ናሬንድራ ሞዲ በፓርላማ ንግግር አደረጉ፤ ህንዳዊያ ከ5ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርገዋል፤ ግንኙነቱ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል
የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሩ የየሁለቱን አገራት ትስስር ማስፋትና ማጠናከር የሚያስችል እርምጃ መሆኑን የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መናገራቸውን በስፍራው ተገኝተው ከዘገቡ የመንግስት ሚዲያዎች ለመረዳት ተችሏል።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ አስቀድሞ መዘገቡ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት ዛሬ ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህንድ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አንስተዋል።
የሀገራቱ የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረው ህንድ ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጣችበት ማግስት እንደሆነም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ህንድ በባህል እና በትምህርት ያላቸው ትብብር የህዝብ ለህዝብ ቁርኝታቸው ይበልጥ እንዲጠብቅ ማድረጉን ነው የገለጹት።
የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በግብርና፣ ጨርቃጨርቅ እና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
ኩባንያዎቹ ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠራቸውንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።
ሀገራቱ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች እንዳሉም ነው ያነሱት።
ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምዕራፍ ለማሸጋገር መወሰኗን ገልጸው ይህም ኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ማዕድን፣ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ኢኖቬሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል። የሁለቱን ህዝቦች በምግብ ዋስትና፣ በጤና እና አቅም ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግብርና፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እርስ በእርስ በመማማር የጋራ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል።
ህንድ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ህንድን ታማኝ አጋር በማድረጓ አመስግነው ሀገራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር አበክራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጋራ ስብሰባው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለቱ ሀገራት የትስስር ታሪክ እንዳላቸው አውስተው፤ አሁን ያለውን ግንኙነት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ማሳደግ እንደሚገባ በቆራጥነት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና ሕንድ መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በንግድ እና በሌሎች ወሳኝ ዘርፎች የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤው አጽንኦት ሰጥተው እንዳነሱት፣ በመንግሥታት መካከል ያለው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአስቸኳይ ወደ ሁለቱ ሀገራት የላቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና አጋርነት ማደግ አለበት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንን ዘመን ተሻጋሪ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን አፈ ጉባኤ ታገሰ በንግግራቸው አመልክተዋል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






