የድልም የሽንፈትም ዜማ ያልተሰማበት “ኦፕሬሽን ሸረሪና”፤ ከጀርባው ያዘለው ዕቅድ መዳረሻ የት ነበር? “ማስፋት” ወዴትና ለምን? – ከሸረሪናና ግዴማ ዲፖ የተገኘው መሳሪያ ልዩ ሪፖርት

Date:

የሸረሪና ኦፕሬሽን ባለቤት ማን ነው? የድልም ሆነ የሽንፈት ዜና በየትኛውም ወገን በይፋ በዝርዝር ያልቀረበት ይህ ኦፕሬሽን፣ ይዞታን በማስፋት አንዱ ወገን ወደ ሁመራ፣ ከጀርባ ደጀን ሆኖ የሚጥብቀው ኃይል ይህ ያሰበው ከተሳካለት ያሰፋውን አካባቢ ለሱዳንና ሻዕቢያ አስረክቦ ውስን ኃይሉን ከጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጥቂት ታጣቂዎች ጋር በጉሙዝ በኩል በመንደርደር ይዞታውን ማስፋት ነበር። ሸረሪና እና ግዴማ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ዲፖና ከመሬት በታሽ በተዘጋጀ ኮንክሪት በተከማቸው ከባድ የጦር መሳሪያ ፣ ከፍተኛ ሎጂስቲክ እና አስፈላጊ ቁሶች አመቻችቶ የነበረው የትህነግ ኃይል፣ ኦፕሬሽኑን ከመጀመሩ በፊት ከአሜሪካና ካናዳ ወደ ሱዳን ያቀኑ የጋራ መደረኩ ታጣቂ አፈ ቀላጤዎችና አመራሮች ነበሩ። ትህነግ በመግለጫ፣ የአገር መከላከያ በዝምታ ያለፉት ኦፕሬሽን ማን በስኬት ላይ እንዳጠናቀቀው የሚረዳው ነገሩ የገባቸው ብቻ ናቸው።

አዲስ ሪፖርተር (አዲስ አበባ) – “ምዕራብ ትግራይ” ተብሎ ከተሰየመበት ጊዜ አንስቶ የባለቤትነት እና የማንነት ጥያቄ ሲያስተናግድ በኖረው አካባቢ፣ በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ጠርዝ ላይ የሚገኘው አውላላ የልማት ሜዳ ሸረሪና ይባላል። በጦርነቱ ወቅት የሱዳን ኃይሎች ዘልቀው ገብተው የያዙት ይህ ስፍራ፣ ከቆይታ በኋላ የትህነግ ኃይሎች መቀመጫ / ቤዝ እንደሆነ ስለ አካባቢው የሚያውቁ ይናገራሉ።

“በኃይል የተቀማነውን፣ በኃይል አስመልሰናል” በማለት የአማራ ክልል ወልቃይት፣ ጠገዴና ሴቲት ሁመራን ማስተዳደር ከጀመረ አንስቶ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በትግራይ ኃይሎች ስር በቆየው ሸረሪና፣ ትህነግ ከአልቡራን መንግስት ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት አካባቢውን ልዩ የጦር ቤዝ አድርጎት ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይፋ በሆነው “ጽምዶ” በተሰኘ ህብረት የተሰባሰቡ ታጣቂዎች ማዕከል የሆነው የሸረሪና የጦር ማዘዣ፣ ቂጡን ወደ ሱዳን አድርጎ ገባ ወጣ የሚል ግጭት አልፎ አልፎ ያስተናግድ ነበር። ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት የሱዳን ኃይሎች ተቆጣጥረውት የነበረው ይህ ቦታ፣ ወደ ሱዳን በሸሹ የትህነግ ሰራዊት አባላት፣ በሰላም ማስከበር ደቡብ ሱዳን በነበሩ የትግራይ ተወላጅ መኮንኖች፣ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤርትራ እያቆራረጡ ወደ ሱዳን በሚያመሩ የተለያዩ የአርሚ አደረጃጀት ታጣቂዎች በቅጡ ተገንብቶ ነበር። ግጭቱን በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች የመሳሪያና የሎጂስቲክ ሙሉ ድጋፍ ሜካናይዝድ ኃይልም ነበረው። እንግዲህ የሸረሪናን ኦፕሬሽን ትልቅ የሚያደርገው ከላይ እንደተገለጸው ይህ ነው።

