እዚህም እዚያም ተበዳዮች ሲናገሩ ይሰማል። መረጃ ይዘው “የፍትሕ ያለህ” የሚሉ ዜጎችም አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንኑ የሕዝብ ሮሮ በቅርቡ ግብሩን ጠቅሰው “እናጠፋዋለን” ብለዋል። ምክትላቸው አቶ ተመስገንም በተመሳሳይ እሳቸው የሚመሩት ግብረኃይል በርካታ ጥቆማ እንደደረሰው አመልክተው “መንግሥት ለሌቦች ምህረት የለውም” ብለው መናገራቸው ይታወሳል። ሁሉንም በልባችን ይዘን ለዛሬ ወደ መረጥነው ጉዳይ እናመራለን።

ኬዝ ኪለር (Case Killer) ጉዳይ ገዳይ ወይም ጉዳይ አምካኝ

ኬዝ ኪለር (Case Killer) ማለት በሕግና በጥብቅናው ዓለም ውስጥ “የቀረበን ክስ ወይም የክስ መዝገብ ከተገቢው፣ ከሚታወቀውና ሕዝብ ከሚተማመንበት የሕግ አሠራር ውጪ በሴራ፣ በጉቦ፣ በደላላ ወይም ሥልጣንና ባለሥልጣንን በመጠቀም በተፅዕኖ ማምከን፣ ማድበስበስ፣ ማጓተት ወይም ሙሉ በሙሉ መግደል” ማለት ነው።

በአማርኛ “ጉዳይ ገዳይ ወይም ጉዳይ አምካኝ” የሚባሉት እነዚህ አካላት፣ በፍርድ ቤት መዋቅር ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ከዳኞች፣ ከአቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስ እና ከፍርድ ቤት ጸሐፊዎች ጋር የስውር ጥቅምና የጥቁር ገበያ መረብ የዘረጉ አደገኛ መዋቅር ያላቸው ደላሎች፣ ጠበቆችና ባለሥልጣናት የተካተቱበት፣ በከፍተኛ ብር የሚንቀሳቀስ የወንጀል ትብትብ ነው።

የዚህ ቡድን ወይም ድር ዋና ተግባር ባለጉዳዩን ፍርድ ቤት አቅርቦ በሕግና በማስረጃ መሟገት ሳይሆን፣ ከጀርባ በሚደረግ ግንኙነት በገንዘብና በዓይነት በሚፈጸም ሥውር ክፍያ ውሳኔው እንዲቀለበስ ማድረግ ነው። አንዳንዴም ይህ ትስስር የማፊያ መልክ የተላበሰ እንደሆነ በምርመራ ያረጋገጡ አገራት አሉ። ወደ ማፊያነት አድገው አገር እስከማፍረስ የደረሱበት አግባብም አለ።

ይህ ቡድንና አደረጃጀት ምስክር በማስፈራራት ወይም በመግዛት፣ ዋና የሰነድ ማስረጃዎችን ከማህደሩ ውስጥ በማሰረቅ ወይም በማጥፋት፣ የክስ መዝገቡ እንዲዘገይና በጊዜ ገደብ (Limitation) እንዲታገድ በማድረግ፣ ወይም በቀጥታ ለዳኛው ጉቦ በመስጠት ክሱ ሳይታይ “እንዲሞት” (Dismiss እንዲሆን) የማድረግ ሥውር የወንጀል ተግባር ይፈጽማል። ባጭሩ፦ “ኬዝ ኪለር” ማለት ፍትሕን በገንዘብና በኔትወርክ በመግደል፣ የወንጀለኞችን መዝገብ የሚያክሽፍና የሕግ የበላይነትን የሚያሽመደምድ የፍትሕ ሥርዓቱ ጥገኛ ተውሳክ ማለት ነው። ለዚህ ነው እንዲህ ያለ አደረጃጀትና መረብ ሳይፈረጥም በወጠጤነቱ መቆራረጥ እንደሚገባው አዋቂዎች ምሳሌ እያጣቀሱ ምክር የሚለግሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን ባቀረቡት የፓርላማ መዝጊያ ንግግራቸው ላይ በቀጥታ “ኬዝ ኪለር” የሚለውን ቃል ባይጠቀሙም፣ በፍትሕ ሥርዓቱ እና በዳኝነት መዋቅሩ ውስጥ ስላለው የአሠራር ብልሹነትና ሌብነት ጠንከር ያሉ ትችቶችንና ማስጠንቀቂያዎችን ሰንዝረዋል።

