ህውሃት የተጠመቀበት ሆጃቪዝም (Hoxhaism) በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በአልባንያው አምባገነን መሪ ኤንቨር ሆጃ (Enver Hoxha) አማካኝነት የተፈጠረና የተስፋፋ አክራሪ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም ነው። ይህ አስተሳሰብ በዋናነት “ብቸኛውና እውነተኛው የኮሙኒዝም መንገድ የስታሊን አስተሳሰብ ብቻ ነው” በሚል እምነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ከሶቪየት ህብረት እስከ ቻይና ያሉትን ሌሎች የኮሙኒስት መንግስታት “ትክክለኛውን ኮሙኒዝም ከድተዋል” በማለት ያገል ነበር። መለስና ስብሃትን ይህንን እምነት ነበር የቀዱት።ወሓቶች በ1978 ዓ.ም “ማርክሲስት ሌኒኒስት ትግራይ (ማሌሊት)” የተሰኘ ምስጢራዊ ድርጅት ሲመሰርቱ፣ ርዕዮተ ዓለማቸውን በቀጥታ የተቀዱት ከአልባንያው ሆጃቪዝም ነበር። ህወሓት በበረሃ የነበረውን የውስጥ ተቃዋሚዎችን የማጥፋት፣ “06” የተሰኘውን ምስጢራዊ እስር ቤት የመገንባት፣ እና በኋላም ስልጣን ከያዘ በኋላ የዘረጋውን የአንድ-ለአምስት የስለላ መዋቅር ከሆጃቪዝም እና ከሲጉሪሚ ተሞክሮ እንደቀሰመው የተለያዩ የታሪክ ድርሳናትና ጥናቶች ያመላክታሉ።
ነጻ አስተያየት በሂርጳሳ አዱኛ
እንደ መግቢያ – ይህንን እንድጽፍ ያስገደደኝ የኦነግ ሰራዊት፣ የፋኖ፣ አስር ባይሞሉክም የኦብነግ እና የተወሰኑ ኃይሎች በሻዕቢያ አደራጅነት፣ በግብጽ በጀት ከህወሃት ጋር የፈጠሩት “ጽምዶ” የተባለ መሰረት የሌለው ጥምረት ነው። ህወሃት በተለይ በኦሮሞና እና በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው መጠነ ሰፊ እና የማይረሳ ግፍ ተረስቶ ዛሬ በኦሮሞ ስም እንታገላለን፣ በኦጋዴን ህዝብ ስም እንሞታለን፣ የአማራን ሕዝብ መከራ እናስቀራለን ለሚሉ ወገኖችና ለራሱ ለህወሃት “አንረሳም” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።
ሲጉሪሚ የሆጃ የአፈና ማሽን፣ የእነ መለስ መሃላ
የ“ሲጉሪሚ” እና የህወሓት የስለላ ተቋማት ሚስጥራዊ ቁርኝት አስገራሚም አስደንጋጭም ነው። ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወይም ህወሓት ብሎ የሚጠራው ቡድን የዘረጋው የአፈና መዋቅር ከ“ሲጉሪሚ (Sigurimi)” ጋር ተመሳሳይ ነው። እንዲያውም ህወሓት ኮሚኒዝምን ከአልባንያ ሲቀዳ አብሮ የወሰደው የወንበርና የፓርቲ ህልውና ማስጠበቂያ ስልቱ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በትጥቅ ትግሉ ዘመን የህወሓት መሪዎች ከአውሮፓ አገራት መካከል የጠበቀ ርዕዮተ-ዓለማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት ከአልባንያው የኤንቨር ሆጃ አገዛዝ ጋር ነበር። ዩጄ ፕሬስ “የትህነግ ማበብና መሞት” በሚል ሰፊ ትንተናው የህወሓት ከፍተኛ መሪዎች በተለይም የስብሃት ነጋ እና የመለስ ዜናዊ ቡድን ለአልባንያው አምባገነን መሪ ለኤንቨር ሆጃ አክራሪ ማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ-ዓለም ከፍተኛ ታማኝነት እንደነበራቸው አመልክቷል።
