በመረጃ መበለጥ አገርንም ህዝብንም ዋጋ ያስከፍላል፤ መንግስት ሆይ የኮሙኒኬሽን መዋቅርህን ፈትሽ! አስተካክል፣ አርቅ፣ ካልሆነም እርምጃ ውሰድ!!

Date:

በአርሲ የተፈጸመው “የሽብር ወንጀል ነው” የሽብር ወንጀልን በስሙ መጥራትና ዓለም እንዲያወግዘው መሰራት አለበት። ዛሬ ጥግ የተጀመረ ሽብር ነገ መካከል ይመጣል። ሽብር በባህሪው የሚመከተው በህዝብ ነውና አንድ ዐይነት አቋም እንዲያዝን የመንግስት የኮሙኒኬሽን መዋቅር ከንቅልፉ ሊነቃ ይገባል። ዘወትር የአምቡላንስ ስራ ከመጠመድ መውጣት አለበት። በአርሲው የሽብር ወንጀል ሕዝብ አዝኗል። ተናዷል። ተቆጭቷል። ከምንም በላይ ሃሰተኛ መረጃዎች ያደረሱት ጫና በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ መንግስት መዋቅሩን ነገ ዛሬ ሳይል ይመርመር!! ያጽዳ፣ ያፍርስ …

አዲስ ሪፖርተር ዜና አዲስ አበባ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት መንግስት በተለያዩ ተቋማት ላይ ያከናወነው ስር ነቀል ለውጥ የሚታይና የሚጨበጥ ስለ መሆኑ አያነጋግርም። ጥያቄው ግን በርካታ የሚመሰገኑ ለውጦችን ያካሄደ መንግስት “ምነው በኮሙኒኬሽን ዘርፉ ዙሪያ አልቀና አለው?” የሚል ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ ብልጽግና በኮሙኒኬሽን ስራ ላይ ልፍስፍስ ነው። ይህን ስንል በሚጨበጥ ማስረጃ ነው። የኮሙኒኬሽን ህጸጽ አለ ስንል ራሱን የኮሙኒኬሽን ዘርፉንና መዋቅሩን ታዝበን ነው።

የኮሙኒኬሽን ዘርፉን ባለስልጣናት ጨምሮ ስንት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው በሚታወቁ የማህበራዊ ሚዲያዎች በሚመሩት አገር ላይ የህዝብ ግንኙነት ሆነው እየሰሩ ያሉት? ስንቶቹስ ቢያንስ ራሳቸው ስለሚመሩት ተቋም በየማለዳው ራሳቸው ወይም በስራቸው ያሉ የኮሙኒኬሽን ሰራተኞች መረጃ እንዲሰጡ ያደርጋሉ? መልሱን ለራሳቸውና እንዲህ እንዲሆኑ ለፈቀደላቸው መዋቅር ወይም መንግስት እንተወዋለን።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስቴት ሴክሬተሪ አለው። ነገር ግን እንደሌሎች አገራት (ለምሳሌ እንደ አሜሪካ) በጠዋት ከአገሪቱ ሚዲያዎች ጋር በመገናኘት መረጃ ለህዝብ ያቀብላል? ለዚህም መልሱን ለራሱ ለጽህፈት ቤቱ፣ ለተሿሚዎቹና ከምንም በላይ ለህዝብ እንተወዋለን።

ወደ ዋናው የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት እናምራ። ተቋሙ ከፍተኛ በጀት ተበጅቶለት፣ ትልቅ ህንጻ ተሰጥቶት፣ ባለስልጣናት ተመድበውለት፣ ኤክስፐርቶችና በየደረጃው የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ተመድበውለት በአዋጅ የተቋቋመና ስራው በውል የሚታወቅ ነው። “ህዝብና መንግስትን በመረጃ ማገናኘት፣ ህዝብን ከስህተት መረጃ መጠበቅ” ቁልፍ ተግባሩ ነው። እዚህ ላይ ምንም ብዥታ የለም።

የአንድ አገር ኮሙኒኬሽን (በተለይም የመንግስት ኮሙኒኬሽን) ዋና እና መሰረታዊ ተግባር በመንግስትና በህዝብ መካከል ግልጽ፣ ተደራሽ እና እውነተኛ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ ነው ካልን፣ ተቋሙን በሴሚናር ብዛት፣ ሪባን በመቁረጥና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ብቻ አንገመግመውም። ምክንያቱም ስብሰባ፣ ሴሚናር ወይም የምርቃት ስነ-ስርዓቶች ተቀጽላ እንጂ ዋናው የተቋሙ ምሰሶ አይደሉምና!

