የደም እንባ ምስክርነት፣ በትህነግ ወረራ ሕይወታቸውን ያጡ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና የታፈኑ 871,801 ንጹሐን እና አፋብን ለአማራ ህዝብ ያበረከተው ውለታ

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – በአማራ ክልል በቆቦ እና በአጋምሳ ብቻ ከ600 በላይ ንጹሐን መሞታቸውን፣ በማይካድራ እና አካባቢው ከ1 ሺህ 100 በላይ ንጹሐን በሕወሃት ቡድን አባላት በጅምላ መገደላቸውን፣ ከ837 ሺህ በላይ ንጹሐን ዜጎች በወረራ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን፣ ከ7 ሺህ በላይ ንጹሐን ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ ከ18 ሺህ 400 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳተኛ እንደሆኑ፣ ከ1 ሺህ 939 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው እና 7 ሺህ 462 የሚሆኑት በኃይል ታፍነው መወሰዳቸውን ለአብነት በመዘረዘር፣ ይህን ሁሉ ወንጀል ከፈጸመው ትህነግ ጋር የሚደረግ ጥምረት ክህደት መሆኑን አሚኮ ያሰራጨው ዘገባ አመለከተ።

ተቋሙ፤ “የደም እንባው ሳይደርቅ የተፈጸመ ክህደት!” በሚል ባሰራጨው ጽሑፍ ለአብነት እንደማሳያ ያቀረባቸው መረጃዎች ከተለያዩ የመብት ተቆርቋሪዎች እና ጥናት ካካሄዱ አካላት የተገኙ መሆናቸውን በዝርዝር አስረድቷል።

የጥልቁ ክህደት እና “ያልተቀደሰው ጋብቻ” በማለት፣ ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን በሚል ጠመንጃ አንስተው ይህንን እና ያልተዘረዘሩ በደሎችን በአማራ ሕዝብ ላይ ከፈጸመ “ነፍሰ በላ” ድርጅት ጋር ስለመጣመራቸው የዓለም አቀፍ ተቋማት የሰጡት ማረጋገጫ የሚከተለው ነው፦

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2021 እና በ2022 ባወጧቸው ሪፖርቶች ጅምላ ጭፍጨፋውን አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ ወቅት አሶሺየትድ ፕረስ የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠቅሶ በሠራው ዘገባም በቆቦ እና በአጋምሳ ብቻ የሟቾች ቁጥር ከ600 በላይ እንደሚደርስ ይፋ ማድረጉን፣ ኢሰመጉ በ2014 ዓ.ም ባወጣው የምርመራ ሪፖርት እንዳረጋገጠው በማይካድራ እና አካባቢው ከ1 ሺህ 100 በላይ ንጹሐን በጅምላ መገደላቸውን ጠቅሷል። በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ባሳተመው ጥናት ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን የጠቀሰው ዘገባ፣ ድርጊቱን “የደም እንባው ሳይደርቅ የተፈጸመ ክህደት” በማለት ሕዝብ ፍርዱን እንዲሰጥ ጠይቋል።

“የሕወሃት የፖለቲካ ጉዞ ከተመሠረተበት የደደቢት በረሃ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ በረቀቀ የጥላቻ ትርክት እና ሰነድ የተቃኘ ነው። ቡድኑ የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት ይህንን ስልታዊ የጥፋት ሰነድ በመዋቅራዊ መንገድ ተፈጻሚ አድርጎታል” በማለት የኮነነው ሪፖርት፤ “ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ከባድ ሰቆቃን አድርሷል። በመላው ኢትዮጵያም የማይሻር የታሪክ ጠባሳን ጥሎ አልፏል። ሀገሪቱንም ለማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት እና የብጥብጥ ፈንጂ አጥምዶ ለምስቅልቅል ዳርጓታል” በማለት ያለፈውን የጥፋት መጠንና አሁንም ያለውን ትርምስ ገልጿል።

“በ2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባ በመውጋት የጦርነት እና የጥፋት ጉዞውን በይፋ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ ለዓመታት ባካሄደው የቡድኑ ወረራ ቀጥተኛ ሰለባ የሆነው የአማራ ክልል ነበር” በማለት የትህነግን በደል ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ቡድኑ በአማራ ክልል ያደረሰውን ጥፋት “ሆን ተብሎ ክልሉን ለማውደምና ሕዝቡን መከራ ውስጥ ለመክተት ታስቦና ታቅዶ የተሠራ” ሲል ገልጾታል።

