አዲስ ሪፖርተር – የዓለም ኃያላን አገራት፣ የትግራይ ተቃዋሚ ፓሪዎች፣ የክልሉ ሲቪክ ማህበራትና የምሁራን ጉባኤ፣ አብዛኛው ትግራይ ላይ የሚያተኩሩ ሚዲያዎች፣ ከምንም በላይ ህዝብ ጦርነትን እያወገዙ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ “በስላምና በጦርነት ቀጭን ገመድ ላይ ነን” በማለት ያለፉትን አምስትና ስድስት የትግራይ ትውልድ ከበላ ጦርነት ውስጥ ዳግም ላለመግባት የሚቻለው ሁሉ ጥንቃቄ እንዲወሰድ አሳሰቡ። ትግራይ ወደ ጦርነት ተንሸራቶ ለመግባት አፋፍ ላይ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
ጦርነትን እንደ አማራጭ ያደርገውን ኃይል የወቀሱትና “አንዳችም ለትግራይ የሚበጅ መፍትሄ አያመጣም” ያሉትን ቡድን “በርካቶች የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረቡ ነው። በውይይት ወደ እዛ መፍትሄ እናምራ” ብለዋል። ሙሉውን መልዕክት ከስር
“የትግራይን ህዝብ ወደ ሌላ ዙር የውድቀት አዙሪት የሚወስደውን ጉዞ በመግታት መጻኢ እድሉን እናለምልመው”
ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት የተላለፈ መልእክት
ለዘመናት ከውጭ ኃይላት ጋር የተደረጉ የጦርነት እና የሰላም ጉዞዎቻችን፣ በውስጣችን ያጋጠሙ የመከፋፈል፣ የአንድነት፣ የትግል እና የድል ታሪኮቻችን፣ እንዲሁም የገጠሙን እጅግ ከበድ ያሉ ውስብስብ ፈተናዎችን አልፈን እንደ ህዝብ ዛሬ ላለንበት መድረክ በቅተናል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ፍላጎታችንን፣ መጻኢ እድላችንን እና ነገአችንን በአግባቡ ባለመመለሳችን ምክንያት፤ ባለፉት 5 ወይም 6 ትውልዶች ውስጥ ጦርነት ያላጋጠመው ወይም በሰላም ያለፈ ትውልድ በትግራይ የለም ማለት ይቻላል። አሁንም ቢሆን ካለፈው የታሪክ ጠባሳ የሚያላቅቅ ስልታዊና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሳናደርግ በዛው ጉዞ ቀጥለናል።
ህወሓት እንደ ድርጅት የቀደመውን ሥርዓት አፍርሶ አዲስ ሥርዓት የተካበት፣ የ17 ዓመታት ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ ብርቱ ተጋድሎ ያደረገ፣ በትግራይ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ሙሉ ህዝባዊ አንድነት ፈጥሮ ለማንነቱና ለክብሩ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ድል እንዲረጋገጥ የታገለ ድርጅት ነው። ከዚያ በኋላ በነበሩት 27 ዓመታትም መሠረታዊ የሚባሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ፣ በሰው ሀብት ልማትና በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ እድገት እንዲመጣ፣ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲረጋገጥና ተሳትፎ ያለው ህዝብ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ድርጅቱ ትልቅ ሚና ነበረው። እንዲሁም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጂኦ-ፖለቲካን በአግባቡ በመረዳት በኢትዮጵያ ታሪክ ረጅም የሚባለውን የሰላምና የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ዘመን በማምጣት ረገድ የመሪነት ሚና የተጫወተ ድርጅት ነው።
በነዚያ ጊዜያት ውስጥ ድርጅቱ የማይታለፉ የሚመስሉ ውስብስብ ፈተናዎችን የመረዳትና መርቶ የማሻገር ብቃት ነበረው፤ ከዛ ባሻገር በየጊዜው ራሱን የሚያድስ ብልህ፣ ተማሪ፣ ስልታዊ አመራር፣ ቁርጠኛ አባልና ህዝብ ስለነበረው፣ በእርግጥም ህወሓት መድረስ የሚገባው ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው።
ይሁን እንጂ ባለፉት 10 ዓመታት ከአንድ ውድቀት ወደ ሌላ ውድቀት እየተሸጋገርን፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የነበረንን ቦታ ሙሉ በሙሉ አጥተን በትግራይ ክልል ብቻ እንድንወሰን ተደርጓል። በእኛ ላይ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ጦርነት የተፈጸመበት፣ ሕገ-መንግስታዊ ወሰኖቻችንን ያጣንበት፣ እንደ ህዝብ የተፈናቀልንበት፣ “ይከበር” ብለን ዋጋ የከፈልንበትና ድምፃችንን ያሰማንበት ሕገ-መንግስት ሳይታደገን የቀረበት፣ እንዲሁም ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎ የተደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት ባልተተገበረበት ሁኔታ ውስጥ በጦርነት ጠባሳ ውስጥ እንገኛለን።
አሁን ያለንበት መድረክ በሰላምና በጦርነት መካከል ባለች እጅግ ቀጭን መንገድ ላይ ቆመን፣ ያልተገፈፈው የጦርነት ደመና ዳግም ሊዘንብ የሚችልበትና በቀላሉ ወደ ጦርነት ተንሸራትተን ልንገባ የምንችልበት አደገኛ ሁኔታ ላይ ነን። በዚህ ወቅት በዓይነቱ፣ በይዘቱና በውጤቱ በታሪካችን ገጥሞን የማያውቅ አደገኛ ፈተና እያስተናገድን እንገኛለን። በዚህ ፈተና ውስጥ አሁንም የመውደቅ ዕድላችን ሰፊ ቢመስልም፣ እንደ ህዝብ አንድ ሆነን ለመቀጠል ያለን ብቸኛ አማራጭ ግን ይህንን ፈተና በፅናት ማለፍ ብቻ ነው።
ከገጠመን ውስብስብ ችግር ለመውጣት፣ በለመድነው የቀድሞ ተሞክሮና ልምድ ራሳችንን አስረን የምናልፍበት ጊዜ አይደለም። “እልህ” እና “እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን” የሚል አስተሳሰብ፣ የችግሩን ጥልቀት ካለመረዳት፣ የትግራይን ህዝብ፣ የሀገርንና የቀጣናውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ካለማገናዘብ የሚመነጭ ነው።
የዚህ ሁሉ ውድቀት ምንጭ አመራሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተገለጸ ጉዳይ ነው። ሁኔታዎችን በብስለት ከመገምገም፣ የዛሬን ችግር በቅጡ አውቆ ለነገ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ የተለየ ሐሳብ ያራመደን ማፈን፣ ስትራቴጂን በታክቲክ ለመተካት መዳከር፣ የህዝብን አቅምና ትግል ማዳከም፣ ሰዎችን አሰባስቦ ከመከራ የሚያወጡ ስትራተጂዎችን ከመንደፍ ይልቅ ስም ማጥፋትና ጥላሸት መቀባባት ላይ ማተኮር፣ የትግራይን ፖለቲካ አሁንም ወደ ውድቀት መንገድ እየመራው መሆኑ ሊደበቅ የማይችል ጥሬ ሀቅ ነው።
አንድ አስተሳሰብ ብቻ ይዞ፣ ያንኑ አስተሳሰብ በጠባብ መድረክ ወስኖ “ውሳኔዬን ተቀበሉ” ማለት፣ የተለየ ሐሳብን ችላ ብሎ ደጋፊን ብቻ ይዞ ለመቀጠል መሞከር ተጨማሪ አደጋን ይፈጥር ይሆናል እንጂ የሚፈታው ችግር የለም። የዚህ ችግር መፍትሔ ከማንኛውም ፖለቲካዊ መዋቅር፣ ከመንግስት፣ ከድርጅት፣ ከግለሰባዊ ሥልጣን በላይ ነው።
ብዙ የትግራይ ልጆች፣ ተደራጅተው በሚገኙባቸው አደረጃጀቶች ውስጥም ሆነ እንደ ግለሰብ የራሳቸውን የመፍትሔ ሐሳብ እያቀረቡ ነው፣ እንዲሰሙም ይፈልጋሉ። በእርግጥም ተጋሩን ከችግር የሚያወጣ መፍትሔ በመፈለግ ረገድ የምንሰባሰብበትና አንድነት የምንፈጥርበት ምቹ ሁኔታና ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
ከዚህ ውጭ “ሌላውን አልሰማም” በማለት “እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን” የሚል ጭፍን አካሄድ ውጤቱ ሌላ ዙር ውድቀት እንጂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። “ወስኛለሁ” ብሎ በኃይል ለማስፈጸም መሞከር ደግሞ ከሱም የባሰ አደጋ ነው። የተለየ ሐሳብ ላለው አካል የሐሳብና የክርክር መድረክ ከመፍጠር ይልቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንደጠላት በመፈረጅ ስም ማጥፋትና በውሸት ላይ የተመሰረተ የበሰበሰ ፖለቲካን ማራመድ ውድቀታችንን ያፋጥን ይሆናል እንጂ ጥቅም የለውም።
በዚህ የእውር ድንብር አካሄድ መሄድን ከመረጥን የሚገጥመን ውድቀት የአንድ ድርጅት ወይም የጥቂት ግለሰቦችን ሳይሆን፣ እንደ ህዝብ እንደምንወድቅና ዋጋ እንደምንከፍል ግልጽ ነው። አሁን ያለው ወቅታዊ ችግር እንደ ህዝብ አንድ ሊያደርገን የሚችል ምቹ አጋጣሚ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ያንን ከመፍታት ይልቅ ልዩነቱና ስንጥቁ ይሰፋ ዘንድ ሆን ተብሎ እየተሰራ ነው።
አሁንም የትግራይን ህዝብ ወደሌላ ዙር የውድቀት አዙሪት እንዲያመራ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ስለሆነም፣ መላው የትግራይ ህዝብ በአጠቃላይ፣ በተለይም የዚህ አደጋ ዋነኛ ሰለባ የምትሆኑ ወጣቶችና እናቶች፣ እዚህ አደጋ ላይ የሚጥለንና ብልሃት የጎደለውን ውሳኔ፣ ሙሉ በሙሉ ወደ አደጋና መበታተን እንደሚያስገባን አውቃችሁ እዚህ ችግር ውስጥ ከመግባታችን በፊት እንድታስቆሙትና ላለንበት አጭር የሽግግር ወቅት የሚሆን ከተለያዩ አማራጮች የተወጣጣ የተሻለ ሐሳብ የሚመነጭበት የውይይት መድረክ እንዲፈጠር የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ታደሰ ወረደ ተስፋይ (ሌ/ጄነራል)
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕረዚዳንት
ሚያዝያ 26/2018
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