የኮሙኒኬሽን ተቋማት በየትኛውም ደረጃ የተቋቋሙበትን ግብ ለማሳካት የሚያከናውኗቸው መሰረታዊ ተግባራት ዓለም አቀፋዊ ናቸው። መረጃ ማድረስ (Inform ማድረግ)፣ የመንግስትን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎች እና የዕለት ተዕለት ውሳኔዎችን ለህዝብ በግልጽ ማብራራት እና ማሳወቅ የተቋሙ ግዴታ ከሆነ፣ በዚህ አግባብ “የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትና መሪዎቹ ከወዴት ናችሁ?” ብለን ስንጠይቅ መልሱ “እንጃ” ነው።

በአገራዊ ጥቅሞች፣ ልማቶች እና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ወጥ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረውና የጋራ አቋም እንዲይዝ ከመስራት አንጻር፤ የአገሪቱን መልካም ገጽታ፣ ባህል፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም አማራጮችን ለውጭው ዓለም ማስተዋወቅ (የህዝብ ዲፕሎማሲ)፤ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን (Crisis Management) በአስቸኳይ ጊዜያት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም በአገራዊ የጸጥታ ስጋቶች ወቅት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት በማሰራጨት ውዥንብርን እና የሐሰት ወሬዎችን መከላከል፤ ህዝብን ከማረጋጋት አንጻር፤ የህዝብን ስሜት፣ ፍላጎት፣ ቅሬታና አስተያየት በማዳመጥና በመተንተን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች ከማድረስ አኳያ (ባለሁለት አቅጣጫ ግንኙነት መፍጠር) የአንድ አገር ኮሙኒኬሽን መሰረታዊ ተግባር ነው።

ይህም በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር፣ የመንግስትን ተጠያቂነትና ግልጽነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም የአገርን ገጽታና ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ከመሆኑ ጋር አዛምደን የአገራችንን የኮሙኒኬሽን መዋቅር ስንፈትሽ የሚሰጠው ውጤት የትምህርት ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጉትን የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ አይነት ውጤት ነው። ካላሽሞነሞንደው ማለታችን ነው!

በኮሙኒኬሽን አገልግሎት የደከሙ እና ህዝባቸውን በተሟላ፣ እውነተኛና ወቅታዊ መረጃ ማስታጠቅ ያልቻሉ አገራት በረጅምም ሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለከፍተኛ ቀውስ ይጋለጣሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት በኮሙኒኬሽን ስራ የተፋዘዙ ወይም የወደቁ አገራት አምስት ዋና ዋና አደጋዎች ያጋጥሟቸዋል፦