እንደ አባይ ፀሐዬ ያሉ የድርጅቱ ቁልፍ አመራሮች በምስጢር ወደ አልባንያ በመጓዝ የፖለቲካ ሥልጠና እና የሬዲዮ ቴክኖሎጂ ድጋፎችን አግኝተዋል። ይህ ጉዞ በበረሃ “ማሌሊት” የተባለ አክራሪ ማርክሲስታዊ ፓርቲ እንዲመሰረት በር የከፈተ ሲሆን፣ የአልባንያው ሚስጥራዊ ፖሊስ (ሲጉሪሚ) የዜጎችን መብት ለመጨቆን ይጠቀምበት የነበረው የአፈና ስልት፣ በህወሓት ዘንድ ’06’ የተሰኘውን አስፈሪ ድብቅ እስር ቤት ለመገንባትና የውስጥ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት እንደ ትልቅ አርአያ ሆኖ አገልግሏል።
በአልባንያ የኮሙኒስት አገዛዝ ዘመን እ.ኤ.አ ከ1944 እስከ 1991 ሲጉሪሚ በመባል የሚታወቀው የሀገር ውስጥ ደህንነትና የስለላ መዋቅር፣ ሕዝቡ የመሪያቸውን የኤንቨር ሆጃ (Enver Hoxha) አገዛዝ እንዲቀበል፣ እንዲፈራ እና እንደ አምላክ እንዲያመልክ ያደረገበት መንገድ በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከነበሩት በጣም ጨካኝ እና ሁሉን አቀፍ የስነ-ልቦና ቁጥጥር ስልቶች አንዱና ምን አልባትም ቀዳሚው ሆኖ ተቀምጧል።
ሆጃ ከአውሮፓ መሪዎች ሁሉ እጅግ ታማኝ የስታሊን አስተሳሰብ አራማጅ (“Europe’s Last Stalinist”) ነበሩ። አልባንያን ከአለም ነጥለው የራሳቸውን የጭቆና አገዛዝ የመሰረቱት እኚሁ ሰው፣ ስታሊን በሶቪየት ኅብረት ይጠቀምባቸው የነበሩትን ጨካኝ የፖለቲካ ስልቶች ማለትም ተቃዋሚዎችን መረሸን፣ በሚስጥር ፖሊስ ማሳደድ፣ ሰዎችን ስውር እስር ቤት ውስጥ ማሰቃየትና እስከ መጨረሻው መሰወር የመሳሰሉትን ክፉ ወንጀሎች ፈጽመዋል።
ሲጉሪሚ የእያንዳንዱን ዜጋ የቤተሰብ ታሪክ (የፖለቲካ ታማኝነት) በመዝገብ ይይዝ ነበር። የአንድ ቤተሰብ አባል “የሕዝብ ጠላት” ከተባለ፣ ሙሉ ቤተሰቡ፣ ዘመዶቹ እና ልጆቹ ከዩኒቨርሲቲ ይባረራሉ፤ ከመደበኛ ስራ ይወገዳሉ፤ ወይም ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ተወስደው በግዳጅ እንዲሰሩ ይደረጋል። ይህ አሰራር ሰዎች የራሳቸውን ቤተሰብ አደጋ ላይ ላለመጣል ሲሉ አገዛዙን በግድ እንዲቀበሉ እና እንዲያመልኩ አድርጓቸዋል።
በተመሳሳይ ህወሓት ራሱን ለትግራይ ሕዝብ የተላከ መለኮታዊ ኃይል ያለው አድርጎ ያቀረበ ድርጅት ሲሆን፣ እሱ ከሌለ የትግራይ ሕዝብ እስትንፋስ እንደሚቆም ያሳመነ “ታቦት” ነበር። ህወሓት ይህን አመለካከቱን ሌሎችን በመፈረጅና አስፈሪ አድርጎ በመሳል ትግራይን ከሌሎች ነጥሎ ያደቀቀ፣ ሕዝቡን በስሙ እየማለ “አንድ ለአምስት” በሚባል የስለላ መዋቅር ተብትቦ፣ የፍርሃት ድባብን አንግሶ ሲመለክ ቆይቶ አጋጣሚ ተመቻችቶለት ኢትዮጵያን ለመግዛት የቻለ ድርጅት ነው።

ፎቶ በስተቀኝ ማዕከላዊ ሲሆን በስተግራ የፖትስዳም የኬጂቢ እስር ቤት የሶቪየት ኮምኒስት ሥርዓትን የሚቃወሙ ጀርመናውያንን ሰላዮችን በድብቅ የሚያሰቃዩበት የምርመራ ቤት ነው።
ህወሓትም ከበረሃ ጀምሮ ስውር እስር ቤቶች የነበሩት፣ በሐሳብ የሚቀናቀኑትን የበላ፣ መንግሥት ከሆነም በኋላ በተመሳሳይ የአፈና ስልቱ ሕዝብ መተንፈስ እስኪፈራ ድረስ የስለላ መዋቅሩን እስከ ግለሰብ ቤቶች በመዘርጋት ሲሰራ የነበረ ድርጅት ነው። ተቃዋሚዎችን በማፈን፣ በማሰቃየትና በመሰወር የሚታወቀው ህወሓት ከሲጉሪሚ የወረሳቸውን ባህሪያት አሁን ድረስ እንዳልተላቀቀው መረጃዎችን በማጣቀስ እየተከሰሰ ይገኛል።
