የአዲስ አበባ የ”ጥቁር ገበያ” የቤት አከራይ ማጅራት መቺዎች? የውጭ ዜጎችና ከሕግ ውጪ የሆኑ የኪራይ ልምዶች፤

Date:

  • አዲስ ሪፖርተር – ሰመረ በስዊዲን የምትኖር እህቱ በየወሩ ገንዘብ የምትልክለት የኤርትራ ዜግነት ያለው ስደተኛ ነው። ሰመረ ከካምፕ ከወጣ በሁዋላ የሚኖረው አንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ነው። ከካምፕ ወጥቶ ከተማ ውስጥ ለመኖር የሚያስችል ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የለውም።

በዚያ ትልቅ ግቢ ውስጥ እሱን መሰል በርካታ ኤርትራዊያን ይኖራሉ። ቤቱን የተከራየው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚታወቅ ኤርትራዊ ሲሆን ቤቱ ውስጥ ያሉት የተከራይ ተከራይ ገንዘብ የሚከፍሉት ለእሱ ነው። ዋናው የቤቱ አከራዮች ሰመረ ለሚኖርበት ቤት ዋና ተከራይ ለማከራየት የተስማማሙት ከቤቱ መሰረታዊ ዋጋ እላፊ እንደሚከፍል ደላሎች አጋብብተው ነው። በአዲስ አበባ በዚህ መልኩ የተያዙ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኤርትራዊያን በርክታ ናቸው። ቀበሌዎች አብዛኞቹን ቤቶች ያውቋቸዋል ግን የትግባቡ ይመስላል። ይህ ደላሎችን ጨምሮ ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች የተሰበሰበ አስተያየት ጭማቂ ነው።

ብግምት 23 ዓመት የሚሆናት የዶላር ምንዛሬ ላይ የምትሰራ አንድ ኤርትራዊ “ቤቱን ማን እንደተከራየው አላውቅም። ስራዬ “ገንዘብ ገብቶልሻል። ይህን ያህል ገንዘብ ለእገሌ አስገቢ ወይም ስጪ ስባል ማድረስ ነው” ትላለች። “ቤት ኪራይ የለብኝም። በጋራ የምንኖርበት ግቢ አለን። ግቢ ውስጥ አንድ ክፍል አለኝ። ብዙ ነን አብረን የምንኖረው” ስትል በጥቁር የተመነዘረውን ገንዘብ ለሰጠቸው ዳያስፖራ ማጫወቷን አዲስ ሪፖርተር ከምስክሩ ሰምታለች።

ከላይ የተባሉት በርክታ ጉዳዮች ሚስጢር አይደሉም። የህግ ክፍሉም፣ ፖሊስም፣ ቀበሌም፣ ሰላም ማስከበርም፣ አካራይም፣ ጎረቤትም፣ ተከራይም ወዘተ የሚያውቁት ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። አዲስ አበባ የቤት ኪራያቸው ውድ የሆኑ ከተሞች ተርታ መሰለፏ ይፋ ሲሆን፣ ዜናውን በመቀባበል የሚያሰራጩ ሚዲያዎችም ቢሆኑ ይህን ሃቅ ያውቃሉ። ግን ችግሩን የሚነካው፣ ጠልቆ የሚሰራው ሚዲያ የለም። ጉዳዩ የፖለቲካ ገበያ ከማድረግ በዘለለ በዘርፉ ያለውን ሌብነት የሚያጠና የለም።

ኤርትራዊያን ብቻ ሳይሆኑ ቻይናዎችን ጨምሮ የሌላ አገር ሰዎች በኢትዮጵያ ብር እየከፈሉ የሚኖሩባቸው ቤቶች ጥቂት አይደሉም። በሚከራዩባቸው ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ህገወጥ ምርቶችን የሚያመርቱ ወንጀለኞች እንዳሉም መረጃዎች አሉ። እነሱንም የሚነካቸው የለም።

አዲስ አበባ በ2025 ከፍተኛ የቤት ኪራይ ከሚያስከፍሉ የአፍሪካ ከተሞች ተርታ መመደቧን ተከትሎ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል ሕግን ያልተከተሉ የኪራይ አሠራሮች፣ ከውጭ አገር ዜጎች ኤርትራውያንን ጨምሮ በጓሮ የሚደረግ ስምምነትና የጥቅም ትስስር እንደሆነ ለአዲስ ሪፖርተር ገለጹ።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለአዲስ ሪፖርተር አስተያየታቸውን ሲሰጡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ሰለሞን ገብሩ እንደገለጹት ፣ የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ መናር መንስኤ ከአቅርቦት እጥረት ባሻገር፣ በዋነኝነት የሚመራው በሕጋዊ ገበያ ባልተደገፉና አሠራሮችን በጣሱ የኪራይ ልምዶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፣ ችግሩን ከሚያባብሱ ዋና ምክንያቶች አንዱ የውጭ ዜጎች ቤት የሚከራዩበት አግባብ ነው። አሰራሩ ዜጎችን ለከፋ ወጪና እንግልት ዳርጓል።

