ባለፉት ጥቂት ቀናት በሰሜን ምስራቅ ድንበር በኩል “አዲስ ወረራ” (Incursion) መፈጸሙን መጥቀሱ ጉዳዩን ከተራ የድንበር ውጥረት ወደ “ቀጥተኛ የታጠቀ ጥቃት” (Armed Attack) ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያስገነዝባሉ። ይህ ዓይነቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተባበሩት መንግስታት የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ 3314 መሰረት እንደ “ወረራ” (Aggression) የሚፈረጅ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በቻርተሩ አንቀጽ 51 መሰረት ያላትን “ራስን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት” (Inherent Right to Self-Defense) ለመጠቀም የሚያስችላትን ሕጋዊ መሰረት እንደሚያጠናክርላት ምሁሩ ይተነትናሉ።
አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገድዮን ጢሞቴዎስ ለኤርትራው አቻቸው የላኩት ደብዳቤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማክረር ወደ ግጭት እንዳያመራ በሚል ብዙዎችን ስጋት ውስጥ ጥሏል።
ደብዳቤው በዋነኝነት የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ እየፈጸመ ነው ያላቸውን ተከታታይ ጥሰቶች በዝርዝር ያቀርባል። የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ግዛት ወሮ መቆየቱን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ቀጥተኛ የቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን የሚገልጸው ይህ ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥሰቶች እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ጥሪ ብታደርግም የኤርትራ መንግስት ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱን በቅሬታ ያነሳል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የኤርትራ መንግስት ግጭቱን ወደ ከፋ ደረጃ የሚያሸጋግር (further escalation) መንገድ መምረጡን ደብዳቤው ያመለክታል። የኤርትራ ጦር በሰሜን ምስራቅ የኢትዮጵያ ድንበሮች በኩል አዲስ ወረራ (incursion) መፈጸሙ እና በሰሜን ምዕራብ በኩል ከአማጽያን ቡድኖች ጋር የጋራ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ እነዚህን ድርጊቶች ተራ ትንኮሳ ሳይሆኑ “ግልጽ የወረራ ተግባራት” (acts of outright aggression) ስትል ፈርጃቸዋለች። ይህም ለተፈጠረው “ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ” አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ፣ የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ግዛት በአስቸኳይ እንዲያስወጣ እና ከአማጽያን ጋር ያለውን ትብብር እንዲያቆም የሚጠይቅ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንዲከተል አድርጓል።
ደብዳቤው ወታደራዊ ውጥረቱን ወደ ዘላቂ ሰላም ለመለወጥ የሚያስችል ስልታዊ የድርድር አማራጭ ያቀርባል። የኤርትራ መንግስት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክብር የሚሰጥ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የአሰባን ወደብ አጠቃቀምና የባህር ጉዳዮችን (access to the sea through the port of Assab and maritime affairs) ጨምሮ በሁሉም የጋራ ጥቅሞች ላይ በቅን ልቦና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል። ይህ የሰላም ጥሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የግጭት አዙሪት ሰብሮ ወደ አዲስ የትብብርና የብልጽግና ዘመን ለመሸጋገር የቀረበ “የመልካም ፍላጎት መግለጫ” (good will gesture) ተደርጎ ተቀምጧል።
አዲስ ሪፓርተር የዚህ ደብዳቤ ይዘት በሁለቱ ሃገራት መካከል ስለሚፈጥረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት፣ ደብዳቤው ከዓለም አቀፍ ህግ እና በቀጠናው የጂኦፓቲካ የሃይል አሰላለፍ አንፃር አንድምታው ምን ሊሆን እንደሚችል አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የድሬድዋ ዩንቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አለቃው ዳርጌ እና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲቱዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ደኮተር ደረጀ ደገፍን አስተያየ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል።
ደብዳቤው ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ሲፈተሽ
