“አዲስ አበባን ኦሮሞ ዘረፋት? እውነቱን ልንገራችሁ” ተሳታፊ አባል The Truth About Addis Ababa: A National Dialogue Panelist’s

Date:

የቀረበውን ጽሑፍ ይዘትና መልእክት ሳይለወጥ፣ የፊደልና የሰዋሰው ግድፈቶች (ስፔሊንግ፣ የቃላት ጥረት እና የሥርዓተ-ነጥብ ግድፈቶች) ተአርመው እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል፦

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — የጻፍኩት ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የማውቀውን፣ የገባኝን እውነትና እውነት ብቻ ነው። የተመካከርነው፣ ወይም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመመካከር የተቀመጥነው ከበፊት ጀምሮ የተከመሩ ያላግባቡን፣ ከለመግባባት አልፎ እያጋደሉን ያሉ፣ እንዲሁም ዘወትር ስጋት ላይ ስለነበርን ነውና ከብዙ ልዩነቶች ጥቂት ጉዳዮች ባያግባቡ አይገርምም። አራትና ሦስት ጉዳዮች ላይ ከመግባባት አለመደረሱ ዜና እንኳን ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም ድሮም አላግባቡንምና። እንደ እኔ እምነት በርካታ ጉዳዮች ላይ የተወሰዱ አቋሞች ድንቅ ናቸው። መግባባት ላይ ባለመደረሱ ይበልጥ እንዲሰራባቸው ምክረ-ሐሳብ በተለያዩ አማራጮች በማቅረብ የተጠናቀቀን ጉባኤ ማንቋሸሽ ወይም ጭራና ቀንድ እያበጁ ማራከስ ልክ አይመስለኝም። መጀመሩ በራሱ ታላቅ ነው። ውጤቱም አኩሪ ነው። የጎደሉትን በቀጣይ በማሟላት ጅምሩ ድል ይበልጥ ሙሉ ይሆናል። እናም ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ግጥም አድርጋ አሸንፋለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት በሀገራችን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ እንደ ሌላ “አድዋ” ሊቆጠር የሚችል ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ነው። ለአምስት ዓመታት ገደማ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግበት የቆየው፣ ከታች ከማህበረሰቡ መገኛ ጀምሮ ወደ ላይ አጀንዳዎችን ያሰባሰበው ይህ ሂደት፣ 4,000 ተመካካሪዎችን በማሳተፍ ለ46 ቀናት የፈጀ ጥልቅና ታሪካዊ ውይይት አስተናግዷል። ይህ ሂደት ለትውልዳችን የተከፈተ ልዩ አሻራና የብሩህ ተስፋ መሰረት ነው።

ከዚህ ታላቅ መድረክ የተገኘው ከምንም በላይ የላቀው ድል፣ በአዲስ መልክ የዳበረው የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ የማይነገሩ፣ መነጋገር የማይቻልባቸው እና ለማንሳት የሚያሸማቅቁ በርካታ ጉዳዮች በግልጽ ወደ መድረክ መጥተዋል። ተመካካሪዎች በነፃነት ተነጋግረዋል፣ ተከራክረዋል፣ ተጨቃጭቀዋል፤ ነገር ግን አንዱ የሌላውን ህመም በመረዳትና ራስን በሌላው ጫማ ውስጥ በማስገባት፣ ከብዙ ፍጥጫ በኋላ በመቀራረብ ወደ መሃል መምጣት ችለዋል። ይህ እርስ በርስ የመተሳሰብ ባህል የሀገራችን የሰላም ጽኑ መሰረት ነው።

ይህንንም ተከትሎ በመድረኩ ከቀረቡት ከ400 በላይ ምክረ-ሐሳቦች ውስጥ፣ 396ቱ ሀገራችንን ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት በሚያመራ መልኩ በታላቅ ስምምነትና በአንድነት መንፈስ የጋራ መግባባት ተደርሶባቸዋል። አንድ አይነት ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው እና ለቀጣይ ውሳኔ በአማራጭነት የተያዙት አራት ዋና ዋና አጀንዳዎች ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም በሚከተለው መልኩ በዝርዝር ቀርበዋል፦