“በተለይም ከኤርትራ የሚመጡ ዜጎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ (hard currency) ተደግፈው፣ ከአገር ውስጥ ተከራዮች አቅም በላይ የሆነ ዋጋ በመክፈል ገበያውን ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ማባባሳቸውን ጠቁመዋል። ይህ መረን የወጣ አሰራር ልጓም እንዲበጅለት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ባነጋገሩበት መድረክ ቦታ፣ ቀበሌና መንደር ተጠቅሶ ቀርቦላቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይህ አሠራር በሀገሪቱ ያለውን የኪራይ ሥርዓትና የዋጋ መወሰኛ መስፈርት የሚጣረስ መሆኑን ገልጸዋል። ባለሙያው የችግሩን ውስብስብነት ከፍ የሚያደርገው፣ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች የሚያደርጉት ድርጊት መሆኑን አክለዋል።

 የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ከመንግሥት አካላት ክትትል ለመሰወር ወይም ቤቱን እንደ ምሽግ ለመጠቀም ሲሉ፣ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል እየተከራዩ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል። ይህ የባለሙያው አስተያየት የህግ አስከባሪውን ሰፈር መዳሰስ እንደሚያሻው የሚያመለክት ነው።

በሕጋዊ መንገድ መከራየት ባለመቻላቸው፣ ከባለቤቶች ጋር በሚያደርጉት ድብቅ ስምምነት የመኖሪያ ቤቱን ዋጋ ከመደበኛው በላይ በመጨመር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ ነው ያሉን። ይህም በአካባቢው ያሉ ቤቶች በሙሉ የኪራይ ዋጋ እንዲንር እንደሚያደርግ ነግረውናል።

ይህ የኪራይ አሠራር የሀገሪቱን የግብርና የኪራይ ቁጥጥር ሥርዓቶችን የሚጻረር ሲሆን፣ በአገር ውስጥ በራሳቸው ብቸኛ ገቢ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ ዝርዝር ጉዳይ አንስተው ገልጸዋል።

ይህ ከሕግ ውጪ ያለው የኪራይ አሠራር በቀጥታ በአገር ውስጥ ነዋሪዎች ላይ አሳሳቢ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑ አብራርተዋል። አንዳንዶች መንግስት ይህን ጉዳይ በጥብቅ እንዲያየውም ይመክራሉ።

አቶ ሰለሞን እንዳሉት፣ የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ምንዛሬ እየተቀየረላቸው የሚከፍሉ ተከራዮች በመጡ ቁጥር የአገር በቀል ባለቤቶች በሕጋዊ መንገድ መከራየት ቢከለከሉም እንኳ ከፍተኛውን ዋጋ ስለሚመርጡ የአገር ውስጥ ነዋሪዎች የሚከራዩበት አማራጭ እየጠበበ ይሄዳል።

የህግ ባለሙያው አይናገሩ እንጂ በውጭ አገር ያሉና አዲስ አበባ ቤት ካላቸው ሰዎች ቤቱን በኮንትራት መልክ እየወሰዱ ውስጡን የሚቸረችሩት እንዲህ ላለው ተጋባር እንደሆነ ደላሎች ምስክር ናቸው።

ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ከአዲስ አበባ መሀል ከተማ እንዲፈናቀሉ የመገደዳቸው አንዱና ዋናው ምክንያት ይኸው የቤት የጥቁር ኪራይ ገበያ ጣጣ ነው።

ባለሙያው በመጨረሻም መንግሥት የውጭ ዜጎች የኪራይ ውል አፈጻጸም ላይ ያለውን ቁጥጥር በአስቸኳይ ማጠናከር፣ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ሰዎች አሠራር መመርመር እና ለዜጎች የሚከራዩ ቤቶችን ዋጋ በሚመለከት ግልጽ መመሪያ ማውጣት ወይም ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ቤት አከራዮች የዛሬ አርባና ሰላሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ በራቀ ጊዜ የሰሩትን ቤት በምን ሂሳብ ስሌትና አምክንዮ ወገናቸው ላይ እንደሚቆልሉ ግልጽ ሊሆንላቸው ያልቻለ በዚህ አግባብ ሚዲያዎች ዝምታውን መስበር አለባቸው።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related