አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — “ትብብር ፈጠርን ያሉ ሃይሎች በተለያዩ አሰላለፎችና ተቃርኖዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያደሙ የኖሩ እንጂ አዲሶች አይደሉም” በማለት እነዚህ ኃይላት እንደ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ህልማቸው የማይታረቅ ታጣቂ ሃይሎች በማደረጀት ኢትዮጵያዊያንን መንግሥት አልባነት(failed state) ለማድረግ የቆረጡ በመሆናቸው “አገሬን” የሚሉ ሁሉ በጥንቃቄ ሂደቱን እንዲመረመሩ፣ አገራቸውን እንዳይከስሩ ሰክነው እንዲራመዱና አሳባቸውን እንዲያመክኑ የወልቃይት አስመላሽ ኮሚቴ አሳሰበ።
ኮሚቴው በወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ ህዝብ ለ40 ዓመት በመላው አማራና ኢትዮጵያ ለ27 ዓመት ለሰራው ግፍ አምኖ ሃላፊነት ሳይወስድ አሁን ድጋሚ መሰሎቹን አሰባስቦ ከጀርባ ሌላ አጀንዳ የሚያራምደው ህወሃት ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካል ውድቀት የሚጋብዝ እንደሆነ ማንም እንደሚረዳው አስታውቋል። ህዝብ ከአገር መከላከያ ጎን እንዲቆም አሳስቧል። ሙሉ መግለጫውን ያንብቡ።
“በሕዝባችን ማንነት፣ ህልውና እና ወሰን ላይ የሚደረጉ ህገ-ወጥ የጀርባ ሴራዎችንና ስምምነቶችን የአማራ ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥንቃቄና በንቃት ሊመለከት ይገባል”
ከወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ አስቸኳይ የአቋም መግለጫ
ለዘመናት የምናውቀው ህወሓትና አስተሳቡ አሁንም ቅርፁን እየቀያየረ እየታገለን ይገኛል።ቡድኑ ላለፉት 50 ዓመታት በወልቃይት ጠገዴ፣በመላው አማራና ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸመው ማንነትን የማጥፋት፣ ህዝብን የመከፋፈል፣የግፍና የበደል ታሪክ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ህዝባችን ባደረገው መራራ ትግል ድርጅቱ ከማዕከላዊ መንግሥት የበላይነቱ ከተወገደ በኋላም ቢሆን፣ ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ስጋት የሚሆኑ አደገኛ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ለአብነትም በቅርብ ጊዜ በሸረሪና ግንባር ሐምሌ 25 ቀን የከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት፣በወልቃይት ግንባር መስከረም 7 ቀን ያደረገው የወረራ ሙከራ እና ከዚያም በፊት በጠለምት የሰነዘረው ጥቃት በህዝባችንና በመከላከያ ሰራዊታችን ክንደ ብርቱ ምት መመከት መቻሉ የሚታወስ ነው። ቅርፁንና ስልቱን እንደ እስስት በመቀያየር የሚታወቀው ይህ እኩይ ድርጅት በአሁኑ ወቅት «በትብብርና በጥምረት» ስም የአማራን ታሪካዊ ግዛቶችና ማንነቶችን ለመንጠቅ ኢትዮጵያንና ቀጠናውን ለማተራመስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ከጀርባ የሚሸረቡ ውሎች የሕዝባችንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው አጥብቀን የምንቃወማቸውና የማንቀበላቸው መሆኑን እንገልጻለን።
መላ ኢትዮጵያዊያን ፣ የአለም ማህበረሰብ እንዲሁም በመላ የአማራና የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ዘንድ እንደሚታወቀው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በሚል ከተመሰረተ ጀምሮ ህጋዊና ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ አንስቶ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የትግራይ አካል ሳይሆን የጎንደር አማራ አካል ነው መሬቱም በጌምድር ነው በሚል ብቻ ሳይሆን ትግራይ በቀል የሆነው ትህነግ ወይም ህወሓት የሚባል ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ሃይል አማራ በመሆናችን ለይቶ ገድሎናል:ዘርፎናል፣ወሮናል ብሎም ቀዝቃዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሞብናል በሚል ጭምር ነው።