በጥናቶች መሠረት ከሦስት ወይም ከአራት አልባንያውያን መካከል አንዱ ከሲጉሪሚ ጋር ስለሚሰራ በየቀኑ መረጃ ይቀርባል። ወላጅ በልጁ፣ ባል በሚስቱ፣ ጎረቤት በጎረቤቱ፣ የስራ ባልደረባ በባልደረባው ላይ እንዲሰልል ይገደድ ወይም በጥቅም ይደለል ነበር። በዚሁ ምክንያት ሕዝቡ “ግድግዳዎች እንኳ ጆሮ አላቸው” ብሎ እንዲያምን ተደርጓል። ይህም ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እንኳ ስለ መንግሥት ወይም ስለ ኤንቨር ሆጃ መናገር ወይም ቅሬታ ማቅረብ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ኤንቨር ሆጃ አልባንያን ከአሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ዩጎዝላቪያ እና ቻይና “የወረራ ስጋት” ያዳነ ብቸኛ ነጻ አውጪ እና አባት ተደርጎ እንዲሳል ይደረግ ነበር። በተመሳሳይ ህወሃትም ትግራይን የታደገ፣ ለትግራይ ሕዝብ ህልውና የሆነ፣ በትግራይ ላይ ብቸኛ ወኪልና እሱ ከሌለ ህልውና ሊኖር እንደማይችል ተደርጎ ተስሏል።
የትምህርት ቤቶች፣ ጋዜጦች፣ መጻሕፍት፣ ሙዚቃዎች እና ፊልሞች በሙሉ ሆጃን እና የኮሙኒስት ፓርቲውን የሚያሞግሱ ብቻ እንዲሆኑ ሲጉሪሚ በጥብቅ ይቆጣጠር ነበር። ከመንግሥት ትረካ ውጪ የሆነ ማንኛውም ሐሳብ “የካፒታሊስት አሻጥር” ተብሎ ይፈረጅ ነበር።
የሲጉሪሚ የቴክኒክ ክፍል (Technical Directorate) በባለስልጣናቱ መኖሪያ ቤቶች ሳሎን፣ መኝታ ቤት እና ቢሮዎች ግድግዳ፣ ጣሪያ፣ ኤሌክትሪክ ሶኬቶች እና ስልኮች ውስጥ በጥቃቅን ማይክሮፎኖች (Bugs) ድምፅ ይቀርጽ ነበር። ከእነዚህ ቤቶች የሚወጡት የምስጢር ድምፅ ማስተላለፊያ ሽቦዎች በቀጥታ የተያያዙት በአቅራቢያው ከሚገኘው House of Leaves (የቅጠሎች ቤት) ከተሰኘው የሲጉሪሚ ማዕከላዊ የስለላና የድምፅ ማዳመጫ ህንፃ ጋር ነበር። ይህ ብቻ አይደለም፤ በባለስልጣናቱ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ አገልጋዮች፣ ፅዳቶች፣ ሹፌሮች እና ምግብ ሰሪዎች በሙሉ በሲጉሪሚ የተቀጠሩ ወይም መረጃ እንዲሰጡ የተገደዱ ነበሩ። የራሱን ባለስልጣናት የማያምነው ይህ መዋቅር በርካቶችን መብላቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
አልባንያ በወቅቱ እጅግ ደሃ እና ከውጭ ዓለም የተገለለች ሀገር ብትሆንም፣ ለድምፅ ጠለፋ እና ለኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች ከፍተኛ በጀት ታወጣ ነበር። በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ አልባንያ ከሶቪየት ህብረት (KGB) እና ከቻይና ጋር ጥሩ ግንኙነት በነበራት ወቅት፣ ዘመናዊ የስልክ ጠለፋ፣ የሬዲዮ ሞገድ መከታተያ እና የድምፅ መቅረጫ መሳሪያዎችን ታገኝ ነበር። ግንኙነቱ ከተቋረጠ በኋላም ቢሆን በምስጢር ከምዕራብ አውሮፓ (በተለይም ከምዕራብ ጀርመን እና ጣሊያን) በሦስተኛ ወገኖች በኩል የድምፅ ጠለፋ መሳሪያዎችን ትገዛ ነበር።
