አዲስ ሪፖርተር ዜና አዲስ አበባ — የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባው ለቀጣዩ ለ2019 በጀት ዓመት የሚውል ከ2.3 ትሪሊዮን ብር በላይ ረቂቅ በጀት በሙሉ ድምፅ አጽድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

ለቀጣዩ ዓመት የቀረበው አጠቃላይ የበጀት መጠን 2 ትሪሊዮን 339 ቢሊዮን 268 ሚሊዮን 126 ሺሕ 738 (2,339,268,126,738) ብር ሲሆን፤ ይህ በጀት ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የ2019 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት የፌደራል መንግሥት ለ2018 በጀት ዓመት መድቦት ከነበረው 1.93 ትሪሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ409.2 ቢሊዮን ብር (ወይም የ21.2 በመቶ) ብልጫ አሳይቷል። ካለፉት አራት ዓመታት አጠቃላይ የበጀት ጉዞ አንጻር ሲታይም የዘንድሮው በጀት በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። የፌደራል መንግሥት በጀት ከ2015 ዓ.ም. (786.6 ቢሊዮን ብር) አንጻር ሲነጻጸር በአሁኑ ወቅት በሦስት ዕጥፍ ገደማ (297.4%) ዕድገት ማሳየቱን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ የ2019 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት የተዘጋጀው የ2018 በጀት ዓመት “የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ” መሆኑን ገልጿል። ይህም አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ እና ኃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም እና የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም ያገናዘበ መሆኑ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ ከ2019 እስከ 2023 ዓ.ም. በሚኖረው የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ በሰፊው የተወያየ ሲሆን፤ “የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካሉበት ተግዳሮቶች እየተላቀቀ እና የኢኮኖሚው መሠረቶችም እየተጠናከሩ መጥተዋል” ሲል አስታውቋል። ይህ የ2019 ዓ.ም. በጀትም በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ረቂቅ በጀቱ አሁን ባለው ይዘት ላይ ምክር ቤቱ አስፈላጊ ግብዓቶችን ካካተተበት በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት በፓርላማው ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