የሸረሪና ኦፕሬሽን ጉዳዩን የያዘው አካል፣ በቪዲዮ፣ በምስክሮችና ዕቅዱን ባሰሉት ባለሙያዎች ተደግፎ በዝርዝር ሲያቀርበው፣ አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ “ከምን ጉድ ወጣን!” የሚያስብል ስለመሆኑ ጥርጥር እንደሌለው እዛው አካባቢ ያሉ የመዋቅር ሰው ለአዲስ ሪፖርተር ሲያስረዱ ከላይ ለመጠቆም የተሞከረውን በመዘርዘር ነው።

በሽርፍራፊ መረጃዎች ስጋና ደም እየተቀላቀለባቸው የወጡት የማህበራዊ ሚዲያ ዜናዎች ከሚገልጹት በላይ በታሪክ የሚመዘገብ ትርጉም ያለው ስራ መሰራቱን ያመለከቱት እኚሁ የአካባቢው መዋቅር ሰው፣ የከሸፈው ሁመራን ለመቆጣጠር የተደረገው ዝግጅት ብቻ ሳይሆን፣ ከጀርባ ወደ ቤኒሻንጉል ቆርጦ ለመግባት የተዘጋጀ ኃይል ፍላጎት ነው የመከነው።

ትግራይን እያስተዳደረ ያለው የትህነግ አንድ ክንፍ ኦፕሬሽኑን “የትግራይን ሕዝብ የማጥፋት ዘመቻ” በማለት ጦርነቱ በተካሄደበት ሌሊት ማለዳ ላይ ቀድሞ መግለጫ በማውጣት በደፈናው “ተነሱ” የሚል ጥሪ ከማቅረቡ ውጭ ስለ ጉዳቱ መጠን ያለው ነገር የለም። ከዛም በኋላ ተደጋጋሚ መግለጫ ሲያወጣ ስለደረሰው ሰብአዊም ሆነ ቁሳዊ ጉዳት ምንም አላነሳም።

በሱዳን የሚገኘው እና ውስን ታጣቂዎች ያሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነጻ አውጪ መሪ አተይብ አሚንን ኦፕሬሽኑ ከመካሄዱ ሁለት ሳምንት በፊት የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ አግኝቶት ነበር። ብዙ መናገር የማይፈልገው የጽምዶ አባል ድርጅት መሪ አተይብ፣ “ከሁለት ሳምንት በኋላ በቤኒሻንጉል በኩል ሰብረን እንገባለን” በማለት በጋራ የማጥቃት ዕቅድ እንዳለው አመልክቶ ነበር።

የግንቦቱ ምርጫ እንዳይከናወን ለማጨናገፍ በሰላማዊ ትግል እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ስም አቶ ነዓምን ዘለቀና አቶ ልደቱ አያሌው አባሎቻቸውን ተቀላቅለው የመሰረቱት የጋራ መድረክ የቅርብ ቀን ስብሰባ ላይ፣ “በትህነግ በኩል ዝግጅቱ አልቋል። ውጊያው መጀመሩ የቀን ጉዳይ ነው፤ የድሮን ጥቃት በመስጋት በጋማ ከብት ነጥብ አካባቢዎች ላይ ሎጂስቲክ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ ነው” በማለት አቶ አባይ ግደይ የሚባሉት የትህነግ ተወካይ መናገራቸውን ዘግበን ነበር። አቶ አባይ በዚሁ መድረክ በተደጋጋሚ ሱዳን እንደሚመላለሱ የሚናገሩና ለኦፕሬሽኖች ቅርብ ስለሆኑ መረጃቸው አንደኛ ደረጃ እንደሆነ ዙሪያቸው ያሉ ይገልጻሉ።

