አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ መንግስታት፣ በተለያዩ ኃላፊዎች የተለያየ መልክ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ስማቸው ጎልተው ከሚጠሩ ተቋማት መካከል አንዱና ምን አልባትም ከፊት ተርታ የሚሰለፍ ነው።
ይህ ታሪካዊ ተቋም ባለፉት በርካታ አሥርታት ውስጥ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመደገፍ፣ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ የመንግሥትና የግል አገልግሎቶችን በማቀላጠፍ እንዲሁም ለሚሊዮኖች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ያበረከተው ሚና እጅግ የጎላ እንደሆነ ይገለጻል።
በተለይም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ዋና አስተዋጽኦ የሚያበረክት አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን ሲያገለግል ይገኛል።
የክፍያ ሥርዓቶችን በዘመናዊ የዲጂታል አማራጮች ከመተካት ጀምሮ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የንግድ እና የባንክ ዘርፎችን በዘመናዊ የመረጃ መረብ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ረገድ ተቋሙ የማይተካ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ይገለጻል። ይህ ግዙፍ ተቋም የቀጣዩ አድማስ የሦስት ዓመት ስትራቴጂ የመጀመሪያ ዓመት አፈጻጸም እና ውጤቶችን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም የሚተገበረው የሦስት ዓመት የቀጣዩ አድስ ስትራቴጂ የመጀመሪያ ዓመት አፈጻጸም በስኬት መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የአንደኛውን ዓመት አፈጻጸምና የሁለተኛውን ዓመት ዕቅድ አስመልክተው በሰጡት አጠቃላይ መግለጫ፣ በ2018 የበጀት ዓመት ተቋሙ 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።
ይህ የተመዘገበው ገቢ የተቋሙን የዓመቱን ዕቅድ 99.7 በመቶ ማሳካት ያስቻለ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀደመው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33.2 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚሁ የበጀት ዓመት የኩባንያውን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር 90.12 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የዓመቱን የደንበኞች ቁጥር ዕቅድ 101.7 በመቶ ማሳካቱን አመልክተዋል።
የቴሌብር የዲጂታል ገንዘብ እንቅስቃሴን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ኩባንያውን ከተለምዷዊ የድምፅና የመልእክት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት ወደ ዘመናዊና ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ ተቋምነት (TechCo) የመሸጋገር ሂደቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ ተጠቅሷል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ማብራሪያ፣ የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ፤ የዲጂታል አገልግሎቶችን እና የዲጂታል ፋይናንስ ተደራሽነትን በሰፊው ማስፋፋት፤የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን ወደ አሠራር ሥርዓቱ ማካተት፤የሥራ ቅልጥፍናን፣ የአገልግሎት ጥራትን እና የደንበኞችን እርካታ ማደግ፤የሰው ኃይል ልማትን ማበልጸግ እና የሰራተኞችን አቅም መገንባት፤ዘላቂና አካባቢን ያገናዘበ የድርጅት ዕድገትን ማረጋገጥ።
ይህ ስትራቴጂ ከቁጥራዊ እና ከገንዘብ ነክ ውጤቶች ባሻገር ሰው ተኮር ልማትን ማዕከል ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በስትራቴጂው የሦስት ዓመት ሙሉ የትግበራ ዘመን ውስጥ በሀገሪቱ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ለመፍጠር ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የ2019 በጀት ዓመት የገቢ፣ የታክስ እና የውጭ ምንዛሬ ግቦችን በተመለከተ እንደተገለጸው
ተቋሙ በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን ወደ 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን ይፋ አድርጓል። ይህ ለማሳካት የታቀደው የገቢ መጠን ከቀደመው የበጀት ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ36.7 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ለዚህ የገቢ ዕድገት ዋነኛ ምንጭ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውና ከፍተኛውን ድርሻ 34.6 በመቶ የሚይዘው የዳታ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚሆን ተመላክቷል። የድምፅ አገልግሎት ደግሞ 20 በመቶ ድርሻ በመያዝ ሁለተኛው ዋና የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ተገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እና ለበጀት ገቢ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ በተመለከተ
በበጀት ዓመቱ 83.8 ቢሊዮን ብር ግብር እና ታክስ ለነፃ ገቢ ባለስልጣን ለገቢዎች ሚኒስቴር ለመክፈል ማቀዱ፤ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ለአክሲዮን ባለድርሻዎች እና ለስቴት ዲቪደንድ ለማከፋፈል መታቀዱ ተጠቅሷል።
ኩባንያው የውጭ ምንዛሬ የማመንጨት አቅሙን ለማጠናከር ሰፊ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም መሰረት ዓለም አቀፍ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎቶችን እንዲሁም የመሠረተ ልማት መጋራት አሰራሮችን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትስስር ማጠናከር ተልዕኮ ተይዟል።
በዚህም መርሃ ግብር በበጀት ዓመቱ 253.7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም እስከ 33 ቢሊዮን ብር የማይክሮ ብድር ለመስጠት አቅዷል
ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 ዓ.ም. የሚያስፈጽመው የ“Next Horizon: Digital & Beyond 2028” ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ አማካይነት የቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በማስፋፋት እስከ 33.08 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የማይክሮ ብድር ለማቅረብ አቅዷል።
ዕቅዱ ከግለሰቦች በተጨማሪ ለአነስተኛ ንግዶች የዲጂታል ብድር ተደራሽነትን ማስፋፋትን ያካትታል። በዕቅዱ መሠረት የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 67.69 ሚሊዮን እንዲደርስ ታቅዷል።
በተጨማሪም የቴሌብር ግብይቶች ዓመታዊ ዋጋ 7.4 ትሪሊዮን ብር እንዲደርስ እና የግብይቶች ብዛትም 4.99 ቢሊዮን እንዲደርስ ኩባንያው ግብ አስቀምጧል። የዲጂታል ቁጠባንም ከ18.75 ቢሊዮን ወደ 26.42 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዷል።
ይህም የቁጠባ ባህልን ከማጠናከር ባለፈ ለዜጎችና ለአነስተኛ ንግዶች የመደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የታለመ ነው።
የመሠረተ ልማት፣ የኔትወርክ አቅም እና የቴክኖሎጂ ዘመናዊነት ማስፋፊያ ዕቅዶች በተመለከተም
በአዲሱ የበጀት ዓመት የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ እና ማዘመኛ መርሃ-ግብርን በተጠናከረ ሁኔታ በመተግበር፣ አጠቃላይ የኔትወርክ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ማሳደግ የሚያስችል አቅም ይገነባል። በዚህም የተቋሙ አጠቃላይ ደንበኞችን የመሸከምና የማስተናገድ አቅም ወደ 135.7 ሚሊዮን ከፍ ይላል ተብሏል።
ለዚህም ስኬት በበጀት ዓመቱ ውስጥ 1,628 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች የሚገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 605 ያህሉ በገጠራማ፣ በራቁት እና የቴሌኮም አገልግሎት አነስተኛ በሆነባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚተከሉ መሆናቸው ተገልጿል።
የኔትወርክ ቴክኖሎጂን ከማሳደግና ከመተካት አንጻር የተያዙ ዝርዝር ዕቅዶች
የ4ጂ አገልግሎትን ለተጨማሪ 300 ከተሞች ተደራሽ በማድረግ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውን ከተሞች ቁጥር ወደ 1,500 ማሳደግ፤
የ4ጂ የኔትወርክ ሽፋን መጠኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ 95 በመቶ ማድረስ፤
የ4ጂ አውታረ መረብ ተጠቃሚዎችን የማስተናገድ አቅም ወደ 35.31 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ።
የ5ጂ አገልግሎትን ለተጨማሪ 40 ከተሞች በመዘርጋት አጠቃላይ የ5ጂ አገልግሎት የሚያገኙ ከተሞችን ቁጥር ወደ 83 ማሳደግ፤
የ5ጂ የማስተናገድ አቅምን ከነበረበት 0.41 ሚሊዮን ተጠቃሚ ወደ 2.70 ሚሊዮን በእጥፍ በላይ ማሳደግ ይገኝበታል።
በአገልግሎት ጥራት በኩል ከቴክኖሎጂ ዘመናዊነትና ከመሳሪያዎች አለመናበብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የኔትወርክ መቆራረጦችንና ፍጥነት መቀነስን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመቅረፍ መስራት፤
150 ሺህ ደንበኞችን ከአሮጌ የኮፐር መስመር ወደ ተሻለና ፈጣን የፋይበር ቴክኖሎጂ ማሸጋገር፤
የከተሞችን የፋይበር መስመር ዝርጋታ በ300 ኪሎ ሜትር በማስፋፋት አጠቃላይ የፋይበር መረብ አቅምን ከ15 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ማድረስ። ይህ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የመሠረተ ልማት ማሻሻያ የደንበኞችን ወቅታዊ ፍላጎት ያገናዘበ ነው።
የደንበኞች የአጠቃቀም ባህሪ ቀደም ሲል ከነበረው መረጃዎችን የመመልከትና የማውረድ ፍላጎት፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ የቪዲዮ፣ የዳታ እና የፋይል ይዘቶችን የመጫን፣ የማስተላለፍና በቀጥታ ስርጭት የማስተላለፍ ፍላጎት ጋር ለማጣጣምና ለማስማማት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአዲሱ የበጀት ዓመት አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር ከአሁኑ 90.1 ሚሊዮን ወደ 96.2 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደ ሲሆን፣ የቴሌብር የዲጂታል ገንዘብ መተግበሪያ ደንበኞቹን ደግሞ ከ67 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ ግብ አስቀምጧል።
ቴሌብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ 9 ትሪሊየን ብር የገንዘብ ዝውውር የተካሄደበት ሲሆን፣ በ2019 የበጀት ዓመት ዕቅድ ብቻ በቴሌብር የሚደረገውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ወደ 7.40 ትሪሊየን ብር ለማሳደግ ታቅዷል።
ደንበኞች አሁን ላይ ቴሌብርን ከቀደመው ጥቃቅን የገንዘብ ዝውውር ባለፈ ለከፍተኛ የንግድ ክፍያዎች፣ ለደመወዝ፣ ለግብር እና ለግዥዎች ጭምር በሰፊው እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ያመለከቱት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት በቴሌብር ላይ የተቀመጠው የዕለታዊና የነጠላ ገንዘብ ዝውውር ገደብ ክፍተቶችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ከደንበኞች፣ ከንግድ ተቋማት እና ከአገልግሎት ተቀባዮች ተደጋጋሚ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌብር የዲጂታል ገንዘብ ማንቀሳቀሻ መተግበሪያ ላይ የተቀመጠውን የገንዘብ ዝውውር ገደብ ለማንሳት ወይም ከወቅቱ የንግድና የገበያ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ እንዲሻሻል ለማድረግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የበላይ አመራሮች ጋር ድርድርና ውይይት ለማድረግ ማቀዳቸውን አስረድተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






