አዲስ ሪፖርተር | ሰኔ 25 ሮይተርስ — በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) መካከል የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው። በፓራሚሊታሪው ቡድን (RSF) ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች አዲስ የታተሙ የሚመስሉ የሱዳን ፓውንድ ምንጩ ያልታወቀ የገንዘብ ኖቶች መሰራጨት መጀመሩ የሀገሪቱን የመከፋፈል አደጋ ይበልጥ አግንኖታል።
ሚያዝያ 2023 ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት ከሱዳን መደበኛ ጦር ጋር አብሮ ይሰራ የነበረው RSF፣ በአሁኑ ወቅት ሰፊውን የምዕራብ ዳርፉር ክልል ጨምሮ በርካታ የሀገሪቱን አካባቢዎች መቆጣጠሩን የሮይተርስ ዘገባ ለስጋቱ መንሻ ያደረጋል።
የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ፉክክር
በሱዳን የገንዘብ ቁጥጥር ጉዳይ ከ2024 ጀምሮ ትልቅ የውዝግብ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። በወቅቱ አገሪቱን የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት አሮጌዎቹን የሱዳን ፓውንድ ኖቶች ዋጋ ቢስ ማድረጉን አስታውቆ፣ አዲስ የ500 እና የ1,000 ፓውንድ ኖቶችን ማተም ጀምሮ ነበር። RSF በበኩሉ እነዚህን አዳዲስ ኖቶች ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ በእሱ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ተከስቶ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ነገር ግን ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የሲቪል ሰራተኞች እና የRSF ተዋጊዎች ደመወዛቸውን በአዲስ የሱዳን ፓውንድ መከፈላቸውን ተከትሎ የገንዘብ እጥረቱ ጋብ ብሏል። ለሮይተርስ የደረሱት ፎቶግራፎች እንደሚያሳዩት፣ እነዚህ አዲስ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ኖቶች የ”ግንቦት 2022″ ዕትም የሚል የዘመን አቆጣጠር ያለባቸው ሲሆን፣ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከነበሩት ኖቶች ጋር በእጅጉ ይመሳሰላሉ። በዳርፉር ኒያላ ከተማ የሚገኝ አንድ የባንክ ባለሙያ ኖቶቹ አዲስ የታተሙ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የ”ታሲስ” (Tasis) ትይዩ መንግሥት ሚና

RSF ባለፈው ዓመት “ታሲስ” የተሰኘ ትይዩ ካቢኔ (መንግሥት) ባቋቋመባቸው አካባቢዎች የሲቪል ሰራተኞችን ደመወዝ መክፈልን ጨምሮ የመንግሥትን ተግባራት ቀስ በቀስ ለመረከብ እየሞከረ ይገኛል።
አዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች የሱዳን ማዕከላዊ ባንክ የቀድሞ ገዥ የነበሩትን ሁሴን ያህያ ጃንጎልን ፊርማ የያዙ ሲሆን፣ እኚሁ ግለሰብ ኖቶቹ መሰራጨት ከመጀመራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ግንቦት 21 ቀን በRSF ለሚመራው አዲስ የማዕከላዊ ባንክ ዋና ገዥ ሆነው መሾማቸው ሁኔታውን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።
የ”ታሲስ” ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሀሰን አል-ታኢሺ የገንዘቡን ምንጭ ከመግለጽ የተቆጠቡ ቢሆንም፦”ማንኛውም የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ወይም የፈሳሽ አቅርቦት ዝግጅቶች የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመጠበቅ እና የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት የታለሙና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ቴክኒካዊ ዕቅዶች ናቸው” ብለዋል።
በተጨማሪም በጦሩ የሚመራውን መንግሥት “ገንዘብ በመቀየርና ገበያውን በማድረቅ ገንዘብን እንደ ጦርነት መሣሪያ እየተጠቀመበት ነው” ሲሉ ከስሰዋል።
የዲፕሎማሲ እና የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ
የሱዳን ግልጽነት እና ፖሊሲ ትራከር (Sudan Transparency and Policy Tracker) የተባለው የምርምር ተቋም ኃላፊ ሱሊማን ባልዶ፣ ብዙ ሀገራት ይህንን ትይዩ የባንክ ሥርዓት ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ RSF ግን ያጋጠመውን ከፍተኛ ችግር ለመፍታት ወደፊት እየገፋበት መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በነበረበት ወቅት አብዛኞቹ ሱዳናውያን በኮርቱም ባንክ የሚመራውን እና በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የሚያገለግለውን “ባንካክ” (Bankak) የተሰኘ የኦንላይን ክፍያ መተግበሪያ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። አሁን ግን በRSF ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች “ፊውቸር ባንክ” (Future Bank) የተባለ ተቀናቃኝ የገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎት መጀመሩና ለግንቦት ወር ደመወዝ ክፍያ መዋሉ ተገልጿል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሱዳን ፓውንድ ዋጋ በእጅጉ ያሽቆለቆለ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አንድ ዶላር ከ600 ፓውንድ በታች ይሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት አንድ ዶላር ወደ 5,000 ፓውንድ ደርሷል።
ይህ የሮይተርስ ዘገባ የብሩ ህትመት ሱዳን ዳግም ወደ መበታተን ሊያመራ የሚችል ስጋት አድርጎ ያቀረበው ከላይ ባስቀመጠው መረጃ ተደግፎ ነው።
የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎችን RSF ራሳቸውን ልሂቅና የሱዳን ገዢ አድርገው የሚያዩት ሰሜነኞቹ፣ RSF ምንም እንኳን አብዛኛውን ቁጥር ቢይዝም፣ የመንግስትን ስልጣን ሊይዝ የማይገባ “ህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን” (Militia) ነው ብለው ያምናሉ። ሀገሪቱን በታጣቂ ቡድን መመራት እንደ ሀገር መፍረስ አድርገው ይቆጥራሉ። ከዚያም በላይ መጤ፣ መሃይም፣ አድራሻ የሌላቸው አድረገው ሲገሏቸው ኖረው አሁን ላይ ግን ሊያስቆሟቸው ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።
የጄኔራል አልብርርሃን የሚመራው የሰሜን ሱዳን ወታደራዊ መንግስት፣ ከኢራን፣ ከግብጽ፣ ከቱርክ እና በዚህ ክበብ ውስጥ ባሉ አገሮች የሚደገፍ ሲሆን፣ ኤርትራና ህወሃትም እንደ አቅማቸው ያግዛሉ። ኤርትራ የሎጂስቲክና ስልጠና ማዕከል ሆና ስታገለግል፣ ህወሃት የትግራይ ታዳጊዎች ለሱዳን እንዲዋጉ በማድፈግ፣ በምትኩ ገንዘብ እየተቀበለ መሆኑ መረጃ ወጥቶበታል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