ኦፕሬሽን ሸረሪና

ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ንጋት 12:00 ግድም አርሚ 70፣ አርሚ 15 እና አርሚ 13 በሚል ስያሜ የሚታወቁት የጦር አሃዶች፣ እንደ ወትሮው ሳይሆን ከጀርባቸው በቂ ደጀን ኃይል ተበጅቶላቸው፣ ሜካናይዝድ ኃይል ከፊት አሰልፈው ከሸረሪና ቤዛቸው ሙሉ ጦርነት ለመገጠምና ሁመራን በሰዓታት ጦርነት ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ነው “ቀድሞ መረጃ ነበረው” የተባለው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ በከባድ መሳሪያ፣ ፈጣን፣ የተቀናጀ፣ ከሁሉም አቅጣጫ በሚሰነዘር፣ በአየርና በምድር የተደገፈ ጥቃት የከፈተው።

“ጥቃቱ እንደተጀመረ ሙሉ በሙሉ ሜካናይዝድ ኃይሉን አወደሙት፤ ቀጥለው ከጀርባ ደጀን የቆመውን ኃይል መቱት፤ ከዚያ በኋላ እጅ የሰጠው እጅ ሰጠ፣ ያልታደለውም ህይወቱ አለፈ። አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጠረ” በማለት በአጭር ሰዓት ስለተጠናቀቀው ውጊያ የገለጹት ለስፍራው ቅርብ የሆኑ የመዋቅር ሰው፣ ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ 900 የሚጠጉ የተለያዩ የአርሚ ተዋጊዎች እጅ መስጠታቸውን ገልጸዋል። እጅ ከሰጡት በላይ ህይወታቸው ማለፉንም አመልክተዋል። ያልቻሉት ወደ ሱዳን ሸሽተዋል።


ትሕነግ ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ለመበተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ኃይሎች በግዥና በስጦታ፣ እንዲሁም ቀደም ሲል የቀበረውን መሳሪያ በሸረሪና ግንባር አከማችቶት ማከማቸቱ ቢታወቅም በዚህ ደረጃ ይሆናል ብሎ ያስበ አልነበረም። ይህ ክምችት የአገር መከላከያ ሰራዊት ሸረሪናን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከተደበቀበት ተገኝቷል። ዜናውን ያጋሩን እንደሚሉት፣ ይህ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ትጥቅና ስንቅ ወደ ማዕከል እየተጓጓዘ እንደሆነም አዲስ ሪፖርተር አረጋግጣለች። በሸረሪና ከተደመሰሰውና ከተማረከው የጦር መሳሪያ ባሻገር ከሸረሪና ካምፕ ወጣ ብሎ ግዴማ በተባለች ቦታ መጋዘን ውስጥ እንዲሁም ከመሬት በታች በኮንክሪት በተሰራ ግዙፍ ምሽግ ተከማችቶ የተገኘው ተተኳሽ፣ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ፣ ሮኬት፣ የአጭር እና መካከለኛ ርቀት ሚሳይሎች፣ RPG-7፣ የሳተላይት ስልኮች፣ የሬዲዮ መገናኛ፣ የቅኝት ድሮኖች፣ የመኪና መለዋወጫዎች እና ለጊዜው ምንነታቸውን ለመለየት ያልተቻሉ የጦር መሳሪያዎች ናቸው። አዲስ ሪፖርተር ባላት መረጃ፣ በጥቆማ ከተገኘው ሌላ የመሳሪያ ክምችት ወይም ዲፖ ውጪ በትናንትናው እለት ብቻ ከሸረሪና እና ግዴማ ካምፕ ሰላሳ አንድ ከባድ ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ከተሕነግ ወደ ማዕከል ተጓጉዘዋል። ከግዴማ አቅራቢያ በተሰራ ሌላ የመሳሪያ ማከማቻ ላይ የተማረኩ ባሰጡት መረጃ መሰረት አሰሳና ብርበራ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል።

