አቶ በረከት ስምዖን ሰሞኑን ኢትዮሪቪው ባቀረበችው ዜና ላይ ተንተርሰው መልስ መስጠታቸውን ከኢትዮፎረም ለመረዳት ተችሏል። “እውነት እኔ እንዲህ የምል ይመስላችኋል?” በማለት ስማቸው በተነሳበት ዜና መልኩ “እንደማይንቦራጨቁ” መናገራቸውም በዚህ ምላሽ በተባለው መልዕክት ተመልክቷል።
አቶ በረከት ስማቸው ተጠቅሶ ዜና የተሠራው በኢትዮሪቪው ሆኖ ሳለ ለምላሹ ለምን ኢትዮፎረም እንደተመረጠ ወይም እንደተመረጠላቸው በዘገባው አልተገለጸም። ራሱ ሚዲያውም ያለው ነገር የለም።
ኢትዮፎረም፣ በስም ባይጠቅስም፣ ኢትዮሪቪውን “የብልጽግና ቀለብተኛ’ በማለት እየፈረጀና እያጣጣለ “የአቶ በረከት ምላሽ” ሲል ያቀረበው ሪፖርት የተላከው ከአቶ በረከት “ልጆች” እንጂ ከሳቸው አንደበት እንዳልሆነ አመልክቷል። በቀረበው የማስተባበያ ሪፖርት አቶ በረከት የኮሙኒኬሽን ሳይንቲስት፣ የሕዝብ ግንኙነት ጠበብት፣ ምንግዜም ሊረሱ የማይችሉ የዘርፉ አይተኬ ባለሙያና የተማሪዎቻቸው ሁሉ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል።
ብአዴንን “የአማራ ሕዝብ ወኪል ፓርቲ ነው” በሚል ከትግል ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአመራር እርከኖች በመምራት ሳይነኩ የቆዩና ቱባ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ በረከት በለውጡ ማግስት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በሹመት ቤተመንግሥት መግባታቸው አይረሳም።
በ1997 ዓ.ም የኢህአዴግ የምርጫ አዝማች ሆነው በቅስቀሳ ዓቅም ማጣትና ባዘጋጇቸው የፓርቲው ተከራካሪዎች ደካማነት ሳቢያ እርሳቸውን ጨምሮ በየመድረኩ በመዘረራቸው ጓድ መለስ በመሩት የድርጅቱ ጉባኤ የግምገማ ዱላ ወርዶባቸው እንደነበር ስብሰባውን የተሳተፉ ያስታውሳሉ።
በዚሁ ጓድ መለስ በመሩት የሃዋሳው የድርጅቱ ጉባዔ ላይ የምርጫ 97ን ውድቀት ተከትሎ በታየው የቅስቀሳ ችግር ሳቢያ በእነ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ አርከበና በመካከለኛ አመራሮች የተወቀሱት አቶ በረከት እዚያው ጉባዔ ላይ ነበር “ቀሽም የፕሮፓጋንዳ አዝማች” ተብለው ከኃላፊነት የተነሱት። ይህም በግልጽ በዓቅም ማነስ መነሳታቸው እንደ ሪፖርተር ባሉት ሚዲያዎችና በመንግሥት ተቋማት መዘገቡ አይዘነጋም።
በቅንጅት የምርጫ ክርክር ወቅት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “በቃን” ያሉ ዜጎችን “ቦዘኔዎች፣ ቦዘኔ ለውጥ አምጥቶ አያውቅም” ብለው ነበር። በበረከት ልጆች “የኮሙኒኬሽን ልሒቅ” የተባሉት አቶ በረከት። በዚህም ንግግራቸው መላው በሚባል ደረጃ የሕዝብ ቁጣ ነድዶባቸው የነበሩት አቶ በረከት፣ አሜሪካ በግል ከሚግባቡት የትህነግ ሰው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው ስለ አገሪቱ ፖለቲካ የተነጋገሩትን ነበር ኢትዮሪቪው “የበረከት ትዝብት – ከቆይታ በሁዋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ መሬት ይቀያየራሉ” በሚል ርዕስ የተዘገበው።
