በችኮላ የሚወጡ ሕጎች የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱን እያዳከሙ መሆኑ ተገለጸ

Date:

በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋት ላይ የተካሄደ ጥናት፣ በችኮላና በጥድፊያ የሚወጡ ሕጎች ተደጋጋሚ ማሻሻያ፣ መሻርና የሕጎች መጣረስ እንዲበረክት እያደረጉ መሆኑን አመላከተ

አዲስ ሪፖርተር – በኢትዮጵያ ሕግ ማውጣት ለመንግሥትና ለሕብረተሰቡ ግንኙነትን ለመምራት፣ የዜጎችን መብትና ግዴታ ለመወሰን እንዲሁም የመንግሥት ተቋማትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለማስቀመጥ ወሳኝ ሥርዓት ነው። ሆኖም ሕጎች በበቂ ጥናትና ምክክር ሳይዘጋጁ በፍጥነት መውጣታቸው የሕግ ሥርዓቱ ወጥነትና መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል።

ጥናቱ «የሕግ አወጣጥ ሥርዓት መረጋጋት በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን፣ ዓላማው በሀገሪቱ ያለውን የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ እንዲሁም የሕግ አወጣጥና አፈጻጸም ሥርዓት በመመርመር የሚታዩ ችግሮችን መለየትና የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ ነው።

ጥናቱ ከ2010 እስከ 2018 ዓ.ም. በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡ አዋጆችን በሙሉ በመመርመር የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በማየት የኢትዮጵያን ሕጋዊና ተቋማዊ ሥርዓት ለማነጻጸር ተሞክሯል።

ሕግ መረጋጋት ለምን አስፈለገ?

ሕግ የማኅበረሰብንና የመንግሥትን መስተጋብር የሚመራ መሣሪያ ነው። ሕጎች በግልጽና በተገማች መንገድ ከተዘጋጁ ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን ማወቅ ይችላሉ። ባለሀብቶችም የሚያደርጉትን የረጅም ጊዜ የንግድና የኢንቨስትመንት ውሳኔ በተረጋጋ የሕግ ማዕቀፍ ላይ መመሥረት ይችላሉ።

በተቃራኒው አንድ ሕግ ከወጣ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደጋግሞ ከተሻሻለ፣ ከሌሎች ሕጎች ጋር ከተጣረሰ ወይም የሚፈጽመው ደንብና መመሪያ ከአዋጁ ጋር ከተቃረነ የሕግ ሥርዓቱ ተገማችነት እና ታዋቂነት ይቀንሳል።

ጥናቱም የሕግ ሥርዓት መረጋጋት ማለት ሕጎች ፈጽሞ እንዳይለወጡ ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባል። ሕጎች ከማኅበረሰብ፣ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ ለውጦች ጋር ሊሻሻሉ ይችላሉ። ነገር ግን ማሻሻያው በጥናት፣ በምክክርና በተገቢ ግምገማ ሊመራ ይገባል።

በችኮላ የሚወጡ ሕጎች ምን ያመጣሉ?

ጥናቱ በተለይ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ በርካታ አዳዲስ ሕጎች ቢወጡም፣ አንዳንዶቹ በቂ የሕዝብና የባለሙያ ምክክር ሳይደረግባቸው በፍጥነት መዘጋጀታቸውን ጠቁሟል።

ይህም ሕጎቹ ከጸደቁ በኋላ በሚታዩ ክፍተቶች ምክንያት ደጋግመው እንዲሻሻሉ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል። አንዳንድ ሕጎች ከወጡ በኋላ በሳምንታት ውስጥ እንኳን ማሻሻያ የተደረገባቸው መኖራቸው በጥናቱ ተጠቅሷል።

ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን መልሶ ለማቋቋም የወጣው አዋጅ በተመሳሳይ ዓመት በሌላ አዋጅ መሻሻሉንና ከሁለት ዓመታት በኋላም በ2015 ዓ.ም. እንደገና መሻሻሉን ጥናቱ እንደምሳሌ አቅርቧል።

እንዲሁም የኤክሳይዝ ታክስን የሚመለከቱ ሕጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሻሻያ የተደረገባቸው መሆኑ በጥናቱ ከተነሱ ምሳሌዎች መካከል ነው።

ሌላኛው ደንብና መመሪያ የሚፈጥሩት ችግር ሲሆን
የሕግ አወጣጥ ችግሩ በአዋጆች ብቻ እንደማይገደብም ጥናቱ ያሳያል። ከአዋጅ በታች የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ከዋናው ሕግ ጋር ተጣጥመው እንዲወጡ በቂ ቁጥጥር አለመኖሩ ተጠቁሟል።

አንዳንድ መመሪያዎችና ደንቦች ከመውጣታቸው በፊት ለበቂ ግምገማ እንደማይቀርቡም ተገልጿል። ይህም ከአዋጁ የሚጋጭ ድንጋጌ እንዲኖር ወይም በተግባር ሕጉን ለመፈጸም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል።

በተለይም በግብር ዘርፍ የሚወጡ የበታች ሕጎች በቂ ግምገማ ሳይደረግባቸው መውጣታቸው እንደ አንዱ የችግሩ መገለጫ ተጠቅሷል።

የሕጎች መጣረስና መሻርን ስንመለከት ጥናቱ በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ውስጥ የአዋጆች መሻርና መጣረስ እየታየ መሆኑንም ለይቷል።

