ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተቋምነት እየተሸጋገረ ነው፤ ደንበኞቹ ከ90 ሚሊዮን አለፉ

Date:

የ4ጂ ሽፋን 82.23 በመቶ አደገ፤ 340 የ5ጂ ጣቢያዎች ወደ ሥራ ገቡ፤ 242 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መከላከሉን አስታውቋል

አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ ኢትዮ ቴሌኮም በደንበኞች ብዛት፣ በኔትወርክ ሽፋን፣ በዳታ ማዕከላት አቅም ግንባታ፣ በ5ጂ ቴክኖሎጂ እና በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የተመዘገቡት ውጤቶች ኩባንያው ከቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት ወደ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተቋም የሚያደርገውን ሽግግር የሚያጠናክሩ መሆኑን መረጃ ዘርዝሮ አስታወቀ። “ስኬት” ሲል የዘረዘራቸው ተግባራቱ ተቋሙ ላስቀመጠው ዕቅድ መዳረሻ ማሳያ መሆናቸውን አመልክቷል።

ኢትዮ ቴሌኮም “ቀጣዩ አድማስ፣ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” በተሰኘው የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ የመጀመሪያው የሆነውን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል። ኢትዮ ቴሌኮም እንዳለው በደንበኞች ብዛት፣ በኔትወርክ ማስፋፊያ፣ በዲጂታል አገልግሎቶችና በሳይበር ደህንነት ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።

በሪፖርቱ መሠረት የኩባንያው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 90.12 ሚሊዮን በመድረስ የዓመቱን ዕቅድ 101.7 በመቶ ማሳካቱ ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ 72.09 ሚሊዮን ንቁ የሞባይል ደንበኞች ሲሆኑ፣ 51.53 ሚሊዮን የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች፣ 66.95 ሚሊዮን የድምፅ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እና 65.65 ሚሊዮን የአጭር ጽሑፍ (SMS) ተጠቃሚዎች መሆናቸው ተመልክቷል። ድርጅቱ እነዚህ ውጤቶች ከባህላዊ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ሁሉን አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ (Telco-to-TechCo) በመሸጋገር እየተከተለው ያለውን ስትራቴጂ የሚያጠናክሩ እመርታዎች እንደሆኑ አመልክቷል።

በቴሌኮም መሠረተ ልማት ዘርፍ 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው ጠቅላላ ቁጥራቸው 10,613 መድረሱ ተገልጿል። ይህም 10.2 ሚሊዮን ተጨማሪ የኔትወርክ መሸከም አቅም መፍጠር ያስቻለ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል። በተመሳሳይ የ4ጂ ተጠቃሚዎች ሽፋን ከ70.83 በመቶ ወደ 82.23 በመቶ ከፍ ሲል፣ 264 አዳዲስ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት በማግኘታቸው በጥቅሉ የ4ጂ ተደራሽነት ለ1,200 ከተሞች ተደራሽ መሆኑን በሪፖርቱ በስኬት ተጠቅሷል። 

የ5ጂ አገልግሎትም በፍጥነት መስፋፋቱን ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ በበጀት ዓመቱ 7 ተጨማሪ ከተሞች በ5ጂ አገልግሎት ተካተው አጠቃላይ ቁጥራቸው 33 ከተሞች ደርሷል፤ 340 የ5ጂ ጣቢያዎችም ለአገልግሎት መዋላቸው፣ በተጨማሪ 793 ኪሎ ሜትር አዲስ የባክቦን ፋይበር በመዘርጋት ጠቅላላ የፋይበር ኔትወርኩ 23,442.1 ኪሎ ሜትር ሲደርስ፣ 841 የሞባይል ጣቢያዎችም በፋይበር መገናኘታቸው ሪፖርቱ አስረድቷል።

በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ ስድስት የTier III ደረጃ ዳታ ማዕከላት 5 ሜጋ ዋት የኦፕሬሽን አቅምና 640 የሰርቨር ማቀፊያዎችን እንዳዘጋጀ ገልጿል። እነዚህ ማዕከላት ከ880 በላይ የመንግሥት ተቋማትን፣ 340 የግል ድርጅቶችን እና ሌሎች ተቋማትን እያገለገሉ ሲሆን፣ 12,400 ቨርቹዋል ማሽኖችንና 8.4 ፔታባይት የመረጃ ማከማቻ አቅም እንዳላቸው ተመልክቷል። በተፈጥሮ አየር የማቀዝቀዣ ሥርዓት በመጠቀም የኃይል ፍጆታን 34 በመቶ መቀነስ መቻሉንና የPUE መጠኑን 1.3 በማድረስ ከዓለም አቀፍ አማካይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ኩባንያው በሪፖርቱ አካቷል።

በሳይበር ደህንነት ዘርፍም 242,459 የሳይበር ጥቃቶችን በ2018 በጀት ዓመት ለይቶ ማክሸፉን ያስታወቀው የኢትዮ ቲሌኮም ሪፖርት፣ 78,845 የRemote Code Execution ጥቃቶች፣ 67,537 የMalware ጥቃቶች፣ 67,042 የPhishing ጥቃቶች እና 2,210 የDDoS ጥቃቶች መሆናቸው በዝርዝር አስረድቷል። በተጨማሪም የሰራተኞች የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ከ44.8 በመቶ ወደ 79.5 በመቶ ማደጉን እና የሲስተሞች የአገልግሎት ዝግጁነት (Uptime) 99.99 በመቶ መድረሱን ከድርጅቱ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related