ይህ የግል ወዳጃቸው አሁን ላይ ያለውን የትህነግ እንቅስቃሴ ባይደግፍም በአጠቃላይ ግምገማቸው በመበሳጨቱ ተናዶ ለኢትዮሪቪው የአሜሪካ ተባባሪ የሰማውን አጫውቶ ነበር። በመረጃው መሠረት ኢትዮሪቪው ሪፖርት አቅርባለች። የኢትዮሪቪው የአሜሪካ ተባባሪ በታማኝ ሪፖርቶቹ የሚታወቅ፣ የውጭ ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ ምንጮች ያሉት ስለመሆኑ ለሚረዱ ዜናው ጥርጥር ውስጥ የሚከት አይደለም።
ይሁን እንጂ ሪፖርቱ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና ድረገጾች፣ እንዲሁም የዩቲዩብ ዐውዶች በሥፋት መሰራጨቱ “የሌቦች ስብስብ ሆኗል” ለተባለው የትህነግ አንዱ አንጃ አስደሳች እንዳልሆነ የኢትዮሪቪው የመረጃ ሰዎች ማስተባበያው ሳይወጣ አስታውቀውን ነበር።
በቅብብል የሰሞኑ አጀንዳና ገዢ ጉዳይ ሆኖ የሰነበተው የአቶ በረከት ግምገማ በውጭ የእነ አቶ ስብሃትን ቡድን፣ በአገር ቤት የዚሁ ቡድን ሴል የሆነው የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን አስኮርፏል። አስቆጥቷል። በዚሁ ሳቢያ ነው ማስተባበያ እንዲሠራ የተወሰነው።
ሪፖርቱ የትህነግ የበላይ ባለቤቶቹን፣ በትህነግ ሥር ያሉ ሚዲያዎችን፣ ደጋፊዎችንና በተለይም አቶ በረከትን በሚጠሉ ዘንድ ባለመወደዱ፣ አቶ በረከት እንዲያስተባብሉ በሚቀርቧቸው ሰዎች አማካይነት ግፊት ለማድረግ ቢሞከርም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሌላ የማስተባበያ መንገድ መፈለጉን የአሜሪካ ተባባሪያችን አስቀድሞ መረጃ ደርሶት ነበር።
በዚሁ ምክንያት “አቶ በረከት ስምዖን ምላሽ ሰጡ” ያሉ ክፍሎች ብቅ እንዲሉ ተደረገ። እነዚህ ራሳቸውን “የበረከት ልጆች ነን” ሲሉ የጠሩ ክፍሎች አቶ በረከትን ወክለው ምላሽ ሰጥተዋል። ራሳቸውን በራሳቸው ከመወከላቸው በስተቀር አቶ በረከት በእርግጥም እነሱን ስለመወከላቸው በማስተባበያው ሃተታ ላይ ምንም አልተባለም።
አቶ በረከትን ምጡቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሳይንስ ጠቢብ፣ ለፕሮፓጋንዳ ዓይናቸውን በጨው አጥበው መድረክ ላይ የሚተውኑ ካድሬዎችን በማምረት ረገድ ወደር የሌላቸው፣ እነሱም በዚህ አግባብ የሳቸው የእጅ ሥራ ውጤት ተደርገው መፈጠራቸውን ያልሸሸጉ ክፍሎች ኢትዮሪቪው ያወጣችው ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላ “እንዴት አባታችን ይህን ይናገራል” በሚል ሲብሰለሰሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ከዚያም በላይ አቶ በረከት ተናገሩት በተባለው ጉዳይ እንቅልፍ አጥተው መክረማቸውን ደጋገመው ይናገራሉ።