1ኛ – የመንግስት አወቃቀር ሥርዓት፦

ሀገራችን አሁን እየተከተለችው ባለው የፓርላማ ሥርዓት (Parliamentary System) እንዲቀጥል ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ መራሔ-መንግሥቱን በተመለከተ “ጠቅላይ ሚኒስትር” የሚለው ቀርቶ፦

  • አማራጭ አንድ፦ ከፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዚዳንት ይሁን የሚል እና፣
  • አማራጭ ሁለት፦ በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጥ ፕሬዚዳንት ይሁን የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት።

2ኛ – የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነት ውክልና፦

  • አማራጭ አንድ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በቀጥታ በሕዝብ ምርጫ የሚወከሉበት አሰራር ይዘርጋ
  • አማራጭ ሁለት፦ አሁን ባለው የአወካከል ሥርዓት ይቀጥል የሚሉ 2 አማራጮች የቀረቡበት።

3ኛ – የሰንደቅ ዓላማ አርማ፦

በሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ልዩነቱ ያለው በመሃል ላይ በሚኖረው አርማ ላይ ነው። በዚህም፦

  • አማራጭ አንድ፦ አሁን ያለው አርማ እንዳለ ይቀጥል
  • አማራጭ ሁለት፦ አርማው በጥናት ተሻሽሎ ይፅደቅ የሚሉ ሁለት አማራጮች ናቸው የቀረቡበት።

4ኛ – የአዲስ አበባ ጉዳይ፦

በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይም ከቀረቡት በርካታ ነጥቦች ውስጥ በአብዛኛዎቹ ላይ ፍጹም መግባባት የተፈጠረ ሲሆን፣ በጣም በጥቂት ጉዳይ ላይ ብቻ አማራጭ ሐሳብ ቀርቧል።

በቅድሚያ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች፦

አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት (የኢትዮጵያ) ርዕሰ ከተማ መሆኗን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እና ነፃነት እንዳለው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት እንደሚሆን፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወከሉ ሲሆኑ፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ተጠቅሶ የነበረው የኦሮሚያ ከአዲስ አበባ “ልዩ ጥቅም” ታገኛለች የሚለው ሐረግ አሁን በተደረገው ውይይት ተቀይሮ “የጋራ ተጠቃሚነት” በሚለው እንዲተካ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ የአፍሪካ፣ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱና የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗን ሁሉም ተመካካሪዎች በሙሉ ድምፅ ተስማምተውበታል።

ልዩነት ተፈጥሮ በአማራጭነት የተያዘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው። ይኸውም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆኗ በፌዴራል ሕገ-መንግሥቱ ውስጥ እንዴት ይካተት በሚለው ላይ ነው፦

  • አማራጭ አንድ፦ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ፣ በአስተዳደርና በአገልግሎት የተሳሰረች በመሆኗ እንዲሁም ላለፉት 35 ዓመታት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አዲስ አበባ ሆና ስላገለገለች ይህ በፌዴራል ሕገ-መንግሥቱ ላይ በግልጽ ይጠቀስ የሚል፣
  • አማራጭ ሁለት፦ የኦሮሚያ ከተጠቀሰ የሁሉም ክልል ዋና ከተማ በፌዴራል ሕገ-መንግሥቱ ላይ በግልጽ ይጠቀስ (ይካተት) የሚሉ ሁለት አማራጮች የቀረቡበት ናቸው።

