የዘመን ክስተት አደዋና የምክክር ኮሚሽኑ ጥሪ!! ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ሰዎችም ያልፋሉ፤ ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች!

Date:

አዲስ ሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ – “…አንድ የአፍሪካ አገር በአውሮፓ ኃይል ላይ እንዲህ ያለ ከባድ፣ አሳማኝና አስደናቂ ድል የተቀዳጀበት ጊዜ የለም።” ሲል እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ ጆርጅ በርክሌይ በ1902 ዓ.ም በጻፈው ታሪካዊ መጽሐፉ ላይ የአድዋን ታላቅነት ከታሪክ አኳያ ገልጦት ነበር።

እንግሊዛዊው ተመራማሪ ይህንን ምስክርነት የሰጠው የአድዋን ድል ከቀላል ወታደራዊ ግጭት በላይ አውጥቶ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ በክፍለ ዘመናት አንዴ ብቻ የሚከሰት ግዙፍ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ለማሳየት ነበር።

“The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” የተሰኘውን ድንቅ መጽሐፍ የጻፈው አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ (Raymond Jonas) የአድዋን አስገራሚነት እንዲህ ሲል ያጠቃልለዋል፦ “አድዋ አውሮፓውያን ‘ዓለምን ለመግዛት የተፈጠርን ነን’ የሚሉትን ትዕቢትና አስተሳሰብ እንድንጠራጥር ያደረገ፣ የዓለምን የኃይል ሚዛንና የዘር የበላይነት ትረካ ሙሉ በሙሉ የገረሰሰ ድንቅ ክስተት ነው” ሲል አግዝፎታል።

የሁለቱ ጸሐፍት እይታና ድምዳሜ የሚያስረዳን የአድዋ ድል አስገራሚነት በጥቂት ቃላት ሲጠቃለል፤ አይሸነፍም፣ አይነካም ተብሎ የሚታመነውን የአውሮፓ ኃያል ጦር፣ ምንም ዘመናዊ ወታደራዊ ሥልጠና ባልነበራቸው፣ ነገር ግን በአገራዊ ፍቅርና በአንድነት በቆሙ ኢትዮጵያውያን መሸነፉንና የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ መቀየር መቻሉን ነው።

በአድዋ ጦርነት ወቅትና ከጦርነቱ በፊት የነበረውን አገራዊ ሁኔታ በተመለከተ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ካስተላለፏቸው መልዕክቶች መካከል እጅግ ታዋቂውና ሕዝቡን ለአንድነትና ለጦርነት ያነሳሳው የክተት አዋጅ ዘላለም የሚታወስ የእሳቸውም፣ የአገርም ማኅተም ነው።

መስከረም 17 ቀን 1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጣሊያን ለወረራ መዘጋጀቱን አስመልክተው ለአገሬው ያስተላለፉት የክተት አዋጅ “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፤ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም” በሚል ጽኑ እምነታቸው ይነሳል።

አክለውም የመጣውን ጠላት ክፉነት ከአገር እስከ ግል ቤትና ሕይወት ድረስ የሚያስከትለውን አደጋ አሳይተው፦ “…ቀደም ሲል እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብል፤ ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልምርህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም” ብለው ነበር። በውጤቱም ዛሬ ድረስ ዓለም የሚደነቅበት፣ መላው ጥቁር ሕዝብ የሚኮራበት ድል ተመዘገበ። ያንን ቀን ነው “በክፍለ ዘመን አንዴ የሚከሰት” ሲሉ ታሪክ ጸሐፍት ያጎሉት።

“ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የአድዋን መንፈስ ሰንቀን ለሀገር ግንባታ ያዳበርነውን ወደ ምክክር እና መግባባት መቀየር ያስፈልገናል” ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚያካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሚሳተፉ ተመካካሪዎች የቅድመ ምክክር ገለጻ ሲሰጡ፣ አንድ ክፍለ ዘመን ወደኋላ ሄደው አንድነት “በክፍለ ዘመኑ አንድ ጊዜ ብቻ የሚከሰት ድንቅ ታሪክ” ባለቤት እንደሚያደርግ ያስታወሱት።