ለምሳሌ፣ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ብቻውን 18 አዋጆችንና 35 ደንቦችን መሻሩ በጥናቱ ተጠቅሷል። ይህ የሕጎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሕጎቹ መካከል ያለው ተያያዥነትና ወጥነት በቂ ትኩረት እንደሚፈልግ ጥናቱ ያመላክታል።

አንዳንድ አዋጆች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጩ ድንጋጌዎች እንዳሏቸውም ጥናቱ ጠቁሟል። በሕገ መንግሥቱ ራሱም አሻሚ ቃላት፣ ግልጽነት የጎደላቸው አንቀጾችና በአንዳንድ ጉዳዮች የሚጣረሱ መርሆዎች እንዳሉ ጥናቱ አመላክቷል።

ችግሩ በዜጎችና በኢንቨስትመንት ላይ ያለው ተጽዕኖ ደግሞ የሕግ መረጋጋት የሚመለከተው የሕግ ባለሙያዎችንና የመንግሥት ተቋማትን ብቻ አይደለም። የሕግ ለውጥ በተደጋጋሚ ሲከሰት ዜጎች የሚከተሉትን ሕጋዊ መስፈርት ለመረዳት ይቸገራሉ።

ለምሳሌ አንድ ባለሀብት በአንድ ዘርፍ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ቢያደርግና ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግብር፣ የንግድ ወይም የፈቃድ ሕጉ ቢለወጥ፣ የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ውሳኔ ሊጎዳ ይችላል። ይህም ባለሀብቱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ውሳኔ እንዳይወስን ሊያደርገው ይችላል።

በዜጎች በኩልም ተመሳሳይ ነው። የመብትና ግዴታ መስፈርት በተደጋጋሚ ከተቀየረ ሕጉን ማወቅና በትክክል መከተል ይከብዳል።

ለዚህ በዋናነት እንደምክንያትነት የሚቀርበው የተቋማት ድክመት ነው። ጥናቱ የሕግ አወጣጥ ችግሩን ከሕጎች ይዘት ብቻ ጋር አላያያዘውም። የባለሙያ እጥረት፣ የተቋማት አለመናበብ፣ የአመራር ትኩረት ማነስና ወጥ የሆነ የሕግ ረቂቅ ዝግጅት ሥርዓት አለመኖር እንደ ዋና ዋና ድክመቶች ለይቷል።

በሌላ በኩል ግን በሕግ አወጣጥ ሂደት ውስጥ የሚደረገው የሶስት ደረጃ የምርመራና የንባብ ሂደት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር የማጣራት ሚና፣ የሕግ ማዕከልና አማካሪዎች መኖር እንደ አዎንታዊ ጎኖች ተጠቅሰዋል።

ከሌሎች ሀገራት የተወሰደ ተሞክሮ ስናነሳ ጥናቱ ከቦትስዋና፣ ጋናና ደቡብ አፍሪካ የሕግ አወጣጥ ተሞክሮ በመነሳት የሕግ ሥርዓት መረጋጋት በተለያዩ ተቋማዊ መሠረቶች ላይ እንደሚመሠረት ለይቷል።

ከእነዚህም የሕገ መንግሥት የበላይነት፣ ውጤታማ የሥልጣን ክፍፍልና ሚዛን፣ ጠንካራ የፓርላማ ኮሚቴ ሥርዓት፣ በሙያ የታገዘ የሕግ ረቂቅ ዝግጅት፣ ትርጉም ያለው የሕዝብ ተሳትፎና ገለልተኛ የዳኝነት ቁጥጥር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የጥናቱ ምክረ ሀሳብ

ጥናቱ የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱን ለማረጋጋት ሁሉን አቀፍ የሕግ አወጣጥ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ መክሯል። በተጨማሪም የሕግ ረቂቅ ዝግጅት ሙያዊ አቅምን ማሳደግ፣ የፓርላማ ኮሚቴዎችን ማጠናከርና የሕዝብ ተሳትፎን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክቷል።

እንዲሁም ከአዋጆች ጋር የሚጣረሱ ደንቦችና መመሪያዎች እንዳይወጡ የተጠናከረ የክትትል ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ የሕገ መንግሥት ተጣጣሚነት ግምገማን እንዲጠናከርና በዩኒቨርሲቲዎች የሕግ ረቂቅ አዘገጃጀት ሥልጠናና ትምህርት እንዲጎለብት ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት በቁጥር ብዙ ሕጎችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሚወጡት ሕጎች ጥራት፣ ግልጽነት፣ ወጥነትና ተገማችነት እንዲኖራቸው ማድረግ ዋናው ጉዳይ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።

ሕጎች በችኮላ ከመዘጋጀት ይልቅ በቂ ጥናት፣ የባለሙያ ግምገማ፣ የሕዝብ ምክክርና የተቋማት ቅንጅት እንዲያልፉ ማድረግ የሕግ ሥርዓቱን ለማረጋጋት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል። ይህ በተግባር ከተረጋገጠ ዜጎች ስለመብትና ግዴታቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ባለሀብቶችም በተረጋጋ የሕግ ማዕቀፍ ላይ የረጅም ጊዜ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related