በዚሁ የስለላ ትብትብ በአልባንያ የኮሙኒስት አገዛዝ ዘመን (እ.ኤ.አ ከ1944 – 1991) በቆየው የኤንቨር ሆጃ ልዩ የደህንነትና የስለላ መዋቅር በነበረው ሲጉሪሚ (Sigurimi)፣ የአገዛዙን የበላይነት ለማስጠበቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት በግፍ ቀጥፏል። በታሪክና በሰብዓዊ መብት ሰነዶች መረጃ መሠረት፣ በጥብቅ የስለላ አውታር የተያዙ ከ6,000 በላይ አልባንያውያን “የሕዝብ ጠላት፣ ከዳተኛ ወይም የውጭ ሰላይ” ተብለው በይፋ እና በምስጢር በግፍ እንዲረሸኑ ተደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም በድብቅ የተገደሉ የበርካታ ዜጎች አስከሬን በምስጢር በመቀበሩ ደብዛቸው ጠፍቶ የቀሩ ቁጥራቸው ብዙ ነው። ከ1,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደ ስፓች (Spaç) ባሉ ጭካኔ በተሞላባቸው የግዳጅ ስራ ካምፖች ውስጥ በሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ድብደባ፣ የምግብ እጥረትና የከባድ ማዕድን ስራ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከቀጥታ ግድያው ባሻገር፣ ሲጉሪሚ የተጠቀመበት “የጋራ ቅጣት” (Biografia) እና የስነ-ልቦና ሽብር አሰራር መላውን ሀገር የፍርሃት ሰለባ በማድረግ የብዙ አስር ሺዎችን ህይወት አበላሽቷል። በሆጃ ዘመን ከ34,000 በላይ ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ከ50,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው ወደ ገጠራማና ገለልተኛ አካባቢዎች በግዳጅ ግዞት (Internal Exile) እንዲኖሩ ተደርገዋል። በአጠቃላይ የሲጉሪሚ አሰቃቂ እርምጃዎች አልባንያን በዓለም ላይ እጅግ ጨቋኝ ከነበሩት አምባገነናዊ መዋቅሮች አንዷ አድርጓት አልፏል።
በህወሓት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን የነበረው የእስርና የስለላ መዋቅር ከላይ እንደተገለጸው በጭካኔው የትግል ዘመን የተጀመረ ነው። በበረሃ የትግል ዘመኑ ከነበሩት የዋሻዎች እስር ቤቶች ጀምሮ እስከ ጄል ኦጋዴን፣ ማዕከላዊ፣ ሸዋ ሮቢት እና ጦላይ በመሳሰሉት ማዕከላት ሰዎች ይታጎሩ፣ ይሰቃዩ ነበር። በዳታ የተደገፈ መረጃ ይፋ ባይሆንም በዜጎች ላይ ሲፈጸም የነበረው ግፍ ወሰን አልነበረውም። ይህ በወላቃይት ዙሪያ የቀረቡትንና በወጉ ሊጠኑ የሚገባቸውን የሚስጢር እስር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች ሳያካትት ነው።
ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ ተግባር በአልባንያ በኤንቨር ሆጃ የአፈና ተቋም በሲጉሪሚ (Sigurimi) ይፈጸም ከነበረው ዘግናኝ የአምባገነንነት ስልት ጋር ፍጹም ይመሳሰላል። ህወሓት ገና በትግሉ ወቅት በትግራይ በረሃዎች ውስጥ ባሉ ዋሻዎችና ገደሎች እንደ «ባሕሪ 4» እና «መጋቢት» ባሉ የስለላ ክፍሎቹ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸውን ታጋዮችና ገበሬዎች በምስጢር ያሰቃይና ይረሽን እንደነበረ ሁሉ፣ አልባንያውያንም በስፓች (Spaç) የታሰሩ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በተራራማ ማዕድናትና ዋሻዎች ውስጥ አጉረው ያሰቃዩ ነበር። ህወሓት ስልጣን ከያዘ በኋላም ይህንን የበረሃ ልምድ በማስፋፋት በመሃል አገር