እነዚሁ የአቶ በረከት የፕሮፓጋንዳ ሎሌዎች መሆናቸውን ከማስታወቅ ውጪ ስማቸውን ያልጠቀሱ ሦስት የአቶ በረከት “ልጆች” አራት ኪሎ ለመመለስ ከሚሠሩ ህዋሶች ወገን መሆናቸውንም ለምላሽ ባዘጋጁት ዘገባ ላይ ገልጸዋል። እንግዲህ እነዚህ “መንግሥትን እስከምናስወግድ አንተጋለን” ያሉት ክፍሎች ናቸው አቶ በረከትን በመከላከል በሚል ትህነግ ላይ የተሰጠውን ግምገማ ለማስተባበል “በልጅነት” ስም ብቅ ያሉት።
በዚህ ዘገባ “ህዋስ” የተባሉት በገሃድ ራሳቸውን ያልገለጹት እነዚህ ቡድኖች “ሦስት ልጆቹ ነን” ሲሉ መሰየማቸው ብቻ ሳይሆን፣ “ሦስቱ የበረከት ልጆች” ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው የብልጽግና መንግሥት ውድቀት የሚያውጁና አድራሻቸው የማይታወቅ በመሆኑ ነው። ከዚህም በላይ ራሳቸው አቶ በረከት ዓላማቸውን የማይደግፉላቸው መሆኑ ነው። ምክንያቱም ኢትዮሪቪው ባላት መረጃና አቶ በረከት አሜሪካ ከገቡ በኋላ፤ መንግሥትን ለመጣል ከትህነግ ባለቤቶች የቀረበላቸውን ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል። ከለውጡ ቀደም ሲል ጀምሮ በገሃድ ትህነግ/ኢህአዴግ እንዳበቃለት ጽፈዋል። አደባባይ ተናግረዋል።
“ምስለኔ” ሆነው በተቆርቋሪነት “እርሳቸውን በስልክ ጠይቀናል” ሲሉ ምላሽ የሰጡት የበረከት ልጆች፣ የመረጡት ሪፖርቱ ያልታተመበትን ሚዲያ ኢትዮፎረምን ነው። ለምላሽ ኢትዮፎረም መመረጡ ተባባሪያችን እንደሰማው መረጃ ከሆነ የትህነግ ሰዎች ደስተኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ነው። ኢትዮፎረም ሚዲያውና የሚዲያው አዘጋጆች ራሳቸው ስነድ አዘጋጅተው “የብልጽግና ሰነድ እጃችን ገባ” በማለት የዳበረ ተደጋጋሚ የሽምጠጣ ልምድ ስላላቸው፣ እንዲሁም ያቋቋማቸው ይኸው ያኮረፈው የእነ አቶ ስብሃት ቡድን በመሆኑ ምክንያት በለመደው አግባብ ድርሰት እንዲያዘጋጅ ታዝዞ ነው።
ራሳቸውን የ“ፕሮፓጋንዳ አባታቸው” ጠበቃ አድርገው በ“ልጅነት” ሥልጣን “አባታችን እንዴት ስምህ ተነሳ? እውነት ይህ ብለሃል እንዴ?” በሚል ጭንቀትና ተቆርቋሪነት ስልክ በመደወል መረጃ መሰብሰባቸውን አመልክተው ነው ምላሹን ያዘጋጁት። “የበረከት ልጆች” ሰጡት የተባለው ማስተባበያ በአቶ በረከት በኩል በግልጽ የቀየረው ነገር አልተሰማም።
በረከት የሚናገሩበትን ከዐውዱ ጋር የማይገጥም፣ ይልቁኑም አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሚቀጠቅጥ የቆየ የቪዲዮ ዲስኩር ታጅቦ የቀረበው የኢትዮፎረም ምላሽ በርካታ ጉዳዮችን አግተልትሏል።
አቶ በረከት በዜናው ውስጥ አንድም ቦታ ስማቸው ያልተነሳውን አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ንጉሡ ጥላሁን እያነሱ ሲዘልፉ የነበረበትን የቆየ ቪዲዮ እንደ መረጃ በመጠቀም ኢትዮፎረም ማቅረቡ ዜናውን ለማስተባበል ከተሞከረው በላይ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮፎረም አቶ ደመቀና አቶ ንጉሡን ነቅሶ የሚቀጠቅጥበትና የሚያስቀጠቅጥበት ዋና ምክንያት ወደፊት በዝርዝር ይቀርባል።
“ልጆቹ” [ትህነግ] ለምን ኢትዮፎረምን መረጡ? በረከትስ ኢትዮፎረምን ይመርጣሉ?
