በፈጠራ ዜናዎች ዘመቻ እንዲከፈትበት ከፍተኛ በጀት የተመደበለት ብሄራዊ የምክክር መድረክ ነገ ቅዳሜ ይጠናቀቃል፤ ከዋና አከራካሪ ጉዳዮች ውስጥ ለመረጃ አንኳር ነጥቦች

Date:

በተለይ አዲስ ሪፖርተር ትኩረት በመስጠት ስትከታተለው የቆየችው በሻዕቢያ የሚደገፈውና የሚነዳው አመጽ አመቻች ግብረ ኃይል “በሚቻለው ሁሉ አገራዊ የመከከር ኮሚሽኑን ተዓማኒነት ለማሳጣት፣ አጀንዳዎቹን ለማዛበት፣ በተሰብሳቢዎቹ መካከል መጠራጠር ለመፍጠር መስራት አለብን” በማለት አቋም የወሰደበትን መረጃ አስቀድመን በማቅረባችን “ይህ መረጃ እንዴት ወጣ” በማለት በመካከላቸው ብጥብጥ ተነስቶ ነበር። በአገር ደረጃ መሻሻል እንዲደረግባቸው በተለያዩ አግባቦች ላለፉት አርባ ዓመታት እና ከዛም በላይ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ጉዳዮችን ብልጽግና በዚህ መድረክ ምላሽ ከሰጠ “አጀንዳ አልባ እንሆናለን” በማለት ለሚዲያ ዘመቻ በጀት ያሰራጨው ይህ መድረክ ከቅዳሜ በኋላ ምን ይል ይሆን? ተከታዮቻቸውን ምን ብለው ያሳስቱ ይሆን? የምክክር አባላቱ በድህንነቶች ታፈኑ ያሉ ሚዲያዎች “ይቅርታ የታፈነ የለም” በማለት ሃፍረታቸውን ይፋ አደረጉ። መሳይ መኮንን በሰበር ዜና “የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኦህዴድ አስፈራቷቸው ኮበለሉ” በማለት ባጯጯኸበት ልክ ባይሆንም ይቅርታ በማለት ሃፍረቱን አሳየ። ስምምነት ስላለነበር የተሰበሰበን ጉባኤ “ተወዛገበ” በማለት ቀደም ሲል ስምምነት ኖሮት አሁን ለመወዛገብ እንድተሰበሰቡ አድርገው ሲያቀርቡ የከረሙ ሚዲያዎች ከቅዳሜ በኋላ ሌላ የመስከረም የትርምስ አጀንዳ እየናፈቁ ይቆያሉ። ለመረጃ እስካሁን የሆነው ይህ ነው። ሲቋቋም፣ በዛው ዕለት “እንፈርሳለን አሉ” ያሉ ሚዲያዎችም የዚህ ታሪክ አባላት ናቸው።

አዲስ ሪፖርተር — በኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይት ከሚመከሩባቸው ስምንት አጀንዳዎች መካከል በሀገር ግንባታ አጀንዳ ሥር በብሔራዊ ቋንቋ፣ በፌዴራል የሥራ ቋንቋ፣ በሰንደቅ አላማና በብሔራዊ መዝሙር ዙሪያ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ይኑራት ወይስ አይኑራት፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ስንትና የትኞቹ ይሁኑ፣ የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማና አርማ እንዲቀጥሉ ወይም እንዲሻሻሉ፣ እንዲሁም ብሔራዊና የክልሎች መዝሙሮች በምን መልኩ እንዲቀጥሉ የሚሉ ጉዳዮች በተመካካሪዎች መካከል በስፋት ተነስተዋል።

በውይይቱ ሂደት ከስምንቱ ቡድኖች የተመረጡ 120 አባላት ያሉት አዘጋጅ ቡድን በተለያዩ ቡድኖች የቀረቡትን ምክረ ሀሳቦች በማሰባሰብ፣ ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ሀሳቦችን በማጣጣምና በማስወገድ አንድ የተጠናቀረ ሰነድ አዘጋጅቷል። ይህ ሰነድ እያንዳንዳቸው 500 ተመካካሪዎችን ለያዙት ስምንቱ ቡድኖች ቀርቧል።