ስማቸውን “ኬዝ ኪለሮች” በማለት ባይጠቅሱም፣ “ገንዘብ ያለው ሰው ወንጀል ሠርቶም ቢሆን ፍትሕን መግዛት የሚችልበት፣ ደሃው ግን እውነቱ ሳይታይለት የሚበደልበት አሠራር ሰፍኗል” በማለት በዳኞችና በባለጉዳዮች መካከል የሚደረገውን የገንዘብ ልውውጥ ኮንነዋል። አክለውም ውሳኔዎች በፍርድ ቤት አዳራሽ ሳይሆን፣ አስቀድሞ በካፌዎች፣ በሆቴሎችና በስልክ ጥሪዎች በደላሎች (በዚህ ጽሑፍ አገላለጽ ኬዝ ኪለሮች) አማካኝነት እንደሚወሰኑ ጠቁመዋል። ይህ የስልክና የደላላ መረብ ካልተበጠሰ በስተቀር የፍትሕ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል አመልክተዋል። ይህ ገለጻቸው በሌሎች አገራት የታዩ የኬዝ ኪለር መረብ ተዋናዮች ባሕርያት ናቸው፤ ትንታኔውም መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው አመልካች ነው። ጥያቄው ይህ ክፉ ልማድና አደገኛ መረብ መቼ ይበጣጠሳል፣ “ሳንጃውስ መቼ ከአፎቱ ይወጣል” የሚለው ነው።

ሙስናው በዳኞች ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከመጀመሪያው የምርመራ ጣቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ድረስ የተዘረጋ ሰንሰለት እንዳለው ሲያስረዱ፦ የተወሰኑ የፖሊስ መርማሪዎች፣ ዓቃብያነ ሕግ፣ ጠበቆችና ዳኞች በጋራ በመናበብ መዝገብ የሚያጠፉበት ወይም ጥፋተኛውን ንጹሕ፣ ንጹሑን ደግሞ ጥፋተኛ የሚያደርጉበት የተደራጀ መዋቅር (Cartel) መኖሩን ጠቁመዋል።

በርካታ ዳኞች፣ ዓቃብያነ ሕግና የፖሊስ አባላት በሙስና ምክንያት ከሥራ እንዲሰናበቱና በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን አመልክተዋል። ወደፊትም ቢሆን ይህንን “የፍትሕ ሌብነት” ለማስቆም ጠንካራና ተከታታይነት ያለው የማጽዳት እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስጠንቅቀዋል።

አዲስ ሪፖርተር እንደመነሻ ከተለያዩ አካላት የተገኙ ጥቆማዎችን በመንተራስ፣ በራሱ በተደረገ ምርመራ ቅድሚያ በግርድፉ ከላይ የተገለጸውን የሌብነት ድር መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው፣ አለያ አያያዙ ሕዝብ በፍትሕ ተቋም ላይ እምነት እንዲያጣና “ምን አመጣለሁ” ወደሚል ተስፋ መቁረጥ ከማምራቱ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ መዋቅሩን እንዲመረምርና እንዲያጸዳ አጋዥ ማሳሰቢያና ጥቆማ ለመስጠት ይህ ሪፖርት ቀርቧል።

አገር በፍትሕ ካልተዳደረች፣ አገር በሕግ ካልተመራች አደጋው የከፋ በመሆኑ፣ ይህ በአገራችን “ክራባት ለብሶ” ፍትሕን በአፍጢሙ ለመትከል እየተውተረተረ ያለ ኃይል “መንግሥት ከፈለገ” በአንድ ጀንበር ሊያጠፋው እንደሚችል በማመን የቀረበው ሪፖርት፣ ለጊዜው የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማንሳት አደጋውን ማሳየት ይወዳል። “መንግሥት ከፈለገ” በሚል የተቀመጠው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ የዚህን ቡድንና ትብትብ መገለጫዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ እየሰማ በአደባባይ በመናገራቸው የሚጠበቀው እርምጃ እንደሆነ ለማስመር ነው።