እነዚህን ጥቂት በአማራጭነት የተያዙ አጀንዳዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው የአዲስ አበባን ጉዳይ ነጥሎ በተዛባ መልኩ የሐሰት መረጃ በመሰራጨቱ ትክክል አይደለም። አጉል ትርምስ ለመፍጠርና የሌሎችን የሚታወቁትን አካላት ፍላጎት በጓሮ ለማሳካት የሚደረግ ሩጫ እንደሆነ በመረዳት አደብ መግዛቱ ይመረጣል። ከላይ የቀረቡት አማራጮች “ለምን ቀረቡ” ከሆነ፣ ስብሰባው ዓላማው እንዲህ መሰል አከራካሪ ጥያቄዎች ከጠብመንጃ በራቀ በወረቀትና በሰነድ እንዲቀርቡ ማድረግ በመሆኑ፣ ነገም ከነገወዲያም የተለያዩ ሐሳቦች መነሳታቸው አይቀርምና “መልመድ ይበጃል” የተባለውን ተረት ማስታወስ እወዳለሁ። ከዚህ ውጭ ምንም ጉዳይ መወሰን በማይችል ኮሚሽን ጥያቄ ቀረበ ብሎ አገር ያያዝ ማለት የምክክሩንም አውድ የሚያስት ስለሆነ በዚሁ ቢስተካከል ለማለት እወዳለሁ።

እነዚህ አማራጮች ከጥቃቅን የቡድን ውይይቶች ጀምሮ 500 ተሳታፊዎች እስከነበሩበት መድረክ ድረስ የተደረጉ ክርክሮች፣ የቃለ-ጉባኤ ጽሑፎች፣ እንዲሁም የድምፅና የምስል መረጃዎች በሙሉ ተፈትሸው የትኛው አማራጭ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ይጠቅማል የሚለውን በጥልቀት በመመዘን እና አብዛኛው ተወያይ የደገፈውን አማራጭ ለይቶ የምክክር ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጠው አሰራር መሠረት የመጨረሻውን የውሳኔ ሐሳብ ለመንግሥት እንደሚቀርብ ገልጿል።

እውነታው ግን ይህ ነው፦ የምክክር ሂደቱ እና የተሳታፊዎቹ ውይይት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በቃለ ጉባኤ፣ በቪዲዮ እና በምስል በአግባቡ የተሰነደና በታሪክ ማህደር የተቀመጠ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል! ይህ የምክክር ሂደት የተራራቀውን ያቀራረበ፣ የጠነከረውን ያለዘበ እና ለጋራ መግባባት በሩን ወለል አድርጎ የከፈተ ታሪካዊ የድል ብሥራት ነው። እንዲህ ዓይነት ታላቅ ሀገራዊ መድረክ ተፈጥሮና በርካታ አጀንዳዎች ላይ ከዳር እስከ ዳር ስምምነት ተደርሶ ሳለ፣ “እኔ ካልሰራሁት”፣ “የኔ ፍላጎት ብቻ ካልተሟላ” ወይም «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል» በሚል ኋላቀር እና አፍራሽ አስተሳሰብ በማህበራዊ ሚዲያ የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት የምክክሩን ሂደትና የሕዝቡን ስኬት ለማጠልሸት የሚሞክሩ አካላት ድርጊት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሊወገዝ የሚገባው ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርስ በመደማመጥና በመከባበር ትልቅ ድል አስመዝግቧል። ይህንን የተወሳሰበ ሀገራዊ ሂደት በስኬት እንድናጠናቅቅ፣ በሕዝቦች መካከል የመግባባት መንፈስን ላሰፈነ እና ኢትዮጵያውያንን ለዚህ የድል ምዕራፍ ላበቃ ፈጣሪ አምላክ የላቀ ምስጋና ይገባዋል።

— ገዛህኝ (ከምክክር ተሳታፊዎች አንዱ)

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“እንደ ልጅ ተጫውቼ አላውቅም፣ መጫወት ናፍቆኛል፣ የቻለ ተከዜ ገባ፣ የቻለ ወጣ፣ ያለቀው ብዙ ነው …”ትንሿ ልጅ

አዲስ ሪፖርተር – “እንደ ልጅ መጫወት ናፈቀኝ፤ ተጫውቼ አላውቅም”...