  • የሐሰት ወሬና የፕሮፓጋንዳ መጫወቻ መሆን፦ መንግስት ክፍተቱን በወቅታዊ መረጃ ካልሞላው፣ ያንን ክፍተት የውጭ ኃይሎች፣ አክራሪ ቡድኖች እና የሐሰት ወሬ አናፋሾች (Misinformation/Disinformation) ይቆጣጠሩታል። ይህም ህዝቡ በቀላሉ እንዲታለልና እንዲደናገጥ ያደርጋል።
  • የመንግስትና የህዝብ መተማመን መሸርሸር፦ ግልጽነት በሌለበት አገር ውስጥ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለው መተማመን ይጠፋል። ህዝቡ የመንግስትን ፖሊሲዎችና መግለጫዎች መጠራጠር ይጀምራል፤ ይህም የጋራ ብሄራዊ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም አስቸጋሪ ያደርገዋል።
  • የውስጥ አለመረጋጋትና የገጽታ መበላሸት፦ መረጃን በአግባቡ አለመያዝ በቀውስና በአስቸኳይ ጊዜያት (ለምሳሌ በግጭቶች ወይም በኢኮኖሚ ቀውሶች) ውስጥ ህዝብን ማረጋጋት እንዳይቻል ያደርጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የአገሪቱ ገጽታ እየቆሸሸ ስለሚሄድ ዲፕሎማሲውና ኢንቨስትመንቱ ይጎዳል።
  • የዜጎች በራስ መተማመን ማጣትና መገለል፦ ህዝቡ ስለ አገሩ እውነተኛና በቂ መረጃ ከሌለው የተሸናፊነት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይወርሰዋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የመረጃ ፍጥነት መከተል ስለማይችል ዜጎች በዲጂታልና በዕውቀት መድረክ ወደ ኋላ ይቀራሉ።
  • የመሪነትና የሉዓላዊነት ስጋት፦ ኮሙኒኬሽን የሉዓላዊነት መገለጫ አንዱ አካል ነው። የራሷን ትረካ (Narrative) መቅረጽ ያቃታት አገር፣ የሌሎች አገራትና የሚዲያ ተቋማት የትርክት ሰለባ ትሆናለች። ይህ ደግሞ ብሄራዊ ጥቅምን አሳልፎ ለመስጠት ይዳርጋል።

በጥቅሉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ደካማ የሆነች አገር ውስጧ በጥርጣሬና በትርምስ የሚታመስ፣ ውጭዋ ደግሞ በሌሎች የተሳሳተ ትረካ የሚናጥ ይሆናል። ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ምን ያህሉ እኛን እንደ አገር አይመለከተንም የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ በሰሞኑ በአርሲ የተፈጸመውን በንጹሃን ላይ ያነጣጠረ “የሽብር ጥቃት” በስሙ ካለመጥራት ጀምሮ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቀዳሚው ተጠያቂ ተቋም እንደሆነ አምኖ መቀበል የሚበጅ ይሆናል።

ሶስት ሰዎች ብቻ እንደሞቱ፣ የሞቱት በስም የሚታወቁ ሁለት ክርስቲያኖችና አንድ ከብት እያገደ የነበረ ሙስሊም መሆኑን፣ ሚሊሻና የክልሉ ጸረ-ሽምቅ ኃይሎች ዋጋ መክፈላቸውን ወዘተ የመሳሰሉትን መረጃዎች ባለው መዋቅር አሰባስቦ ለህዝብ ቢቻል ቀድሞ፣ ካልሆነም ሳይዘገይ ማሳወቅ ሲገባው ይህን አላደረገም። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በክልሉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለነገ የማይባል ጥፋት ነው።

ግንቦት 23 የተፈጸመውን “የሽብር ጥቃት” ገልብጠው መንግስት እንደፈጸመው፣ መንግስት የድርጊቱ ተጠያቂ እንደሆነ፣ መንግስት ህዝብን መጠበቅ አለመቻሉን፣ “መንግስት የኦርቶዶክስ እምነትን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል፤ ለማተብህ ተነስ፣ ቤተክርስቲያንህን ታደግ፣ ወገኖችህ ደማቸው ፈሷል፣ ሰራዊት ገንባ፣ ተደራጅ፣ ታጠቅ…” ወዘተ ተብሎ በተጋነነ መረጃ ህዝብ ሲናጥ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን መዋቅር ለቀናት ተኝቶ ነበር።

አንዳንድ ሚዲያዎች ስልክ ደውለው ሊያናግሯቸው የሞከሩ ባለስልጣናት “መረጃ የለንም” በማለት ህዝብን ያስቆጣ ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል። ይህ አስነዋሪ ምላሽ የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ ደካማነት ወይም ግዴለሽነት፣ አለያም ሌላ እነሱ ራሳቸው የሚያውቁት ጉዳይ ከመሆን አይዘልም።