የሲንጋፖር የፍትሕ እና የሕግ አስከባሪ መዋቅር በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ፣ በተለይ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከመውጣቷ እና ከማሌዢያ ከመገንጠሏ በፊት ባለው ጊዜ የደረሰበት የውድቀት ደረጃ እጅግ አስከፊ እና ሥር የሰደደ ነበር። በወቅቱ የነበረውን አጠቃላይ መበስበስ ለሚያውቁ ዛሬ ሲንጋፖር እዚህ ደረጃ ትደርሳለች ብሎ ማሰብ አይቻላቸውም። ድንቅ መሪዎችና ቁርጠኛ ዜጎች አገራቸውን ከበሰበሰችበት አዘቅት አወጡና የዛሬውን ጸዳል አላበሷት።

በሲንጋፖር በወቅቱ የፍርድ ሂደቶች በኬዝ ኪለሮች ተጠልፈው ስለነበር ፍርድ ቤቶች “የጨረታ ፍርድ ቤት” መሆን (Justice for Sale) እስከ መባል ደርሰው ነበር። በወቅቱ ፍርድ ቤቶች ሕግና ማስረጃ የሚመዘንባቸው ሳይሆኑ፣ በኬዝ ኪለሮች እና በደላሎች አማካኝነት ከፍተኛ ገንዘብ ላቀረበ አካል ውሳኔ የሚሸጥባቸው “ጉሊቶች” ሆነው ነበር። ፍርድ ቤትን የሚያክል ታላቅ ተቋም በሌቦች ተጠልፎ፣ ዳኛውም፣ ፖሊሱም፣ አቃቤ ሕጉም፣ ሁሉም በገሃድ የሚዘርፉበት መሻቀጫ ሆኖ ነበር።

ወንጀለኞች፣ ቁማርተኞች እና የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፣ በደላሎች በኩል ለዳኞች የሚደርሰው ሥውር የገንዘብ ክፍያ መዝገቡ እንዲዘጋ፣ ማስረጃው እንዲጠፋ ወይም ተከሳሹ በነፃ እንዲሰናበት ያደርግ ነበር። ፍልሚያው በሕግ ዕውቀት ሳይሆን በገንዘብ አቅም ብቻ ሆኖ “ፍትሕ አደባባይ ተሰቅላ” ነበር። በአገራችን በአንድ ወቅት ገንዘብ በፌስታል አጭቀው “ገንዘብ ሲናገር ፍትሕ ጭጭ ትላለች” ያሰኙ በስም የሚታወቁ ማፊያዎች አቆጥቁጠው እንደነበር ለሚያውቁ፣ ያ ድር ዛሬ ስለመቆራረጡ ማረጋገጫ የላቸውም።

የሲንጋፖር ጎዳናዎች “ትሪያድስ” (Triads) በሚባሉ የተደራጁ የቻይና ወንጀለኞች እና ምስጢራዊ ማኅበራት ቁጥጥር ሥር ነበሩ። እነዚህ የወንጀል ቡድኖች የራሳቸውን ጠበቆች እና የኬዝ ኪለር መረቦችን አዋቅረው ነበር። አንድ የቡድናቸው አባል ሲታሰር የትኛውን ዳኛ መቅረብ እንዳለበት፣ የትኛውን ፖሊስ መደለል ወይም ማስፈራራት እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር፣ የፍትሕ መዋቅሩን የወንጀለኞች መከላከያ ጋሻ አድርገውት ነበር።

የኬዝ ኪለሮች መረብ የሚጀምረው ከፍርድ ቤት ሳይሆን ከመጀመሪያው የምርመራ ጣቢያ ነበር። የሲንጋፖር ፖሊስ በወቅቱ ሕዝብ ጨርሶ የማይተማመንበት ተቋም የሆነው፣ በዚሁ ተግባሩ ከማጅራት መቺ ቡድኖች ጋር በመመሳጠሩ የተነሳ መሆኑን በወቅቱ የተሰራጩ መረጃዎች ያስተምራሉ።

ፖሊሶች ከትናንሽ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ጀምሮ እስከ ትላልቅ የፖፒየም (የዕፅ) አዘዋዋሪዎች ድረስ ወርሃዊ “የመከላከያ ክፍያ” (Protection Fee) ይፈጸምላቸው ነበር። ገንዘብ የከፈለ ወንጀለኛ መዝገቡ ላይ ያለው ፎቶ እና የጣት አሻራ ሳይቀር “በድንገት” ይፋቅለት ነበር።