ይኸው ከሱዳን እግረኛ ጦር፣ ከሱዳን ሚሊሻዎችና ከኤርትራ የሻዕቢያ ሚሊሻ አካላት ጋር በመጣመር በሸረሪና፣ በረከት እና ሁመራ ግንባሮች በድንገት ጥቃት ለመሰንዘር የተነሳ ኃይል፣ ሀገር መከላከያን የጎረቤት አገራትን ኮሪዶር በመጠቀም ከጀርባ የመውጋት እና ድንበር የማደፍረስ ዓላማ እንደነበረው ወታደራዊ ባለሙያዎች አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ላለፉት ስድስት ዓመታት የትሕነግ ዋና ማዘዣና ምሽግ ሆና ስታገለግል የነበረችውን ስትራቴጂካዊዋን ሸረሪናን መነሻ በማድረግ፣ የትሕነግ ክንፍ ከውጭና ከውስጥ አጋሮቹ ጋር በመቀናጀት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የደቀነውን ወታደራዊ ትንኮሳ ሙሉ በሙሉ ማክሸፉ ይፋ ከመሆኑ ውጭ ዜናውን ራሱ ሀገር መከላከያ በዝርዝር አላቀረበም።

እጃቸውን ከሰጡ ታጣቂዎች የሰሙትን እንዲሁም በቅርብ የሚያውቁትን በመዘርዘር ኦፕሬሽኑ ታላቅ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ያመለከቱት አካላት፣ የትህነግ ኃይሎች ሁመራን መቆጣጠር ቢችሉ፣ ከጀርባ ደጀን የሆናቸውን የሱዳን፣ የሻዕቢያ ሚሊሻና የቤኒሻንጉልን ጥቂት ታጣቂዎች በመያዝ በቤኒሻንጉል አቅጣጫ ሰብሮ በመግባት ወደ አሶሳ ማቅናት እንደነበር ጠቁመዋል።

ይህንኑ ዕቅድ እውነት የሚያደርገው ለአዲስ ሪፖርተር የደረሰ መረጃ እንደሚያመልክተው፣ ኦፕሬሽኑ ከመካሄዱ ቀናት በፊት ከአሜሪካና ካናዳ የታጣቂ አፈ ቀላጤ ነን የሚሉና የታጣቂ መሪ የተባሉ ወደ ሱዳን አምርተው ነበር። ወደ ሱዳን ያመሩት አካላት ስም ተዘርዝሮ በጋራ መድረኩ ስብሰባ ላይ ስብሰባ ያልተገኙበት ምክንያት ሲገለጽ ተጠቁሞ ነበር። የተጠቀሱት ሰዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ የፋኖ እና የጋምቤላ ታጣቂዎች የውጭ ክንፎች ነበሩ።

ይህ በሆነ በቀናት ልዩነት ወ/ሮ ፈትለወርቅ የታጣቂዎችን ስም በመዘርዘር አብረዋቸው እንደሆኑ አመልክተው እንደነበር አይዘናጋም። ዶ/ር ደብረጽዮንም “የውጭ ኃይሎች ሳይቀሩ አብረውን ናቸው” በማለት በተመሳሳይ በተለያዩ መድረኮች አመልክተው ነበር። “የሕዝብ ለሕዝብ” የተባለው ግንኙነት በገሃድ የጦር አውድ ጥምረት እንደሆነ ይፋ በሆነበትና “የትግራይ ሕዝብ አትፍራ” ለሚለው ቅስቀሳ በዋለበት ማግስት በሸረሪና የተከናወነው ኦፕሬሽን ዜና ተሰምቷል።

“ለውጭ መንግስታትና ለዲፕሎማሲ ስሙ ይጠቅመናል፤ አገር ቤትም ደጋፊዎቻችን ሲነኩ ለመጮህ ያመቸናል” በሚል ስሌት ራሱን በሰላማዊ ትግል ስም የሚጠራው ስብስብ ላይ በተደጋጋሚ እንደተሰማው ይህ ጦርነት እንደሚጀመር ግልጽ ነበር። አዲስ ሪፖርተርም የስብሰባውን ቅጂ ይፋ በማድረግ በተደጋጋሚ አስታውቃ ነበር።

