አዲስ ሪፖርተር ከሀገረ አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ የቢሊየን ዶላሮች ዘረፋ ዜና ብቅ ብቅ ማለት ጀመረዋል። ይህ ሪፖርት ከመሰማቱ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ግልጽ ባይሆንም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሶማሊያ ዜጎችን አስመልክቶ የከረረ ንግግር አድረገው ነበር። “አንፈጋችሁም” እስከማለት የደረሰ ዛቻ አሰምተዋል።
የማንሀትን ኢንስቲትዩት መርማሪ ሪፖርተር ርያን ቶርፕ “The Largest Funder of Al-Shabaab Is the Minnesota Taxpayer” በሚል ርዕስ ይዞት እንደወጣው ዘገባ ከሆነ በግዛቷ አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝ ዘመነ ስልጣን ከግብር የሚሰበሰበው ረብጣ ገንዘብ ድንበር ተሻግሮ በሶማልያ የከተመውን የአል ሸባብ አሸባሪ ቡድን ቀለብ ሲሰፍር ፣ ሲያስታጥቅ ቆይቷል። ይህ ሪፖርት ሻዕቢያን ጭምወሮ በግልጽ ከሚታወቁና የህቡዕ አደረጃጀት ዘርግተው ለሚንቀሳቀሱ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍ ለሚያደርጉ ዜጎች የማስጠንቀቂያ ደወል ስለመሆኑ እየገለጹ ያሉም አሉ።
ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ተያይዞ ባይገለጽም አሜሪካ ሰሞኑን ኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ላይ የቪዛ ማዕቀብ ማድረጓን ይፋ ስታስታውቅ “…. በተለይም ከሶማሊያ የሚመጡ የሽብርተኝነት ስጋቶች መኖራቸው” ስትል እንደ ተጨማሪ ምክንያት ገልጻ ነበር።
ከሚኖሶታ በጥናትና ምርመራ ታግዞ በዳታ የቀረበው የዘረፋ እና የማጭበርበር ድርጊት እንዲሁ በዘፈቀደ እና በአጋጣሚ የመጣ እንዳልሆነ ከላይ የተጠቆመው መነሻ አብነት ይሆናል። ሪፖርቱ ምዕራብያኑ እስከ ምስራቅ አፍሪካውያኑ ሀገራት ድረስ በብዙ ሰንሰለት የተሳሰረ እና እጅግ የተጠና እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ህልውናን ለማፈራረስ ተወጥኖ በእቅድ የሚካሄድ ተግባር እንደሆነ በዝርዝር ያስረዳል።
ይሄ የዘረፋ እና የማጭበርበር ድርጊት እነዲሁ በዘፈቀደ እና በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ከምዕራብያኑ እስከ ምስራቅ አፍሪካውያኑ ሀገራት ድረስ በብዙ ሰንሰለት የተሳሰረ እና እጅግ የተጠና እንድሁም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ህልውናን ለማፈራረስ ተወጥኖ በእቅድ የሚካሄድ ተግባር ነው።
በዚህ የተቀነባበረ የወንጀል ሰንሰለት ድርጊት ላይ የድርሻቸውን የሚተውኑት አካላት እነማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ የምርመራ ሪፖርቱ ምላሽ አለው።

ለዚህ የማይነጥፍ የገንዘብ እርዳታ የአንበሳውን ሚና የሚጫወተው የሚኒሶታ ግዛት የመኖርያ ቤቶች አገልግሎት(Housing stabilization services) ነው። የዚህ መስርያ ቤት የተቋቋመበት ዋና ዓላማ “የተቸገሩትን ለመርዳት እና አስተማማኝ የቤት አገልግሎትን ማረጋገጥ ነው” ቢባልም ነገር ግን ገቢው ቁልፍ ቦታውን በተቆጣጠሩ ሶማሌያውያን በኩል አሸባሪ ኪስ ውስጥ ሲከማች መኖሩን ነው የምርመራ ሪፖርቱ ያመለከተው። ለዚህም ሪፖርቱ እንደ ማሳያ የሚወሰደው ከዓመታት በፊት የዚህ መስሪያ ቤት ግምታዊ ወጪ ይሆናል የተባለው 2.6 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቢሆንም ቁጥሩ አሻቅቦ ከዓመታት በኃላ 104 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገደማ ደርሷል።
በሴፕቴምበር ላይ አንዳንድ የሃሰተኛ HSS ስራዎችን አስተባብረዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ቀርቦ ነበር። አቃቤ ህግ ስርዓቱን ለማጭበርበር ብቻ የተፈጠሩ ኩባንያዎችን ገልጾ አጭበርባሪዎች እንዴት እቅድ ላይ ሲደራደሩ እንደነበር ይፋ አድርጓል። ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚጠቅም ሀብት እንዴት እንደሚያሟጠጡ አብራርቷል። ነገር ግን የፖለቲካ መሪዎች መዋቅራዊ ውድቀቱን ከመጋፈጥ በመቆጠባቸው ለዓመታት ይህ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ሳይደረግበት ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቶ ዝምታ የመረጡትን ከሷል።
የዚህ መስሪያ ቤት የማጭበርበር ተግባር ብቸኛው የአል ሸባብ መጋቢ ምንጭ አይደለም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ2019 ጀምሮ ቢያንስ 28 ዋና ዋና የማጭበርበር ተግባረራት ታይተዋል፣ ብዙዎቹ ደግሞ ተመሳሳይ ተዋንያንን የሚያሳትፉ ናቸው። ከማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ መረጃ ነጋሪዎች እና የቀድሞ መርማሪዎች እንኳን የተሳትፎው መጠን እውን እንደሆነ እና ከአሁን በኋላ ችላ ሊባል እንደማይገባ አምነዋል።