ለሲንጋፖር የፍትሕ ውድቀት ትልቁ ማሳያ በ1951 ዓ.ም የተከሰተው ታዋቂው የኦፒየም መርከብ ዘረፋ ነው። በወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሕገ-ወጥ ዕፅ (ኦፒየም) የያዘች መርከብ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ፣ በቁጥጥር ሥር ያዋሉት የጉምሩክ እና የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ራሳቸው ዕጹን ሰርቀው ለሌሎች ወንጀለኞች መልሰው ሸጡት። ይህ ጉዳይ እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደረሰ ሲሆን፣ በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉት ከፍተኛ መኮንኖች በኬዝ ኪለሮች አማካኝነት ከፍርድ እንዲያመልጡ ተደረገ። ይህ ክስተት ሥርዓቱ ምን ያህል እንደበሰበሰ ለዓለም ያሳየ፣ የሲንጋፖር የሌብነት ግልሙትና የሚገለጥበትና ዛሬ ድረስ የአደባባይ ውንብድና ማስተማሪያ ሆኗል።

ከላይ በተጠቆሙትና በተለያዩ አግባቦች የሲንጋፖር ሕዝብ የፍትሕና ርትዕ ማስፈጸሚያ የሆኑትን ፍርድ ቤቶችን ፍትሕ ማግኛ ሳይሆን “የሙሰኞች መጫወቻ፣ የኬዝ ኪለሮች መጋለቢያ” አድርጎ አያቸው። ዜጎች ወንጀል ሲፈጸምባቸው ለፖሊስ ማመልከት ወይም ወደ ፍርድ ቤት መሄድ አቆሙ። ምክንያቱም ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ተጨማሪ የደላላ እና የጉቦ ወጪ እንደሚያስከትል፣ በመጨረሻም ወንጀለኛው በገንዘቡ ነፃ እንደሚወጣ ያውቁ ነበር። በውጤቱም ሕዝቡ ችግሮቹን በመደበኛ የሕግ አግባብ ከመከታተል ይልቅ፣ በወንጀለኞች ቡድን አማካኝነት መፍታትን መረጠ፤ ይህም የሕግ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ አጠፋው። በሲንጋፖር ሕግ በአፍጢሟ ተተከለች።

በወቅቱ ያጤኑና የመረመሩ ሲንጋፖርን “የወንጀለኞች ገነት፣ የሙሰኞች መፈንጫ” አሏት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኳን ዩ ሥልጣን ሲይዙ አገሪቱ የወደቀችበትን ይህንን አዘቅት አይተው “ይህንን ካላጠፋን አገር መሆን አንችልም” በሚል ፍጹም ቁርጠኝነት መራራውን ትግል ተጋፈጡ። እናም ሲንጋፖር ከዚህ አስከፊ መዋቅር ወጥታ ዛሬ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ንጹሕና ሙስና የሌለባቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍ አስቻሉ። አገራቸውን በዚህ ልዕልና 31 ዓመት መርተው በዘጠና አንድ ዓመታቸው አረፉ። አገር የሚበሉ ነቀዝ መሪዎች በታሪክ ሲዘነጠሉ እንደሚኖሩት ሁሉ፣ እሳቸው በሲንጋፖራውያን፣ ብሎም በዓለም በመልካም የሚነሱ መሪ ሆኑ።

ሊ ኳን ዩ የኬዝ ኪለሮችንና የሙስና መዋቅሩን ሙሉ በሙሉ ያጠፉበት “ፍጹም ምህረት የሌለውና ስልታዊ” (Ruthless and Systemic) ስልት ነው። መዋቅሩን ለማፈራረስ አራት ቀጥተኛ እርምጃዎችን መውሰዳቸው በስፋት ይነገራል።