ለአድዋ ድል በዋናነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኅብረትና “እምቢ ለአገሬ” የሚለው መንፈስ የሚጠቀሰውን ያህል፣ ዛሬ የምንኮራበት ድንቅ ታሪክ እንዲመክን ከጠላት ጋር ሆነው የሠሩ ባንዳዎችም ነበሩ። ተገዝተው በአገራቸው ላይ የተነሱና ያሴሩ ባንዳዎች፣ መረጃ በማሳት፣ መንገድ በማሳየት፣ አልፎም ወደ ወገን በመተኮስ የጠላት መሣሪያ ሆነው ማገልገላቸውን ታሪክ ያስረዳናል።

ዛሬም ልክ እንደ ቀደመው ጊዜ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ገረድ ሆነው በሚችሉት ሁሉ በአገራቸው ላይ የዘመቱ እያየን ነው። ኢትዮጵያ ሆን ተብሎ፣ ባለማወቅ ወይም በዘፈቀደ የተጫኑባትን ጣጣዎችና ሕገ-መንግሥታዊ አበሳዎች እንዳትሻገራቸው፤ በሚዲያና በማኅበራዊ አውታሮች ተሰናስለው አሳች፣ እርስ በርስ የሚያባላና የሚያጋድል ፕሮፓጋንዳ ከመርጨት ጀምሮ፣ በገፊና ጎታች ስልት ሴራና እልቂት እየደገሱ አገር ለማተራመስ የሚሠሩ ኃይሎችን እያየን ነው።

ከምንም በላይ ደግሞ ለታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በመገዛት በኢትዮጵያ ዙሪያ ሁሉ ጦርነት እንዲቀሰቀስ በግልጽ በአሳች ፕሮፓጋንዳ እየሠሩ ነው። እነዚህ ባንዳዎች “ኢትዮጵያዊ ነን” እያሉና በኢትዮጵያ ባንዲራ ተጠቅልለው፣ በእምነትና በብሔር ውስጥ ተደብቀው ኢትዮጵያን እንደ ሙቀጫ ልጅ ሲደበድቡና ሲረግጡ፣ ከመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ልክስክሶች እየተጠቀሙ በአገራቸው ላይ ሲያሴሩ ውለው ያድራሉ።

ኢትዮጵያ የተከመሩ ችግሮቿን ጨምሮ አሁን አንቆ የያዛትን አበሳ በመመካከር ለማስወገድ ገና “አሃዱ” ብላ ስትጀምር ያሟረቱ “ቅምጥ ሚዲያዎችን” ጨምሮ፣ ኮሚሽኑ ሥራውን እንዳያከናውን ብዙ ብዙ ሲባል ቆይቶ ዛሬ ላይ ተደርሷል። በወጉ ለሚረዱ ሁሉ ዛሬ ያለንበት መስቀለኛ መንገድ ከምንም በላይ የተወሳሰበ ነው። ወቅቱ ይህ ትውልድ ይህን ውስብስብ ወቅትና ታሪክ ያሸከመውን ዕዳ አጥቦ የሚሻገርበት የታሪካዊ ድል ዋዜማ ላይ ነው የሚባለው ለዚሁ ነው። ያኔ እንደሆነው ሁሉ፣ የልዩነትና የግጭት መነሻ እንዲሁም ያለመግባባት መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች በዘመኑ አንዴ እንደተገኘው የአድዋ ድል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ፣ የዚህን ዘመን “ሌላ አድዋ” መድገምና ጠላትን አጀንዳ ቢስ የሚያደርግ ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል።