ረዳት ፕሮፌሰር አለቃው ድርጌ የደብዳቤውን ይዘት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በመገምገም የሰጡት አስተያየት፣ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ላይ ወታደራዊ ይዞታ መፍጠሩን ደብዳቤው መጥቀሱ ጉዳዩን በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2(4) ስር ወደሚወድቅ ቀጥተኛ የሕግ ጥሰት እንደሚወስደው ያስረዳሉ። የሕግ ምሁሩ እንደገለጹት፣ አንድ ሉዓላዊ ሀገር የሌላን ሀገር ድንበር ጥሶ መያዙ በዓለም አቀፍ ሕግ “ሕገ-ወጥ ይዞታ” (Illegal Occupation) ተብሎ የሚፈረጅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህ ጥሰት እንዲታረም በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጓን መግለጿ ነገ ለሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ሕጋዊ ቅድመ-ሁኔታን (Legal Precondition) የማሟላት ሂደት አካል ተደርጎ ይወሰዳል።
በሁለተኛው ነጥባቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ ደብዳቤው ባለፉት ጥቂት ቀናት በሰሜን ምስራቅ ድንበር በኩል “አዲስ ወረራ” (Incursion) መፈጸሙን መጥቀሱ ጉዳዩን ከተራ የድንበር ውጥረት ወደ “ቀጥተኛ የታጠቀ ጥቃት” (Armed Attack) ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያስገነዝባሉ። ይህ ዓይነቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተባበሩት መንግስታት የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ 3314 መሰረት እንደ “ወረራ” (Aggression) የሚፈረጅ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በቻርተሩ አንቀጽ 51 መሰረት ያላትን “ራስን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት” (Inherent Right to Self-Defense) ለመጠቀም የሚያስችላትን ሕጋዊ መሰረት እንደሚያጠናክርላት ምሁሩ ይተነትናሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር አለቃው ከሕግ አንፃር ሌላው ትኩረት የሚሻው ነጥብ ኤርትራ ለታጣቂ ቡድኖች “ቀጥተኛ የቁሳቁስ ድጋፍ” (direct material assistance and support) እየሰጠች መሆኑ በደብዳቤው መገለጹ እንደሆነ ያብራራሉ። ይህ ተግባር በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (International court of Justice) የኒካራጓ ብይን መሰረት፣ አማፅያንን ማሰልጠንና ማስታጠቅ እንደ “ሕገ-ወጥ የኃይል አጠቃቀም” የሚቆጠር በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ክስ በይፋዊ ደብዳቤ ማቅረቧ ኤርትራ ለምታደርገው ድርጊት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ተጠያቂነትን (State Responsibility) እንድትሸከም የሚያደርግ ሕጋዊ ጫና እንደሚፈጥር ምሁሩ ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ምሁሩ የኤርትራ መደበኛ ጦር ከአማፅያን ጋር “የጋራ ወታደራዊ ልምምድ” (joint military maneuvers) ማድረጉን የሚገልጸው ነጥብ፣ ኤርትራ አማፅያኑን እንደ መደበኛ የጦር ክንፏ እየተጠቀመችባቸው መሆኑን እንደሚያመለክት ያስረዳሉ። እንዲህ ዓይነቱ ትብብር ኢትዮጵያ የኤርትራን መንግስት ለአማፅያኑ ድርጊት በቀጥታ ተጠያቂ እንድታደርግና ለጥቃቱም ተመጣጣኝ ወታደራዊ ምላሽ እንድትሰጥ ሕጋዊ መብት የሚሰጣት ሲሆን፣ ደብዳቤው ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትወስደው እርምጃ “ሁሉንም ሰላማዊ የሕግ መንገዶች ተጠቅመን ነበር” የሚል የሕግ የበላይነት እንድትይዝ ያስችላታል።
በአጠቃላይ የኤርትራመንግስት ወታደሮቹን ከአሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት በአስቸኳይ እንዲያስወጣ የቀረበው ጥሪ አፋጣኝ መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ ጉዳዩ ወደ ተሟላ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ሙህሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በደብዳቤው ላይ “ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ” ስትል የገለጸችውና ጦሯን እንድታወጣ የጠየቀችው ጥሪ፣ ኤርትራ ለምትፈጽመው ማንኛውም የወረራ ተግባር (acts of outright aggression) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን የሚያሳይ እንደሆነ ምሁሩ ትንታኔያቸውን ያጠናቅቃሉ።
የዲፕሎማሲና የጂኦፓለቲላካ አንድምታ
አየውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ደረጀ፣ ደብዳቤው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ከመደበኛ የዲፕሎማሲ ንግግር አውጥቶ ወደ “መጨረሻ ማስጠንቀቂያ” (Ultimatum) ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው። ኢትዮጵያ በደብዳቤው ላይ የኤርትራን ድርጊት “ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ” (unacceptable state of affairs) በማለት መግለጿ፣ የዲፕሎማሲያዊ ትዕግስት ገደብ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሰላም መስመር እጅግ እየጠበበ መምጣቱን የሚያመለክት እንደሆነ ተመራማሪው ያስረዳሉ።