ማዕከላዊ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በጅጅጋው «ጄል ኦጋዴን» እስር ቤት ውስጥ ዜጎችን፣ እናቶችንና ህፃናትን በአውሬዎች ከማስበላት ጀምሮ፣ በኤሌክትሪክ ንክኪ እና በተለያዩ ከባድ የማሰቃያ ስልቶች ዜጎችን መከራ ያሳይ እንደነበር ሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) “the shame of Ogaden or Ethiopia’s hidden shame” በሚለው ዘግናኝ የቪዲዮ ማስረጃ እና የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ይፋ ያደረጉት የወቅቱ መንግሥት ነውር ነበር። ከዚህም በላይ በማይካድራና በወልቃይት የተከያዩ አካባቢዎች የተገኙ የጅምላ መቃብሮችና የቁም ስቃይ ታሪኮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአዲስ አበባ ማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ እንዲሁም በጦላይና አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፖችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ አፍኖ በማጎር ተመሳሳይ ድርጊት የፈጸመው የወቅቱ የስለላ መዋቅር ነውር የማዕከላዊ ግድግዳዎችና ተጎጂዎች በገሃድ የመሰከሩት ሀቅ ነው።
በሌላ በኩል፣ አልባንያውያን በ”House of Leaves” የስለላ ማዕከል አማካኝነት የድምፅና የስልክ ጠለፋ ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS) በየከተሞቹ በተከራያቸው ምስጢራዊ ቪላዎችና ህንፃዎች ውስጥ ሰዎችን አፍኖ በመሰወርና በኤሌክትሮኒክስ መዋቅር በመሰለል ፍርሃት የተሞላበት ቁጥጥር ዘርግቶ ነበር።
በተለይም ለሽብር መከላከል አሜሪካ የሰጠችውን የስልክ መጥለፊያ በመጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባዎችንና ንግግሮችን በመጥለፍ፣ ይህንኑ ወንጀል ህጋዊ ፈቃድ እንዲኖረው በአዋጅ በማስደገፍ ዜጎችን ያሸማቅቁ እንደነበር ማንም አሌ ሊለው የማይችለው የወቅቱ መንግሥት መሪዎች ሌላው ሃፍረታቸው ነው።
የሁለቱ አገዛዞች ሌላው ትልቅ ተመሳስሎ ደግሞ ተቃውሞን ለማክሸፍ ይጠቀሙበት የነበረው የስነ-ልቦና ሽብር እና ማህበራዊ መሰረትን የማፍረስ ስልት ነው። አልባንያውያን በሲጉሪሚ የ”ጋራ ቅጣት” (Biografia) ስልት ምክንያት የቤተሰብ አባሎቻቸው በግዳጅ ግዞት (Internal Exile) እንዲኖሩ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ፣ በህወሓት ዘመንም ማንኛውም የመንግሥት ፖሊሲን የተቃወመ ዜጋ ወይም የኦነግ እና የኦጋዴን ግንባር (ONLF) ደጋፊ ተባሎ የተጠረጠረ ሰው አጠቃላይ ቤተሰቡ ለእስር፣ ለስደት እና ለማህበራዊ ማግለል ይዳረግ ነበር። ዛሬ አልባንያ እነዚህን አሰቃቂ ቦታዎች ወደ BunkArt እና House of Leaves ሙዚየሞች በመቀየር “ታሪክ እንዳይደገም” ለትውልድ ማስተማሪያ እንዳደረገችው ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ለውጡን ተከትሎ እነዚህ ጥቁር የኢትዮጵያ የታሪክ ገጾችም ለአዲሱ ትውልድ አምባገነንነት ያስከተለውን ጥፋትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያስተምሩ ትልቅ ምልክቶች ሆነዋል።
