አዲስ ሪፖርተር መቀለ – በትግራይ የተጀመረውም መፈንቀለ መንግስት ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ መሪ የቀድሞው ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ “ጽንፈኛ” በሚባለውና ከሻዕቢያ ጋር በገሃድ ጥምረት የመሰረተው ቡድን አካል እንደሆኑ በሚነገርላቸው በአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም ቤት እንዲያርፉ መደረጉ ታወቀ። የታደሰ ወረደ ፍስሃ አስገዶም ቤት መቀመጥ በርካቶችን አስገርሟል። መፈንቀለ መንግስት ለርማድረግ የሞከሩትና የክልሉን መሪ ቢሮ የተቆጣጠሩት ታጣቂዎች አካል የሆኑ ድምጸ ወያኔ የሚባለውን የሬዲዮና ቴሌቪዝን ማሰራጫ መቆጣጠራቸውም ተረጋግጧል።
በመቀለ እየሆነ ያለውን በመከታተል ሪፖርት የሚያደርገው የትግራይ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ እንዳለው ከሆነ የትግራይ ጊዜያዊ መሪ ታደሰ ወረደ ይህ እስከተዘገበ ድረስ የሚያስጋቸው ነገር አልገጠማቸውም። ይሁን እንጂ አሜሪካ ሆነው የ”ጽንፈኛ” ኃይሉን ሲመሩና ሲያስተባበሩ ከነበሩት አቶ ፍስሃ አስገዶም መኖሪያ ቤት እንዲቀመጡ የተደረገበት አግባብ ግልጽ አይድለም።
78 የሚጠጉ የአንድ ኮር አባላት የክልሉን አስተዳደር ቢሮ የወረሩና የተቆጣጠሩት የ”ጽንፈኛው” ትህነግ አንድ ክፋይ ታጣቂዎቾ የድምጸ ወያኔን ቢሮ መያዛቸውና ሰራተኞቹን በሙሉ ማባረራቸውን ተባባሪያችን የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ አመልክቷል። ማን እንዳደረገው ባይታወቅም ይህ እስከታተመ ድረስ ድምጸ ወያኔ ከሳተላይት እንዲወርድ ወይም አገልግሎቱ እንዲስተጓጎል ሆኗል።
ታደሰ ወረደ ስልጣን ከያዙ በሁዋላ የሾሟቸው የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽነር ገብረ ዴላ የአስራ ሶስት አርሚ አዛዦችን በጽህፈት ቤታቸው ሰብስበው በተፈጠረው መፈንቅለ መንግስት መሰል ድራማ ዙሪያ እያወያዩ መሆኑ ታውቋል። ይህ እስከታተመ ድረስ የስብሰባው ውጤት አልታወቀም። የክልሉም መንግስት በገሃድ ያለው ነገር የለም።
የአርሚ አዛዦቹ ስብሰባ ውጤት ለጊዜው ባይታወቅም የአዲስ ሪፖርተር ታማኝ የዜና አቀባዮች እንዳሉት ከሆነ ታደሰ ወረደን የሚደግፉት ተበራክተዋል። በዚሁም ምክንያት ታደሰ ወረደ በአሸናፊነት እንደሚወጡ አመልክተዋል። ይህን ያሉት ወገኖች ታደሰ ወረደ በአቶ ፍስሃ አስገዶም መኖሪያ ቤት እንዲያርፉ መደረጉን አስመልክቶ “ግራ ገብቶናል” ሲሉ ተሰምተዋል። ምክንያቱም ፍስሃ አስገዶም በትግራይ ጦርነት ወቅት ግንባር ቀደም ሆነው የውጩን ግንኙነት ሲመሩ የነበሩ፣ በድብቅ በተደረገውና የመንግስት ደህንነት ይፋ ባደርገው የመንግስት ለውጥ እነ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅና የሚታወቁ ነጮች በተሳተፉበት የመንግስት ግልበጣ ምክክር ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ የነበሩና ከሻዕቢያ ጋር የተጀመረውን ግንኙነት ውጭ አገር ሆነው ያሳለጡ ቁልፍ ሰው መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በፌደራል መንግስት የአውሮፓና አሜሪካ ታዛቢዎች ባሉበት፣ በዝርዝር የሚያከናውኗቸውን ጉዳዮች ወደውና ፈቅደው ለመተግበር ቃል ገብተው ትግራይን እንዲመሩ የተሾሙት ታደሰ ወረደ፣ ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለባት በግልጽ ከሚናገሩት መካከል መሆናቸውን በርካታ የቪዲዮ ማስረጃዎች በሚቀርብባቸው ፍሰሃ አስገዶም መኖሪያ ቤት ለጊዜውም ቢሆን “በግዞት” መቀመጣቸው የትግራይን ፖለቲካና የፖለቲከኞቹን አሰላለፍ ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለሚናገሩ አላስገረመም።
የጽዮን ማርያም ዓመታዊ ንግስ በዓል ከመከናወኑ አንድ ቀን በፊት ድምጸ ወያኔ በግፍ በሻዕቢያ የተጨፈጨፉ የትግራይ አክሱም ተወላጆች መታሰቢያ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት መካሄዱን፣ መታሰቢያውም በየዓመቱ እንደሚደረግ ዘግቦ ነበር። ይህ ዘገባ ከሻዕቢያ ጋር የተፈጠረውን አዲስ ወዳጅነት “ጽምዶ” እንደሚጎዳው የተበሳጩ የኤርትራ መንግስት ደጋፊዎች ሲወቅሱ ነበር።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