እንዲሁም ኢትዮጵያ “በቅን ልቦና ለመደራደር” (engage in good faith negotiations) ዝግጁ መሆኗን መግለጿ ስትራቴጂካሊ የዲፕሎማሲ የበላይነት (Moral High Ground) ይሰጣታል ይላሉ። ይህ አካሄድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግጭቱን ሲመለከት ኢትዮጵያን እንደ ሰላም ፈላጊ፣ ኤርትራን ደግሞ በሰሜን ምስራቅ ድንበር በኩል “አዲስ ወረራ” የፈጸመች (incursion) እና ግጭትን የምታባብስ ወገን አድርጎ እንዲፈርጃት የሚያስገድድ ዲፕሎማሲያዊ ስልት እንደሆነ ተመራማሪው ያብራራሉ።
ዶክተር ደረጀ በስፋት የጠቀሱት ሌላው ቁልፍ ነጥብ፣ የአሰብ ወደብን እና የባህር ጉዳዮችን (Access to the sea and maritime affairs) ከደህንነት ስጋቱ ጋር አቆራኝቶ ማቅረብ የደብዳቤው ዋነኛ ጂኦፓለቲካዊ ግብ መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ የኤርትራን ወታደራዊ ጫና እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ የቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ ብቻ መሆኑን በድርድር ጠረጴዛው ላይ ማስቀመጧ፣ የቀይ ባህርን ጂኦፓለቲካ ሚዛን የሚቀይር ብልህ አካሄድ መሆኑን ዶክተሩ ይጠቁማሉ።
ተመራማሪው የኤርትራ መደበኛ ጦር ከአማፅያን ጋር “የጋራ ወታደራዊ ልምምድ” (joint military maneuvers) ማድረጉ በዲፕሎማሲው መድረክ ኤርትራን “የቀጠናው ስጋት” አድርጎ ለመፈረጅ እንደሚረዳ ያስረዳሉ። ይህ መረጃ በይፋዊ ደብዳቤ መውጣቱ፣ እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ያሉ ዓለም አቀፍ ተዋንያን በኤርትራ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያደርጉና የኢትዮጵያን ራስን የመከላከል እርምጃ በበጎ እንዲመለከቱት በር የሚከፍት እንደሆነ ገልፀዋል።
ዶክተር ደረጀ ሃሳባቸውን ሶያጠቃልሉ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ደብዳቤ እንደ “መልካም ፍላጎት መግለጫ” (good will gesture) አድርጎ ማቅረቧ ታሪካዊ ኃላፊነትን በኤርትራ ላይ የሚጭን እንደሆነ ይገልጻሉ። ኤርትራ ወታደሮቿን ከአሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት በማስወጣት ወደ ድርድር ካልመጣች፣ የምትመርጠው “የማባባስ መንገድ” (path of further escalation) ለሚከተለው ማንኛውም ወታደራዊ መዘዝ ተጠያቂው የኤርትራ መንግስት ብቻ እንደሚሆን ደብዳቤው በዲፕሎማሲያዊ ቃላት አስሮ መልዕክት ማስተላለፉን ገልፀዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አለቃው ድርጌ የሕግ መቃኛቸውን፣ ዶክተር ደረጀ ደግሞ የዲፕሎማሲ ስልት ትንታኔያቸውን መሠረት በማድረግ፤ የሁለቱን ምሁራን ዕይታ በማነጻጸር ቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሀኔታዎችን መገመት ይቻላል።
የመጀመሪያው በቀጣይ ቀናት ኤርትራ ወታደሮቿን የማታስወጣ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በመውሰድ ኤርትራን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማግለልና የማዕቀብ እርምጃ እንዲወሰድባት ግፊት ልታደርግ ትችላለች።
ሁለተኛው፣ ዶክተር ደረጀ ደብዳቤው የአሰብ ወደብን እንደ ድርድር አጀንዳ ማቅረቡን እንደ ትልቅ ስልታዊ ዕድል ይመለከቱታል። ሆኖም ረዳት ፕሮፌሰር አለቃው እንደሚጠቁሙት፣ ኤርትራ በአማፅያን በኩል የምታደርገውን “የውክልና ጦርነት” እና የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የማታቆም ከሆነ፣ የሰላም ድርድሩ የመሳካት ዕድሉ አነስተኛ ነው። በዚህም ምክንያት፣ ኤርትራ ለሰላም ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጠች፣ በድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት (Direct Armed Conflict) የመቀየር ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ምሁራኑ ይስማማሉ።
ሶስተኛ ሁለቱም ምሁራን እንደሚስማሙት፣ ይህ ውጥረት የአፍሪካ ቀንድንና የቀይ ባህርን ጂኦፓለቲካ የሚቀይር ነው። ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትንና የሰላም አማራጭን ይዛ መቅረቧ፣ እንደ አሜሪካና የዓረብ ሀገራት ያሉ ቀጠናዊ ተዋንያን ኤርትራ ላይ ጫና እንዲያደርጉ በር ይከፍታል። በቀጣዩ ጊዜ፣ እነዚህ ኃይሎች ግጭቱን ለማርገብና ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የአሰብ ወደብን ያካተተ “ሁለገብ ስምምነት” ወደ ተግባር ለመቀየር አደራዳሪ ሆነው ሊመጡ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።
ቀጣዩ ጊዜ የሚወሰነው በኤርትራ ምላሽ ላይ ነው። ኤርትራ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ካልመጣች፣ የረዳት ፕሮፌሰር አለቃው የሕግ ትንታኔ እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል እርምጃ መውሰዷ የማይቀር ሲሆን፤ ዶክተር ደረጀ እንደሚሉት ደግሞ ይህ እርምጃ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ይኖረዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