ጥያቄው የሚሆነው “ይህ ሁሉ ገንዘብ የት ሄደ?” የሚል ነው። መርማሪዎች ከሚኒሶታ ወደ ሶማሊያ የሚላከው ግዙፍ የገንዘብ ዝውውር ላይ ባደረጉት ማጣራት አንድ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በምርመራው ሪፖርት መሰረት የመርማሪዎቹ ግኝት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሐዋላ፣ መደበኛ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውር፤ ጎሳ ላይ በተመሰረተ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይከናወናል። በዚህ መልኩ ከሚዘዋወረው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነው ሆን ተብሎም ይሁን “ባለማወቅ” በምስራቅ አፍሪካ ለአስርት ዓመታት ለዘለቀው ደም መፋሰስ ተጠያቂ በሆነውና የአልቃይዳ አንድ ምዕራፍ ወይም አካል ከሆነው የሽብር ቡድን በአልሸባብ እጅ ገብቷል። ምርመራውንም “አጅ በአፍ” ያሰኘው ይህ ግኝት ነው።
ይህን ቀውስ ለመፍታት የማይመችውን እውነት መቀበልን ግድ ይሆናል። የሜኒሶታ የበጎ አድራጎት ስርዓቶችን የሚጠቀሙ የምስራቅ አፍሪካ የግጭት ቀጠናዎች የማያባራው የዓለም አቀፍ የሙስና ሰንሰለት አካል ናቸውና ይህን ሰነስለት መበታጠስ ቀዳሚው ተግባር ነው።
በሚኒሶታ የሚዘረፈው እያንዳንዱ ዶላር አሜሪካ ያላትን አመኔታ ያዳክማል፤ በውጪ ያሉ አክራሪ ቡድኖችን ደግሞ ያጠናክራል። የፖለቲካ መሪዎች እና ሚዲያዎችም ይህንን እውነታ ከፍርሃት ይልቅ በድፍረት እስኪጋፈጡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ምስኪኑ የምስራቅ አፍሪካ ህዝብ ሆኖ ይቀጥላል።
የቀድሞው የሚኒሶታ ግዛት ሴናተር የነበሩት ጌይዘር በዚህ የወንጀል ድርጊት ላይ በሰጡት አስተያየት የሚኒሶታ ዋና ዋና ሚዲያዎች የዚህን የወንጀል ድርጊት አሳሳቢነት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው መተዋቸው ጉዳዩ እንዲህ የተወሳሰበ ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል።
ዛሬም በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን በስውርና በገሃድ በመናበብ የሚፈጸም አሳሳቢ ጉዳዮች ሚዲያዎች በማወቅ ወይንም ሆነ ብለው በሚፍለገው መጠን አያነሱትም። ጉዳዩን ከመጋረጃ ጀርባ ካመመልከት ይልቅ ዝምታን መርጠዋል። ከአልሸባብና ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በገሃድና በህቡዕ የሚፈጸሙ፣ እየተፈጸሙ ያሉ “ሽብር” የሚመስሉ ተግብራት ተበራክተዋል። በአሜሪካ የሽብርተኛነት ሊስት ውስጥ ያሉ ተቋማትን በይፋ እየጠሩ ከሚሰሩ፣ በድብቅ በሶማሊያ ጋር ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር የሚሰሩትን ጨምሮ ለተለያዩ ቡድኖች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍና እርዳታ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ዘገባ ምን ይማራሉ? ወደፊት ሚኖሶታ ምን እርምጃ ልትወስድ ትችላለች? ትራምፕ በግልጽ ተናግረዋል።
የሚኖሶታ ኮንግረንስ አባል የሆነችውን ኢልሃንን አስታከው ዶናልድ ትራምፕ “ኢልሃንኮ ቆሻሻ ናት፣ አዎ ቆሻሻ ናት! ጓደኞቿም ቆሻሻ ናቸው…አገራችን ላይ ላያቸው አልፈልግም፤ አንፈልጋቸውም! …ካለምክንያት እንዳይመስላችሁ አገራቸው ዋጋ ቢስ የሆነው፤ በዚህ ባህሪያቸው ነው። …ቆሻሻውን ከአገራችን ላይ ማፅዳት አለብን። አገራችን ለውጥ ላይ ናት! ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን። …ጠራርጎ ማባረርና ነገሩን ማስተካከል ነው በቃ!” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ የሰጥቻቸውን ኢትዮጵያዊያን “ኢትዮጵያ ብትመለሱ ምንም አይገጥማችሁም በ60 ቀናት ውስጥ ውጡ” ማለቷ፣ ከኤትዮጵያ ጋር ችብርተኛነትን ለመዋጋትና በአፍሪቃ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ አብራ ለመስራት ከመስማማቷ ጋር ተያያዞ ወደፊት ይፋ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ታክቲክል ጉዳዮች ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያዊያን ከወዲሁ ራሳቸውን ከሽብር አካባቢ በገንዘብ ድጋፍም ሆነ በሌላ ተግባር እንዲያሸሹ የሚመክሩ አሉ።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