በዚህ ደረጃ የቀረቡት ሀሳቦች የተመካካሪዎችን ልዩ አመለካከቶች ወደ አንድ የጋራ ምክረ ሀሳብ ለማምጣት የተደረገ ሂደት እንጂ የመጨረሻ የሕግ ወይም የፖሊሲ ውሳኔ አለመሆኑ ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ቋንቋ አያስፈልግም የሚል ምክረ ሀሳብ

በብሔራዊ ውይይቱ የቋንቋ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች አንዱ ሆኗል። ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ሊኖራት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጥያቄ ተመካካሪዎችን ሲያከራክር መቆየቱ ተገልጿል።

በዚህ ውይይት አንድ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲኖር ከተሰጡ ሀሳቦች መካከል አማርኛ ወይም አፋን ኦሮሞ እንዲመረጡ የሚሉ ምክረ ሀሳቦች ነበሩ። ሆኖም የተጠናቀረው የውይይት ሰነድ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ቋንቋ እንደማያስፈልግ የሚለውን ሀሳብ አስቀምጧል።

በተሳታፊዎች የተገለጸው መረጃ መሠረት “በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ብሔራዊ ቋንቋ አያስፈልገንም” የሚለው ሀሳብ የበላይነት አግኝቷል። በቀጣይ ግን ብሔራዊ ቋንቋ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ካሉት የሀገሪቱ ቋንቋዎች መካከል በተገቢው መስፈርት ተመርጦ እንዲወሰን የሚል አማራጭም ቀርቧል።

ይህ ምክረ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት አንድን ቋንቋ ከሌሎች ቋንቋዎች ለይቶ ብሔራዊ ቋንቋ ከማድረግ ይልቅ የቋንቋዎችን ብዝሃነት በመጠበቅ ለወደፊት አማራጭ እንዲቀመጥ የሚል አቅጣጫ ነው።

አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ

የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ጉዳይ በብሔራዊ ውይይቱ ሌላው ዋነኛ የክርክር ነጥብ ሆኗል። በተለያዩ የውይይት ደረጃዎች አምስት ቋንቋዎች እንዲሆኑ እስከ 13 ቋንቋዎች ድረስ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል። በተጠናቀረው የውይይት ሰነድ ግን አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። እነዚህም አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ሶማሊኛ ናቸው።

በተመካካሪዎች የቀረበው ሀሳብ እነዚህ ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችም በተወሰነ መስፈርት መሠረት ወደ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሊገቡ የሚችሉበት አሠራር እንዲዘረጋ ነው።

በዚህ መሠረት ቋንቋዎች በተናጋሪዎቻቸው ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስፈርቶችም እየተመዘኑ ለወደፊት የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የሚያስችል አቅጣጫ እንዲቀመጥ ቀርቧል። ከተጠቀሱት ቋንቋዎች መካከል ወላይትኛ፣ ሲዳምኛ፣ ጉራግኛ፣ ከምባትኛ፣ አገውኛ፣ ከፊቾ/ከፍኛ እና ጋሞኛ ይገኙበታል።

ይህም በአንድ ጊዜ የሥራ ቋንቋ የሚሆኑትን ቋንቋዎች በመወሰን ሌሎችን ቋንቋዎች ከሂደቱ ውጭ ከማድረግ ይልቅ፣ በቀጣይ የሚያሟሉት መስፈርት ተወስኖላቸው የሥራ ቋንቋ ሊሆኑ የሚችሉበት አማራጭ እንዲኖር የሚል ነው።

የሰንደቅ አላማ ጉዳይ እና የአርማ ለውጥ ሀሳብ

የሰንደቅ አላማ ጉዳይም በብሔራዊ ውይይቱ ከፍተኛ ውይይት ከተደረገባቸው የሀገር ግንባታ ጉዳዮች አንዱ ነው። በውይይቱ ወቅት አሁን ያለው ሰንደቅ አላማ እንዲቀጥል፣ አርማው እንዲቀየር ወይም አዲስ አርማ እንዲዘጋጅ የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል። ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል የሕዳሴ ግድብ፣ የዓድዋ ድል፣ እርግብና ሌሎች ምልክቶች በአርማው ላይ እንዲካተቱ የሚሉ ሀሳቦች ነበሩ። በኋላ በተጠናቀረው ሰነድ ላይ ግን “አሁን ያለው ይቀጥል፣ አርማው በአካታች መልኩ ለወደፊት ይታይ” የሚል ሀሳብ ቀርቧል።