  • የሕግ የበላይነቱን በቅጣት ማረጋገጥ (Total Enforcement)፦ በአንደኛ ደረጃ፣ ሙስና ሲፈጸም ከተገኘ የሚከተለው ቅጣት እጅግ አሰቃቂና የፖለቲካም ሆነ የሙያ ማንነትን ሙሉ በሙሉ የሚያሳጣ እንዲሆን ተደረገ። በጉቦ የተገኘ ማንኛውም ንብረት ወይም ገንዘብ በቀጥታ ይወረሳል። አንድ ጠበቃ ወይም ዳኛ በትንሽ ስህተት እንኳ ከተገኘ፣ የሕግ ፈቃዱ ለዘላለም ይሰረዛል፤ ሁለተኛ ወደ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ እንዳይገባ ይታገዳል። እንዲህ ያሉቱ ሌቦች ስማቸውና ፎቷቸው በጋዜጣና በቲቪ ላይ በዋና ዜናነት እየቀረበ የሕዝብ መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሆኑ ተደረገ።
  • የስለላ መረብን በፍርድ ቤቶች ላይ መዘርጋት (Infiltration)፦ የሙስና ምርመራ ቢሮው (CPIB) በራሱ በፍርድ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎችና በጠበቆች ማኅበር ውስጥ ሥውር ሰላዮችንና መረጃ አቅራቢ መኮንኖችን (Undercover Agents) አሰማራ። በዚህም የትኛው ጠበቃ ከየትኛው ዳኛ ጋር ካፌ እንደሚቀመጥ፣ የትኛው የፍርድ ቤት ጸሐፊ መዝገብ እንደሚያገላብጥ በሥውር ክትትልና በስልክ ጠለፋ መረጃ ይሰበሰብ ጀመር። ይህ ሲሆን ኬዝ ኪለሮች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት መሬት ጠፋ፤ ምክንያቱም አብሯቸው የሚጠጣው ሰው ወይም ጥቅማጥቅም የሚያቀርብላቸው ባለጉዳይ ራሱ የCPIB ሰላይ ሊሆን እንደሚችል ስላወቁ ፍርሃት ነገሰ። መተማመን ጠፋ።
  • “አቅርቦትን” ማድረቅ (Starving the Network)፦ ደላሎችና ኬዝ ኪለሮች የሚኖሩት የመንግሥት አሠራር ውስብስብና የተጓተተ ሲሆን በመሆኑ፣ ሲንጋፖር ይህንን ለሌብነት የሚያመች ሁኔታ ሲስተም በመዘርጋት አጠፋች። የፍርድ ቤት አሠራሮች፣ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና የኮንትራት ውሎችን ጨምሮ ማንኛውም የመንግሥት አገልግሎት ፈጣንና ግልጽ እንዲሆን ተደረገ። አንድ ባለጉዳይ ጉዳዩን ለማስፈጸም ወራት መናፈቅና መቸገር ሳያስፈልገው መስተናገድ የሚያስችለው የአሠራር አግባብ ሲዘረጋ፣ ዜጎች ወደ ደላላ የመሄድ ፍላጎታቸው መነመነ። ይህ ደላሎችን የመፈለግ “ፍላጎት” (Demand) ሲጠፋ ኬዝ ኪለሮች “ገበያ” አጡ፤ ቀስ በቀስም ከሰሙ።
  • ምሳሌ የሚሆን ከባድ ቅጣት (Exemplary Punishment)፦ መንግሥት የትኛውንም ትልቅ ሰው እንደማይምር በተግባር አሳየ። ከኬዝ ኪለሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚኒስትሮች፣ በወቅቱ የነበሩ እጅግ ታዋቂ ጠበቆችና ከፍተኛ የፖሊስ አዛዦች ሳይቀሩ በቁጥጥር ሥር ውለው ረጅም ዓመታት እንዲፈረድባቸው ተደረገ። በቴሌቪዥን እየቀረቡ መሳቂያና መሳለቂያ ሆኑ። ይህ እርምጃ በፍትሕ መዋቅሩ ውስጥ ለነበሩት ኬዝ ኪለሮች አስደንጋጭ መርዶ ሆነ። ነገሩ ማንንም እንደማይምር ሲታወቅ ኬዝ ኪለሮች መግቢያ መውጫ አጡ። የመንግሥትን ቁርጠኛ እርምጃ ተከትሎ “ሲንጋፖር ውስጥ በሙስና መበልጸግ አይቻልም፤ ብልጽግናው ቢመጣም መጨረሻው እስር ቤትና ውርደት ነው” የሚል እሳቤ ተተከለ። በዚህ መንገድ መዋቅሩን ፍርክስክሱን አውጥተው አጠፉት።

የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎች አሉ። እንደየ አግባቡ እናነሳቸዋለን። ሲንጋፖርን የመረጥነው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ካቢኔያቸውን ይዘው እዚያው በማምራት ሲንጋፖርን “ከጉልምትናዋ” ካጠቧት መሪ አሻራ እና ይህንኑ አሻራ ካስቀጠሉት መሪ ትምህርት ልምድ እንደቀሰሙ ስለነገሩን ነው። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ካቢኔዎቻቸው በየዘርፋቸው የቀሰሙትን ተርከውልናልና ነው። በተለያዩ መስኮች ልምዶችን የቀሰሙ ቢኖሩም ኢትዮጵያን እየፈተነ ካለው ሌብነትና “ኬዝ ኪለሮች” መረብ ለመውጣት የሚያስችል የከረረ እርምጃ አላየንም፤ አልሰማንም። የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ላይ ተደርቦ የተቋቋመውና ሌብነት ላይ ዘመቻ ይከፍታል የተባለው፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው ግብረኃይልም በርካታ ጥቆማ እንደደረሰው ከመገለጹ ውጪ ስላስገኘው ውጤት አልተነገረንም።