ዛሬ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት አገራቸውን እንዲታደጉና ከሐሰተኛ መረጃ እንዲከላከሉ ማብቃት የዘመናችን ትልቁና የመጨረሻው የመረጃና የኮሙኒኬሽን ጥበብ (Modern Strategic Communication) ነው።

በአሁኑ የዲጂታል ዘመን ኮሙኒኬሽን ከመንግስት ወደ ህዝብ የሚፈስ ባለአንድ አቅጣጫ (Top-down) መዋቅር መሆኑ አብቅቶለታል። ስማርት ስልክና የኢንተርኔት ግንኙነት ያለው እያንዳንዱ ዜጋ ራሱ የዜና ምንጭ፣ አሰራጭና ተጠቃሚ በሆነበት ዓለም ውስጥ፣ የመረጃ ጦርነትን የመከላከያ ግንብ መገንባት የሚቻለው በራሱ በዜጋው ልብና አእምሮ ውስጥ ብቻ ነው። ከዚህ አንጻር የአገራችን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማለዳ እየተነሳ ምን ያህል ዜጎቹን ትክክለኛ መረጃ ያስታጥቃል የሚለው ሲመዘን “ምን ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” የሚለውን ተረት ከማስታወስ ውጭ ሌላ መልስ የለንም።

  • የህዝብ ብረት-ለበስ መከላከያ (Civic Immunity)፦ ዜጎች መረጃን የመመራመር፣ እውነታን የማጣራት (Fact-checking) እና የሐሰተኛ መረጃን (Disinformation) አጀንዳ የመረዳት ክህሎት ሲኖራቸው፣ አገሪቱ ከማንኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ የፕሮፓጋንዳ ጥቃት የሚከላከል የማይበገር የዜጎች ጋሻ ታገኛለች።
  • የትረካ ባለቤትነት (Ownership of Narrative)፦ አገርን ለመታደግ በራሱ ተነሳሽነት የሚንቀሳቀስ ዜጋ፣ የአገሩን መልካም ገጽታ ለመገንባትና እውነቱን ለዓለም ለማሳወቅ የመንግስትን መግለጫ አይጠብቅም። እያንዳንዱ ዜጋ የአገሩ ዲፕሎማትና ተሟጋች ይሆናል።
  • በመንግስትና በህዝብ መካከል አጋርነት መፍጠር፦ ኮሙኒኬሽን የጥቂት ባለስልጣናት ስራ መሆኑ ቀርቶ የጋራ አገራዊ ኃላፊነት ይሆናል። ይህም ህዝቡ በችግር ጊዜ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እንዲቆም ያደርገዋል።
  • የቴክኖሎጂን አደጋ በሰውኛ ጥበብ መመከት፦ በአሁኑ የኤአይ (AI) እና የዲፕፌክ (Deepfake) ዘመን ቴክኖሎጂን በቴክኖሎጂ ብቻ መከላከል አይቻልም። ትልቁ መፍትሔ የዜጎችን ንቃተ-ህሊና ማሳደግ እና “የሚዲያና መረጃ እውቀትን” (Media and Information Literacy) ማጎልበት ነው።

ሲጠቃለል የድሮው የኮሙኒኬሽን ጥበብ ህዝብን “እንዲሰማ ማሳመን” ነበር፤ የዘመኑ የኮሙኒኬሽን ጥበብ ግን ህዝብን “አስብና አገርህን ጠብቅ” ብሎ ማስታጠቅና ማብቃት ነው። ይህ ካልተደረገ ግንባር ላይ በዘመናዊ መሳርያ የሚደረገውን ውጊያ ማሸነፍ ቢቻል እንኳ፣ በሀሰተኛ መረጃ የሚደረገውን የልብና የአእምሮ ውጊያ (Information Warfare) መቋቋም አይቻልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚሳተፉባቸው አንዳንድ ጅምሮች ቢኖሩም፣ እንደ ክብረ በዓል ዛሬ ተደርገው ነገ የሚተው፣ ወጥነት የሌላቸው እንደሆኑ ይስተዋላል። ተወደደም ተጠላም የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ተወርዋሪ፣ ትጉ፣ የሚያስብ፣ አልፎ የሚፈነጥር፣ የመፍጠር አቅም ያለው፣ በመረጃ የሚቀድም፣ መረጃን በረጃነቱ ወይም በዜናነቱ ሳያበቃ ወቅታዊ አድርጎ ለሕዝብ የሚያደርሱ ባለሙያዎችና መሪዎች ሊኖሩት ይገባል።

አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች በሚገርም ሁኔታ ከሚያከናውኑት ያልተቆጠበ አገርን ከሃሰተኛ መረጃ የመከላከል አኩሪ ተግባር በተሻገረ መልኩ፣ የመንግሥት ሰክሬታሪ፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በተለይም የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ በየማለዳው ህዝብን መረጃ በማስታጠቅ፣ አጀንዳ በመትከል፣ ስራቸውን እለት እለት ያለመታከት ሊሰሩ ይገባል። ካልቻሉም “አልቻልንም” በማለት ጥሩ ምሳሌ ሆነው ራስን ማግለል ይሻላል።

በሃሰት መረጃና አይናቸውን በጨው ባጠቡ የሽብር ጫጩቶች አጀንዳ ህዝብ ሲደናገር፣ ሲሰቃይ፣ ሲጨነቅና ተስፋ ሲያጣ እውነተኛ መረጃ ታቅፎ ዝም ማለት በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም። በዚህ ዘመን ሊደበቅ የሚችል አንድም ጉዳይ ስለሌለ፣ ተሽቀዳድሞ እውነቱን ይፋ በማድረግ ሃሰተኛ መረጃዎችንና የሰበር ዜና ጋጋታን ማስቆም ካልተቻለ መንሸራተት ግድ ይሆናል።

እናም መንግስት ሆይ፤ የኮሙኒኬሽን መዋቅርህን መርምር፤ አጥራ። ካልሆነም አፍርስና እንደ ሌሎች ተቋማት አስደናቂ ሪፎርም አድርግ። አለበለዚያ ራስህም አገርም ዋጋ ይከፍላሉ። ዘመኑ የግራጫ ጦርነት (Hybrid Warfare) ነውና በመረጃ መበለጥ አደገኛ እንደሆነ ለካድሬዎችህ አስተምር! እርምጃ ውሰድ!

ይህን ያልነው ብዙ አይተን፣ መርምረን፣ መረጃ ስንጠይቅ “አንተ ማን ነህ? ተገምግመህ ስታልፍ ነው…” ወዘተ የሚሉ ምላሾችን ከዋና ኃላፊዎች ከሰማን በኋላ ነው። በርካታ የሚዲያ አውታሮች መረጃ ይፈልጋሉ፤ ቤቱ ግን ዝግ ነው። ይህ አካሄድ አያስኬድም። ይብቃ! ከአርሲው ቀውስ እንማር!

የአርሲው “የሽብር ጥቃት” ከተፈጸም ሶስትና አራት ቀን በኋላ ከመንግስት የተሰማው መግለጫ፣ የሰላም ሚኒስትር ማብራሪያ፣ የመንግስት ሚዲያዎች በቅብብል ያደረጉት ሁሉ የዘገየ፣ የህዝብ ስሜት በሃሰትና በጦዘ የቅብብሎሽ ዜና ከተጎዳ በኋላ ባይሆን ይመረጥ ነበር። መቶ ሰው ማለቁን ያልሃፍረት የሚናገሩ የሽብር እልቂቱ አመቻቾች በዚያ ደረጃ ህዝቡን ሲፕውዙት የዲጂታል ሚዲያው ያበረከተው አስተዋጾ ሊደነቅና ለመሰገን የሚገባ ነው። ለዚህ ተግባር በግልጽ እውቅና መስጠትና “ስራችንን ሰራችሁልን” በማለት ማሞገስ ይግባል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አንደበት የቆለፈው የትራምፕ መመሪያ ተቃዋሚዎች ተስፋ አስቆርጧል፤ አሜሪካ ስለምርጫው ለምን ዝም አለች?

አሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ የአገሪቱ ዲፕሎማቶች በሌሎች አገራት...