ትህነግ የቀድሞ ታጣቂዎችን ከተሃድሶና ከዲሞቢላይዜሽን ሂደት እንዲመለሱ በማድረግ፣ አዳዲስ ወጣቶችን በአፈሳ መልክ በማስገባትና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር መሳሪያዎችን በሱዳንና ኤርትራ በኩል ሲያጓጉዝ መቆየቱን ምስክሮች በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ እንደነበርም አይዘናጋም። ከትህነግ የወጡ ከፍተኛ መኮንኖችና አመራሮችም በገሃድ ይህንኑ ሲያረጋግጡ ነው የሰነበቱት።

ትግራይን ከውጭ ዓለም ጋር የሚያገናኝ የሱዳን ድንበር ኮሪደርን የመቆጣጠር፣ ከሱዳን አማፂያን ጋር “ፅምዶ” በተሰኘ ጥምረት እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ፣ በወልቃይትና ሁመራ አቅጣጫ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ መሬት ማስፋት፣ እንዲሁም በትግራይ ውስጥ ያለውን የውስጥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ወደ ውጫዊ ስጋት የመቀየር ዓላማ ብቻ እንዳለው የሚገልጹ የትህነግ ደጋፊዎች “ኦፕሬሽኑ የጽድቅና የፍትህ ነው” በማለት ከህልውና ጋር ያገናኙታል።

ኦፕሬሽኑ የአገር መከላከያ ወይስ የትህነግ የሚለውን ሁኔታውን የገመገሙ ሊወስኑት እንደሚገባ የሚናገሩ የአካባቢው ምስክሮች እንደሚሉት፣ “በሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ቀኝ ቀኙን እየታከከ ወደ ቤኒሻንጉል እንዲሰርግ የተዘጋጀው ኃይል፣ ትግራይ ከሱዳን ጋር አዋሳኝ ክፍት ድንበር ከማግኘቷ ጋር ምን አያገናኘውም?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

እነዚህ ወገኖች መንግስት በቤኒሻንጉል በኩል እንዲሰብር መንገድ እየተጠረገለት ያለውን ኃይል፣ የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በማወቅ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲከታተል የነበረው የዕቅዱን መዳረሻ ስለሚያውቅ እንደሆነ አመልክተዋል። በዚሁ መሰረት የትህነግ ኃይሎች ሁመራ ሲገቡ የሚፈጠረውን ክፍተትና የኃይል ሽግሽግ ተንተርሶ ወደ ቤኒሻንጉል ለመንደርደር የተዘጋጀውን ኃይል የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ያደመሰሰው፣ በተመሳሳይ ሰዓት ከሸረሪና ሊነሳ ሲያሟሙቅ የነበረውን የትህነግ ኃይል ቀድሞ ባጠቃበት ቅጽበት ነው።

የሰሜን ምስራቅ ዕዝ እና የተከዜ ዘብ ኃይሎች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ቦታቸውን ሲይዙ፣ የከባድ መሳሪያ ምድበተኞች እና አየር ኃይል በግማሽ ሰዓት ውስጥ ስራቸውን ጨርሰው ቃርሚያውን ለእግረኛ አቀብለዋል። ምስክሮች እንዳሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት በዚህ ደረጃ በቅጽበት ጠጣር የተባለ እርምጃ ሲወስድ፣ እንዲህ ያለ ከባድ መሳሪያ ሲጠቀም አይተው አያውቁም።

የመከላከያ አየር ኃይል ዘመናዊ የውጊያ ድሮኖችን በማሰማራት በሸረሪና መስመር በሚገኙ የታጣቂው የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች፣ የጦር ኮንቮዮች፣ ስንቅና ጥይት የጫኑ ከባድ የጭነት መኪኖች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽሞ የትህነግን ተዋጊዎች ከውጊያ ውጭ እንዳደረጋቸው የሚገልጹት ምስክሮች፣ የተከዜ ኃይሎች ልዩ ትኩረት ከውስጥ የሚነሱ የተሸጡ ኃይሎች የሚሞክሩት ትንኮሳ ካለ መመከት ላይ እንደነበር አመልክተዋል።