በዩቲዩብ ገጹ ላይ “ዓላማው ጋዜጠኝነትን መተግበር ብቻ ነው። ግቡ ድምፅ አልባ የሆኑ ዕውነቶችን ድምፅ እንዲኖራቸው አድርጐ ለሕዝብ ማድረስ ነው” ሲል ያስቀመጠው ኢትዮፎረም ENN በሚል ስም በትህነግ አውራዎች መመሪያ ከወቅቱ የደህንነት መዋቅር ጋር በመሆን በ፣እቶ ሚሊዮኖች ብር ተመድቦለት እንዲቋቋም ተመቻችቶለት የነበረ ሚዲያ እንደነበር በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም።

ከትግራይ ሚዲያ ሃውስ በፊት በመንግሥት በጀት ከኢቲቪ ጎን ለጎን እንዲሰራ ትህነግ የመሠረተው ይህ ሚዲያ፤ በመካከሉ ለውጡ መጣና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አይሆንም” በማለታቸው ሳቢያ ዕቅድ ብቻ ሆኖ ቀረ። ተዋንያኖቹም ብሩ እጃቸው ሳይገባ፣ ከኢቲቪ ጎን ለጎን እነ አቶ ስብሃት ነጋን የሚያገለግል ሚዲያ ለመክፈት የወጠኑት የጋራ ዕቅድ መክሸፉን በወቅቱ በርካቶች ዝርዝር መረጃ አቅርበውበት ነበር።
ይህ ሕልመኞች ከፍተውት የነበረው ሚዲያ ስንዝር ሳይጓዝ በመክሸፉ ቁጭትና ንዴት ተዳምረው ኢትዮፎረም እንዲወለድ ሆነ። ኢትዮፎረም ሲመሠረት ጀምሮ ዓላማው የሚታወቅ በመሆኑ በቅርብ የሚያውቁት፣ በተለይም በኢቲቪ ውስጥ የነበሩ ምሥጢሩን በአደባባይ ስም እየጠሩ አጋልጠውት ነበር።
ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ኢ.ኤን.ኤን. ቴሌቪዥን ጣቢያ በበጀት ችግር ሳቢያ ስርጭቱን እንደሚያቋርጥ መገለጹ የሚታወስ ነው። በወቅቱ በጀት በመከልከሉ 110 የሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞቹን በይፋ አሰናብቶ ነበር። የዛሬው ኢትዮፎረም በወቅቱ በትህነግ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራ ነበር።
ኢኤንኤን ከስርጭት ስለሚወጣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ ለጣቢያው መስጠት አቆሙ። በመመሪያ ስፖንሰር ሆነው የነበሩት ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ በድንገት ውላቸውን አቋረጡበት። በዚህም ሳቢያ ገቢው ነጠፈ።
ጣቢያው በትህነግ ሰዎች መመሪያና የጎንዮሽ ግንኙነት ከዳሽን ባንክ በብድር ሊያገኝ የነበረው 500 ሚሊየን ብር ብድር በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ተቋረጠበት። ለመነሻ የተፈቀደለት ብር ቀሪ ክፍያ ቆመበት።
ኢኤንኤን በሃገሪቱ ሕዝባዊ ተቃውሞ በተፋፋመበት ወቅት ሁከት አባባሽና “ብሔር ከብሔር ለማጋጨት የሚቀሰቅስ” ዘገባ በማቅረብ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር። ሐሰተኛ ምስል መጠቀሙና ዘገባው የተላለፈበት ሰዓት ተዳምረው ጣቢያው “ስውር ተልዕኮ አለው” የሚል ውንጀላም እንደቀረበበት ዋዜማ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
