የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቡድንና ስርዓት በለቀቀ የብድር አሰጣጥ ተሽመድምዶ ከመውደቅ ተርፎ፣ ራሱን በለውጥ አርቆ ስህተቱን እያረመ በመጓዝ ላይ ቢገኝም፣ የቀድሞው ምድበተኞች አሻራና ኮቴ አሁንም ድረስ አልጸዳም። ይህ ሃቅ ለውጭ አካላት ባይገባም እዛው እውስጡ ያለን የጎሪጥ የምንተያይ እንረዳዋለን። ይህንን ስል አሁን ላይ ባንኩ ውስጥ እጸጽ የለም ለማለት ሳይሆን ሆን ብለው ሊሰብሩት ሞክርተው ያልተሳካላቸው ገዝጋዞች እንዳሉ ለማሳየት ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍርስራሽ ላይ የራሳቸውን ባንዲራ ለመትከል አሲረው የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገው ስለተገለበጡ ህልመኞች ለመጠቆም ነው። እነዚህ ህልመኞች ታዲያ በከሸፈባቸው ህልማቸው ላይ ሆነው የቻሉትን ሁሉ ቢቆፍሩ፣ በርቀት ሆነው ኢትዮጵያን እየገዘገዙ መሃል ከተማ ድርጅቶቻቸው ከሚያመርቱት የሚታወቅ ሃብታቸው ቢረጩ ምን ይላቸዋል። የሚቆረቁረን ዜጎች ካለን “መንግስት ሆይ ምን እያደረክ ነው” ማለት እዚህ ላይ ነበር።
አዲስ ሪፖርተር – በኢትዮጵያ ላይ አዲስ ተከፈተ የተባለው ዘመቻ ዕቅድ በሰላማዊ ትግል ህዝብን ማሳመጽ የሚለውና የ“ግራጫ ጦርነት” ስልትን መከተል እንደሆነ በተለያዩ አውዶች ተሰምቷል። ስልቱን በስም አይጥሩት እንጂ የኢትዮጵያን ዋንኛ ተቋማትና ቁልፍ አመራሮችን፣ የቁልፍ አመራሮች ደጋፊ የሆኑ ትጉ የሚባሉ ኃላፊዎችንና አስፈጻሚዎችን በጅምላ ማጠልሸት፣ ማሸማቀቅ፣የስልቱ መተግበሪያ ዋናውን ካርድ እየተጫወቱበት ነው።
በተለያዩ አውዶችና በመከረኛዋ ኢትዮጵያ ስም በተቋቋሙ ንቅናቄዎች፣ ህብረቶች፣ ቅንጅቶች ወዘተ ከጠብ መንጃው ጎን ለጎን በተጀመረው የኢትዮጵያን ተቋማት የማጠልሸት ዘመቻ የዚሁ የግራጫው ጦርነት አካል ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
አሁን አሁን ለየት ባለ ዘመቻ የተጀመረው ይህ የሳይበር ጦርነት፣ “መሪ ዕቅድ” የመንግስት ቁልፍ ተቋማትና ተቋማቱን የሚመሩ ትጉሃንን ማጥቆር ነው። ይህ የተቀነባበረና ባለቤት ያለው ዘመቻ የሚካሄደው ከወስጥ በተሰገሰጉ የቢሮ ውስጥ “ሽፍቶች” የዚሁ ዘመቻ ተባባሪ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ“ የሚሉ የቀበሮ ለምድ ለባሾች፣ ሲሆን በዋናናት አኩራፊዎች፣ የጎደለባቸውና የተሸጡ የሚመሩት ነው።
ያደጉት አገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር እንደሚያደርጉት የ“ግራጫ ጦርነት” (Gray Zone Warfare)ዓይነት ይዘት ያለው ዘመቻ በዋናነት ለሃገር ብሄራዊ ደህንነት እና ልማት ቁልፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ፣ የአገር መከላከያ ላይ፣ የሳይበር ጥቃት ሲፈጸም ይታያል። ይህ ሆን ተብሎ በመናበብና፣ በመቀናጀት የሚሰራው ተቋሞችን አቆሽሾ የማስለል ተግባር ገና ተጀመረ እንጂ ብዙ አልተኬደበትም። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያ የሚነዳቸው ዜጎች በበዙበት አገር ይህን ዘመቻ ሳይውል ሳያድር መቀንደብ አስፈላጊ ይመስለኛል።