ስለሆነም ይህ ሃይል ከወልቃይት ጠገዴና ከአማራ ህዝብ ጫንቃ መውረድ አለበት ብለን በህግ ተሟግተን ትግል ከጀርን እንሆ ድፍን 11 ዓመት አስቆጥረናል። ከመላ አማራ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብረን በመታገላችን ምክንያት ህወሃት/ትህነግ ከስልጣኑ ወርዶ የለውጥ መንግስት እንዲመጣም ምክንያት ሁነናል። በጠንካራ ትግላችንና በለውጡ መንግስት ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ከህወሓት አፋኝ ቡድን ከባርነት ነፃ ወጥተናል። ይህ ለውጥ ተከትሎ የማንነትና ወሰን አስተዳደር መስርተን ራስ በራሳችን መተዳደር ከጀመርንና ነፃነታችንን ካጣጣምን ድፍን 6 አመት አስቆጥረናል።
ይህ የማንነትና ወሰን የመብት ጥያቄ የፌደራል መንግስት በህጋዊ እውቅና እንዲሰጥ፣ ተገቢው መደበኛ በጀት ሆነ የልማት በጀት እንዲመድብ ጠዋትና ማታ በህጋዊ መንገድ አቤቱታ እያቀረብን ባለነበት ወቅት የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ ፀረ አማራ የሆነና ከጅምሩም የህወሓት/ትህነግ የደህንነት ሃላፊ የአቶ ጌታቸው አሰፋ ምልምል እንደሆነ በተደጋጋሚ በብዙዎች ሲነገርለት የነበረ በስመ የአማራ ፋኖ እታገላለሁ በሚል ግለሰብ በትግራይ ቴሌቪዥን የተሰጠውን መግለጫ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በፅኑ ይቃወመዋል።
የመንግስት ለውጥ ሲመጣ የህወሓት የደህንነት ሰዎች ቀድሞውንም የነሱ የነበሩ ሰዎች እየመለመሉ በአማራ ትግል ስም አስርገው በማስገባት አማራውን እርስበርስ ለማባላትና ለመከፋፈል እየሰሩ ነው በሚል በውስጥ መስመር ኮሚቴው ለሚመለከተው አካል ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። በወቅቱ ሰሚ አላገኘም። በድጋሜ የአማራ ፋኖ ብሎ እንቅስቃሴ ሲመጣ አሁንም “የስርዓት ለውጥ ለማበላሸት የህወሓት ሴራ አለበት፣በአማራ ህዝብ ጥያቄ ስም ትግሉን የመጥለፍ እንቅስቃሴ ስለሆነ ምክንያታዊ አይደለም መላ የአማራ ህዝብ ይረጋጋ ብሎ” ኮሚቴው በአደባባይም በሚስጥርም ምክር አቅርቦ ነበር።
በተገላቢጦሽ ግን ከአማራ ህዝብ ድጋፍና አድናቆት ለመነጠል ሲባል የዚህ ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ ሴረኛ ሃይል የፕሮፓጋንዳ ክንፍ ኮሚቴውን ሆነ የወልቃት ጠገዴ ህዝብ ትግል ከአማራ ትግል ለመነጠል በውስጥም ሆነ በውጭ መጠነ ሰፊ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ ከርሟል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ትግል አሳንሶ ለማሳየትም በፕሮፖጋንዳ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። እውነት ግን ተደብቆ አይቀርም። ኮሚቴው ሁሌም እውነትንና ምክንያት ይዞ ስለሚታገል አሁንም ከወልቃይት ጠገዴ ሆነ ከመላ የአማራ ማህበረሰብ ጎን እንደቆምን እንገኛለን። ይህ ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ ሃይል ዛሬ በግልፅ ሳያፍር ከመነሻው አማራ የታሪክ ጠላቴ ነው ብሎ 27 ዓመት በማያባራ በስውርና በግልፅ ሲገድል የነበረ አፋኝ ጠባብ ቡድን አባል ሁኖ የአማራ ህዝብ እሴት ሳያስፈራው በግልፅ ‘የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሃይሎች ትብብር ለህልውና’ በሚል የዳቦ ስም የህወሓት ተልእኮና ፕሮጀክት ተቀብሎ መቀሌ ከህወሓት ፅ/ቤት ወንበር ቁጭ ብሎ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ በትብብር እንታገል በሚል ሰበብ የተሰጠው የፅሁፍ መግለጫ ሲያነብ የሰማው ኮሚቴያችን በሆነው ድርጊት እጅግ በጣም አዝኗል፣አፍሯልም። ያዘነበት ምክንያት ለአማራ ነፃነት እታገላለሁ ፣ አማራን ወክያለሁ ብሎ ሲያበቃ የዋናው ጠላታችን ፕሮጀክት አስፈፃሚ ሁኖ አንሶ ሲገኝ ማየታችን ነው።
በመሆኑም:-
1ኛ. ህወሓት የአማራ ህዝብ ችግር መዋቅራዊና ስርዓታዊ በማድረግ ችግሩ ለመፍታት ያወሰበሰበው የህወሓት ስርዓት ሁኖ ሳለ:-
2ኛ.በወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ ህዝብ ለ40 ዓመት በመላው አማራና ኢትዮጵያ ለ27 ዓመት ለሰራው ግፍ አምኖ ሃላፊነት ሳይወስድ:-