በትህነግ አመራሮች የተቋቋመውና በዶክተር ደብረጺዮን ቦርድ አመራርነት ሲተዳደር የነበረው ኢኤንኤን ለውጡ እንጥሉን ስለመታው በበቀል ዋናዎቹን ይዞ በኢትዮፎረም ስም ከሙያ ስነምግባር ውጪ የሚሠራ፣ በተለይም በኅልውናው ጦርነት ወቅት መከላከያና ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከፍቶ የነበረ ሚዲያ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃ ማቅረብ እንደማያስፈልግ በርካቶች ይስማማሉ።
ኢትዮፎረም በውል የሚታወቀው ራሱ ሰነድ አዘጋጅቶ፣ ራሱ “በምሥጢር የተዘጋጀው ሰነድ እጃችን ገባ” በሚል ተውኔቱ እንደሆነ በስፋት የሚያውቁት በተደጋጋሚ የሚናገሩት ጉዳይ ነው። ራሱ ያዘጋጀውን ሰነድ አረፋ እየደፈቀ የሚተፋ፣ ለዲጂታል ወያኔ በተዋረድ የቅጥፈት ሰነድ እየተዘጋጀ የሚረጭበት፣ በኩርፊያ ሽንት ተጸንሶ፣ በኩርፊያ ማኅጸን ውስጥ ፋፍቶ፣ በክፋት አዋላጆች አማማጭነት የተወለደ፣ በክፋት ልሂቃን የሰለጠነ፣ ከሚዲያ ስነምግባር ጋር የማይተዋወቅ፣ ትህነግ ወደ ሥልጣን እስኪመለስ የክፋት እሣተ ጎመራ እንዲተፋ ሆኖ የተፈጠረ የእርመኞች ስብስብ እንደሆነ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የሚያውቁት በስፋት የሚናገሩት የስብሃት ነጋ አሽከር ሚዲያ ነው። አፈጣጠሩ ይህ ሆኖ ሳለ “ዓላማው ጋዜጠኝነትን መተግበር ብቻ ነው” በሚል ይመጻደቃል።
በረከት ተናገሩት የተባለው መረጃ የተሰራጨው በኢትዮፎረም አልነበረም። አቶ በረከት ለሚቀርቡት የሚዲያ ሰው ያወሩት ወይም ያጫውቱት በኢትዮ ሪቪው ተዘግቦ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በዩቲዩቡ ዐውዶች፣ በተለያዩ ዘመን አመጣሽ የመገናኛ አማራጮች ሁሉ መነጋገሪያ የሆነ ሪፖርት ለምንና እንዴት በኢትዮፎረም በኩል ማስተባበያ እንዲቀርበበት ተወሰነ? ለሚለው ኢትዮፎረም ምክንያቱን አላስታወቀም።
ይሁን እንጂ ከላይ አጠር ተደርጎ የቀረበው አፈጣጠሩ በአቶ በረከት በኩል ተመርጦ ሳይሆን ጋላቢዎቹ አዘውት፣ በፈጠራ የአቶ በረከትን ሽንት ተውሶ፣ ሦስት መንታ ልጆች ወልዶላቸው፣ ልጆቹን በአቶ በረከትን አባትነት ሰይሞ፣ በቅጥፈት ሰነድ ዝግጅት ልምዱ በ“ልጅነት ሥልጣን” ራሱን በመቀባት ያዘጋጀው ማስተባበያ እንደሆነ ለመረዳት ጠቢብ መሆን የሚጠይቅ አይሆንም። ልምዱም፣ ወጉም፣ አፈጣጠሩም ይህንኑ ያስረዳል።
“አቶ በረከትን ቢናገሩ እንኳን እንዴት በብልጽግና ሚዲያ ይናገራሉ?” በሚል የሚጠይቁት የአቶ በረከት ልጆች ኢትዮሪቪውን በተቀላቢነት ማንጓጠጣቸው ሳይሆን ገለልተኛ ሚዲያ ለመምረጥ የደከሙት ድካም ማድነቅ አስፈጋጊ እንደሆነ በርካቶች በምጸት ሲናገሩ ተሰምቷል። የኢትዮሪቪው የአሜሪካ ተባባሪ አቶ በረከት መናገር እንኳን ቢፈልጉ በምንም መስፈርት ኢትዮፎረምን እንደማይመርጡ ወዳጃቸው አጫውቶታል። ምክንያቱም አቶ በረከትና ትህነግ ካሁን በኋላ የጋራ ነገር አይኖራቸውምና።
ከመንም በላይ አቶ በረከት “ENN ግጭቶችን በማባባስ ኢህአዴግ እንዲወድቅ መንገድ ከፍቷል ወይም አባብሷል” የሚል ግምገማ እንደነበራቸው እና ዚሁ ድምዳሜያቸው ሳቢያ