ተጠግቶ የነበረው ደጀን በገጠመው ያልተጠበቀ ምት መነሻ ከአርሚ 70 (ኮር 702) ተቆርሶ ከሱዳን ብሉ ናይል ግዛት (ከጀበል ሞያ ተነስቶ በሲንጃህ በኩል) ወደ ሸረሪና ድጋፍ እንዲሰጥ ሊገሰግስ ሲል በድሮን ጥቃት ባለበት ከጥቅም ውጭ መሆኑ ተመልክቷል።

በአገር መከላከያ የህዝብ ግንኙነት ወይም የሚታወቁ ይፋዊ ገጾች ባይገለጽም፣ የመከላከያ ሰራዊቱ እጅግ የላቀ የኮሙኒኬሽን መዋቅር የመጥለፍ ታክቲክ በመጠቀም አሳሳች የራዲዮ ትዕዛዛትን ማስተላለፉ ተመልክቷል። በዚህ የተሳሳተ መልዕክት የትሕነግ ኃይሎች ለጥቃት ወደ ተጋለጠ አቅጣጫ እንዲገቡ መደረጉ የኦፕሬሽኑ ሌላው ብስለት ተደርጎ ተወስዷል። ይህ መረጃን በማወናበድ የተፈጸመ ጥቃት በወገን ሰራዊት በኩል ዜሮ ኪሳራ ያስመዘገበና ወደፊት በጦር አካዳሚዎች በጉዳይ ጥናት ደረጃ ሊጠና የሚችል የላቀ ወታደራዊ ታክቲክ እንደነበር ስማቸው ያልተጠቀሰ መኮንኖችን ጠቅሰው የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል። አዲስ ሪፖርተር ይህንን ለማረጋገጥ ሞክራ አልተሳካላትም።

ለ23 ሰዓታት ያህል ሲካሄድ የቆየው ከባድ ውጊያ በመከላከያ ሠራዊቱ ሙሉ አሸናፊነት መጠናቀቁን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) አረጋግጧል። የዜና አውታሩ የትሕነግ ታጣቂዎች የመከላከያ መደበኛና ከባድ መሳሪያዎችን መቋቋም ባለመቻላቸው እግሬ አውጪኝ በማለት ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን ሪፖርት አድርጓል። ውጊያው ሃያ ሶስት ሰዓታት መፍጀቱን አስመልክቶ አዲስ ሪፖርተር ካላት መረጃ ጋር የተለያየ ነው።

ኤኤፍፒ እንዳለው ላለፉት ስድስት ዓመታት የትህነግ ኃይሎችና የሱዳን ሰራዊት ምሽግ የነበረው ስትራቴጂካዊው የሸረሪና ወታደራዊ ካምፕ፣ በረከት እና አካባቢው ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በሸረሪና፣ በረከት እና ሁመራ ግንባሮች በተካሄደው ኦፕሬሽን በትሕነግ ኃይል ላይ የደረሰው ኪሳራ እንደሚከተለው ተመዝግቧል፡