አሁን ባለንበት የሃያላን ሃገራት የፉክክር ዘመን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች በየጊዜው እየተፈጠሩ ይገኛሉ። በዚህ ወቅት፣ ሃገራት በሌላ ሃገር ላይ ያላቸው ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ውዴታ ላይ የተመሰረተ የንግድ፣ የፋይናንስ የኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ማባበያ በመስጠት (Accommodation) ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በሃይል የማስገደድ (coercion) ተግባራትን ይፈፅማሉ። እንግዲህ እንደ አቅሚቲ ኢትዮጵያ ላይ የተጀመረው ይህ አካሄድ ነው።
አዲስ ሪፖርተር ከዚህ ቀደም የ“ግራጫ ጦርነት” (Gray Zone Warfare) ዘመቻ ጥቃት የሆኑ ሁለት የኢትዮጵያ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ ዘመቻው ቀጣይነት እንዳለውና በብሄራዊ ባንክ፣ በንግድ ባንክ፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በአገር መከላከያ፣ አገሪቱን ሊያሻግሩ ይችላሉ በሚባሉ ተቋማት ላይ፣ ከዚያም አልፎ ቁልፍ በሆኑ አመራሮች ላይ ያተኮረ ዘመቻ እንደሚከፈት ማሳሰቡን ማስታወስ እወዳለሁ።
የዘመቻው መሐንዲሶች “ሀሰተኛ መረጃ አምርቶ በማሰራጨት፣ ታዋቂ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ግድያ በማቀነባበር እና ሌሎች መሰል ጥቃቶችን በመፈፀም በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን መተማመን በመሸርሸር፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተማኝነት በማሳጣት፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሽባ በማድረግ፣ ሕዝብ ለህዝብ እንዲጠራጠር ወዘተረፈ በማድረግ በሂደት ሃገርና መንግስትን በማዳከም ስትራቴጂክ ግባቸውን ያሳካሉ።” ሲል ነበር አዲስ ሪፖርተር መረጃ እንደደረሰው ጠቅሶ ያሳሰበው።
የኢትዮጵያ የደም ስሯ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በማቆሸሽ፣ የግለሰብና የፓርቲ ተቋምም በማድረግ የዘመነ ወይኔን የጸጸት ጊዜ ያስታወሱን እነዚህ ቡድኖች ሰሞኑን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ከውስጥና ከውጭ ተናበው ዘመቻ ከፍተዋል። እዚህ ላይ ችግር ካለ መጠቆም የለባቸውም ለማለት ሳይሆን፣የምቃወመው መረጃቸውን እንደ ዓይነቱ ለይተው፣ እንደ አስፈላጊነቱ ቋንቋ እየለዩ መርጨታቸውን ነው። ወደፊት ቃል በቃል ስም እየጠቀስኩና የመረጃ ምንጮቻቸውን እየለየሁ እመለስበታለሁ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ለሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ቁልፍ ሚና እየተጫዎቱ የሚገኙ በመንግስት እና በግል አጋርነት ስምምነት መሰረት ለግል የተሰጡ ወይም በጋራ የሚተዳደሩ ስትራቴጂክ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዚህ ግራጫ ጦርነት ጥቃት ሲፈፀምባቸው ተስተውሏል። አባይ ግድብ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የድፍድፍ ዘይት ማጣሪያ፣ የቱሪዝም መዳረሻ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ወዘተ ይጠቀሳሉ። የዛሬውን ተረኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስላለሁበት ላስቀድም።
በኢትዮጵያ የልማት ደርጅቶችና እንዲፈርሱ የዘመቻ ማቆሸሽ ቅባት ለመቀባት ከተሰለፉት የመንግስት ተቋማትና አገልግልት ሰጪ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የፋይናንስ ሴክተሮች ገቢ የሚተዳደሩት ከመሃል፣ ከውጭ ደግሞ የትጥቅ ትግልን ጀምረው ሲነቃባቸው ባፈገፈጉና የኢትዮጵያን የፋይናንስ ተቋማት ተደራጅተው ባጠቡ ግለሰቦች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መደበኛ ጠላቶች በሚጥሉላቸው ትራፊ ተደራጅተው በቅብብሎሽ ባንኩን እየወቀጡት ነው። የሌብነቱንና መስመር የቀረቀሩትን ኃላፊዎች እያጠልሹና ለማሸማቀቅ እየተውተረተሩ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባ ከመቶ የሚጠጋውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተሸከመ ተቋም ፣ እንደመሆኑ መጠን ይህን ተቋም ለመጉዳት የተጀመረው ዘመቻ ከላይ የጠቀስኩት የግራጫው ጦርነት አካል በመሆኑ ከወዲሁ በንቃት እንድንከላከል ማሳሰብ ፈልጌ እንደ ዜጋ ያዘጋጀሁት ማሳሰቢያዬ ያገባኛል ሚሉ አካላት ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቡድንና ስርዓት በለቀቀ የብድር አሰጣጥ ተሽመድምዶ ከመውደቅ ተርፎ፣ ራሱን በለውጥ አርቆ ስህተቱን እያረመ በመጓዝ ላይ ቢገኝም፣ የቀድሞው ምድበተኞች አሻራና ኮቴ አሁንም ድረስ አልጸዳም። ይህ ሃቅ ለውጭ አካላት ባይገባም እዛው እውስጡ ያለን የጎሪጥ የምንተያይ እንረዳዋለን። ይህንን ስል አሁን ላይ ባንኩ ውስጥ እጸጽ የለም ለማለት ሳይሆን ሆን ብለው ሊሰብሩት ሞክርተው ያልተሳካላቸው ገዝጋዞች እንዳሉ ለማሳየት ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍርስራሽ ላይ የራሳቸውን ባንዲራ ለመትከል አሲረው የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገው ስለተገለበጡ ህልመኞች ለመጠቆም ነው። እነዚህ ህልመኞች ታዲያ በከሸፈባቸው ህልማቸው ላይ ሆነው የቻሉትን ሁሉ ቢቆፍሩ፣ በርቀት ሆነው ኢትዮጵያን እየገዘገዙ መሃል ከተማ ድርጅቶቻቸው ከሚያመርቱት የሚታወቅ ሃብታቸው ቢረጩ ምን ይላቸዋል። የሚቆረቁረን ዜጎች ካለን “መንግስት ሆይ ምን እያደረክ ነው” ማለት እዚህ ላይ ነበር።
አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው ዘር ላይ ያተኮረ የንግድ ምልክትና ስያሜ በመያዝ ከተከፈቱት ባንኮች ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለማፍረስ የተጉ እንደነበሩ፣ ዛሬም ድረስ እነዚህ ቡድኖች ፈተና መሆናቸውን እያንዳንዱ የባንኩ ማህበረሰብ፣ እንዲሁም በዚሁ ማዕበል ተጠርገው የተወሰዱት በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞች ያውቁታል። መረጃውን ለመጠቆም ያህል እንጂ የነጻ ገበያው የፈጠረው እድል ስለሆነ ስፍራ መቀየር በዘርም ይሁን በሌላ መብት እንደሆነ አስምሬ ማለፍ ግን እፈልጋለሁ። ችግር የሚሆነው አካሄዱ በሴራና በሌላ ዓላማ መሆኑ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰማኒያ ሚሊዮን ብር ለገዙት ንብረት 140 ሚሊዮን የሚውስዱ ጋንጊስተር ባለሃብቶች መኖራቸውን የተጠየቀውን ስትፈቅዱ የነበራችሁ የሙስና ተሰላፊዎች ታውቁታላችሁ። ሰማኒያና መቶ አርባ ለምሳሌ ቀረቡ እንጂ ብዙ ከላይ አናቱ ላይ እንደ ጊንጥ ተጣበቅ የሙስና ድራማ ስንኮሞኩም ነበር። ይህን ሳስብ “ድሮ ቀረ ብድር” የሚለው የአሁን ለቅሶና ሴራ ትርጉም ገኖ ይታየኛል። “የብር እጥረት ለቅሶም” ያስፈግገኛል።
አጋነንክ አትበሉኝ እንጂ የዛኔዎቹ ጋንጊስተር “ባለሃብቶች” ወይም ሌላ ስም አውጡላቸው፣ አለቃ ቢሮ ገብተው ጥቡቋቸውን በመሰብሰብ በቡጢ ጠርጴዛ በመደብደብ “የጠየኩትን አታጽድቅና ከዚህች ወንበር ትነቀላለህ” በማለት ያስፈራሩ እንደነበር ለምናውቅ የዛሬ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ የተደራጀ ዘመቻ የጋንጊስተሮቹ ብስጭት የወለደው ስለመሆኑ መጠራጠር ሞኝነት ብቻ ሳይሆን፣ ድንቁርናም ነው።
ከዓመታት በፊት በከና ያልነበረው ባንካችን፣ 100 ሚሊዮን የሚሞላ ምንዛሬ ወይም ተጠባባቂያ ሃብት ያልነበረው ክዝናችን፣ ዛሬ በሰማነው ደረጃ ላይ መድረሱ ምን አልባትም ዛሬ በዚሁ የሳይበር ዘመቻ የሚቀጠቀጡት አመራሮች ጥረት ስለመሆኑ ለምናውቅ በዘመቻ ማጠልሸት ሲካሄድባቸው ዝም ማለት አይቻልም። እኔም የተነፈስኩት በዚሁ ስሜት ነው።
በቀጣይ ዘርዝር ባሉ መረጃዎችና አሃዞች ላይ በመንተራስ የምለው ይኖራል። ተከራካሪም ካለ በተራ ስም ማጥፋት ሳይሆን እውነት ላይ ተደግፈን፣ በተለይም ባንክ ከቁጥር ጋር በተያያዘ ማብራሪያዎች የሚቀርቡበት በመሆኑ ልሟገት ዝግጁ ነኝ። ባንካችን የሚጎዱና አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅሞች በሚያሳጡ ጉዳዮች ላይ ክፋት ካለ በጋራ ለማረቅ የምሰራ አገር ወዳ መሆኔን አስቀድሜ እገልጻለሁ። በተራ ስም ማጥፋት ሰልፍ ገብታችሁ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ በመናበብ የምትዘምቱትን ደግሞ በግል እታገላለሁ። የሚመለከተው የመንግስት አካልም እውነታውን ያጠራው ዘንዳ እንደ ዜጋ እማጸናለሁ። ይከው ነው!! ይህ ተነቅሎ ያላለቀ ሰንኮፍ ይህ አካሄዱ ከጥፋት መስመሮቹ መካከል አንዱ ሲሆን ነገም እንደ ተስቦ ሌሎች ጋር መሄዱ አይቀርም። እናም ያልተነቀለውን ኮቴውን ከመንቀል አንጻር ብዙ ይጠበቃል።
የንግድ ባንክ ሰራተኛ ነኝ
ዝግጅት ክፍሉ አስተያየቱ የተላከልን በስም እና በአድራሻ ነው። ጽሐፊው ስማቸው እንዳይወጣ በጠየቁት መሰረት አላተምነውም። ይሁንና ምላሽ ያላቸው ማናቸውም ወገኖች በዝግጅት ክፍሉ አድራሻ ቢልኩልን እናስተናግዳለን።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