ሲጉሪሚ እንዳደረገው ሁሉ ሌሎች ሚስጢራዊ ወንጀሎችን ሳያካትት የዓምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ በ2007 ዓ.ም. (2014 እ.ኤ.አ.) “They Choice to Suppress” በተሰኘው መግለጫው ላይ እንደጠቀሰው፣ ከ2004 እስከ 2014 እ.ኤ.አ. ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ20,000 በላይ ኦሮሞዎች በፖለቲካ ምክንያት፣ “የኦነግ ደጋፊ ናችሁ” ወይም “የመንግሥት ተቃዋሚ ናችሁ” በሚል ሰበብ ለእስር ተዳርገዋል። ኦነግ ደግሞ ከአርባ ሺህ በላይ ኦሮሞዎች መታሰራቸውንና የእስር ቤት ቋንቋ ኦሮሚኛ እስከመሆን መድረሱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።
ከሲጉሪሚ የተገለበጠው የህወሓት የደህንነት መዋቅር ሰዎችን በምስጢር የመሰወር እና ለቤተሰብ መረጃ ያለመስጠት ስልትን በሰፊው ይጠቀም ነበር።
ከማዕከላዊ እና ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ውጪ በግል መኖሪያ ቤቶች፣ በወታደራዊ ካምፖች እና በምስጢር ቤቶች (Secret Detention Sites) ውስጥ ሰዎች ተሰወረው እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። ከኦህዴድ እና ከቀድሞ ታጋዮች፣ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የተቃወሙ ፖለቲከኞች፣ የኦሮሞ አርቲስቶች፣ ተማሪዎችና ገበሬዎች በብዛት ይጠፉ ነበር።
በትክክል የጠፉ ወይም የተሰወሩ ሰዎች ቁጥር ባይገለጽም በሺዎች የሚገመት ሲሆን፣ የብዙዎቹ ደብዛ እስከ ዛሬ ድረስ አልተገኘም። አንዳንዶቹ ከዓመታት በኋላ በድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ ሲገኙ፣ ሌሎች ደግሞ ህይወታቸው አልፎ በምስጢር መቃበራቸው አገዛዙ ከተቀየረ በኋላ የተወሰኑ መረጃዎች ወጥተዋል።
ዜጎችን በፍርሃትና ራስን ሳይቀር በመጠራጠር ስሜት ውስጥ የከተተው የሲጉሪሚ አፈና፣ ከሆጃ ሞት በተጨማሪ ሕዝቡና የራሱ የስለላ መዋቅር ማመጹ ከኮሙኒዝም መፍረስ ጋር ተዳምሮ ተፈረካከሰ። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝም በተመሳሳይ ከውስጡ በተነሱ የለውጥ ኃይሎች ተቦረቦረ፤ ሕዝብ “በቃኝ” ብሎ ተነሳና ደረመሰው።
የአፈና መዋቅሩን ሲመራው የነበረው ህወሓት ወደ ትግራይ በመሄድ መዋቅሩን አስቀጥሏል። ይህ የስውር መዋቅር ሙሉ በሙሉ ስላልተነቀለ ትግራይ ተቀምጦ መላዋን ኢትዮጵያን ያምስ ጀመር።
“የሆጃቪዝምን ተጽዕኖ” ተግቶ፣ እንደ ሆጃቪዝም እምነት አልባ ሆኑ፣ በአልባንያ ኮሚኒዝም ተጠምቆ ከበረሃ ጀምሮ በአፈና መዋቅሩ የሚፈታተኑትን እየበላ መንግሥት የሆነው ህወሓት፣ ከስልጣን ከወረደ በኋላም በተመሳሳይ መንገድ ቀጥሏል። የግዳጅ አፈና፣ እስርና የቤት ለቤት ስለላ ተቋሙ የገፋበት ህወሓት፣ ዛሬ ልክ የሆጃ መንግሥት እንዳጋጠመው ዓይነት ተቃውሞ በራሱ አባላትና የመዋቅር ሰዎች እየነደደበት ይገኛል። አራት ኪሎ ገብቶ ዳግም ኢትዮጵያን ሊነዳ ይቻለዋል? መጨረሻውን እናያለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