“አካታች በሆነ መልኩ” የሚለው ሀሳብ የአርማውን ለውጥ በአንድ ቡድን ወይም በአንድ ወቅት ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ሕዝቡ በቀጣይ በሂደቱ ተሳትፎ እንዲያደርግና እንዲወስን የሚል መሆኑ ተገልጿል። በዚህም የሰንደቅ አላማው መሠረታዊ ቅርጽ በአሁኑ ወቅት እንዲቀጥል እያለ የአርማው ጉዳይ ግን ለወደፊት በሕዝብ ተሳትፎ እንዲታይ የሚል አቅጣጫ ቀርቧል።

ብሔራዊ መዝሙሩ እንዲቀጥል

በብሔራዊ መዝሙር ጉዳይም የተለያዩ ሀሳቦች በውይይቱ ወቅት ተነስተዋል። በዛሬው የውይይት ውሎ ግን “አሁን ያለው ብሔራዊ መዝሙር እንዳለ ይቀጥል” የሚል ምክረ ሀሳብ መቅረቡ ተገልጿል። የክልሎች መዝሙሮችን በተመለከተም መዝሙሮቹ እንዲቀጥሉ ነገር ግን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በአካታች መልኩ እንዲያንጸባርቁ ተመክሯል። በመዝሙሮቹ ውስጥ ያለአስፈላጊነት የገቡ፣ የሌሎችን መብት ሊነኩ ወይም ግጭትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሀሳቦች ካሉም እንዲታረሙ የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። ይህም የክልሎች መዝሙሮች እንዲኖሩ እያለ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን የማይገልሉና የሌሎችን መብት የማይጋፉ እንዲሆኑ የሚል አቅጣጫ መሆኑ ተገልጿል።

ከስምንቱ አጀንዳዎች የተሰበሰቡ ሀሳቦች ለ4 ሺሕ ተሳታፊዎች ይቀርባሉ

በሀገር ግንባታ አጀንዳ ላይ ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ባሻገር በሌሎች የብሔራዊ ውይይቱ አጀንዳዎችም ተመካካሪዎች የተለያዩ ሀሳቦችን አቅርበዋል። እነዚህ ሁሉ ምክረ ሀሳቦች በአንድ ሰነድ ተጠናቅረው ከተደራጁ በኋላ በተሳታፊዎች እንዲገመገሙ ተደርጓል። ከዚህ በኋላ የተጨማሪ አስተያየቶች ካሉ እንዲካተቱ ተደርጎ የመጨረሻው ሰነድ እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል። የተጠናቀረው ሰነድ በቀጣይ ለ4 ሺሕ ጉባዔተኞች ቀርቦ ከተመከረበት በኋላ የመጨረሻ ሰነድ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህም ማለት በአሁኑ ውይይት የቀረቡት የብሔራዊ ቋንቋ፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማና የመዝሙር ሀሳቦች የመጨረሻ ውሳኔዎች ሳይሆኑ ወደፊት ለሚደረገው የውይይትና የውሳኔ ሂደት መነሻ የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።

በተለይ የቋንቋ ጉዳይ በኢትዮጵያ ያለውን የብዝሃነት እውነታ በማገናዘብ እንዲታይ፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎችም ከአሁኑ አምስት ቋንቋዎች ባሻገር በተቀመጠ መስፈርት ሌሎች ቋንቋዎች የሚጨመሩበት አማራጭ እንዲኖር በምክረ ሀሳቡ ተካቷል። በተመሳሳይ የሰንደቅ አላማና የመዝሙር ጉዳዮችም በአካታችነትና በሕዝብ ተሳትፎ እንዲታዩ የሚሉ አማራጮች ቀርበዋል።

በመጨረሻም፣ የብሔራዊ ውይይቱ ሂደት በርካታ አጀንዳዎችን በማስተናገድ ወደ መጨረሻ ምክረ ሀሳብ የማዘጋጀት ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በቋንቋ፣ በሀገራዊ ምልክቶችና በሌሎች የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ የቀረቡት ሀሳቦች ግን በቀጣይ በ4 ሺሕ ጉባዔተኞች የሚመከሩና የሚጠናቀቁ በመሆናቸው የመጨረሻ አቋም ተደርገው የሚወሰዱ ሳይሆን “መንግስት ሆይ ይህ ምክር አሳብ ቀርቦልሃል” ብሎ ከማሳሰቢያ ጋር ማስረከብ ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related