“ጋዜጠኛ” የሚባሉት የእነ አቶ ስብሓት አንደበቶች፣ ጥርስ የነከሰባቸው በመሆኑ እነሱን መርጠው ምንም ዓይነት መረጃ እንደማይሰጡ በቅርብ ስለ ኝኙነታቸው የሚያውቁ ይመስክራሉ።
በረከት ስምዖንን በአሜሪካ ለሚጠመቀው የሤራ ፖለቲካ ተባባሪ እንዲሆኑ የትህነግ ቁንጮዎች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አልተሳካላቸውም። በተደጋጋሚ በረከትን እንደማይወዱ በአደባባይ የሚናገሩት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ በአቶ በረከት ላይ ጥርስ ነከሰው ስለቆዩ “ሌቦች፣ የሌቦች ስብስብ” ተብለው መጠራታቸው ከኖረው ቂም ጋር ተዳምሮ ቁጣ ፈጥሯል። ይህ ነው ኢትዮፎረምን የማስተባበያ ድርሰት እንዲረጭ ዋነኛ የሆነው ምክንያት።
ሦስቱ “ልጆች” የተባሉት “በረከትን በስልክ ስንጠይቃቸው በሰሞኑ ጉዳይ ተስፋ ቆርጠው፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ መከታተል አቁመው ነው ያገኛናቸው” ብለዋል። አክለውም “በስማቸው ስለወጣው ዘገባ ስንጠይቃቸው ‘እናንተ ምን አላችሁ’ አሉን” ማለታቸውን ኢትዮፎረም ገልጿል።
እውነታው ይህ ከሆነና የኢትዮጵያን ፖለቲካ መከታተል ካቆሙ፣ ኢትዮሪቪው ላይ የተጻፈውን ዜና ጠቅሰው ሲጠይቋቸው፣ አቶ በረከት “ምን ተፈጠረ? ምን ተባለ?” በሚል መጠይቅ ነበረባቸው። ወይም “አዎ እኔ እንኳ መከታተል ስላቆምሁ ሰው ነግሮኛል” ማለት ነበረባቸው። ይህም ካልሆነ፣ ኢትዮፎረም እንዳለው በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ ከቆረጡ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እርግፍ አድርገው ከተውት ምንም ሊሰሙ አይችሉምና “እንዲህ ብለዋል” ተብለው ሲጠየቁ አቶ በረከት “ሊንኩን ላኩልኝና ላንብበው ይሉ ነበር” የሚል የአመክንዮ መከራከሪያ የሚያነሱ ውሸት ስለማይደገም “ኢትዮፎረም የድርሰቱ ባለቤት መሆኑን ማሳያ ነው” ይላሉ።
“ኢትዮ ፎረም” ገና “ለውጡ” በመጣ ማግስት ከሚያዝያ 2010 ጀምሮ የቀድሞው የኢትዮጵያ የመረጃ እና የደኅንነት ተቋም አባላት ከትህነግ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት፤ ከ“ለውጡ” በፊት “ENN” ይባል ከነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የተመለመሉ ሁለት ወጠጤ “ጋዜጠኞችን” ከፊት አሰልፎ አንዴ ከአዲስ አበባ፣ ሌላ ጊዜ ከመቐለ አሁን ደግሞ ከአውሮፓ ከተሞች “በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ልብ ወለድ ዘገባዎችን” (black propaganda) ያለማቋረጥ እያሰራጨ ይገኛል፤ ሲሉ አቶ ኦሉማ የተባሉ ጸሐፊ በቅርቡ መረጃ ማጋራታቸው አይዘነጋም።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