  • ሰብዓዊ ኪሳራ፡ በሸረሪና ግንባር 800 የሚጠጉ እጅ ሰጥተዋል፤ ከ777 በላይ ታጣቂዎች ሲገደሉ፣ 703 ደግሞ ከባድና ቀላል የቁስል ጉዳት አስተናግደዋል። በሌላ አቅጣጫ ከ195 በላይ ተደመሰሱ፣ 176 ቆስለዋል። ተራራው ራስ ጉና የተባለው ክፍለ ጦር አዛዡን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ሲበተን፣ 141 የታጣቂ ቡድኑ አባላት (1 የሻለቃ አዛዥን ጨምሮ) እና በሌላ ዞን 121 ታጣቂዎች (ከነ ኮሎኔል አዛዡ) እጃቸውን ሰጥተው ተማርከዋል። ይህ አሃዝ በትህነግ በኩል ማስተባበያም ማረጋገጫም አልቀረበበትም። ይልቁኑም “የብልጽግና መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ጄኖሳይድ ፈጽሟል” በማለት በዕለቱ ማለዳ መግለጫ አውጥቷል። ለትግራይ ህዝብ፣ ልሂቃን፣ የመብት ተከራካሪዎች፣ ለዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች ጥሪ ያቀረበው መግለጫው ስለ ጉዳቱ ዝርዝር ያለው ነገር የለም። በተከታታይ በወጡ መግለጫዎች ትህነግ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጥቃት እንደፈጸሙበት ጠቅሶ ከሷል።
  • የጦር መሣሪያና ቁሳቁስ፡ 3 በፓትሮል የተጫኑ ዙ-23፣ 1 ባለ 107 ሚ.ሜ ሮኬት፣ 2 የኮርኔት መሣሪያዎች፣ 1 ባለ 120 ሚ.ሜ እና 1 ባለ 82 ሚ.ሜ ሞርታሮች፣ 9 ድሽቃዎች፣ 6 አር.ፒ.ጂ፣ 54 ብሬኖች፣ 5 ስናይፐሮች፣ ከ1,800 በላይ ክላሽንኮቮች፣ 183 የራዲዮ መገናኛዎች፣ የኦራልና ፓትሮል ተሽከርካሪዎች፣ ጄኔሬተሮች፣ የጥይት ዴፖዎች እና የህክምና ቁሳቁሶች ተማርከዋል/ወድመዋል። መባሉን አስመልክቶ ትህነግ በተመሳሳይ ምንም አላለም። የአዲስ ሪፖርተር ምንጮች እንዳሉት በሸረሪና ግንባር የተሰለፈው ሜካናይዝድ አሃድ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል።

ከዚህ ኦፕሬሽን በኋላ የትህነግ ኃይሎች በራያ፣ በጸለምት፣ በሰቆጣ ኃይል የማሰባሰብና ስምሪት የመስጠት ስራ ላይ መሰማራታቸውን የሚያሳዩ የቪዲዮ መረጃዎች እየተሰራጩ ነው። ጠላትን ለመቀነስ በሚል በሃራ መሬት ላሉ የትግራይ ሰላም ኃይሎች “ኑ ይቅርታ ይደረግላችኋል፤ ወደ ግቡ” የሚል ጥሪም አስተላልፏል።

የትህነግን አዲስ ስምሪት አስመልክቶ በማይጽብሪ ጠለምት ግንባር ያነጋገርናቸው እንዳሉት፣ መረጃው ስላለ በተጠንቀቅ ቆመዋል። ከተከዜ ወዲያና ወዲህ ሁለቱም ኃይሎች ድንበራቸው ላይ መስፈራቸውን ያመለከቱት እንዳሉት ይህ እስከተጻፈበት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት ውጊያ የለም።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

መንግሥት በሕገ ወጦች፣ በሌብነት እና የኢኮኖሚ አሻጥር በፈጸሙ ላይ የወሰደውን እርምጃ ይፋ አደረገ

አዲስ ሪፖርተር - የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወ/ሮ...

አሜሪካ “ከኤርትራ ጋር አላሴርንም” የማሳድ ቡሎስ ተደጋጋሚ ማስተባበያ ለምን?

አዲስ ሪፖርተር | የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአረብና የአፍሪካ...

የሰኔ 15 ግድያ የዛሬ የአማራ ክልል ትርምስ መነሻ

 “ዓብይ አህመድን ገዳይ አድርጎ ገዳይንና ሟቸን እኩል ማጀገን በሚል...

የትግራይ የፖለቲካ አቅጣጫና የቀጠናው ጂኦፖለቲካ፤ የግብጽ፣ ሱዳንና ሻዕቢያ የ”ጽምዶ” ቃል ኪዳን ይፈጸማል?

ለአዲስ አበባ የሚወረወሩ ወጥመዶች፡ ድርጅቱ ባለው የዲጂታል ሰራዊት እና...