በዚህ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚነሱና የሕዝብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለፈራጁ ሕዝብ እንዲተው የሚደረጉ ጉዳዮች የብልፅግና ወይም የዚህ መንግሥት ጉዳዮች ተደርገው እንዲቀርቡ ለማድረግ፤ “አጀንዳችንን በሙሉ ብልፅግና ቀማን፤ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ ተከፋፍለዋል። የምንጠይቃቸው አጀንዳዎች ምላሽ ካገኙ ለምን እንደክማለን? የሚሉ ኃይሎች እየተነሱ ስለሆነ አጀንዳውን በማስቀየስ እንሥራ” በማለት፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች (ግብፅ፣ ሻዕቢያና የልባቸው እንዳይሰምር ከተፈረካከሱት ጋር) የሚርመሰመሱ ኃይሎች እየተወራጩ ይገኛሉ።

እኛ ግን እንደ ሚዲያ የጎደሉ ጉዳዮች እንዲሟሉ፣ አገርን የሚጠቅሙ ሐሳቦች እንዲጎለምሱ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ከችግር የምትላቀቅበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥጋት የሆኑ ሕጎች፣ አሠራሮችና አደረጃጀቶች እንዲከስሙ የሚያደርግ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ፣ ከምንም በላይ ደግሞ አፍራሽ ሐሳቦችን እየተከታተሉ ማምከን የታሪኩ ባለቤት ያደርጋልና እዚህ ላይ አተኩረን እንሠራለን። አዲስ ኢትዮጵያ ትወለድ ዘንድ ወደፊቱን እያሰብን አፍራሽ ሐሳቦችና አካሄዶችን እንታገላለን። ሌሎችም በዚሁ አገርንና ትውልድን በሚያራምድ ሐሳብ ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን። የዚያ ዘመን ባንዳዎች እንደተሸነፉ ሁሉ የዚህ ዘመን አሽከሮችም በተመሳሳይ መዋረዳቸው አይቀሬ ነውና አገርና ሕዝብን እናስብ! በዘመን አንዴ ለሚከሰት ታሪካዊ ድል እንተባበር! ገዥም፣ ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ሰዎችም ያልፋሉ፤ ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች!

ነጮች ሳይቀር የዘመን ክስተት አድርገው የሚገልጹትን ድንቅ ታሪክ የሚያንቋሽሹና የሚያበሻቅጡ ያሉትን ያህል አሁንም ይህንን ታሪካዊ የምምክክር ጊዜ ውጤቱን አስቀድሞ በመረዳት የሚያንኳስሱ የህዝብ መከራ ሰርጋቸው፣ የአገር ውድቀት ስለታቸው፣ የሆነ ሁሉ ወደ ቀላባቸው የሚመለሱበት የታሪክም፣ የጀግንነትም ጫፍ ላይ ነንና ብርታት ያስፈልገናል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

50 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር የሚከፍል ድርጅት እንዴት “የፍትህ ያለህ” ጩኸት ተሰማበት

አዲስ ሪፖርተር ዜና - የዚህ ሪፖርት አቅራቢ ወደ ሬስቶራንቱ...

ትህነግና ሻዕቢያ በጋራ የተቃውሞ መግለጫ አወጡ፤ “ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አትፈቅድም”

አዲስ ሪፖርተር - በመጥረቢያው ብረትና በእንጨቱ እጀታ የተሳሉት ሻዕቢያና...

በኩርሙክ ግንባር የቀጠለው ጦርነት የአርሚ 70 ተዋጊዎችም ከባድ ጉዳት ድርሶባቸዋል

አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ/ካርቱም | ሐምሌ 9 ቀን...

“ወደ ጦርነት መመለስ የለም፤ በስቃይ ፊት ዝምታ አይኖርም፤ የትግራይ ሕዝብ ሥቃይ ሊቆም ይገባል…”

"ይህ የአቋም መግለጫ የጋራ ጥሪያችን ነዉ፤ ወደ ጦርነት መመለስ...