ይህ የመሟሟቂያ ጽሑፋችን ነው። በአገራችን ጨዋ የሕግ ባለሙያዎች፣ ሕግ አስከባሪዎችና ባለሥልጣናት ያሉትን ያህል፣ ከኬዝ ኪለርስ ጋር የሚሰሩና ከደላሎች ጋር የተወዳጁ መኖራቸውንና እንዴት እንደሚሰሩ አዲስ ሪፖርተር መረጃ ሰብስባለች። አካሄዱ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ከአገር አይበልጥምና ከፍትሕ ወዳዶችና ቀና ልቦና ካላቸው ዜጎች ጋር በኅብረት እንሄድበታለን።

የአንድን አገር የፍትሕ ሥርዓት የሚያበሰብሱ፣ ሕዝብ ከሕግ አግባብና ከፍትሕ ደጆች በተስፋ መቁረጥ እንዲያፈገፍግና በምትኩ ለዚህ ኢመደበኛ የሆነ የማጅራት መቺዎች ስብስብ እንዲሰግድ የሚያደርግ ክፉ ልምምድ በመሆኑ፣ ይህን አደገኛ አዝማሚያ መታገስ አገርንም ዋጋ እንደሚያስከፍል በማሳሰብ፣ የጉዳዩ አደገኛነት የሚያሳስባችሁ ሁሉ ልምዳችሁን ታካፍሉን፣ ትጽፉልን፣ ጥቆማችሁን ታደርሱን ዘንድ ልባዊ ጥሪ እናቀርባለን። ፍትሕ የአንድ ማኅበረሰብ የሞራል ውበት መገለጫ ነውና በዝምታ ሲንጋፖር በሃምሳዎቹ መጨረሻ በነበረችበት የገለማ የሌብነት መዋቅር ውስጥ ለመኖር አንፈቅድም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አታቆላምጡት፤ በስሙ ጥሩት” ያሉት ሌብነት በመዋቅር እንዲያመንዥገን፣ ፍትሕን በጸዳ መንገድ የሚናፍቁ ድሆች በጥቂት የተደራጁ ሌቦችና ደላሎች የጥቅም ትስስር በአደባባይ የሀቅ መስፈሪያዋ ተሰብሮ ሲያነቡ ማየት እንደ አገር ውርደት፣ እንደ መንግሥትም ኃፍረት ነውና ሚዲያዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ፣ ከምንም በላይ “ሕዝብን እናገለግላለን” በሚል የማላችሁ የፍትሕ ባለሙያዎች ለዚህ ሪፖርት ቀጥተኛ ድጋፍ ታደርጉ ዘንድ እንጠይቃለን።

በአገራችን ወፈር ወፈር ያሉ ጉዳዮችን ከታች እስከ ላይ ባሉ መዋቅሮች በጥቆማና በመልዕክተኛ እንዴት ቀበኞቹ “ኬዝ ኪለሮች” ዘንድ እንደሚደርስ በስፋት መረጃ ሰብስበናል። ድርድሩ እንዴት እንደሚደረግ ይህንኑ የሚያመላክቱ ማስረጃዎችም አሉን። ሁሉንም በአግባቡና የተቋሙን ክብር በመጠበቅ በጥንቃቄ እንዘግባለን። አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንማጸነው ይህ ጉዳይ አሳሳቢና በዜጎች ትብብር ጭምር ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባው የምታምኑ ድጋፋችሁን ስጡ። የዜግነት ግዳጃችሁን ተወጡ!!

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

አገራዊ ምክክሩን ለማሰናከል ስምሪት ተሰጠ፤ ኮሚሽኑ በአንድም አጀንዳ የመወሰን ስልጣን እንደሌለው አስታወቀ

አዲስ ሪፖርተር - አገራዊ ምክክሩ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በአገሪቱ...

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ መሪነት ወደ አፍሪካ ኃያልነት እየተሸጋገረች ነው፤ ፈርስት ፖስት

አዲስ ሪፖርተር - ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)...