ቡድኑ በአማራ ክልል በፈጸማቸው ወረራዎች ላይ ታሪክ የማይረሳው መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የአስገድዶ መድፈር እና የቁሳዊ ውድመት ወንጀሎችን መፈጸሙን፣ በተለይም በማይካድራ፣ በጭና፣ እና በቆቦ አጋምሳ የተፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋዎች የቡድኑን የጭካኔ ጥግ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች እንደሆኑ አስታውቋል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት ከሰጡት ማረጋገጫ በተጨማሪ፣ በሰብዓዊ ደረጃ የደረሰውን በጥናት የተደገፈ መረጃ በመዘርዘር ሪፖርቱ “እንዴት ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ከዚህ ቡድን ጋር ይጣመዳሉ?” በሚል ለሕዝብ ፍርድ እንዲያመች የሚከተሉትን የጥፋት ሰነዶች ጠቅሷል፦

ከ837 ሺህ በላይ ንጹሐን ዜጎች የትህነግ የጥቃት ወረራ ሰለባ ሆነዋል፤ ከ7 ሺህ በላይ ንጹሐን ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ18 ሺህ 400 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 1 ሺህ 939 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ተፈጽሟል፣ 7 ሺህ 462 የሚሆኑት በኃይል ታፍነው ተወስደው ደብዛቸው ጠፍቷል በማለት ጥናት አቅራቢዎቹን ጠቅሶ በሪፖርቱ አመልክቷል።

በቁሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ዘርፍ የአማራ ክልል እንዲወድምና እንዲደቅ መደረጉትን የዘረዘረው ሪፖርቱ፣ በትህነግ ወረራ ከ291 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውድመት ማድረሱ በጥናት መረጋገጡ ተገልጿል። ይህ የገንዘብ መጠን ክልሉ በ2013 በጀት ዓመት ከነበረው የ62 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት አንጻር ሲሰላ የአራት ዓመት ተኩል በጀቱን ሙሉ በሙሉ ማጣት እንደማለት ነው።

“የጥልቁ ክህደት እና ያልተቀደሰው ጋብቻ” ማረጋገጫ እንደሆነ በማሳየት ሪፖርቱ እንዳለው፣ “ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ የታጠቁ ኃይሎች ከዚህ የጥፋት ኃይል ጋር የጥቅም ትብብር መፍጠራቸው አስገራሚ ነው” በማለት በክልሉ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ክህደት ኮንኗል። ክህደቱም ከደረሰበት የከፋ ውድመትና ሐዘን ገና ባላገገመ ሕዝብ ላይ ከአጥፊው ወገን ጋር አብሮ ዳግም ክልሉን ማውደም፣ ሕዝቡን ማሰቃየት በየትኛውም ዘመን የማይረሳ ክህደት እንደሆነ አመላክቷል።

“በተለይም ራሱን የሕዝብ ወገን አድርጎ የሚጠራው ቡድን መሪዎች፣ የአማራ ሕዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ በደም የተጨማለቀውን እጁን ካላጸዳው፣ በግፍ የጨፈጨፋቸው ዜጎች ደም ሳይደርቅ፣ ሐዘኑ የመታቸው ቤተሰቦች ልብ ሳይሽር፣ የወደመው ሀብትና የሕዝብ መገልገያዎች ዳግም ሳይጠገኑ፣ ወዘተ…” ይህን ሁሉ ከፈጸመው ትህነግ ጋር የሚደረግ ቅንጅት ክህደቱን በፈጸሙት በራሳቸው አንደበት በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ የክህደት ሁሉ ክህደት እንደሆነ ተመልክቷል።

“ይህ ተግባር በአማራ ሕዝብ ቁስል እንጨት ከመስደድ እና ሕዝቡን ደጋግሞ የመውጋት ያህል ክህደት ነው። ግብፅን እና ሻዕቢያን የመሰሉ የኢትዮጵያ ጠላቶችን አስተባብሮ ሀገር ለማፍረስ ከሚዶልተው የትህነግ ስብስብ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚደረግ ጥምረትም ፍጹም የሀገር ክህደት እና ያልተቀደሰ ጋብቻ ነው” ሲል ለጊዜና ለታሪክ እንዲቀመጥ ሪፖርቱ አሳስቧል። የሰላም መንገድ እንደሚጠቅምም አስታውሷል።

“የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት ደጋግመው የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪውን ተቀብለው በውይይት በክልሉ ያለውን ችግር እና ሌሎች መሰል ሕዝቡ ላይ ያነጣጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የወሰኑት ሊመሰገኑ ይገባል። ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያን ለመውጋት የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ምኞት ከንቱ ቅዠት በመሆኑ፣ አሁን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጦርነት ሳይሆን ሰላም እና ልማት ነው” ያለው ሪፖርቱ፣ በሀገር ውስጥ ላሉት የታጠቁ ኃይሎች ከጦርነት ይልቅ የውይይት እና የትብብር መንገድ ብቻ አማራጭ እንደሆነ አስምሮበታል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related