3ኛ.በማይካድራና በጭና ለፈፀመው ማንነት መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሳይጠየቅ:-
4ኛ.አሁንም የምታገለው ወልቃይት ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ከተሳካም ተጨማሪ መስፋፋት ፈጥሬ ትግራይን ሃገር ማድረግ ነው ከሚል ፕሮፖጋንዳ ሳይቆጠብ:-
5ኛ.የራያ አማራ ህዝብ በመውረርና በማፈናቅል ህዝባችን እያሰቃየ ባለበት:-
6ኛ.የፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንደ ጊዜ መግዣ ተጠቅሞ ስምነትን ማፍረስና መካድ መገለጫው ከሆነ እኩይ ድርጅት ጋር ትብብር በመፈጥር እጅግ የሚውሰበሰብ እንጂ የሚመለስ የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ እንደሌለ ኮሚቲያችን በፅኑ ያምናል።
ከህወሓት ጋር የሚደረግ ትብብር በተለይ ለአማራ ህዝብ ታክቲካልም ሆነ እስትራቴጅካል ውድቀት የሚያመጣ እንደሆነ ኮሚቴው ቀድሞ ሲያሳስብና ሲያስገነዝብ ቢቆይም በትብብር ስም መግለጫ በሰጠው ከሃዲ ሃይል ክንፍ ተገልብጦ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የአማራ ህዝብ ትግል እንደካደ ተደርጎ የሃሰት ፕሮጋንዳ ለመስራት በቻለው ሙከራ ሲያደርግ ነበር።
እውነትና ንጋት እያደረ ይጠራልና ማን የአማራ ህዝብ ጠበቃ ማንስ ነው የአማራ ህዝብ የካደ የሚለው የሚታይበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል።
ኮሚቴያችን በትብብር ስም ተሰጠ በተባለው መግለጫ ቢያፍርም ግን ደግሞ ደስ የሚሰኝበት ጎንም አለው። ኮሚቴውን ደስ ያሰኘበት ምክንያት ተደብቆ የህወሓት መረጃ ሁኖ አማራን ሲገድል፣ ሲያስገድልና ሲገዘግዝ የነበረ የዚህ ሃይል አደረጃጀት ለጥፋት ነው፣ፀረ አማራ ነው ስንል በነበረ ሰዓት ሰሚ ብናጣበትም ዛሬ ራሱ በአደባባይ ህወሓትን አዝሎና መንገድ መርቶ ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ ለህወሓት እጅ መንሻ ለማስረከብ ፣አማራ የሚባል ማህበረሰብ ለማጥፋት ብሎም የኢትዮጵያ ስርዓተ መንግስት ለማፍረስ ሲሰሩ ከኖሩና አልሳካ ካላቸው ሃይሎች ጋር ተማምሎ እየመጣ እንደሆነ በግልጽ ሳያፍር በአደባባይ ራሱን አጋልጧል።
ስለሆነም ኮሚቲያችን የሚከተለውን ጥሪ ያስተላልፋል
1ኛ. ከህወሃት ጋር የሚደረጉ ማናቸውም ድብቅ እንቅስቃሴዎችና የጀርባ ስምምነቶች በአማራ ህዝብ ላይ የሚያመጡት አደጋ የከፋና የታወቀ በመሆኑ በመላው የአማራ ህዝብ መስዋዕትነት የተመለሱትንና ያስከበራቸውን የማንነትና የወሰን መብቶቹን ለማስከበር፣ ከጀርባ የሚደረጉ ማናቸውንም ሴራዎችና ውሎች በጥንቃቄና በከፍተኛ ንቃት እንዲከታተልና ህልውናውን እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
2ኛ.ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት አሁን ላይ ትብብር ፈጠርን ያሉ ሃይሎች በተለያዩ አሰላለፎችና ተቃርኖዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያደሙ የኖሩ እንጂ አዲሶች አይደሉም። ሃገራችን እንደምናያቸው አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ህልማቸው በማይታረቅ ታጣቂ ሃይሎች ለመንግሥት አልባነት(failed state) እንዳትጋለጥ ከወዲሁ በአንድነት መቆም እንደሚገባ እናሳስባለን።
3ኛ.ትግሉ እውነትም የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሚመልስ መስሏችሁ ጫካ ለወጣችሁ አንዳንድ ወንድሞቻችን ማሳሰብ የምንፈልገው ህወሓት ከሚመራው የትግል አሰላለፍ ወጣችሁ የአማራን ህዝብ በሚጠቅምና ክብሩን በሚያስጠብቅ አሰላለፍ እንደትሰለፉ ማስገንዘብ እንወዳለን።
4ኛ. የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ከወቅቱ የትግል አሰላለፍ አንፃር ሲሰላ የያዝከው የትግል መንገድ ልክ ስለሆነ ልትኮራ ይገባሃል። በያዝከው መንገድ ለመከላከያ ሰራዊትና ለተከዜ ዘብ የምታደርገውን ደጀንነት አጠናክረህ እንድትቀጥል እናሳስባለን።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሁመራ 11/01/2019
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






